የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከውኃና ከመንፈስ መወለድ


“ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው” /ዮሐ. 3፡3/፡፡ ልጅነትን በተመለከተ በዮሐንስ ወንጌል ለሁለተኛ ጊዜ የተነገረ ነው ፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም”/ዮሐ.1፡12-13/፡፡ ወንጌላዊው ይህን ቃል የተናገረበት ምክንያት ወልድ በሚታይ ልደት እንደ መጣ ወይም ቃል ሥጋ እንደሆነ ሊተርክ ነው ፡፡ እኛ ከሚታይ ልደት ተወልደን እንደገና ከማይታይ ልደት እንወለዳለን ፡፡ የሚታይ ልደት ያለው የማይታይ ልደት እንዴት ይወለዳል? ቢባል የማይታይ ልደት ያለው ቃል የሚታይ ልደት እንደ ተወለደ ማሰብ ነው ፡፡ እርሱ የሰው ልጅ ሲሆን እኛ የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን ፡፡ ለኒቆዲሞስ ዳግም ልደት የተነገረው የእግዚአብሔር መንግሥት የምትወረሰው በልጅነት መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ 
ሰው ዳግመኛ ሳይወለድ የመንግሥቱ ጥገኛ ፣ የጌትነቱ ሎሌ ሆኖ መኖር ይችላል ፡፡ የጥገኝነቱ ዋጋ ፣ የሎሌነቱ ደመወዝ መብልና መጠጥን እያገኘ እስከ ጊዜው ይኖራል ፡፡ ከጌታው ፍቅርና ውርስን ተስፋ አያደርግም ፡፡ በዚያ ረክቶ የኮንትራት ሰው ሁኖ ይኖራል ፡፡ ልጅነት ግን ባለ መንግሥቱን አባት ማድረግ ፣ የውርሱን ሰነድ በዚህ ዓለም ማየት በሚመጣው ዓለም መውረስ ነው ፡፡ በዚህ ዓለም የተወለደ ልጅ ነገ የሚወርሰውን ሰነድ ፣ የአባቱን የሀብት መጠን ሲያይ ይኖራል ፡፡ አባቱ በሕይወቱ የተናዘዘለትን በአባቱ ሞት ይወርሰዋል ፡፡ እስከዚያው ሀብቱ በጥቂቱ እየተቆነጠረ ማደጊያ ይሆነዋል ፡፡ አባቱ የሞተ ቀን ግን ውርሱ ይጸናለታል ፣ ሀብቱ ይዞርለታል ፡፡ እንደዚሁ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ሀብቱን አሳወቀ ፡፡ የመንግሥቱን ሰነድ ለሚፈልጉ ገለጠ ፡፡ በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ አለ በማለት የመቆያው ዓለም ያታከታቸውን ሰዎች ልባቸውን አነሣሣ /ዮሐ. 14፡2/ ፡፡ ኑዛዜው እንዲጸና እርሱ መሞት ነበረበትና ሞተ ፡፡ ይኸው በተስፋ ወረስን ፡፡ በሚመጣው ዓለም ያንን ሀብት መቀበል በሚችል ማንነት በትንሣኤ አካል ሁነን ርስቱን እንቀበላለን ፡፡ ሞቶ የሰጠንን ሞተን እንቀበላለን ፡፡ ሞት ከክርስቶስ ጋር የህልውና መነሻ ነው ፡፡ ለመነሣት መሞት ያስፈልጋል ፡፡ ሞት ሁለት ዓይነት ሲሆን ትንሣኤም በዚያው መጠን ሁለት ዓይነት ነው ፡፡ ለእኔነት ስንሞት ትንሣኤ ልቡና እናገኛለን ፡፡ እርሱም ዳግመኛ መወለድ ነው ፡፡ በሥጋ ስንሞት ደግሞ ትንሣኤ ሙታን በሚሆንበት ጊዜ በሥጋ እንነሣለን ፡፡ ትንሣኤው እንደ አሟሟቱ ነው ፡፡ በረቂቅ የሞቱ በረቂቅ ይነሣሉ ፡፡ በሥጋ የሞቱ በሥጋ ይነሣሉ ፡፡ የልቡና ትንሣኤ የፈቃድ ነው ፡፡ የሥጋ ትንሣኤ ግን የግድ ነው ፡፡ የልቡና ትንሣኤ የተወሰኑትን የሚያካልል ነው ፤ የሥጋ ትንሣኤ ግን ለሁሉም ነው ፡፡ ከጥገኝነት ወራሽነት ፣ ከሎሌነት ልጅነት ያለበትን ዳግም ልደት ለኒቆዲሞስ በመጀመሪያ ፣ ቀጥሎ ለእኛ ገለጠልን ፡፡ ጌታ በአንድ ሰው አሳብቦ ለብዙ ሰው ይናገራል ፡፡ በብዙ ሰው ፊትም ለአንድ ሰው ይናገራል ፡፡
ጌታችን ለኒቆዲሞስ እየተናገረ ነው ፡፡ ነገር ግን ሰውን አድራሻ ያደረገ መልእክት እየተናገረ ነው ፡፡ “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ” አለ ፡፡ ለኒቆዲሞስ ለግሉ የተነገረ ተግሣጽ እንዳይመስለው ፣ እኛም እኛን አይመለከትም እንዳንል “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ” አለ ፡፡ እግዚአብሔር ሰውን የሚቀበለው በልደት መንገድ ነው ፡፡ ማንም ባል ሚስቱን በአካልነት ፣ ማንም አባት ልጁን በልጅነት ካልተቀበለ ከባድ ነው ፡፡ ባርያን እንደ ልጅ ማየት ይቻል ይሆናል ፡፡ ልጅን እንደ ባሪያ ማየት ግን ከባድ ነው ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን በልጅ መዐርግ ተቀብሎታል ፡፡ በአዳም ውስጥ ከበደልን በአዳም ውስጥ ልጆች ሁነናል ፡፡ ለዚህ ነው ዳግመኛ መወለድ የሚል ቃል የመጣው ፡፡ በመጀመሪያው አዳም ውስጥ የመጀመሪያውን ልደት እንደ ተወለድን በሁለተኛው አዳም በክርስቶስ ውስጥ ሁለተኛውን ልደት እንወለዳለን ፡፡ ሁለተኛ ሊወልደን ሁለተኛ ተወልዷልና ፡፡ የመጀመሪያው ልደት በኃጢአት ፈረሰ ፡፡ አንዱ አዳም በድሎ እኛንም ወክሏልና አብረን በደልን ፡፡ መሪውን የያዘው ሾፌር ገደል ሲገባ አብረው የተሳፈሩት ብዙዎች አብረው ይገባሉ እንጂ ብዛታቸው ለመዳን ምክንያት አይሆንም ፡፡ አንዱ አዳምም ለብዙዎች ውድቀት ምክንያት ሆነ ፡፡ አንዱ ክርስቶስ ደግሞ ለብዙዎች ጽድቅ ምክንያት ሆኗል ፡፡ የመጀመሪያው ልደት የታሰበው በአዳም በኩል ለሰው ሁሉ እንደሆነ ዳግመኛ መወለድም ለሰው ሁሉ የተሰጠ መብት ነው ፡፡ ይህ ልደት ግን ፈቃድ ያለው ልደት በመሆኑ ከሥጋ ልደት ይለያል ፡፡ ለዚህ ነው አዳም ያጣው ፡፡ ለዚህም ነው በማመን የምንቀበለው፡፡
“ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው” /ዮሐ. 3፡3/፡፡ መላልሰን እንመልከተው ፡፡ ጌታ እውነት እውነት እልሃለሁ ማለቱ አጽኦት ለመስጠት ነው ፡፡ ዳግም ልደት የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን የጽድቅና የኩነኔ ጉዳይ መሆኑን ሊገልጥለት ነው ፡፡ አብርሃም አብርሃም ሲል ቀጥሎ የሚነገረውን በተጠንቀቅ ሊሰማውና ሊኖረው የሚገባ መሆኑን ያሳያል ፡፡ ዳግም ልደት የምንዘለው አማራጭ አይደለም ፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታችንን ፡-  “መምህር ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደ መጣህ እናውቃለን አለው” /ዮሐ. 3፡2/ ፡፡ ኒቆዲሞስ ጌታችንን እንደ አንድ ነቢይ መቀበል አልከበደውም ፡፡ ዳግም ልደት ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ ብቸኛም መድኃኒት መሆኑን ማመን ይጠይቃል ፡፡ ኒቆዲሞስ እናውቃለን አለ ፡፡ ጌታችን የሰጠው ምላሽ ግን የሚያስገነዝበን ነገር አለ ፡፡
1-  ከእምነት እንዲጀምር ነገረው ፡፡ የእውቀት መጨረሻው ማመን ነው፡፡ እውቀት መጨረሻው ማመን ካልሆነ እውቀቱ ወደ አለማወቅ ይለወጣል ፡፡
2-  ኒቆዲሞስ እናውቃለን በሚለው ንግሩ ተጨማሪ እውቀት ፍለጋ የመጣ ነው ፡፡ የጌታችን መልስ ግን ያወቅኸው ካላሳረፈህ አሁንም ለማወቅ ብቻ የምታደርገው ጥረት ጥማትህ ይባባሳል እንጂ አይታገሥም ሲለው ነው ፡፡
3-  ኒቆዲሞስ ተጨማሪ ነገር ፈላጊ ነው ፡፡ ግማሽ ሙሉ ነኝ ብሎ የሚያስብ ነውና ከመጀመሪያ እንዲጀምር ነገረው ፡፡
ኒቆዲሞስ የክብርና የመከባበከር ግንኙነት ላይ ብቻ ለመመሥረት የፈለገ ይመስል ይሆናል ፡፡ ለእውቀት እንቅልፍ አጣ ፡፡ ጥያቄውን ባያውቀውም ጥያቄውን ጠይቆ የመለሰለት ግን ጌታችን ነው ፡፡ ጌታችን ስለ ዳግም ልደት በተናገረበት ክፍል ውስጥ፡-
1-  አጽንኦት የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን
2-  ሰውን ሁሉ የሚመለከት እውነት እንደሆነ
3-  ልደት ዓለምን ማያ እንደሆነ /ባንወለድ ይህን ዓለም አናየውም ነበር ፡፡ ካልተወለድንም ያኛውን ዓለም አናየውም /፡፡
4-  በምን እንደሚወልድ / በውኃና በመንፈስ/
5-  የመወለድ ግቡ መንግሥቱን መውረስ መሆኑን
6-  ይህ ልደትም ውጫዊ ማረጋገጫ ስሜታዊ መለኪያ የሌለው በእምነት የሚቀበሉት በኑሮ የሚገልጡት መሆኑን
7-  ይህ ልደት የተሰቀለውን ጌታ በማየት የተመሠረተ እንዲሁም የሚጸና መሆኑን አስረግጦ ያስረዳል ፡፡
“ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው” /ዮሐ. 3፡3/፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ጉዳዩ ግራ አጋባው ፡፡ “ኒቆዲሞስም፡- ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው” /ዮሐ. 3፡4/፡፡ ኒቆዲሞስ አንድ ነገር የገባው ይመስላል ፡፡ ጌታ የተናገረው ሰውን ሁሉ የሚመለከት መሆኑን ተረድቷል ፡፡ ጌታ አይችልም የሚል ቃል ተናግሯል ፡፡ ኒቆዲሞስ ደግሞ እንዴት ይችላል? የሚል ጥያቄ አቀረበ ፡፡ ኒቆዲሞስ እንዴት መወለድ ይችላል? የሚለው ጥያቄ አስጨነቀው ፡፡ ጌታችን ደግሞ መወለድ ሳይሆን አለመወለድ ከባድ መሆኑን ገለጠለት፡፡ ኒቆዲሞስ አሁንም የሚያስበው ስለ ሥጋ ነው ፡፡ ጌታችን ስለ መንግሥተ ሰማያት የሚናገር ከሆነ የሥጋ ልደት ለመንፈሳዊ ዓለም ምንም አይጠቅምም ፡፡ ዓለሙን የሚመስል ልደት ከሌለ ዓለሙን መውረስ አይቻልም ፡፡ ይህ ዓለም ግዙፍ ዓለም ነውና ግዙፍ ልደት እንዳስፈለገ የሚመጣው ዓለም ረቂቅ ስለሆነ ረቂቅ ልደት አስፈልጓል ፡፡
“ኒቆዲሞስም፡- ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል? ሁለተኛ ወደ እናቱ ማኅፀን ገብቶ ይወለድ ዘንድ ይችላልን? አለው” /ዮሐ. 3፡4/፡፡ ኒቆዲሞስ መሢሑን የሚጠብቀው የላሉ ሕጎችን ያጠብቃል ፣ የራቁ ክብሮችን ይመልሳል ብሎ ነው ፡፡ መሢሑ ግን ለማሻሻያ ወይም ለከፊል ለውጥ ሳይሆን ለፍጹም ለውጥ እንደሚመጣ አልተረዳም ፡፡ መሢሑ ሕጉንና መመሪያዎችን በአደባባይ የሚያወግዝና የሚተች አይደለም ፡፡ በአዋጅ የሾመው ራሱ እግዚአብሔር ያንን ሕግ በአዋጅ ሊሽረው አልፈለገም ፡፡ ምክንያቱም አክብሮ ማዋረድ ባሕርዩ አይደለምና ፡፡ ታዲያ ከዚያ ገዥ እንዴት መላቀቅ ይቻላል? ቢባል ጳውሎስ እንደገለጠው አንዲት ሴት ባሏ ሳለ በኪዳኑ ታስራለች ፡፡ እርሱ ከሞተ ነጻ ትወጣለች ፡፡ እርስዋ ከሞተችም ነጻ ትወጣለች ፡፡ እርሱ ከሞተ ሌላ ባል ያሻታል ፡፡ እርስዋ ከሞተች ግን ለጌታ ብቻ ትኖራለች ፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ሕጉን በመግደል ሳይሆን እኛን ለዚህ ዓለም አሠራር እንድንሞት በማድረግ ለእርሱ እንድንኖር አድርጎናል /ሮሜ . 7፡1-3/፡፡ አዲሱንም ኑሮ የምንቀበለው በመወለድ ነው ፡፡
ኒቆዲሞስ በጌታችን ንግግር ግራ አልተጋባም ፡፡ የጌታችን ንግግር ፈሪሳዊ ክብሩን ፣ ያለውን ባለጠጋነት ያላገናዘበ ደግሞም የጽድቅ ሥራውን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ስለመሰለው ነው ፡፡  የፌዝ ንግግር ይመስላል ፡፡ ኒቆዲሞስ ትልቅ አዋቂ ነው ፡፡ ጌታችንም ዝቅ ብሎ፡- “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?”ብሎታል /ቁ.10/፡፡ ዳግም ልደት ታላቅ ዕድልን ላገኙ ሰዎች የሚነገር ነው ፡፡ “እገሌ ዛሬ ነው የተወለደው” ይባላል ፡፡ ታላቅ ደስታን አመልካች ቃል ነው ፡፡ አንድ ሰውም ወደ አይሁድ ሃይማኖት ሲገባ ይህ ቃል ይነገርለታል ፡- “እገሌ ዛሬ ተወለደ” ኒቆዲሞስ ግን ላሳለፈውና ለደከመበት ኑሮ ምንም ዋጋ ያልተሰጠ ሲመስለው ይህን አለ፡
የኒቆዲሞስ ጥያቄ ግን ልደቱ እንዴት እንደሚገኝ ማብራሪያ እንዲሰጥበት አድርጓል ፡፡ “ኢየሱስም መለሰ፥ እንዲህ ሲል፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” /ቁ . 5/፡፡ ስለ ማኅጸን አንሥቷልና ውኃው ማኅጸን ፣ መንፈስ ቅዱስ ወላጅ መሆኑን ነገረው ፡፡ ልጅነቱ በዚህ ዓለም የሚጀምር ፣ በሰማይ የሚቀጥል ነውና ውኃው ከዚህ ዓለም ፣ መንፈሱ ከሰማይ መሆን ነበረበት ፡፡ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባልና የሰማይ ዜጋ የሚኮንበት ነውና የአጥቢያው መሪ ቄሱ በውኃ ፣ የሰማዩ መሪ በመንፈሱ ማጥመቅ አለባቸው ፡፡ ዮሐንስ የውኃውን ጥምቀት በምሳሌ ሲያሳይ ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀትን በተስፋ ሰብኳል ፡፡ ጌታችን ሁለቱንም አበሰረ ፡፡ ዮሐንስ ንስሐ የሚገቡትን ኑዛዜአቸው ብቻ ይበቃል ሳይል በውኃ አጠመቀ ፡፡ እንዲሁም ማመን ብቻውን አይበቃም ፡፡ የማመን ምልክት የሆነውን ጥምቀት መቀበል ያስፈልጋል ፡፡ ዳግም ልደት ዓለምን የመካድ ሥርዓት ነውና በአዋጅ መጠመቅ አስፈልጓል ፡፡ ይህ ነገር እንግዳ ሳይሆን በጥንተ ፍጥረትም የሆነ ነው ፡፡
“እግዚአብሔርም አለ ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሾች ታስገኝ” ተብሎ ተነግሮ ነበር /ዘፍ. 1፡20/ ፡፡ ውኃ እንደ ማኅጸን ሁኖ የሕያዋን ተንቀሳቃሽ ፍጥረታት መገኛ እንዲሆን ታውጆ ነበር ፡፡ ይህ በጥንተ ፍጥረት የተነገረ አዋጅ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ከውኃ ውስጥ ሕያዋን ተንቀሳቃሾን ጠርቶአል ፡፡ እንዲሁም በአዲስ ኪዳን ሕያዋን የሆኑት ማለት በክርስቶስ ሞት የዳኑት ፤ ተንቀሳቃሽ የሆኑትንማለት እምነታቸውን በምግባር የሚገልጡት ሠራዊት ወይም አማንያን በጥምቀት ይገኛሉ ፡፡  ጥምቀት የጌታችን አዋጅ ነው ፡፡ እርሱ ጥምቀትን ከማወጁ በፊት አርአያ ሁኖ ተጠምቋል ፡፡ በጌታችን ጥምቀትም ፡-
1-  ታላቅ ጽድቅ ተገልጦአል፡- ከሚበልጥ አገልጋይ እጅ መጠመቅ ትሕትና ነው ፡፡ በባሪያ እጅ መጠመቅ ግን የትሕትና ትሕትና ነው ፡፡ በማቴዎስ ወንጌል የላቁ ጽድቆች ተገልጠዋል ፡፡ አንዱ በስውር የመተው ጽድቅ ነው /ማቴ. 1፡19/፡፡ ሁለተኛው በሚያንሱን የመገልገል ጽድቅ ነው /ማቴ. 3፡15/ ፡፡ ሦስተኛው ጠላቶችን የመውደድ ጽድቅ ነው /ማቴ. 5፡47/ ፡፡ ጌታችን ወደ ዮሐንስ ዘንድ ሂዶ ጥምቀትን መፈጸሙ ጌቶችና ባለጠጎች መጥታችሁ አጥምቁን እያሉ እንዳይቀናጡ አርአያ ለመሆን ነው ፡፡ ስለዚህ ጥምቀት ሄደን ፣ ፈልገን በቤተ ክርስቲያን የምንቀበለው ነው ፡፡ በግላችን እንደ ጸሎትና ጾም መፈጸም የምንችለው ሳይሆን የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ብቻ የሚያከናውነው ነው ፡፡
2-  የሥላሴ ምሥጢር በገሀድ ተገልጦአል ፡- ወልድ በለቢሰ ሥጋ በፈለገ ዮርዳኖስ ውስጥ አብ በደመና በምስክርነት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል በመውረድ ለዘመናት የተሰወረው የሥላሴ ምሥጢር ተገልጦአል ፡፡ ጥምቀትና የሥላሴ ምሥጢር በጣም ተያያዥ ነው ፡፡ ጌታችንም የጥምቀትን ትእዛዝ ሲሰጥ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ አዝዟል /ማቴ . 28፡19/ ፡፡ በጥምቀት የምንወለደው ከአንዱ የሥላሴ አካል ሳይሆን ከሥላሴ ነው ፡፡ በዚህም አብም አባት ወልድ አባት መንፈስ ቅዱስም አባት ነው ፡፡ ለኒቆዲሞስም በተነገረው ክፍል ላይ ወላጅ ሁኖ የተጠቀሰው መንፈስ ቅዱስ ነው ፡፡ “ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ” ይላልና ፡፡ በሥላሴ መንግሥት አንድ ወላጅነት አለ ፡፡
3-  የወልድ ልጅነት ተመስክሯል ፡- አብ የወልድን ጌትነት አዳኝነት ሳይሆን ልጅነቱን መስክሯል ፡፡ በዚህም በጥምቀት ልጅነታችን እንደሚመሰከር እንረዳለን ፡፡ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ ተብሎአል ፡፡ ውኃ የሚለው ጥምቀትን ነው ፡፡ 
“እግዚአብሔርም አለ፡- ውኃ ሕያው ነፍስ ያላቸውን ተንቀሳቃሽ ታስገኝ” እንደ ተባለ ብዙ የእምነት ሠራዊት በጥምቀት ተገኝቷል ፡፡ ውኃ ከሰው ልጅ ጋር ሰፊ ግንኙነት አለው ፡፡ “እግዚአብሔር አምላክም፡- ሰውን ከምድር አፈር አበጀው ፤ በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስን እፍ አለበት ፤ ሰውም ሕያው ነፍስ ያለው ሆነ” ይላል /ዘፍ. 2፡7/፡፡ የሰው ልጅ የሁለት ነገር ውሁድ ነው ፡፡ ከአፈርና ከመንፈስ ተፈጥሯል ፡፡ እስትንፋስ ወይም ነፋስ ወይም መንፈስ አንድ ትርጉም ነው ፡፡ አፈር የተባለው ሌላው መጠሪያ ውኃ የሚል ነው ፡፡ በሰው ውስጥ ያለው የሚበዛው ውኃ ነው ፡፡ ሦስት አራተኛ የሰው ልጅ አካል ውኃ ነው ፡፡ ሰው ብቻ ይሆን ምድርም ሦስት አራተኛዋ ውኃ ነው ፡፡ ነገር ግን ምድር ወይም አፈር ተብላ ትጠራለች እንጂ በሚበዛው ውኃውኃ የሚል መጠሪያ አላገኘችም ፡፡ እንዲሁም ሰው ከአፈር ተፈጠረ ስንል ከውኃና ከመንፈስ ተፈጠረ ማለታችን ነው ፡፡ ምድር ማለት ማኅደር ወይም መክተቻ ማለት ነው ፡፡ እንዲሁም ዳግም ለመወለድ እነዚህ ሁለት ነገሮች መተባባር አለባቸው ፡፡ እነርሱም ውኃውና መንፈሱ ናቸው ፡፡ ውኃው መክተቻ ማኅጸን ወይም መቃብር ነው ፡፡ ጥምቀት ከክርስቶስ ጋር መቀበርም ነውና ፡፡ ውኃ ብቻውን መንፈሱ ብቻውን አይሆንም ፡፡ እንደ ቃሉ ከውኃና ከመንፈስ መወለድ ያስፈልጋል ፡፡ ውኃው ምን ይሠራል መንፈሱ ብቻ ማለት አንችልም ፡፡ ምሥጢር ነውና ፡፡ ምሥጢር ማለት በሚታይ ሥርዓት የማይታይ ጸጋ የመቀበያ መንገድ ነው ፡፡ ጥምቀት የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤን የምንተባበርበት ነው ፡፡ ክርስቶስ የሞተው ለሥጋችንም ነው ፡፡ ስለዚህ ሥጋችን በግዙፉ ውኃ መሳተፍ አለበት ፡፡ ግዙፍ ሥርዓቶችን ማቅለልና መቃወም ምንጩ የግሪኮች የአማልክት ፍልስፍና የወለደው በኋላም ግኖስቲኮች ያስፋፉት በዘመነ ቤተ ክርስቲያን መናፍቃን የተከተቡበት ነው ፡፡ ቁሳዊው ትውልዳችን ቤትና መኪናን እንደ ትልቅ በረከት ሲቆጥር ግዙፍ ናቸውና ጥምቀትና ቁርባንን ግን ዋጋ የላቸውም ብሎ ያምናል ፡፡ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ