ወደፊት የሚኖር
የሰው ልጅ ስለ ትላንቱ በእርግጠኝነት መናገር ሲችል ስለ ወደፊቱ መናገር ግን በእርግጠኝነት አይችልም። ትላንት የነበረ ወደፊትም የሚኖር እግዚአብሔር ነው። ራሴን አደራ፣ ነገን አደራ የሚባል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ባልመጣው ቀን፣ በነገው ሕይወታችን ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ ነው። ሕፃናቱን ባየን ጊዜ ማደጋቸው፣ የወጣቶቹን እልህ ባስተዋልን ጊዜ መሰንበታቸው፣ ሽማግሌዎችን በጎበኘ ን ቊጥር አድሮ መገኘታቸው ፣ ታማሚዎችን በጠየቅን ሰዓት የነገ ሁኔታቸው ፣ መንግሥታትን በገመገምን ጊዜ የአልጋው መጽናት ፣ ትውልድን አትኩረን በተመለከትን ወቅት የነገ የአገር ዕጣ ፈንታ ፣ የሃይማኖት አባቶችን ባስተዋልን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ጉዞ ያጠራጥረን ይሆናል ። እግዚአብሔር ግን የነገ ስጋት የሌለበት፣ እንኳን ለዛሬ ለነገ የማይጠረጠር እንደሆነ እናምናለን። ትላንት ያልነበረው ነገ የማይኖረው የዛሬው ሰው የታሪክን ባለቤት ፣ የተስፋን አምላክ ከመጣበቅ በቀር ሌላ ተስፋ የለውም። እግዚአብሔር ነገ ላይ ያየው ትውልድ የሚጠበቀው እንግዳ አለው።
ነገ ሁላችንን ስታሳልፍ እርሷ ግን ተረኛውን ነዋሪ ይዛ ትቀጥላለች። ወደፊት የሚኖር ማንም የለም ። አለሁ በእግዚአብሔር እንጂ አለሁ በራሴ የማይባልበት ዓለም ነው። በዚህ ምድር ላይ ከባዱ ነገ መድረስ እንጂ ነገን መኖር አይደለም። ለቀኑ መላ አለው። ቀኑ ላይ ሲደርሱ ሁሉም ነገር ቀላል ነው። ደግሞም እግዚአብሔር የማይኖር ቀን ለማንም አይሰጥም። ነገሥታት ስለ ነገ ለሌላው ዋስትና ለመስጠት ይቅርና ለራሳቸውም ምን እንደሚገጥማቸው አያውቁም:: አገሩን በሙሉ የገዛ ንጉሥ መቀበሪያ ያጣል። ልጆቹ እንኳ የማይኖሩባትን አገር ያስተዳድራል። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልጆች፣ የደርጉ — ልጆች በአገር የሉም። ንግሥናም ከንቱ ነው። በወጅብ፣ በማዕበል፣ በወንዞች ውስጥ ሰላማዊ መንገድ የሚሰጥ፣ ከነደደው እሳት፣ ከፈላው ፍላት የሚያድን ፣ ነገን የሚቆጣጠር አምላክ አለ። ይህን አምላክ በዕድሜ የተማሩት አሟሟቴን አሳምርልኝ፣ ቀባሪ አታሳጣኝ፣ የነፍሴን መንገድ አሳምርልኝ ፣ የልጆችን ነገር አደራ ይሉታል።
ሰዎች የነገ ዋስትናቸው ያደረጉት ልጆቻቸውን፣ ጡረታቸውን፣ ሀብታቸውን ሊሆን ይችላል። የነገ ዋስትና ግን ሕያው እግዚአብሔር ነው። ሁሉን አሳልፎ ዘላለም የሚኖር እርሱ ብቻ ነው። የጌትነቱ ክብር ተነግሮ አይፈጸምም። ዘላለማዊነትንም ለሰዎችና ለመላእክት ሰጥቷል። የዚህ ዓለም መጨረሻም የእርሱ መምጣት ነውና ከዛሬ ይልቅ ነገ የተሻለና ውብ ነው። ዓለም የታጠቃቸው የጦር መሣሪያ፣ እየተራቀቀ ያለው የጦርነቱ ሳይንስ ስጋት እየሆነ ነው:: መልካቸውን የሚለዋውጡ ብዛታቸውን መቍጠር የማይቻል በሽታዎች የሰዎችን አእምሮ ተቆጣጥረው ይዘዋል። በምርጫ ሰዓት የሚነገሩት፣ የመንግሥታት የተስፋ ዳቦዎች የሰውን ልብ አድክመዋል። የነገ ተስፋ ግን እግዚአብሔር ነው። ነገ ላይ የጻፈልን መልካም ነገር ነው:: የነገው አገር፣ የልጆቻችን የሕይወት ምርጫ፣ የመንገዳችን መጨረሻ፣ የፖለቲካው ውጤት ፣ የመገፋፋቱ ድምዳሜ ያሳስበናል። ወደፊትም የሚኖር ጌታ ሁሉን ያበጀዋል።
ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም.