የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የውሳኔ ሰው

“የማትናከስ ከሆነ ጥርስህን አታሳይ ።” ስፔናውያን

በዚህ ዓለም ላይ ማንም ላይ አልደርስም ፣ ስለዚህ ክፉ አያገኘኝም ማለቱ ከንቱ ስሌት ነው ። ሰው ላይ መድረስ ደስ የሚላቸው ብዙ ሰዎች አሉ ። የተኛውን በሬ ቆስቁሰው ቆስቁሰው አውሬ የሚያደርጉ ፣ ዝምተኛውን እንደ መብረቅ የሚያስጮኹ ፣ መስመሩን ጠብቆ የሚጓዘውን ከመስመር የሚያስወጡ አያሌ ናቸው ። እነዚህ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ ሕግም መንግሥትም አስፈላጊ አይሆኑም ነበር ። ልንጠነቀቅ የምንችለው ሰዎችን ላለመንካት ነው ፣ እንዳይነኩን የምናደርገው ጥንቃቄ ላይሰምር ይችላል ። በዚህም ሁለት ነገሮችን እናስታውሳለን፡- የእግዚአብሔር ትእዛዝ እኛን እንጂ ሰዎቹን እያየ የተሰጠ አይደለም ። አትስረቅ እንጂ አይስረቁህ አይልም ። ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ እንጂ እንደ ራሳቸው ይውደዱህ አይልም ። የእግዚአብሔርን ቃል ለራሳችን ማንበብ እንጂ ለሰዎቹ ማንበብ ጥቅም የለውም ። ሁለተኛው ነገር እየበረረና መስመር ስቶ የመጣ መኪናን እየበረርን መስመር ስተን ብንጋጠመው አደጋው ሰው ለወሬ ነጋሪ የማይተርፍበት ነው ። አደጋውን ማስቀረት ባይቻልም መቀነስ ግን ይቻላል ። ከማንም ሰው ጋር ያለን ቆይታ አጭር ነው ። የዚህ ዓለም ዘመኖች በእርቦ የተሰፈሩ እፍኝ ናቸው ።

ሰዎች መስመራቸውን ጠብቀው የማይሄዱት የመጀመሪያው መስመራቸውን አለማወቃቸው ነው ። መስመራቸውን የሚስቱት የመጀመሪያ እኛ እግር እያላቸው እንዘላችሁ ፣ እጅ እያላቸው እናጉርሳችሁ በማለታችን ነው ። ሰዎችን ማንቀራበጥ ለጊዜው ደስ ይላል ። አቅማችን የተወሰነ ፍጡራን ነንና አንድ ቀን ይደክመናል ። የለመዱትን ያጡት ቅምጥሎቻችን እንደ መብት ይጠይቁናል ። እኛው መስመሩን አበላሽተንባቸው እኛው እንበሳጫለን ። ለግንኙነቶቻችን መበላሸት የመጀመሪያ ተጠያቂዎቹ እኛ ነን ። ብላታ ወልደ ጊዮርጊስ፡- የሰው ዘፋኝ ተጫውቶ በመጨረሻ ገንዘብ አምጡ በማለቱ ደስታን ይቀንሳል ። ቢከለክሉት ይሳደባል ።።

ሰዎች መስመራቸውን ጠብቀው የማይሄዱት በአስተዳደጋቸው ያልተገሩ ሆነው ሊሆን ይችላል ። ሰዎች የሚኖሩት የአስተዳደጋቸውን ውጤት ነው ። አስተዳደጋቸውን ደጋግመው ይኖሩታል ። በጊዜ ሂደት እንደተጣመሙ በጊዜ ሂደትም ሊቃኑ ይችላሉ ። አማካሪ እቤቱ ፣ ሐኪምም እመኝታው ክፍል ሳይሆን ሥራው ቦታ ያክማል ። ያልተገሩ ሰዎችንም ወደ ኑሮአችንና ወደ ትዳራችን አካባቢ አምጥቶ መግራት ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል ። ስፍራና ጊዜ መድበን ማነጽ ግን መልካም ነው ። አንድ ሰው መልካምነትን ገንዘብ ሲያደርግ ከዚህ በኋላ ለሚያገኙት ሰዎች መልስ እንጂ ጥያቄ እንዳይሆን እናደርገዋለን ። እኛ ዋጋ ከፍለን ሰዎቹን እናሳርፋለን ። ከሁሉ በላይ ያንን ሰው በማትረፋችን እግዚአብሔር ይደሰትብናል ። ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ፡- “አንተ ከሥጋና ከነፍስ መከራ ስትድን ከምትደሰተው በላይ እግዚአብሔር በመዳንህ ይደሰታል።”

ሰዎች መስመር የሚስቱት በአእምሮ መዛባት ሊሆን ይችላል ። በሱስ ውስጥ ካሉ ፣ በኃጢአት እስራት ከተተበተቡ መስመር ይስታሉ ። ኃጢአት ከእኛ ፣ ከሰዎችና ከእግዚአብሔር የሚጠበቀውን እንዳናውቅ ያደርጋል ። ቢሆንም አህያ ረገጠን ብለን ፈረስ መሆን አይገባንም ። “ከለማበት የተጋባበት” እንዲሉ ። ሰዎች መስመራቸውን ስተው መስመራችንን የሚያውኩት ሊቋቋሙት ያልቻሉት ቅናት ስላሳበዳቸው ሊሆን ይችላል ። በዚህ ዓለም ላይ እንደ ቀናተኛ የተቸገረ የለም ። የሚረዳው የእርዳታ ድርጅት ግን እስካሁን አልተቋቋመም ።

የሊባኖሱ ፈላስፋ ካህሊል ጅብራን፡- “አዋቂ ሰው ሁለት ልብ አለው ፤ አንዱ ሲደማበት በሁለተኛው ይታገሣል” ብሏል ። ላለመጎዳት ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል ። የተወረወረው ጦር ሥጋችንን እንዳይነካ መከላከል አንችል ይሆናል ፤ ልባችንን እንዳይነካ ግን በጸሎትና በእውቀት መከላከል ይቻላል ።

በዚህ ዓለም ላይ ስንኖር ረባሾችን በብዙ መንገድ ማስታገሥ ይቻላል ። የመጀመሪያው የጸጋ መንገድ ነው ። እግዚአብሔር ሰባት ቢሊየን ሕዝብን ተሸክሞ እኔ አንድ ሰው ብሸከምለት ተገቢ ነው በማለት መቻል ቀላል ነው ። ሁለተኛው የሕግ መንገድ ነው ። ሕግ በዓለም ላይ ገደብ እንጂ ፍቅር አይሰጥም ። ሦስተኛው በተሰጠን ሥልጣን መጠን ክፉዎችን ማስታገሥ ነው ። ብዙ ጊዜ መንግሥት ትዕግሥተኛ ሁኖ ነው ይላሉ ። መንግሥት ሥራው መታገሥ ሳይሆን ሕግ ማስከበር ነው ። የሚታገሥማ የተበደለ ነው ። አባት ፣ መምህር ፣ ንጉሥ የማያደርጉትን ነገር ከመናገር ዝም ቢሉ ይሻላቸዋል ። አደርጋለሁ ያሉትን ሲያደርጉ በሚያስተዳድሯቸው ዘንድ ክብር ያገኛሉ ። ቢሆንም የአባትም ፣ የመምህርም ፣ የንጉሥም ሥልጣን የተገደበ ነው ።

ዝምታ የማይፈታ ቅኔ ነው ፣ ሊቃውንት አይደርሱበትም ። ዝምታ እንደ ፈላስፋ እንድንታይ የሚያደርግ ነው ፣ ሰዎች አይንቁትም ። ዝምታ የተከፈቱ አፎችን የሚያዘጋ ነው ፣ ተሳዳቢዎች አይዳፈሩትም ። ዝምታ ሁልጊዜ መልካም አይደለም ። ዝምታ በውስጡ እግዚአብሔርን መጠበቅ ሲኖርበት ኃይል አለው ። ላይቀጣ የሚፎክር አባት ፣ ላይገዝት ዋ የሚል መምህር ፣ ሕግ ላያስከብር ሕግ የሚተነትን ንጉሥ ይናቃሉ ። ብቻ ስፔናውያን፡- “የማትናከስ ከሆነ ጥርስህን አታሳይ” ብለዋል ። አባቶች ይወስናሉ ፣ ውሳኔአችን የት ደረሰ ካላሉ ፣ መምህራን ያስተምራሉ ፣ ትምህርቴ ምን እያፈራ ነው ብለው ካልመዘኑ አደገኛ ነው ። ሁልጊዜ ፎካሪ ፣ ሁልጊዜ ዋ ባይ ሆነን ከመናቅ ዝም ማለት ያስከብራል ። ሥርዓት አልበኞች አፋችንን ሳይሆን ልባችንን ያደምጣሉ ። ውሳኔአችንን አሊያም ዝምታችንን ይፈራሉ ።

ጥርሳችን መንከስ ፣ ውሳኔአችን መከበር ሲጀምር መስመር የሳቱ ሰዎች ወዲያው ዝቅ ይላሉ ። ዝቅታው ግን የመለወጥ ሳይሆን ስሜታችን እስኪበርድ ነው ። ስሜታውያን ሳይሆን እውነታውያን መሆናችንን ሲያረጋግጡ መስመራቸውን ይይዛሉ ።

አቤቱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ የቀናውን መንገድ ምራን ።

የብርሃን ጠብታ 16
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ጥቅምት 19 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ