መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » የክፉ ቀኔ ነው

የትምህርቱ ርዕስ | የክፉ ቀኔ ነው

ሲመሽ አብሮኝ የዋለው የራሴ ጥላ እንኳ ይሰወራል ፣ ጦርነቱ ሲፋፋም የገዛ ልቤ ይከዳኛል ። “እየዬ ሲዳላ” ነውና በስደት በረሃ ወንድሜን ሳላለቅስ ቀብሬ እጓዛለሁ፣ እህል ውኃ ሲቀርብልኝ ልቅሶ እጀምራለሁ ። በክፉ ቀን እኔም ለእኔ አልገኝም። ለሰው የመከርኩት  ይጠፋኛል። ለሌሎች በሸታ ያዘዝኩት መድኃኒት እኔው ስታመም ይሰወርብኛል። አዋቂ  ለራሱ አያውቅም ፣ ሸክላ ሠሪም በገል ይበላል። ልብስ ሰፊ ልብሱ ቀዳዳ ነው፣ የአናጢ ቤት ጣራው ያፈሳል። ጥላዬ ሲከዳኝ ያልከዳኝን፣ ቀልቤን ስስት ያረጋጋኝን፣ አፌ በጥማት ሲደርቅ ያረጠበኝን፣ ብልሃቱ ሲጠፋኝ መንገድ ያሳየኝን፣ የአምላክ መልእክተኛ ሆኖ የመጣልኝን  ያንን ሰው ጌታዬ አስበው። የክፉ ቀን ወዳጄን ባላመሰግን ፣ በእርሱ ዓርብ ላይ የመስቀል ወዳጅ ባልሆን፣ ጎርፉ ሲጎድል ተሸክሞ  ያሻገረኝን  ባላመሰግን ከንቱ ሰው ነኝ።

ወንበዴው “በመንግሥትህ  በመጣህ ጊዜ አስበኝ” አለ ። አንተ ግን ወደ ፊትም ዛሬም እኔው ነኝ ብለህ ዛሬ አሰብከው :: ጌታ ሆይ አንተ ወንበዴን ዛሬ ስታስብ እኔ ወዳጄን ዛሬ አላሰብኩም። አንተ የግብጽ ስደት ባለ ውለታህን ስታስብ እኔ ደብተር ገዝተው ያስተማሩኝን አላሰብኩም። በማልችልበት ቀን ችለው የረዱኝን፣ በምችልበት ቀን ወድቀው ካላነሣሁ የእኔ መኖር ምንድነው? ለአጫዎች፣ ለአሞጋሽ ሳይሆን ከነጣቂ ነጥቀው ያዳኑኝን፣ ዛሬ ጠላት እቤትህ ይመጣል፣ እኔ ቤት ተጠለል ያሉኝን፣ እኔን ለማዳን የራሳቸውን ሕይወት አደጋ ላይ የጣሉትን እነዚያን ቡሩካን አቤቱ እንዳስብ እርዳኝ።

ዝንጉነቴን ገሥጸህ፣ ቀጠሮዬን ሰብረህ ዛሬ ማሰብን ስጠኝ። ከነገው ትልቅ የዛሬው ትንሽ ይሻላል። እኔም እርሱም የዛሬ ሰው ነን። ደግሞም “እኔ የምሞተው  ዛሬ ማታ ገብሱ የሚደርሰው ለፍልሰታ” እንዲሉ አነሰ በዛ ሳልል የክፉ ቀን ወዳጄን እንድደግፍ እርዳኝ። ምን ዋጋ አለው? ሁሉም ከንቱ ነው፣ የኖርኩት ኑሮ ገብስ ዘርቶ እንክርዳድ ማጨድ ነው እያለ ይሆናል። ዛሬ ላይ የሠራውን የሰው ሕንፃ ፣ የገነባውን ውለታ እንድገልጽለት እርዳኝ።

በዓለም ላይ ማጣትም ማግኘትም ጠላት ይገዛል። ሲያጡ ሁሉ ይሸሻል፣ ያጣውም ሰው ከሰው ይሸሻል። ማጣት ዓይኑ ይጥፋ፣ እግሩ ይሰበር። ማግኘትም የካደ አባት እንዲያምን ያደርገዋል። የራቀውን ሁሉ የሽንገላ ፍቅር አስጨብጦ ያመጣዋል። እጅ ሲሞላ እግሮች ይበዛሉ። በእጅ ሲሄዱ በእግር ይመጣሉ። እንዴት እኔን በለጠኝ፣ እንዴት ከልጄ በለጠ ብለው ሥር ማሽ ፣ ቅጠል በጣሽ፣ መርዝ ጠንሳሽ ይነሣል። ማግኘት ካገኙት ገንዘብ በላይ ጠላት ያመጣል። በችግር ቀን የተገኘ ግን ከሁሉ ይበልጣል። ሰውነቱን በምድር አስመስክሯል፣ በሰማይ ዋጋው ይጠብቀዋል። ሰው ማለት ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ ዕለት እንዲሉ ሁሉ ሲሸሽ የቀረበ ወዳጅ አይረሳም። ጌታ ሆይ የመስቀል ወዳጆችህ ቅድስት እናትህና ዮሐንስ ሲታወሱ ይኖራሉ። አቤቱ የዓርብ ወዳጆቼን የማስብበት ሕሊና ስጠኝ። ልቤን ልቤ አይክዳው።

አይቡን አይተው አጓቱን ይጠጡታል የዛሬውን ሳይሆን የትላንቱን ማሰብ፣ የልጁን ጥፋት ሳይሆን የአባቱን ደግነት ማየት ይገባል። እንደ ዳዊት የሳኦልን ሳይሆን የልጁን የዮናታንን ደግነት ማሰብ ይገባል። ሰውነት ዙሪያ ገባውን ማየት ነው። ጌታ ሆይ ያንን የክፉ ቀን ወዳጅ ላልጠላው  እንድወደው እርዳኝ። ውሻ እንኳ ቢመቱት ቢያባርሩት የማይሄደው የመጀመሪያውን ቀን  ደግነት አስቦ ነው:: በደግ የጻፍኩትን በክፉ እንዳልጽፈው አቤቱ ለልቤ  ልብ ስጠው።  የክፉ ቀን ወዳጄን ላልጠላ እንድወደው እጸልያለሁ።

ችግሩን ብቻ ሳይሆን ምን ውጤት ያመጣ ይሆን? ብለው የሰጉትን ፣ ስልኬ ሲጠፋ ድፍረታቸውን ያጡትን፣ ድምፄ ሲጠፋ አገር አቋርጠው የፈለጉኝን የክፉ ቀን ወዳጅን የሚያስብ ሕሊና ስጠኝ። ጠላቴን መውደድ አቃተኝ እያለ ግብዝ ሁሉ ያወራል። ወዳጅን መውደድ አቅቶት ስንቱ ከአውሬ አንሷል።

ክፉ ቀን ድንገት ይመጣል።

መከራ ሲመጣ አይነግርም በአዋጅ ፣
ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጂ ።

ክፉ ቀን ወዳጅ ያሳጣል። ባለቤቱ ለጎደለበት የሚሸሸው ሰው ይበዛል።

ክፉ ቀን አይምጣ ሰው እንዳላጣ ይባላል። ደጉ ቀን እንብላ እንጠጣ ነውና መንገደኛውም ወዳጅ ነው። አብሮ ቀን የዋለ ማታ ላይ ሲለያይ የጠባይ አናሳነት ነው። አልቃሽ ሁሉም ተኰፍሶ ቢያይ፦

አልቅሱ እንላቀስ እንተዛዘን፣
ዛሬ ለእርሱ ቢሆን ነግ ለእኛ ብለን፤

ብሏል። ዛሬ ጥይት የሚዘንበው፣ በረዶ የሚወርደው ለእርሱ ቢሆን ነግ ለእኛ ነው። የተራ ጉዳይ እንጂ ተወድዶ የማይጠላ፣ ተደላድሎ የማይሰደድ የለም። የራሱን ዓርብ እየረሳ እንጂ ሁሉም ዓርብ አለው። ዓርብ መድኃኔ ዓለም የተንገላታባት ቀን ናት። እንደውም ሌላው ሲጎዳ ብልህ ለራሱ ያለቅሳል። በክፉ  ቀን ያዘው ዘንጥለው ሲባል የሚደብቅ፣ አብሮት የበላው ሊገድለው ሲመጣ የሚያስጥል፣ የገዛ ትዳሩ ሲያድምበት ያልፋል ብሎ የሚያረጋጋ የክፉ ቀን ወዳጅ ነው ። ሊያልፍ ቀን ስንቱ ትዝብት ላይ ይወድቃል?! ከብሮ የኖረ፣ አንቱ የተባለ በሰው መከራ ላይ የበለው አዋጅ ነጋሪ ይሆናል:: ክፉ ቀን ዱዳ ያደርጋል፤ ቢያወሩም አድማጭ አይገኝም። ክፉ ቀን ቃልን መራራ ያደርጋል፤ እናንሣው ሳይሆን ምነው ሞቶ ባረፈው የሚል ተናጋሪ ያበዛል። እንዲህ ዘመቻው ሊቋጭ ፣ ዶሴው ሊዘጋ የሰው አድመኝነት ልብ ይሰብራል።  ግን የሆነው ሁሉ ሲሆን የነበረ ነው።

የክፉ  ቀን ወዳጅ እግዚአብሔር ነው። የእርሱን ጠባይ የያዙ፣ መልኩን የለበሱ የክፉ ቀን ወዳጅ ናቸው። ኩባ የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ወዳጅ ተብላ ትወሳለች፣ ጎረቤት ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወር አለሁ ብላለች። የክፉ ቀን ወዳጅ የሚለው የማዕረግ ስም ነው። ከሁሉ የሚበልጥ የክብር ስም ነው። እገሌ የክፉ ቀኔ ነው መባል መብራት ሲጠፋ መብራት መሆን ሊሸቀዳደሙበት የሚገባ ዕድል ነው። ለሰው መገኘት ያለብን ይበልጥ በክፉ ቀኑ ነው። በዚህ ቀን እንደ ጴጥሮስ አላውቀውም ብሎ መካድ ፣ እንደ ይሁዳ መሸጥ ፣ ወዳጅን ለማስያዝ ባንዳ መሆን ሳይሆን እንደ ቅድስት ድንግል ማርያምና እንደ ዮሐንስ ወንጌላዊ የመስቀሉ ሥር ወዳጅ መሆን ይገባል። ታሪክም በርክቶ ከሞት በኋላ ሲወራ ይኖራል።

ሳለቅስ አብሮኝ ያለቀሰ፣ ስከፋ አብሮኝ የተደፋ፣ እንደ ብዙኃኑ ልሁን ሳይል የመውገሪያ ድንጋይ ያላነሣ ፣ ቤቱን ልቡን ለእኔ የከፈተ፣ ከአባራሪ ቀን ያስጣለኝ፣ በማንኛውም ሰዓት ጥራኝ ያለኝ፣ ትዳሬ ፍርድ ቤት ሲያቆመኝ ጠበቃ የሆነልኝ፣ ልጄ በቁም አውርሰኝ ብሎ ሲከሰኝ አትገረም ብሎ ያረጋጋኝ፣ አገሬ ስታሳድደኝ የመውጫ መንገድን ያሳየኝ ፣ እጄ ሲነጥፍ ያረጠበኝ፣ ልጅ ሲታመምብኝ የደረሰልኝ — የክፉ ቀኔ ነው፣ ጌታ ሆይ ለኖረልኝ እንድኖር እርዳኝ።

በዚህ ቀን ለክፉ ቀን ወዳጆቻችሁ አለሁ በሉ። የምስጋና ዕዳችሁን ክፈሉ። ታመው እንደሆኑ ጠይቁ፣ ይህ ቀን ዕድል ነው ፣ ብትታዘዙ ከጸጸት ትድናላችሁ ! ውለታን የማይረሳ ጌታ ያከብራችኋል። ተመስገን የጎደለንን አስታወስከን ፣ ልትባርከን ሰበብ ትፈልጋለህ።

ነሐሴ 6 ቀን 2017 ዓ.ም .

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ