መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -4

የትምህርቱ ርዕስ | የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -4

ተስፋዬ

ተስፋ ያለ እምነትና ያለ ፍቅር ባዶ ነው ። ተስፋ የሚሰጥ መነሻው ፍቅር ነው ፣ ተቀባዩም ዋስትናው እምነት ነው ። ተስፋ በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለ ናፍቆት ነው ፣ አይ ጉድ እግዚአብሔርና ሰው ሳይለያዩ ይነፋፈቃሉ ፤ እግዚአብሔር አሁን እንኳን በድርጊት ላይ ሁኖ አደርጋለሁ ብሎ ተስፋ ይሰጣል ። ተስፋ መስጠት የጌታ ጠባይ ነው ፣ ከጌታ ተስፋ ከባሪያ ጥበቃ የታወቀ ነው ። ጌታ ዓለምን ሳይለያት እመጣለሁ ይላል ፣ ከላይ ሳይታጣ ወረደ ተብሎ ይነገርለታል ። በልባችን እያለ ወደ ዙፋኑ እናንጋጥጣለን ። ሁሉ በሁሉ የሆነው ጌታችን በእኛ ልብ ተስፋን ሲቀበል ፣ በሥልጣኑ ደግሞ ተስፋን ይፈጽማል ። ተስፋ “ነገ” ጌታ እንዳላት የሕያው አምላክ ምስክር ነው ። ጌታ ተስፋውን ለመፈጸም አለመኖር አይጋፋውም ። ተስፋ ሰጪውም ተስፋ ተቀባዩም ያቺን ቀን ይናፍቃሉ ። ተስፋ ሰጪና ተቀባይ ባለ ቀጠሮ ናቸው ። ተስፋ ልመና አይደለም ፣ ተስፋ ስጠኝ ብሎ መለመን ሳይሆን እሰጥሃለሁ ያለውን ቃል ማመን ነው ። የተስፋ መሠረቱ እግዚአብሔር ብቻ ነው ። በግዛቱ ፀሐይ የማይጠልቀው እግዚአብሔር ፣ ታላላቅ አገዛዞች ሲወድቁ አሁንም በመንበሩ ያለው ጌታ የተስፋ ምንጭ ነው ።

እግዚአብሔር ቃሉን ሊፈጽም ይተጋል ። ቃሉ እውነት እንደሆነ ተስፋዋ የሞላላት እስራኤል ሕያው ምስክር ናት ። እስራኤል ሰባት ሚሊየን ሕዝብ ናት ፣ በዙሪያዋ ሰባት መቶ ሚሊየን ጠላት አላት ። እግዚአብሔር ተስፋውን እንደሚፈጽም ፣ ጠላት ቢኖርም ሕይወት እንደሚቀጥል እስራኤል ምስክር ናት ። ነቢዩ ዳዊት እግዚአብሔርን ተስፋዬ በማለት ደጋግሞ ይጠራዋል ። ተስፋዬ በእኛ አገር የሰው ስም ነው ። ይህ ስም ግን የእግዚአብሔር የሙገሳ ስም ነው ። ከአዳም ውድቀት ጀምሮ እግዚአብሔር የሰው ልጅ ተስፋ ነው ። ተስፋ የነገ ዋስትና ነው ፣ ከበደል በኋላ ነገ የሰው ፍርሃት ሆኗልና መድኃኒቱ ተስፋ ነው ። 5500 ዘመን የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ጠብቋል ፣ ተስፋ በማድረግ አዳም እግዚአብሔርን በዘመኑ ፣ በመቃብርና በሲኦል ጠብቋል ። እግዚአብሔርም የ5500 ዘመን ተስፋን ፈጽሟል ። ዘመን ቢረዝምም እግዚአብሔር ተስፋውን ይፈጽማል ። ተስፋው ከሰቀቀን ፣ ከመቃብር ፣ ከሲኦል ያወጣል ። በእግዚአብሔር ተስፋና በፍጻሜው መካከል ምንም ልዩነት የለም ። ያለውን ያደርጋል ፣ የማያደርገውንም አይናገርም ። እግዚአብሔር አለ ብሎ የሚያምን ተስፋ ማድረግን አያቆምም ። ተስፋ የቆረጠ ግለሰብ ፣ አባት ፣ አገልጋይ መሪ በምድር ላይ በራሱና በሌሎች ይጨክናል ።

መጽሐፍ፡- “እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ” ይላል ። እምነት ያለው ሰው ተስፋና ፍቅር አለው ። አማኝ ተስፋ አይቆርጥም ፣ ያመነታል ግን አይክድም ፤ ይንገዳገዳል ግን አይወድቅም ፣ ይፈራል ግን ለምርኮ እጁን አይዘረጋም ፤ ይጣላል ፣ ግን አይጠላም ፤ ይቀየማል ፣ ግን አይበቀልም ። አማኝ ፍቅር አለው ። ፍቅር ወንድሙን ከእኔ የተሻለ ነው ብሎ ያስባል ። ፍቅር በወንድሙ ዕራቁትነት አይስቅም ። ፍቅር ያየውን ክፉ አያሳይም ። ፍቅር ወንድሜ ይዳን እንጂ ይጥፋ ብሎ አያውቅም ። ያለ ፍቅር እምነት ባዶ ነው ። ተስፋም እምነት አለው ፣ እግዚአብሔር ለነገረን ቃል ቼኩ እምነት ነው ። እግዚአብሔር በቃሉ ይያዛል ። እግዚአብሔር የእሳት ላንቃ ነው ፣ በምንም አይያዝም ፣ በቃሉ ግን ይያዛል ። “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል ።” ይላል (ዮሐ. 15 ፡ 7) ቃሉን ማወቅ እንደ ቃሉ በመጸለይ ጸሎትን ኃያል ያደርገዋል ፣ በቃልህ እንዲህ ብለሃልና ሲሉት ይወዳል ። ተስፋ ፍቅር አለው ። ለሰዎች ተስፋ መስጠት ፍቅር ነው ፣ መፈጸም ሃይማኖት ነው ። ተስፋ ሰጥቶ እየቻለ የማይፈጽም ሃይማኖት የለውም ። ከእግዚአብሔር ብዙ ተቀብሎ ትንሽ ለመስጠት የሚሰስት ነው ። መስጠትም ዕድል ነው ፣ አንድ ቀን እጆቻችን መስጠት የማይችሉ በድን ይሆናሉ ።

እግዚአብሔር የተስፋ አምላክ ነው ። ተስፋ ነገን የሚቀድስ ነው ። ተስፋ የዋዜማ ድግስ ነው ። ተስፋ ነገን ማያ የጦር ሜዳ መነጽር ነው ። ሕይወት ሰልፍ ስትሆን ነገን የምናየው በተስፋ ነው ። ሁሉም ነገር ተስፋ ሲያስቆርጥ “አሁንስ ተስፋዬ ማነው እግዚአብሔር አይደለምን?” እንላለን (መዝ. 38፡7)። ንጉሥም ተስፋ ይቆርጣል ፣ የሃይማኖት አባትም በቀቢፀ ተስፋ ይፈተናል ። የለፉለት ነገር መና ሲሆን ፣ ነገ አልታይ ብሎ ሲጨላልም ተስፋ ስንቅ ነው ። ስንቅ ለዛሬ ሳይሆን ከነገ ነው ። ተስፋ የቃል ስንቅ ነው ። ወዳጅ ለአሁን ያበላል ፣ ለመንገድ ይሰንቃል ። እግዚአብሔር ቃሉን ሲልክልን ለአሁን ጥጋብ ለነገ ተስፋ እንዲሆነን ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ ዳር እስከ ዳር የተስፋ መጽሐፍ ነው ። የአብርሃም ተስፋ በኢያሱ ፣ የአዳም ተስፋ በኢየሱስ ተፈጸመ ።

ተስፋዬ አንተ ብቻ ነህ!

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ