መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች » የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -8

የትምህርቱ ርዕስ | የእግዚአብሔር የውዳሴ ስሞች -8

የአብርሃም ጋሻ

ራሱ እግዚአብሔር ለአብርሃም ጋሻህ እኔ ነኝ ብሎታል(ዘፍ 15 ፥ 1 )

አብርሃም ከአጠገቤ ያለው ማን ነው ? የሚል የሰው ረሀብ ገጥሞት ነበር። እግዚአብሔር ማንም የለህም ብሎ ልቅሶውን አላደመቀውም። እኔ ካንተ ጋር ነኝ አለው። በብቸኝነት፣ በተከዳሁ ስሜት ላሉት ሰዎች  እገሌ የፈጸመብህ ግፍ አሞኛል ከምንላቸው ወዳጅና ታማኝ ብንሆናቸው የተሻለ ነው። እግዚአብሔር እኔ ካንተ ጋር በማለት ለአብርሃም ራሱን ሰጠው። የፍቅር ረሀብ በገንዘብ ስጦታ አይመለስም። ፍቅር በፍቅር ብቻ ይካሳል። አብርሃም ይህ ሁሉ ልፋቴ ውጤቱ ምንድነው ? የራሴ ልጅ ሳይኖረኝ 318 የአገልጋዮቼን ልጆች እንደ ራሴ አድርጌ አሳደግሁ፣ ባያስጠቁኝም የሰው ልጅ  የሰው ነው ፤ ከ318 ታማኝ አንድ የራስ ልጅ ይሻላል የሚል አሳብ እየሞገተው ነው። እግዚአብሔርም ዋጋህ ከእኔ ዘንድ ነው አለው። ሰው ዋጋ መክፈል፣ ብድር መመለስ፣ በጎን በበጎ መካስ ፣ የትላንቱን መልካምነት ለማሰብ ዙሮ የሚያይበት አንገትም ፣ የሚከፍልበት አቅምም የለውም።  ዋጋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው።  ከሰው ዋጋ ቢገኝም ትንሽ ነው። እግዚአብሔር ግን የማይጠፋ ዋጋ ይሰጣል::

አብርሃም ለሎጥ ብዬ ከአምስት ነገሥታት ጋር በቤተሰብ አቅም ጦርነት ገጠምሁ ፣ ዛሬ ባሸንፍ ነገ ጠላትን አነቃቅቼ መጥቻለሁ፣ ደግሞም ለከዳኝ ለሎጥ፣ ለራስ ወዳዱ ወንድም ይህን ያህል ዋጋ መክፈል ይገባኛል ወይ ? ይህ ሁሉ ሠራዊት ጦሩን ሲወረውርብኝ እችለዋለሁ ወይ ? ብሎ ስጋት ሲያንዣብበው ከድል ማግሥትም እግዚአብሔር ጋርዶ የሚጠብቅ ጋሻ መሆኑን ገለጠለት። እኔ ጋሻህ ነኝ አለው። በስደት ምድር፣ በዕድሜ ምሽት፣ በድንኳን ቤት ፣ ታዛቢ ዘመድ ፣ ወራሽ ልጅ በሌለበት እግዚ አብሔር አብርሃምን አላስነካህም አለው ። አብሮት የወጣው ሎጥ ከእርሱ ተለይቷል፣  በሰው አገር ላይ ጥሎት ሄዷል። ይህ ድርጊት ጠላት አብርሃምን እንዲደፍረው ፣ ሎሌ እንዲወርሰው መንገድ የሚሰጥ ነው። አብርሃም ግን ያለ አጥር የሚጠብቅ ፣ ያለ ሠራዊት የሚጥል ኃይል አለው ። እርሱም የአብርሃም ጋሻ እግዚአብሔር ነው።

የሚመክተው ጋሻ፣ የሚጠጋበት ዋሻ ላጣ እግዚአብሔር ጦር የማይበሳው ጋሻ ፣ ጠላት የማይደፍረው ዋሻ ነው::  ጠላት በሩቅ ሆኖ ሲወረውር ጋሻው ይመክታል፣  በእግሩ ሲመጣ ዋሻው ይደብቃል። እግዚአብሔር ለሚያምኑት ጋሻ ነው። ጋሻ ጭንቅላትን፣ ዓይንን ፣ ልብን የሚጋርድ ነው። አእምሮህን ጠብቅ ትልቅ ምክር ነው ። የሚወረወረው ስድብ፣ የሚሴረው ሴራ ፣ የሚገመደው ነገር፣ የሚጠነሰሰው ክስ ፣ የሚፈበረከው  ድራማ ውስጥን ሰባራ እንዳያደርግ ልብህን ጠብቅ ብሎ ወዳጅ ይመክራል። የሚያውቁት የመሰለው ሰው የማያውቁት ሲሆን፣ የበግ መንጋ ያሉት የቀበሮ ባሕታዊ ሲሆን፣ ለመዋጥም ለመትፋትም ግራ ሲያጋባ፣ እገሌም አለበት ወይ ? የሚል ማረጋገጫ ሲፈለጉ፣ ሰው የለም ተብሎ እርም ለማውጣት ነጠላ ሲያዘቀዝቁ ፣ ከሺህ ጠላት በላይ አንድ ያመኑት ከዳተኛ ሲያስገርም ወዳጅ ቀረብ ብሎ ልብህን ጠብቅ ይላል። በትልቁ ልብን የሚጠብቅ ፣ ከማበድ፣ አቅልን ስቶ  ፣ ጨርቅን ጥሎ ከመዞር የሚያድን እግዚአብሔር ነው። እርሱ የእውነት ጋሻ ነው። ጉድ ጉድ ከማለት፣ ይገርማል እያሉ በክፉዎች ክፋት  ብቻ ከማውራት የሚያድን እግዚአብሔር ነው።

የሰውነት ክፍላችን ራሱን ይከላከላል ፣ የመምረጥም አቅም አለው። አፍንጫ ክፉ ሲሽተው ይሸሻል፣ ሽቱ ይመርጣል። ምላስም መራራውን ተፍቶ ጣፋጩን ይልሳል። እጅም ሽካራውን ወርውሮ ለስላሳውን ይይዛል። እግርም ማጥና ባሕር ሲሆንበት ይመለሳል፣ ዓለቱ ላይ ይቆማል። ዓይንና ጆሮ ግን መምረጥ ይቸገራሉ። ዓይንም ክፉውን አላይም ማለት አይችልም፤ ጆሮም አልሰማም ብሎ ተደልሎ አይቀመጥም። የዓይንና የጆሮ ጋሻ  እግዚአብሔር ነው፤ በምናየውና በምንሰማው እንዳንጎዳ ይጠብቀናል። እርሱ ጋሻ ነውና። ጋሻነቱ አይታጠፍም፣ ላለፉት ሦስት ሺህ ዓመታት አብርሃምንና ዘሩን ለመጠበቅ ይህ ጋሻ እንደ ተዘረጋ ነው። እሳቱ ሲነድ ወፍ ጫጩቶቿን ለማዳን ክንፏን ዘርግታ ትቃጠላለች። እጆቹን ዘርግቶ፣ ራሳቸውን ማዳን ያልቻሉትን የሰው ልጆች የታደገ አማኑኤል ጋሻ ነው። የስቅለቱ ሥዕል የተዘረጋ እጅ ፣ የተወጠረ ደረት ያሳየናል። ከዚህ ሥዕል ጀርባ የተጋረዱ የሰው ልጆች አሉ።

ጋሻ ከቆዳም ከብረትም ይሠራል። ፍጹም ሰው ፣ ፍጹም አምላክ የሆነው ከጠላት የተጋረድንበት ፣ እሳቱን እያጠፋ ጦሩን እያጠፈ የሚያድን ጋሻችን እርሱ ነው። ወንድም ጋሻ ተብሎ ስም ይሰጣል። በለበሰው ሥጋ ታላቁ ወንድም የተባለ ወንድሞች ብሎ ሲጠራን እኛን ድሪቷሞች ያላፈረብን እርሱ ጋሻችን ነው፡፡ ሰፊ መሬትም አንድና ሁለት ጋሻ እየተባለ ይለካል። ርስታችን መኖሪያችን እርሱ ነው።

የቅርብ ዘመድ በባዕድ ምድር ላይ ጥሎን ሄዶ ይሆን? ለሰርግ ረስተውን ለልቅሶ የሚጠሩን ዘመዶች አፍርተን ይሆን? ጠላታችን በአምስት ነገሥታት የሚመሩ ሺህ ሠራዊት ሆነው ይሆን? በውጭ በቤት ፍርሃት ገጥሞን ይሆን? ዓላማዬን የሚወርስ ማነው እያልን ይሆን? ባላወቀን ማኅበረሰብ፣ ባልተገነዘበን ቤተሰብ መካከል እየኖርን ይሆን? የሠራነው ሁሉ በዜሮ ተባዝቶ ስናይ ሕመሙ ፀንቶብን ይሆን? እግዚአብሔር ዛሬ ጋሻህ እኔ ነኝ ! ጋሻሽ እኔ ነኝ ይለናል። እርሱ ለጥያቄያችን መልስ አይሰጥም፣ የጥያቄአችን መልስ ነው።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሰኔ 27  ቀን 2017 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ