የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመጀመሪያው ፋሲካ

“የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ”
/ዮሐ. 2፡13/፡፡
 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ አራት ፋሲካዎችን አክብሯል ፡፡ በአራተኛው ፋሲካ ላይ ራሱን እውነተኛ ፋሲካ አድርጎ አቅርቧል ፡፡ እንደሚያሳልፈው እያወቀ አልነቀፈውም ፣ አላሳነሰውም ፡፡ እስከ ተወሰነለት ጊዜ እንዲኖር ፈቀደ ፡፡ እርሱም አከበረ ፡፡ እስከ መጨረሻው ማክበር ተገቢ መሆኑን ሲያስረዳ ይህን አደረገ ፡፡ የከበሩትን እስከ መጨረሻ ማክበር ፣ ወዳጆችን እስከ መጨረሻ መውደድ ፣ የሚቸገሩትን እስከ መጨረሻ መርዳት ተገቢ ነው ፡፡ ክብርን ውርደት ፣ መውደድን  ጥላቻ ፣ መርዳትን መሰልቸት ሲተካው አሳዛኝ ነው ፡፡ በዚሁ በዮሐንስ ወንጌል ፡- “ኢየሱስም ከፋሲካ በዓል በፊት፥ ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ አውቆ፥ በዚህ ዓለም ያሉትን ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው” ይላል /ዮሐ. 13፡1/ ፡፡ ይህኛው ፋሲካ አራተኛ ያልነው ፋሲካ ነው፡፡ በዚህ ለሞት በተቃረበበት ሰዓት ደቀ መዛሙርቱን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው ፡፡ እስከ መጨረሻ የሚወድድ እርሱ ብቻ ነው ፡፡ የሰው ፍቅር ኮንትራት ነው ፡፡ የበለጠ ካገኘም የዛሬ ሰው በጨረታው አይገደድም ፡፡ እንዳከበረ ዝም ቢል ፍቅሩን በልቡ እንደ ያዘ ጥላቻውንም በልቡ ቢይዝ መልካም ነበር ፡፡ ፍቅሩን በግሉ ፣ ጠቡን በአዋጅ ማድረጉ ዘመናችንን የሚያስወቅስ ነገር ነው ፡፡ ደቀ መዛሙርቱን እስከ መጨረሻው ስለ ወደዳቸው እርሱ በተያዘበት ቀን ተበትነው አልቀሩም ፡፡ ጴጥሮስም እንደ ካደ አልቀረም፡፡ የእርሱ ፍቅር የመመለስ ዋስትና ነው ፡፡

የብሉይ ኪዳን ፋሲካ እስራኤላውያን ከግብጽ ምድር በድንቅ መውጣታቸው የሚታሰብበት ፣ ግብጻውያንን የገደለ ቀሳፊ እነርሱን እንዳይገድል የፋሲካው በግ አጋጅ እንደ ነበር የሚታወስበት ነው ፡፡ እስከ አዲስ ኪዳን ምሳሌ ሁኖ ቆይቷል ፡፡ ሥዕላዊ መግለጫ የሆነውን ፣ ክርስቶስ እስኪመጣ በጥላ ያገለገለውን ፋሲካ ጌታችን በክብር አስቀመጠው ፡፡ የመጣበትን የረሳ የሄደበት ይጠፋዋል ፡፡ ምንም ትንሽ ቢሆን ትላንት ያለፍንበት ነገር ለዛሬው መሠረት ነው ፡፡ ሁሉም ነገር ዛሬ ጀመረ ማለት የዘመናችን በሽታ ነው ፡፡ ዛሬ ትላንት አላት ዛሬ ነገ አላት ፡፡ ትላንት የሌላትን ዛሬ ከፈጠርን ነገ የሌላትን ዛሬ እንፈጥራለን ፡፡ እንዳጠፋነው እንጠፋለን ፡፡ ትላንት ላስተማሩን ፣ ትላንት ለረዱን ፣ ትላንት ላጽናኑን ዋጋ መስጠት ይገባል ፡፡ ጌታ ለፋሲካ ዋጋ ሰጠ ፡፡ ስለዚህ ለማክበር ወጣ ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ጌታችን አምስት ጊዜ ያህል እንዳከበረ ተዘግቧል ፡፡ የጀመረው በ12 ዓመቱ ነው /ሉቃ. 2፡41/፡፡
“የክፉ ቀን ሚስት ያን ክፉ ቀን መስላ ትታያለች” ይባላል ፡፡ ለምን ትታያለች ? የዛሬውን ደስታ መካፈል ያለባት ክፉውን ቀን የተካፈለች ያች ሴት ናት ፡፡ ሰው ግን መከራውን የሚተወው ከመከራ ዘመን ጓደኞቹ ጋር ነው፡፡ መከራውን መርሳት የደገፉንን ማስታወስ ይገባል ፡፡ ምእመናን በጭንቃቸው ያጽናኑአቸውን አገልጋዮች ይጠላሉ ፡፡ በደስታ ጊዜአቸው ሌላ አባት ይፈልጋሉ ፡፡ በሌላው ዓለም እገሌን አውቀዋለሁ አብሮኝ ብዙ አሳልፏል በማለት ስለ ወዳጅ መከራከር ላሳለፉት ዘመን ዋጋ መስጠት የተለመደ ነው ፡፡ እንዲህ ያለ ውለታ በላ ትውልድ እንዳናተርፍ መጠንቀቅ ያስፈልገናል ፡፡ የአገልጋዮችን ሞት የሚመኙት ከሞት የዳኑት መሆናቸው ያሳዝናል ፡፡ ጌታችን ግን ፋሲካን ለማክበር ወጣ ፡፡
 በእኛ አገላለጽ የብሉይ ፋሲካ እያጣጣረ ነው ፡፡ በአዲሱ ሊተካ እየተቃረበ ነው ፡፡ ጌታችን ግን አንድ ቀን ሲቀረውም አከበረው ፡፡ ትላንት ያገናኘ ፣ እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት የሆነ ፋሲካ አንድ ቀን ቢቀረውም ጌታ አከበረው ፡፡ በበለጠም ፋሲካ ተክቶት ዘላለማዊ አደረገው እንጂ አልደመሰሰውም፡፡ ትላንት ያገናኙን እግዚአብሔርን ለማመስገን ምክንያት የሆኑን ሰዎች ምናልባት ዛሬ ጤናን ከስረው እቤት ቀርተው ይሆናል ፡፡ እስከ መጨረሻው ቀን ልንጎበኛቸው ልናከብራቸው ይገባል ፡፡ የቁመና ወዳጅ መሆን ተገቢ አይደለም ፡፡ ሰው ክቡር ነው ፡፡ የሰው ውለታ እንዴት ይረሳል ? ደግነታቸውን መልካምነታቸውን አርአያ በማድረግ የጀመሩትን መልካምነት በማስቀጠል ዘላለማዊ ልናደርገው ይገባል እንጂ እርሱ እኮ እያልን መተረክ ተገቢ አይደለም ፡፡ ደጎችን በሕይወት ምርጫችን ማሰብ እውነተኛ ዝክር ነው ፡፡ ሰው ክቡር ነው ፡፡ ክርስቶስ የሞተለት ሥጋው እንኳ በክብር ማረፍ በጸጥታ መቀመጥ አለበት ፡፡ ዛሬ እንኳን የቆመው ሬሳም ተፈናቃይ መሆኑ ያሳዝናል ፡፡ የሰው ዋጋ ከወደቀ የዓለም ዘመን አጭር ነው፡፡ ዓለም የተበጀው ስለ ሰው ነው ፡፡ ሰው ግን ለዓለም አልተበጀም ፡፡ ዓለም ለሰው ፣ ሰው ለእግዚአብሔር ክብር ተፈጥሯል ፡፡ ስለ ደን መመናመን እንደምናስብ ስለ ሰው ክብር መመናመን ልናስብ ይገባል ፡፡ ስለ ጠፈር ሳይንስ ስናጠና ጎዳና ስለ ወደቁት ልጆችም ማዘን ያስፈልጋል ፡፡
 ፋሲካ ታሪካዊ ዳራው ምንድነው ? የእስራኤል ልጆች በግብጽ ምድር 430 ዓመታት በግዞት ቆዩ ፡፡ እግዚአብሔርም መከራቸውን አይቶ ለአባቶቻቸው የገባውን ኪዳን አስቦ ሊያድናቸው ወደደ ፡፡ በዚህም ርኅራኄውን ደግሞም ታማኝነቱን ገለጸ ፡፡ ፈርዖን ግን ሊለቃቸው ፈቃደኛ ባለመሆኑ 10 መቅሰፍትን በግብጽ አገር ላይ አወረደ ፡፡ 11ኛው መቅሰፍት ግን ፈርዖንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ ነው ፡፡
መቅሰፍቶቹ፡-
1-  የውኃ ወደ ደም መለወጥ
2-  ጓጉንቸር
3-  ቅማል
4-  ዝንብ
5-  ቸነፈር
6-  ቁስል
7-  በረዶ
8-   አንበጣ
9- ጨለማ
10- ሞተ በኩር
መቅሰፍቶቹ ፡-
1- ግብጻውያንን በሚያምኗቸው አማልክት የቀጣ ነው
 ግብጻውያን በጓጉንቸር ፣ በቅማል መልክ ያመልኩ ነበርና በአማልቶቻቸው መልክ ቀጣቸው ፡፡ በሚያምኑት ተቀጡ ፡፡ እግዚአብሔር ከእርሱ በቀር ሌላ አምላክ እንዲመለክ አይወድምና የአምልኮ ዘማዎችን በሚያምኑበት ነገር መቅጣቱ የተለመደ ነው ፡፡ ዛሬም በምናምነው ሰው ፣ በወደድነው ንብረት የምንቀጣው ለዚህ ሊሆን ይችላል ፡፡
2- ለፈጸሙት ግፍ ተመሳሳይ የነበረ ነው  
 በእስራኤል ሕጻናት ደም የዓባይ ወንዝ ቀልቶ ነበርና ወንዙ ወደ ደም ተለወጠ ፡፡ እስራኤል ለእግዚአብሔር የበኩር ልጅ ነውና የበኩር ልጁን ስለገደሉ ሞተ በኩር ታዘዘ ፡፡ እግዚአብሔር በማንም ላይ ቅጣት አይመዝም፡፡ በቆፈሩት ጉድጓድ እየጣለ ፣ በገመዱት ጅራፍ እየገረፈ ፣ ለሌላው መቅጫ ባዘጋጁት ነገር እየቀጣ ይፈርዳል ፡፡
3- በተናቀ ነገር ግብጻውያንን ያዋረደ ነው
 ፈርዖን የዓለም ተፈሪ ንጉሥ ነበር ፡፡ ግብጽ የዚያኛው ዘመን ልዕለ ኃያል አገር ነበረች ፡፡ ይህን ትልቅ አገዛዝ እግዚአብሔር በቅማልና በአንበጣ አንበረከከው ፡፡ እግዚአብሔር ሲነሣ ኃያላን ነን የሚሉ እንኳን ለክንዱ ለጣቱም አይመጥኑም ፡፡ እግዚአብሔር የት ቦታ ሲመቱ አቤት እንደሚሉ ያውቃልና የመጨረሻው መቅሰፍት ሞተ በኩር ሆነ ፡፡ ፈርዖን እግዚአብሔር ማነው ? ብሎ ነበርና እግዚአብሔር ማንነቱን በኤርትራ ባሕር ደፍቆ አሳየው፡፡ በዚህም እስራኤል የፈርዖንና የሠራዊቱን ፍርሃት ለዘላለም ጣለላቸው ፡፡ ሬሳቸውን አይተዋልና ፡፡ ግብጽም በእስራኤል ልጆች መከራ ስቃለችና አንዱ አንዱን ማጽናናት እስከማይችል በሁሉም ቤት ልቅሶ ሆነ ፡፡ ሰው ባይሞት ከብት ይሞት ነበር ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በግብጽ ዙፋን ላይ የሚቀመጠው በኩር ልጅ ነው ፡፡ ስለዚህ በዚያ ሌሊት የግብጽ አልጋ ወራሽ ሞተ ፡፡ ፈርዖንን ግን አልነካውም ፡፡ አገር ያለ መሪ እንዳይሆን አስቦአልና ፡፡ ፈርዖን ግን እስራኤልን ለመመለስ እንደገና በመነሣቱ በኤርትራ ባሕር ወድቆ ቀረ፡፡ ግብጽ በዚያ ቀን ያለ ንጉሥና ያለ አልጋ ወራሽ ቀረች ፡፡ እግዚአብሔር የት ቦታ ሲመቱ አቤት እንደሚሉ ያውቃል ፡፡
 10ኛው መቅሰፍት ሞተ በኩር ሊመጣ ሲል እግዚአብሔር እስራኤልን አስጠነቀቀ ፡፡ ያንን ቀሳፊ መልአክ አጥርና ዘብ አይመልሰውም ፡፡ ቤተ መንግሥቱም ተደፍሯል ፡፡ የእስራኤል ልጆች የፋሲካውን በግን እንዲያርዱ ደሙንም በቤታቸው መቃንና ጉበን ላይ እንዲቀቡ ታዘዙ ፡፡ የፋሲካው በግ ምንድነው ? ሥጋው ለመንገድ ጥጋብ የሆነው ፣ ደሙ ቅጥር የሆነው ያ የፋሲካ በግ ከቶ ማነው?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ