የእስራኤል አምላክ
. .. የእስራኤል አምላክ የምስኪኖች ሞገስ፣ የድሆች ጌጥ፣ አፍረው ለሚኖሩ ድፍረታቸውን ፣ ቤት ለደበቃቸው ነጻ አውጪአቸው ፤ ማጣት ፍርሃት ፣ ማግኘትም አለመርካት የሆነባቸውን የሚያግዝ ፣ የዱዳዎች አንደበት፣ ጉልበታቸው ለተበዘበዘ ዋጋ አስከፋይ ፣ ጥቁር ቀንን ወስዶ ደግ ቀንን የሚያመጣ፣ አገር ለሌለው አገር የሚሰጥ፣ የስደተኛው ድንኳን፣ ስለ መብቱ መቆም ለማይችለው ጠበቃው እርሱ ነው። ካለቀው የሚጀምር፣ ሞት የተፈረደበትን በሕይወት የሚያኖር፣ ለገዳይ ሞትን ከፍሎ ሟችን የሚያቆይ ፣ ብዙ ጠላት የማይመክተው፣ ብዙ ሽብር የሚያደናቅፈው፣ እንዳለ ያለ ፣ አንድ ሳለ ሺህዎችን የሚረታ፤ መላ ፈልጎ ጠቢብን፣ አቅም ሽቶ ኃይልን የማይጠጋ፣ በራሱ ብርሃን የሚያበራ፣ ጨለማ በእርሱ ዘንድ የማይጨልም የእስራኤል አምላክ ይህ ነው። ቃል ኪዳን አክባሪ፣ አብርሃም ሞተ ብሎ ልጆቹን ያልጣለ፣ አለቀ ሲባል የሚያስጀምር ፤ የሺህ ዓመት ፍቅር፣ የዘላለም ውድ ያለው የእስራኤል አምላክ ይህ ነው።
ዓይኖቹ በጨለማ የሚያዩ፣ የሚጠሩት ወዳጅ ፣ የሚልኩት ልጅ ለሌላቸው አለሁ ባይ፣ የብርሃን ብርሃኑ፣ ትልቅ ሳለ የሚልኩት፣ የተጣሉትን የሚያስታርቅ፣ ልብን የሚለውጥ፣ በሕይወት ምዕራፍ እያሳለፈ የሚያስተምር እኔ ደካማው ዛሬ የምንናገርለት የእስራኤል አምላክ ይህ ነው:: እስራኤል በዙሪያዋ ያሉ በነዳጅ ሀብት የበለፀጉ፣ በሃይማኖትና በቋንቋ የተባበሩ ናቸው። ያለ ነዳጅ ባለጠጋ ፣ ያለ ደጋፊ ኃያል የሆነችው በአባቶች በረከት ፣ በባራኪው በእስራኤል አምላክ ነው። በአምልኮቱ ካልበደላችሁት የእናንተም አምላክ ነው። ሚዛኑ ትክክል፣ ያለ አጥር የሚከልል የኢትዮጵያም አምላክ ነው።
ከእግዚአብሔር የውዳሴ ሰሞች አንዱ የእስራኤል አምላክ፣ የያዕቆብ ረዳት የሚለው ዝነኛ ነው።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 3 ቀን 2017 ዓ.ም.