መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -3

የትምህርቱ ርዕስ | የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -3

የምሕረት አምላክ

የማይቸኩለው ፣ የማይጨክነው ፣ የማያረፍደው ፣ የማይደናቀፈው ፣ የማይሳነው አምላክ ነው ። ነፍሱ በበደል የታሰረችውን ፣ ከሕይወቱ ሞቱን የናፈቀውን በምሕረቱ ያረጥበዋል ፣ በቸርነቱ ባለጠጋ ያደርገዋል ፣ በይቅርታው ሰላም ይሰጠዋል ። ወደ እርሱ የመጣ በደለኛ ከመጣበት ስሜት ጋር አይመለስም ፣ እግዚአብሔር ነጻነትን ሳይዋጉ ይሰጣል ። እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ ነው ፣ ከለመኑት በላይ አትርፎ ይሰጣል ። እንደ ፍጡር ስንከጅል እንደ አምላክነቱ ይሰፍራል ። በረሀብ ግዞት ፣ በጠኔ ቀጠና ላሉት የምሕረት እጁን ይዘረጋል ። የባለጠጋ እጅ ለተቆለፈባቸው ፣ ወላጅ ለካዳቸው እርሱ ምሕረቱን ያዘንባል ። ችግር ትልቅ አይደለም ፣ የዓለም መንግሥታት የአንድ ቀን የጦርነት ወጪአቸውን ቢለቁ ችግረኛ ይጠፋል ። ለማጥፋት የዋለውን ኃይል ለማዳን ማዋል ብቻውን በቂ ነው ። ሰዎች ምሕረትን የሚወደውን አምላክ ሲጠጉ ችግረኞች ከረሀብ እንግልት ያርፋሉ ። ጠዋት ለከሰዓት የሚርበን እኛ ለተራቡት ከማሰብ የበለጠ ምንም ሥራ የለንም ። ቤተ ክርስቲያን ገንዘብን ከምራ የተራቡ ልጆችዋን እንድትመለከት አልተፈቀደላትም ። ልጆችዋ ሲራቡ ተረጋግታ የምትቀመጥ እናት የለችምና ። እግዚአብሔር የምሕረት አምላክ ነው ። የምሕረቱ ዕቃዎችም እኛ ነን ። ቤተ ክርስቲያንም ማለት ነጭ ጥበብ ለብሳ የተቀመጠች አንዲት ሴት ሳትሆን ቤተ ክርስቲያን እኛ ነን ፣ ማኅበረ ምእመናን ፣ የሲኖዶስ አባላት ቤተ ክርስቲያን ተብለው ይጠራሉ ። የምሕረቱ ማስተላለፊያ መስተዋት ቤተ ክርስቲያን ናት ። መስተዋት ንጹሕ እስከሆነ ድረስ ብርሃን ያስተላልፋል ። የተጨነቀ ዓለም የአማኞችን ርኅራኄ ይፈልጋል ።

የበረከት አምላክ

በሰፊ እጁ ሰፍሮ የሚሰጥ ፣ አሰጣጥ የሚያውቅበት ፣ ለማን ምን መስጠት እንዳለበት የሚያውቅ ፣ ሕይወትን አስቀድሞ በረከትን የሚናኝ ፣ በበድን አጠገብ እንጀራ የማያስቀምጥ ፣ የሚጎዳንን የሚከለክል ፣ የሚጠቅመንን የሚያፈስ ፣ ያለ መያዣ ፣ ያለ ብድር የሚሰጥ ፣ ሲሰጥ የማያልቅበት ፣ ሰጠሁ ብሎ የማይናገር ፣ በስጦታው የማያሸማቅቅ እርሱ የበረከት አምላክ ይባላል ። በረከቱ የልጅ ልጅን የሚያጠግብ ነው ። ዛሬ የሠሩት ቤት ልጅ ላይወርሰው ፣ መንገድ ሊያገኘው ይችላል ። የእግዚአብሔር በረከት ግን እንቅፋት አያስቆመውም ። ገንዘብ የያዘ ያልቅበታል ፣ በረከቱን የያዘ ግን አያልቅበትም ። ያዕቆብ ለዘመናት የተመኘው ፣ ስሙን ሳይጠራ የፈለገው ያ በረከት በእግዚአብሔር አርፎ መኖር ነው ። እስኪያገኙ መዋሸት ፣ ካገኙ በኋላ መስጋት የሰው ጠባይ ነው ። ሀብት ሲበዛ የገዛ ወንድም እንደሚያስፈራ ከያዕቆብ ማየት ይቻላል ። እግዚአብሔር ራሱ በረከት ሲሆን ግን የሚታየው አምስት እንጀራ ነው ፣ የሚጠግበው አምስት ሺህ ሰው ነው ። ጎተራ የለም ፣ የሚጎድል የለም ። ያለው ጥቂት ነው ፣ ሲጎድል ግን ይጨመርበታል ። የእግዚአብሔር በረከት በሰዓቱ ይለቀቃል ። ከሰዓቱ በፊት ቢፈልጉት ላይገኝ ይችላል ። አንዱ ከአባት ከእናት ወርሶ ፣ ሌላው ከወንድሙ ተበድሮ ከፍ ይል ይሆናል ። የአንተና የአንቺ በረከት ግን ከእግዚአብሔር እጅ ነው ። የበረከትን ምንጭ ማወቅ መታደል ነው ። ከኵሬ የሚቀዳ ያልቅበታል ፣ ከምንጩ የሚቀዳ ግን በጨለፈ ቍጥር ይጨመርለታል ። እግዚአብሔር ሲባርክ ገንዘብን በመስጠት ሳይሆን ግንዛቤን በመስጠት ሥራውን ይጀምራል ።

የበረከት አምላክ ፣ አሰጣጥን የሚያውቅ ፣ ደብቆ የሚያጎርስ ፣ ከዓይነ ሞት ልጆቹን የሚከልል ፣ ሕያው ሳለ የሚያወርስ ፣ ሳይጎድልበት የሚያፈስ ነው ። ወላጆች ቢያወርሱ ኑዛዜው የሚጸናው የሞቱ ቀን ነው ። ሕያው ሳለ የሚያወርስ ፣ ብርቱ ሳለ እንኩ የሚል እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ወላጅ በሕይወት ሳለ ሰግቶና አቅም አንሶት ሀብቱን ይሰጣል ፣ በሞት ሲጠራ ሌላ እንዳይበላው ልፋቱን የእኔ ለሚለው ያወርሳል ። ሳይደክመው ርስቱን የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የእግዚአብሔር በረከት ባለጠጋ ታደርጋለች ። ሰው ቀምቶ ወይም ተባርኮ ይበለጽጋል ። ቀምቶ የበለጸገ የሚበላበት ሰላማዊ ሕሊና ፣ የሚተኛበት ያረፈ ማንነት የለውም ። በበረከት የበለጸገ ግን በምስጋና ይበላል ። ገንዘብ መምጣቱ ብቻ ሳይሆን የመጣበት መንገድ ለሰላማችን አስፈላጊ ነው ። እግዚአብሔር ሳይቀሙ ፣ ደም ሳይቃቡ መባረክ ይችላል ። እርሱ ጥረትን እንጂ ምኞትን አይባርክምና ምኞታችን ትጋት ያስፈልገዋል ። እግዚአብሔር ሰነፍን ከባረከ ትጋትን ጣለ ። የእጃችንን ሥራ እርሱ ይባርካል ። በተሰየሙበት ድርሻ ትጉህ መሆን እግዚአብሔርን ያስደስተዋል ። ቆሞ የመስበክን ያህል ከልብ መንገድ ማጽዳትም አገልግሎት ነው ። አዎ እግዚአብሔር የበረከት አምላክ ነው ። እግዚአብሔር ያኖራል ። በዘዴው/በመላው ቀኑን ያሳልፋል ፣ ገቢና ወጪ ሳይመጣጠን እርሱ ያጠግባል ። ይህ ቀን ላንተ ምቹ ባይሆንም ቀን አለህና ቀና በል ። የሚያኖረው ሳይጨነቅ ነዋሪው መጨነቅ የለበትም ። ጭንቀት ሲያጎድል እንጂ ሲሞላ አይተን አናውቅም ።

ሃሌ ሉያ ለካ አንተ ነህ የቤቴን ደጃፍ የምትጸፋው ! ግባ ከአዳራሹ ፣ የጎደለውን ሙላው ። አያቅትህ ፣ ፍርሃት ቤቴን ሳያፈርሰው የዚህ ቤት ራስ እኔ ነኝ በለው !

 

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ