የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የክርስቶስ ልደት !!!

በዚህ ዓለም ላይ በመወለዱ የዓለም ደስታ የሆነ ሕፃን ከክርስቶስ በቀር ማንም የለም ። አምላክ በትሕትና ዝቅ ያለበት ፣ ሰው በታላቅ ክብር ከፍ ያለበት ልደት ነው ። በልደቱ ሰማይና ምድር ፣ ሰውና መላእክት ፣ ሕዝብና አሕዛብ ታርቀዋል ። አስታራቂ ልደት ከክርስቶስ በቀር የትም አይገኝም ። ተዋሕዶውም ድልድይ ሁኖ የተራራቁትን አገናኝቷል ። የተወለደው ሕፃን ብቻ ሳይሆን ፍቅር ፣ ሰላም ፣ ኅብረት ተወልዷል ። ሰው መሆን ለአምላክ ውርደት ነው ፣ አምላክ መሆን ግን ለሰው ክብረት ነው ። “ክርስቶስ ዛሬ ተወለደ” እየተባለ ሲዘመር ልደቱ ታሪክ ሳይሆን ሕያው እንደሆነ እየመሰከርን ነው ። እኛ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንባል እርሱ የሰው ልጅ ተባለ ። ዳግም ሊወልደን ሁለተኛ ልደትን ከድንግል ገንዘብ አደረገ ። በምድር አባት የለኝም ለሚሉት መጽናናት እንዲሆን እርሱ ያለ አባት ተወለደ ። በምድር ላይ በአባት የተከዱ እንጂ ያለ አባት የተወለዱ የሉም ። ክርስቶስ ግን ያለ አባት ከድንግል ብቻ ተወለደ !

በዚህም ችሎታውን ፣ ደግሞም የሔዋንን ክብር መለሰ ፣ ሐፍረት ገሠጸ ። በሰማይ እናት የሌለው ክርስቶስ በቤተ ልሔም ያለ አባት ተወለደ ። በሰማይ እናታችን እርሱ ነውና የእናት እንክብካቤ አያስፈልገንም ። በምድር ላይም የእናት እንክብካቤ እስከ አካለ መጠን ድረስ ነው ። የዘላለም እናት ግን በሰማይ ያለው ፣ በዘላለማዊ ልደቱ ያለ እናት የተወለደው ነው ። እኛ ከውኃና ከመንፈስ እንወለድ ዘንድ ክርስቶስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ ተወለደ ። የልደቱን ምሥጢር ሰው ቢረዳውና ቢያስተውለው ይገርም ነበር ። የልደቱ ምሥጢር ግን ከአእምሮ በላይ ነውና ዝማሬ ያሻዋል ። እኛን ወደ ራሱ ያቀርበን ዘንድ ፣ እርሱ የእኛ ዘመድ ሆነ ። ሊለየን ስላልፈለገ ተዋሕዶውን ዘላለማዊ አደረገ ።

በዕፀ በለስ ፣ በስርቆት ያላገኘነውን አምላክነት በተዋሕዶ አገኘነው ። ከንጉሥ ምነው ብዛመድ ፣ ንጉሥ ከወጣበት ጎሣ ምነው ብወለድ ብለን እንዳንቀና አምላክ ዘመድ ሆነን ። ባሕርያችንን ተዋሕዶ አከበረው ። በሦስትነቱ ላይ አራትነት ሳይጨመርበት በመንበረ ሥላሴ የእኛ ሥጋ ተቀመጠ ። አዳምን ከአፈርነት በመንፈስ ቅዱስ እፍታ ያነሣ ፣ አፈር ሥጋችንን በመንፈሱ ተዋሐደ ። መንፈስ ቅዱስም የሥጋዌው አበጋዝ ሆነ ። አብ ለልጁ ማደሪያ የወደዳት ድንግል እንደምን ታደለች ! በእርስዋ መክበር የእኛን ክብር አየን ። ጸጋ የበዛላቸውን አገልጋዮች እንወዳለን ፣ ባለጸጋውን ክርስቶስን የወለደችውን ድንግል እጅግ እንወዳታለን ። እርስዋ ምድራዊት ኪሩብ ናት ። ኪሩቤል ሊያዩት የማይቻላቸውን በቡሩካት ዓይኖችዋ አየችው ። የዓለምን መጋቢ በድንግልናዊ ጡቶችዋ አሳደገችው ። ክርስቶስ በቤተ ልሔም ሲወለድ እኛ ከሰማይ ተወለድን ። የክርስቶስ በሥጋ መወለድ የእኛ መንፈሳዊ ልደት ነው ። በቤተ ልሔም ለሆነችው የተባረከች ልደቱ ምስጋና ይገባል !

“ዛሬ” የማይሰኝ ፣ ዘመኑ የማይቆጠር ፣ ዘላለማዊ ልደትን ከአብ የተወለደው ፤ በታወቀ ቀንና ሰዓት ከድንግል ተወለደ ። እርሱ ሁሉ በሁሉ ነው ። ዘመን የማይቆጠርለት ፣ ዘመን የሚቆጠርለትም ሆነ ። በሚቆጠር ዘመን በሥጋ እንወለዳለን ፣ ዘላለማዊ ልደትን በመንፈስ እንወለዳለን ። ለችሎታው መመርመር የሌለበት ከድንግል ተወለደ ። በዕለተ ሠሉስ ዘርን ያለ ዘር ያበቀለ ፣ ያለ ወንድ ፈቃድ ተወለደ ። ያለ ወገን ፣ ያለ ብቃታችን ሊረዳን እንደሚችል በዚህ ተገለጠ ። ከእኔ ከድሀው ለተባረከች ልደትህ ምስጋና ይገባል ። አዳም ከድንግል መሬት ያለ ወንድ ዘር ተፈጠረ ፣ ክርስቶስም ዳግማዊ አዳም ይባል ዘንድ ከድንግል ማርያም እንበለ ዘርዐ ብእሲ ተወለደ። ኦ አንክሮ ፣ መደነቅ ፣ በተመሥጦ መጥፋት ይገባል !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ