የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ጸጋ

“ለእናንተ ስለ ተሰጠኝ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት በእርግጥ ሰምታችኋል ፤ አስቀድሜ በአጭሩ እንደ ጻፍሁ ፥ ይህን ምሥጢር በመግለጥ አስታወቀኝ፤” ኤፌ. 3 ፡ 2-3።

በእውነት፡- “የአገልጋዮች ጸጋ ለእኔ ስጦታ ነው ፤ አገልጋዮች ስጦታዎቼ ናቸው ። ጸጋቸው ስበድል ለንስሐ ፣ ስመለስ ለጽናት እንድበቃ እግዚአብሔር የላከልኝ አርያማዊ በረከት ነው” ብለን ለመናገር ያብቃን ። ያለ ጸጋ ማገልገል ፣ ያለ አገልግሎት በጸጋ ማደግ አይቻልም ። ያለ ጸጋ ማገልገል አገልግሎትን የትግል ሜዳ ማድረግ ነው ። ያለ አገልግሎትም ጸጋን ማሳደግ የማይቻል ነው ። መክሊትን መቅበር ፣ እሳትን ማዳፈን በጸጋ አለማገልገል ነው ። ያለ ጸጋ የሚያገለግሉ ሊኖሩ ይችላል ። ያለ አገልግሎት ጸጋ አለኝ የሚሉም ይኖራሉ ። ያለ ጸጋ ማገልገል ጸጋ ያላቸውን ለመግፋት ፣ ያለ አገልግሎት ጸጋ አለኝ ማለትም በጉራ ብቻ መኖርን ያስከትላል ። በሥራ ሳይሆን በሴራ አገልግሎትን እናካሂዳለን የሚሉ ፣ ያለ ጸጋቸው የገቡ ሰዎች ናቸው ። ጸጋው ያለው ሰው ለራሱ አይዋጋም/አይታገልም ፤ ጸጋው ይታገልለታል ። መንግሥት ያሰለጠነውን ወታደሩን መሣሪያ ያስታጥቃል ። ያ ወታደር አስቀድሞ በመንግሥቱ መንግሥትነት ማመን አለበት ። ከዚያ ሕይወቴን እሰጣለሁ ብሎ ጓዙን አሳጥሮ ይመጣል ። ከዚያም መንግሥት አሰልጥኖ መሣሪያ ይሰጠዋል ። እግዚአብሔር በባሕርይ አምላክነቱ ፣ በዘላለም መንግሥቱ አምነው ፣ ሕይወታቸውን የሰጡትን ፣ ጓዛቸውን አሳጥረው ፣ ቢቻል በድንግልና በምንኵስና ፣ ባይቻል መስቀሉን ተሸክመውና ራሳቸውን ክደው የመጡትን በቤተ ክርስቲያን ያሰለጥናቸዋል ። ምእመናንን ከዚህ ጠፊ ዓለም አትርፈው ፣ የእግዚአብሔር ገንዘብ ያደርጉ ዘንድ ጸጋን ይሰጣቸዋል ። ወታደር ነጻነትን ማስመለስና ነጻነትን መጠበቅ ትልቅ ድርሻው ነው ።

ጸጋ ያለው አገልጋይም በዲያብሎስም ባርነት ያሉትን በጸጋው ነጻ ማውጣት ፣ ነጻነታቸውን ደግሞ ጠብቀው እንዲኖሩ በትምህርት መጠበቅ ይገባዋል ። ጸጋ የእግዚአብሔር ነው ። ሀብትና ንብረት ከሰው ይገኛል ። ጸጋ ግን ከእግዚአብሔር ነው ። ጸጋው ሊኖርና ሊወሰድ ይችላል ። ጸጋ የሚኖረው በጸጋው ስንጠቀም ነው ። ጸጋ ለግል ጥቅምና ክብር አልተሰጠም ። ለእግዚአብሔር ምስጋና ፣ ለሰዎች በረከት ይሆን ዘንድ ጸጋ ተሰጥቷል ። ወታደር የታጠቀው ለግል ጥቅምና ክብር ሳይሆን ለወገን ደኅንነት ፣ ለመንግሥቱ ክብር እንደሆነ ሁሉ ፣ ጸጋ እግዚአብሔር ያለው አገልጋይም እንዲሁ ነው ። ጸጋ በመቀመጥ የሚበዛ ሳይሆን በመሮጥ የሚበዛ ነው ። ገንዘብ በባንክ ቢያስቀምጡት ዋጋውን እያጣ ይመጣል ፣ ነግደው ቢያተርፉበት ግን ከፍ እያለ ይሄዳል ። ጸጋም መክሊት ነውና በማስቀመጥ ሳይሆን በማገልገል ይበዛል ። ጸጋ ለጌትነት የተሰጠ ሳይሆን ለአገልጋይነት የተሰጠ ነው ። አገልጋይም በጸጋው ካገለገለ በኋላ ዞር ማለት ፣ የዘራው እንዲበቅል የጸሎት ውኃን ማጠጣት አለበት ። ጸጋ የፊት ፉከራ ሲቀድመው ፣ የኋላ ትዕቢት ሲከተለው ጸጋ ከሌላቸው አረማውያን በላይ የሚጥልና የሚያዋርድ ነው ። ጸጋ በራሱ መክሊት ነውና ገንዘብ ለመሰብሰብ ጸጋን መጠቀም አይገባም ። ጸጋ ሊወሰድ ይችላል ። ጸጋ የሚወሰደው የመጀመሪያው ባለማገልገል ሲሆን ሁለተኛው ምእመናን ለዚያ የተገቡ ካልሆነ ነው ። ሦስተኛው ያ ጸጋ ለዚያ ዘመንና ቦታ የማያስፈልግ ከሆነ ሊወሰድ ይችላል ። በዚህ ጊዜ አገልጋዩም ምን አጥፍቼ ነው ብሎ መጨነቅ ፣ ምእመናንም ጸጋ ተለየው ብለው አገልጋዩን ማማት አይገባቸውም ። ቋሚ የሆኑ ጸጋዎች ቤተ ክርስቲያንን ማነጽ ፣ ማስተማርና መስበክ ናቸው ። የተአምራት ጸጋዎች ግን የራቀውን ወገን የመሳቢያ እንጂ የማኖሪያ ስጦታ አይደሉም ። ተአምራት ትልቅ ነገር ቢሆን ኖሮ ጌታችን ከሞቱ በተአምራቱ ሊያድነን በቻለ ነበር ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ