የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የይሉኝታ ነዋሪ

የስድብ ክፉ “አቅሙን አያውቅ” የሚለው ነው ። ሦስት ነገሮች ለኑሮአችን አስፈላጊ ናቸው፡- እነርሱም አቅምን ማወቅ ፣ በልክ መኖር ፣ በኑሮአችን መደሰት ናቸው ። አቅማችንን ባለማወቃችን ለታላላቅ ጭንቀቶች እንዳረጋለን ፣ በልክ ባለመኖራችን ልጆቻችንን ነገ የማይዘልቅ ነገር እናስለምዳቸዋለን ። በዚህ ምክንያት ለዛሬ ጭንቀት ፣ ለነገ ፍርሃት አለብን ። የምንኖረው በጎረቤት አቅም ሳይሆን በራሳችን አቅም ነው ። እነዚያ የሌላቸው እኛ ያለ ጸጋ አለ ። በሁሉ ነገር ሙሉ ፣ በሁሉ ነገርም ጎዶሎ አይደለንም ። ደስታ የሚመጣውን በመቀበል ሳይሆን የያዝነውን በመቀበል የሚገኝ ነው ። በእጁ የያዘው ቀሎበት ከምስጋና የጎደለ ብዙ ሰው አለ ። በርግጥ ከምንቀበለው የተቀበልነው ይበልጣል ። በልካችን መኖር ደስተኛ ያደርገናል ። ከጎረቤት ጋር መወዳደር የራሳችንን ኑሮ እንዳንኖረው ፣ በመንጠራራት መሬት እንድንለቅ ፣ ሳናውቀው ቀናተኛ እንድንሆን ያደርገናል ። ይሉኝታ ከአቅማችን በላይ በመኖር ፣ የነገውን በጀት ዛሬ ላይ እንድንበላው ያደርገናል ። የለኝም ማለት ሐፍረት የሚሆንብን ጊዜ ብዙ ነው ። የለውም እንዳይሉን አይገቡ ቦታ እንገባለን ። የሚያሳፍረውን ከማያሳፍረው መለየት አልቻልንም ።

ፈጥኖ ምላሽ መስጠት ብዙ ጊዜ ዋጋ ያስከፍላል ። ከተበሳጨን አለመናገር ፣ ስሜታዊ ከሆንን እሰጣለሁ ብለን ቃል አለመግባት መልካም ነው ። ስንበሳጭ ዓለም ሁሉ ተሳስቶ እኛ ብቻ እውነተኛ የሆንን ይመስለናል ። ብስጭት የራሳችንን ጉድለት ፣ የሰዎቹን መልካምነት ይጋርድብናል ። ስሜታዊ ስንሆንም ሁሉም ነገር ያለን መስሎ ስለሚሰማን እሰጣለሁ ብለን ቃል ለመግባት እንቸኩላለን ። አምጡ ስንባልም ከቦታው እንጠፋለን ፣ የስልክ ቍጥራችንን ቀይረን እንጠፋለን ። ይህ ሁሉ እግዚአብሔር ያላሸከመን ሸክም ነው ። ይሉኝታ ግን ካላሰብንበት እንድንውል ፣ በሌለን ነገር እሰጣለሁ ብለን ቃል እንድንገባ ያደርገናል ። ዓለምን ለመለወጥ የምናደርገውን ጥረት አቁመን ራሳችንን መለወጥ ያስፈልገናል ። እኛ ስንለወጥ ዓለሙ ይለወጣልና ። ከባለጸጋ ጋር ጽዋ መጠጣት ሥርን ይነቅላል ። በአቅም መኖር ብቻ ሳይሆን በአቅም መዋልም ያስፈልጋል ። እነዚያ ቀሏቸው የሚያደርጉትን እኛ ሥራችን ተነቅሎ እናደርገዋለን ። ልጆቻችን እንዲያዝኑልን ፣ የሚከፈልላቸው ዋጋ እንዲገባቸው ፣ ነገ ላይ ለወጡበት ቤት ራእይ እንዲኖራቸው በልካችን ማሳደግ ይገባናል ። የልጅን ፍቅር የምናተርፈው ብዙ በመስጠት አይደለም ። በገንዘባችን የገዛናቸው ሲመስላቸው ልጆች እየጠሉን ይመጣሉ ። ለዚህ ነው የድሀ ልጅ ወላጆቹን በጣም ሲወድድ የባለጠጋ ልጅ ግን ለወላጆቹ ግድ የለውም ። ሁሉንም ማለታችን አይደለም ።

በሕይወት ላይ ከእግዚአብሔርም ፣ ከሕሊናም ፣ ከገንዘባችንም የማንሆንበት ጊዜ አለ ። እርሱም በይሉኝታ የምናደርገው ነገር ነው ። የይሉኝታ አድራጎታችን በእግዚአብሔር ዘንድ ግብዝ ያሰኘናል ። በሕሊና ፊትም ውሸታም የሚል ስም ይሰጠናል ። የሆንነውን መሆን እንጂ ያልሆነውን እንደሆነው ለመምሰል መሞከር ከንቱ ነው ። ብዙዎች ያልሆኑትን ሲመስሉ ይሰነብታሉ ፣ ወደ ትዳር ሲገቡ ግን እውነተኛው ማንነት አልደበቅ እያለ ሰላም ያጣሉ ። ያኛው ሰውም ይህን ጠባይ እሸከመዋለሁ ብሎ ተዘጋጅቶ እንዲገባ ማስመሰልን ማቆም አለብን ። ሳያውቁ የወደዱን ፣ ሲያውቁን ከጠሉን በጣም ያሳፍራል ። ባለጠጋ ለመሆን መሥራት አንፈልግም ፣ ባለጠጋ መስለን ከተማ መዞር ግን እንፈልጋለን ። የቅብ ኑሮ ፀሐይ ሲወጣ የሚቀልጥ ነው ፣ ሳያውቁ ያከበሩን ለዘላለም ይንቁናል ። ፊታቸውን ሜካፕ የተቀቡ ኀዘናቸውን ለመግለጥ ማልቀስ እንኳ አይችሉም ። ከውስጥ ስሜታቸው ፣ ከደጅ ልፋታቸው እየታገላቸው በሽተኛ ይሆናሉ ። ይሉኝታ ስሜትን እንኳ እንዳንገልጥ ያደርገናል ፣ የቅብ ኑሮ ነውና ። የሚያስጨንቅ ስንት ነገር እያለ ጭንቀት የምንፈጥረው ለምን እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው ።

የብድር ኑሮ አድካሚ ነው ። አብዛኛው ኑሮአችን ደስ ያለንን ማድረግ ሳይሆን ብድር መመለስ ላይ የተመሠረተ ነው ። የማንም አያልፍብኝም የሚል ንግግር አለን ። የእኛ ወደ እነርሱ ሊያልፍ የእነርሱም ወደ እኛ ሊያልፍ ይችላል ። ወዳጅነት ልብን መሰጣጠት እንጂ በቁስ የሚለካ አይደለም ። ወዳጅነት ቃል ኪዳን ነው ። ቢወድቅ ልናነሣው ፣ ቢሞት ልጆቹን ልናሳድግለት ግድ የሚለን ነው ። ወገኖቼ እባካችሁ አብሮ መብላት ቀላል አይደለም ። ይሉኝታ የብድር መመላለስ ኑሮ ውስጥ ይከተናል ። ለወዳጅ የሚሰጠው ትልቅ ስጦታ ገና አለና ባደረግነው መኩራት አይገባንም ። ክቡር ቃሉ እንዲህ ይላል፡- “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” ዮሐ. 15፡13።

ልብን ኩላሊትን በሚፈትን አምላክ ፊት አልዋሽም ብለን እውነተኛ ኑሮ መኖር ይገባናል ። የሕልውናችን መሠረት እግዚአብሔር ብቻ ነው ። ሰው የሕይወታችንን መብራት ለማብራትም ለማጨለምም ድርሻ የለውም ። የእኔ ሕይወትና የእኔ ጉዳይ በእግዚአብሔር እጅ ነው ብለን በእምነት መኖር ይገባናል ። ዕለታዊ ኑሮአችን የይሉኝታ እስረኛ ነው ። ሰዎችን በጣም እንፈራለን ። ተረታችንም፡- “ይሉሽን ብታውቂ ገበያ ባልወጣሽ” የሚል ነው ። ሰዎችን እኛ የምንላቸው ፣ በሕሊናችን የሰጠናቸው መልክ አለ ፣ ሰዎችም እኛን የሚሉን ነገር አለ ። የምባለውን አላውቅምና ገበያ አልወጣም ካለች በረሀብ መሞትዋ ነው ። ሰዎች መልካም ቢሉን መልካም ፣ ክፉ ቢሉን ክፉ አንሆንም ። የምንሆነው የሆነውን ነው ። ደግሞም ትርፉም ኪሣራውም የእኛው ነውና ሰዎች ለሚሉን ነገር መጨነቅ አይገባንም ። ስመኛ አገርና ዘመን ሲገጥመን ንቀን መኖር ይገባናል ። ወረኞችን የሚያነግሣቸው የሰጠናቸው ጆሮ ነው ። በልባችን ዋጋ ሊኖራቸው የሚገባው የሚጸልዩልን ሰዎች ብቻ ናቸው ። የሚሸፍኑንን ትተን የሚገልጡንን ማክበር ነውር ነው ። ይሉኝታ ከግለሰብ ወደ አገር የሚያድግ ነውና ልንጠነቀቀው ይገባል ።

እግዚአብሔር ከይሉኝታ ሰንሰለት ይፍታን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 17 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ