ጌታችን የዘላለም ሕይወትን የሚመለከቱ ነገሮችን ግልጽ ፣ አጭርና ቀላል በሆኑ ነገሮች ገልጾአል፡፡ ሰዎች አልገባንም ብለው በቋንቋ ሐረግ ውስጥ እንዳይደበቁ ፣ ረዝሟልና ለመመልከት ጊዜ አጣን እንዳይሉ፣ ከብዶአልና ለመፈጸም አቅም የለንም እንዳይሉ ግልጽ፣ አጭርና ቀላል አደረገው ፡፡ ለኒቆዲሞስም መዳንን በሚመለከት የተነገረው ቃል ምንም ትርጓሜ የማያሻው ግልጽ ነው ፡፡ አዋቂ ለነበረው ለኒቆዲሞስ የተነገረ ነው እንዳይባል አዋቂውም አልገባውም ፣ ጌታም “ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ” በማለት ለሰው ሁሉ ተናገረ፡፡ ረዝሟልና ጊዜ ሳገኝ አጠናዋለሁ እንዳይባል በአንድ ቁጥር ውስጥ የተነገረ መልእክት ነው ፡፡ ለመፈጸም አቅም የለኝም እንዳይባል ርካሽ በሆነው በውኃ፣ ውድ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ የሚፈጸም ነው ፡፡ ከፍ ያለ ነገር ቢጠይቀን ለመፈጸም እንቸገራለን ፡፡ ትንሹንም ነገር ጠይቆን መፈጸም ተቸግረናል ፡፡ ሥጋዊው አስተሳሰብና ሥጋዊው ተፈጥሮ መንፈሳዊውን ዓለም መውረስ አይችልም ፡፡ ስለዚህ ዳግም መወለድ አስፈላጊ ሆነ ፡፡ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ሊገባ አይችልም” ውኃ የሚለው ጥምቀትን አይደለም የሚል አሳብ የሚያነሡ ሰዎች አሉ፡፡ ጥምቀት በዚህ ክፍል ብቻ ሳይሆን በጌታችን ዋነኛ ተልእኮ ውስጥ ሲጠቀስ የነበረ ነው /ማቴ. 28፡19/፡፡ ጌታችን ሁሉንም ትምህርቶችና ሥርዓቶች በቃል ሲያስተምር ጥምቀትን ግን ራሱ በመፈጸም አርአያ የሆነበት ነው /ማቴ.3፡13-17/፡፡ ጉዳዩ ትርፍ ነገር ሳይሆን በግድ የምንፈጽመው መሆኑን ያስረዳል ፡፡ የጌታችን ታላቅ ተልእኮ ተብሎ በሚጠራው ክፍል ላይ ጥምቀት ከቃለ እግዚአብሔር ጋር ተጠቅሶአል ፡፡ ጥምቀት መወለጃ ሲሆን ቃሉ ደግሞ ማደጊያ ደቀ መዝሙር መሆኛ ነው /ማቴ.28፡19-20/፡፡ ስለ ድኅነት በተነገረ ክፍል ላይ “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” ተብሎ እምነትና ጥምቀት አንድ መሆናቸው ተገልጦአል /ማር.16፡16/፡፡ እንዲሁም ጥምቀት የኃጢአትን ስርየትና የመንፈስ ቅዱስ ስጦታን ለመቀበል ቀዳሚ ሁኖ ተጠቅሶአል /የሐዋ. 2፡38/፡፡ ጥምቀት ከኃጢአት ስርየት ጋር እንደተያያዘ በውስጡም እምነት፣ ምስክርነት፣ ኑዛዜና ልጅነትን እንደሚያስገኝ እንረዳለን ፡፡
በዮሐንስ ጥምቀት ብቻ የነበሩ በጌታችን ስም ተጠምቀዋል ፣ ከዚያም የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብለዋል /የሐዋ .19፡5/፡፡ በመንፈስ ብቻም አይልም ፡፡ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ በውኃ ተጠምቀዋል ፡፡ “በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ መልሶ፦ እነዚህ እንደ እኛ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ እንዳይጠመቁ ውኃን ይከለክላቸው ዘንድ የሚችል ማን ነው? አለ” /የሐዋ. 10፡47/፡፡ አንዱ ብቻ በቂ ቢሆን ይበቃል በተባለ ነበር ፡፡
እምነት ብቻውን በቂ ነው እንዳይባል ያመነው ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ በውኃ ባገኘ ጊዜ ከመጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድነው ብሎ ተጠምቋል /የሐዋ. 8፡36/፡፡ ጥምቀትን ከቃሉ ፣ ከእምነትና ከመንፈስ ቅዱስ ለመለየት የሚደረግ እንቅስቃሴ አለ ፡፡
ጥምቀትና ቃሉ
ጥምቀትና ቃሉ የማይቃረኑ ነገር ግን የተስማሙ ናቸው ፡፡ ምክንያቱም ጥምቀትን ያወቅነው በቃሉ ነውና ፡፡ በመጠመቃችን ቃሉን እናከብረዋለን እንጂ አናቃልለውም ፡፡ ጥምቀት ቃሉን መተካት የለበትም ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ ፡፡ ጥምቀት ግን ቃሉን ተፈጻሚ ያደርገዋል እንጂ አይሽረውም ፡፡ ምክንያቱም ስለ መንፈሳዊ ነገር የሚያወራው ያው ቃል ስለ ግዙፉ ሥርዓት ስለ ጥምቀትም ይናገራልና፡፡ ቃሉና ጥምቀት አንድ ናቸው የምንለው ሁለቱም የመጡት ከእግዚአብሔር ነው ፡፡ ሁለቱም የሚሠሩት በእምነት ነው ፡፡ ሁለቱም ተፈጻሚነትን ማግኘት አለባቸው ፡፡ ልዩነታቸው ቃሉ ለሁሉ ሲነገር ጥምቀት ግን ለሁሉ አይፈጸምም ፡፡ ጥምቀት የክርስትና የመጀመሪያ ተግባር እንጂ የፍጻሜ ተግባር አይደለም ፡፡ ሁልጊዜ መሠረት የለም ፣ መሠረት አንድ ጊዜ ሲሆን ዕድገት የማያቋርጥ ነው /ዕብ. 6፡1-2/፡፡
ጥምቀትና እምነት
ጥምቀት እምነትን ተጨባጭ ያደርገዋል እንጂ አያጠፋውም ፡፡ እምነት በልባችን የምንቀበለው ሲሆን ጥምቀት ደግሞ በአዋጅ የምንመሰክረው ነው ፡፡ እምነት ውስጥን በመቀበል ሲገዛ ውጭን ደግሞ በምስክርነት ይገዛል ፡፡ እምነት እግዚብሔር ያዘዘውን ነገር ከልብ መቀበል ሲሆን ጥምቀት ደግሞ ያንን ተግባራዊ ለማድረግ የዋህ መሆን ነው ፡፡ ለዚህ ነው ያመነ የተጠመቀ የሚለው ፡፡ ያመነ ይጠመቃል፣ የተጠመቀም ያምናል ፡፡ ሁለቱ የሚለያዩ ነገሮች አይደሉም ፡፡ እንደውም ለመጠመቅ የሚከለክል አለማመን ነው ፡፡ እንዴት በውኃ የሚል ፍልስፍና ነው ፡፡ እምነት ግን በውኃው ይህን አገኛለሁ ብሎ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አሠራር በውኃው ውስጥ ይህ ይፈጸማል ብሎ ይበላል ፡፡ እምነት ብቻውን በቂ ነው የሚሉ ወገኖች የሚጠቅሱት ነገር የላቸውም ፡፡ ጥምቀትን አቃለውም እንደገና ካልተጠመቃችሁ ይላሉ ፡፡ ጥምቀትን የሚያከብሩትም የሚንቁትም ይኸው ሲፈጽሙት ይታያል ፡፡ የሚጠቀሰው ፈያታዊ ዘየማን ወይም በጌታ ቀኝ የተሰቀለው ወንበዴ አልተጠመቀም የሚል ነው ፡፡ ለጥምቀት አርአያ ሁኖ በማየ ዮርዳኖስ በዕደ ዮሐንስ የተጠመቀውን ጌታን ትቶ ዳግመኛም ያመነ የጠጠመቀ ያለውን ትእዛዛ ችላ ብሎ ወንበዴውን መጥቀስ ከእምነት ለመሸፈት ማሰብ እኔም ወንበዴ ነኝ ብሎ መናገር ነው ፡፡ ወንበዴው አለመጠመቁ ታሪክ እንጂ መመሪያ አይደለም ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ታሪኩ ሁሉ መማሪያ እንጂ መመሪያ ላይሆን ይችላል ፡፡ ቀጥተኛው ትእዛዝ ምን ይላል ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል ፡፡ ቀጥተኛው ትእዛዝ ተጠመቁ የሚል ነው፡፡ ወንበዴው ያልተጠመቀው ፍልስፍና ውስጥ ግቶ ሳይሆን የነበረው ጊዜ ለማመን እንጂ ለመጠመቅ ስለማይበቃ ነው ፡፡ ጊዜ እያላቸው የማይጠመቁ ግን ከመጠየቅ ነጻ አይደሉም ፡፡
ጥምቀትና መንፈስ ቅዱስ
ጥምቀት ያለመንፈስ ቅዱስ የተሟላ አይደለም ፡፡ አንድ ጽንስ የወንድና የሴት አስተዋጽኦ ከሌለ ጽንስ እንደማይሆን ጽንስ የሁለት ነገሮች ማበር ውስጤት እንደሆነ እንዲሁም ጥምቀት የውኃውና የመንፈስ መተባበር ነው ፡፡ ቀድሞም አዳም ሲፈጠር ከምድር አፈር ከተበጀ በኋላ በመንፈስ ቅዱስ ሕይወት አግኝቷል፡፡ የመጀመሪያው አዳም ከድንግል መሬት በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተፈጠረ እንዲሁም ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ ከድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ተወልዷል ፡፡ ወደ ቀደመው ልጅነት እንድንመለስም ከውኃና ከመንፈስ መወለድ አስፈልጎናል ፡፡ የመጀመሪው ታሳቢ ባይሆን ሁለተኛ አይባልም፡፡ የመጀመሪያው የአዳም ልደት ታሳቢ ስለሆነ ይህ ሁለተኛ መወለድ ተብሏል ፡፡ ዳግም ልደት የመጀመሪያውን ልደት ይመስላል ፡፡ ክብሩ ግን ይልቃል ፡፡ ምድርን ሳይሆን ሰማይን ያወርሳል ፡፡ በአራዊት ላይ ሳይሆን በረቂቃን ተዋጊዎች ላይ ድል ይሰጣል ፡፡
እግዚአብሔር በውኃ አማካይነት ብዙ ነገሮችን አድርጓል ፡፡ የንዕማን ለምፅ በዮርዳኖስ ወንዝ ነጽቷል ፡፡ ጌታችን የፈወሰው ዓይነ ሥውርም በሰሊሆም መታጠቢያ መታጠብ እንዳለበት ተነግሮታል ፡፡ ውኃ በራሱ ለምፅ ማንጻት ፣ እውር ማብራት ስለሚችል ሳይሆን የእግዚአብሔር ኃይል ስለተገለጠበት ነው ፡፡ እንዲሁም ጥምቀት የምንፈጽምበት ውኃ በራሱ ማድረግ ስለሚችል ሳይሆን እምነት ፣ ቃሉና መንፈስ ቅዱስ ስለ ተዋሐዱት ነው ፡፡ ይህንን የምቀበለውና የምንባረከው በእምነት ነው ፡፡ ጥምቀት ማለት መነከር ፣ መረጨት፣ መቀበር የሚል ትርጉም አለው ፡፡ ከእነዚህ ትርጉሞች የተነሣ ጥምቀት በሦስቱም መንገድ መፈጸም ይችላል ማለት ነው ፡፡ በመነከር ወይም በማፍሰስ ፣ በመርጨትና በማጥለቅ ሊፈጸም ይችላል ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥምቀት እንጂ ስለአፈጻጸሙ ወጥ ትእዛዝ አልሰጠም ፡፡ ይህ የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ነው ፡፡ በዓለም ላይ ያሉና በዘመናት ውስጥ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በሦስቱም መንገድ ይፈጽማሉ ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ሦስት የታወቁ ጥምቀቶች አሉ ፡፡ የአይሁድ ጥምቀት ፣ የዮሐንስ ጥምቀትና የክርስትና ጥምቀት ይባላሉ ፡፡ ጥምቀቶቹ በየጊዜው እያደጉ መጥተዋል ፡፡ የአይሁድ ጥምቀት ውጫዊ ቅድስናን የሚያጎናጽፍ ነበር ፡፡ በድን የነካ፣ ለምፅ የነበረበት በዚህ ውኃ ይታጠብ ነበር ፡፡ ከዚህ ይልቅ የዮሐንስ ጥምቀት የንስሐ ስለነበር ነፍስን አድራሻ ያደረገ ነው ፡፡ ከሥጋ ወደ ነፍስ አደገ፡፡ የክርስትና ጥምቀት ግን ሥጋን ፣ ነፍስንና መንፈስን ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ጋር የሚያስተባብር ነውና ከሁሉም የላቀ ነው ፡፡ ጥምቀት በብሉይ ኪዳን ዘመን ብዙ ምሳሌዎች ነበሩት ፡፡ የኖኅ መርከብ ፣ ግዝረት፣ ቀይ ባሕር የጥምቀት ምሳሌዎች ነበሩ ፡፡
መጠመቅ መከራን ያመለክታል ፡፡ ጌታችን ሞቱን መጠመቅ ብሎታል፡ እንዲሁም ጥምቀት የጌታችንን ሞትና ትንሣኤ መተባበር ነው ፡፡ ዓለምን የመካድና ክርስቶስን የመመስከር ልዩ ሥርዓት ነው ፡፡ ስለዚህ ጥምቀት ሰው እንደ ጸሎት በግሉ የሚያደርገው አይደለም ፡፡ በአዋጅ ፣ በአደባባይ ፣ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጸም ሥርዓት ነው ፡፡ ክርስቶስ የሞተውና የተነሣው አንድ ጊዜ ስለሆነ ጥምቀትም አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጸም ነው ፡፡ ከወላጆቻችንም የምንወለደው አንድ ጊዜ ነው ፡፡ እንዲሁም ጥምቀት አንድ ጊዜ የሚፈጸም ነው ፡፡ ሰውዬው በኃጢአት በክህደት ቢያልፍ እንኳ በንስሐ እንጂ በዳግም ጥምቀት አንቀበለውም ፡፡ ጥምቀት የማይደገም ምሥጢር ነው ፡፡ የጥምቀት ብርሃንም ፈጽሞ ሊደበዝዝ አይችልም፡፡ የጸጋ አጥር ነውና ደግሞም ለሁሉም የተሰጠ ስለሆነ ከጥምቀት የምንለየው ማንም መኖር የለበትም ፡፡ የክርስትናን ትምህርት ሲማሩ ተቃውሞ የሚገጥማቸው ከአረማውያን የተገኙ ወገኖች ሲጠመቁ ዘመዶቻቸው ፍጹም ተስፋ ይቆርጣሉ ፣ ይለያያሉ ፡፡ ጥምቀት ከአሮጌው ቤተሰብ ለይቶ አዲስ ቤተሰብ ይሰጣል፡፡ ሰው በግሉ የቤተሰብ አባል ፣ የአገር ዜጋ እንደሆነ እንዲሁም በጥምቀት የተወለደው ሰው የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባልና የሰማይ ዜጋ ነው ፡፡ ጥምቀት በመንፈስ የሚከናወን ሳይሆን በአካል በቤተ ክርስቲያንና በቀሳውስት አማካይነት ይከናወናል ፡፡ ሰው በተወለደበት ቤት እንደሚኖር ወላጅ እንደማይቀይርም እንዲሁም በተጠመቀበት ስፍራ ማደግና ቃሉን መመገብ ይኖርበታል ፡፡
ከውኃና ከመንፈስ መወለድ የሚለው ውኃ የሚለው ጥምቀትን አይደለም ቃሉን ነው የሚል ክርክር ይነሣል ፡፡ የዚህ ክርክር መነሻው ቃሉ የበላይ ነው፡፡ ክርስትናን ያስጀመረን ቃሉ ያስፈጽመናል ፣ ርስትን ያወርሰናል የሚል አስተሳሰብ ያለው ነው ፡፡ ነገር ግን ስለ ጥምቀት የነገረን ቃሉ በመሆኑ ጥምቀትና ቃሉ አይለያዩም ፡፡ ጀምስ ባርተን ኮፍማን የተባለ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቅ ተርጓሚ ሰው ከውኃና ከመንፈስ ካልተወለደ የሚለውን ቃል በማንሣት ውኃ የሚለውን ከጥምቀት ለመለየት የሚደረገውን ሙከራ ይወቅሳል ፡-
“ከዚህ የመጽሐፍ ክፍል የውኃ ጥምቀትን ለመፋቅ የሚደረገው የሰዎች የማያቋርጥ ጥረት ከንቱ ነው፤ በየትኛውም ይህን ማድረግ አይችሉም፡፡ ከውኃ መወለድ ( Born of water ) ለጥምቀት እንጂ ከክርስትና ጋር በተገናኘ ሌላ የተለየ ምንም ትርጉም አልተሰጠውም፡፡ ወንጌል ተቀባይነት ካገኘ ከምዕተ ዓመታት በኋላ እንኳ ከውኃ መወለድ ከጥምቀት ውጪ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አልተሞከረም፡፡
በዚህ ክፍል (ዮሐ 3፡5) ከኒቆዲሞስ ጋር በተያያዘ ፈሪሳውያን የዮሐንስን ጥምቀት አለመቀበላቸውን (ሉቃ7፡30) እንደ መነሻ ይዞ እስከ ታላቁ ተልዕኮ ይዘልቃል፡፡ (ታላቁ ተልዕኮ ማለት በማቴ 28፤18-20 ላለው ክፍል የተሰጠ ስያሜ ነው)
ይህን ክፍል ከክርስትናው ጥምቀት የተለየ አሳብ እንዳለው አስመስሎ ማቅረብ የቅርብ ዘመን አሳብ ነው፡፡ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው ጆን ቦይስ ( 1571-1625 )፣ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን ቄስ እና የካተርበሪ ዲን ፣ ይህን ጽፏል “በጣም ጥቂት ምሁራን ( ያኔ ጥቂት ቢሆንም አሁን ብዙ ሆነዋል – ጀምስ ባርተን ኮፍማን ) እነዚህ ቃላት ዮሐ 3፡3-5 ለጥምቀት ተሰጥተው መተርጎም የለባቸውም የሚል እምነት ይዘው ተነሡ፡ እንደ እነርሱ እምነት ክርስቶስ በዚህ ክፍል ውኃ ያለው መንፈስን ነው፡፡ ስለዚህ ከውኃና ከመንፈስ የሚለው አሳብ መንፈስን ብቻ የሚያመለክት ነው ይላሉ፡፡ ዮሐ 3፡5ን አርጌንስ፣ አፈ ወርቅ ፣ አውግስጢኖስ፣ ቄርሎስ፣ እንደ ሰማዕቱ ጀስቲን፣ ተርቱሊያን፣ አምብሮስ፣ ባስልዮስ ሁሉ ለጥምቀት የተነገረ መሆኑን አበክረው አስተምረዋል፡፡ እንዲሁም ሁሉንም እንዳነበበ የተመሰከረለት አንባቢው ሁከር (Hooker ) “ሁሉም የቀደሙቱ አባቶች ይህንን ነው ያደረጉት ይላል”
ከሉተር የተሐድሶ እንቅስቃሴ በኋላ የተነሡ አንዳንድ መተርጉማን፣ ከሉተር የተሳሳተ የጽድቅ ትንታኔ ጋር ለማስማማት በመፈለግ የዚህን ክፍል አሳብ አጣመውታል፡፡
ለመዳን፣ አንድ ሰው ከውኃ መወለድ ( ጥምቀት ) እና መንፈስ ቅዱስን መቀበል ( ከመንፈስ መወለድ ) አለበት ፡፡ ክርስቶስም፡-: ከውሃና ከመንፈስ በማለት ሁለቱንም በአንድ አጣምሯቸዋል፡፡ እግዚአብሔር አንድ ያደረገውን ሰው አይለያየው ፡፡
ፊሊፕ ቻፍ (1819 -1893 ) የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፕሮፌሰር እና ታዋቂ ምሁር እንዲህ ብሏል፡- ዮሐንስ እንዳጠመቀ፤ ክርስቶስ ራሱ እንደ ተጠመቀ፤ ሐዋርያቱ በስሙ እንዳጠመቁ ( ዮሐንስ 4፡2 ) ስናይ ውኃን ከውኃና ከመንፈስ ልደት መነጠል የማይቻል እንደሆነ ይገባናል፡፡ ዮሐ 3፡5 የካልቪን ትርጉም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለምሥጢሩ፣ ለምሥጢረ ጥምቀት፣ ከሰጠችው ልክ ያለፈ ዋጋ የተነሣ መሆኑን ልብ ማለት አለብን፡፡
በውሃ ጥምቀት ዳግም ልደት ( Babtismal Regenration ) የሚለውን እምነት በመቃወም ውሃ ማንንም ሊያድን አይችልም የሚል አመለካከት ተወለደ፡፡ እርግጥ ነው ማንም ውኃ ያድናል አላለም ፡፡ ጥምቀት ለመዳን ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ አጥብቀው የሚከራከሩትም ውኃ ያድናል አላሉም፡፡ ባብቲዝማል ሪጀነሪሽን ካስቆጣም ማስቆጣት ያለበት የካሊቪንን ዘመን ምሁራን ነው፡፡ እርሱ በነበረበት ዘመን በእምነት በሞተ ሕጻን ላይ የሚረጭ ጥቂት የውኃ ጠብታ የኅጻኑን ነፍስ ያድናል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ካሊቪንም ይንን አሳብ በዘመኑ አጥብቆ የተቃወመ ምሁር ነበር፡፡ ቢሆንም በወቅቱ የነበረው የካልቪን መከራከሪያ፡-
ያመነ የተጠመቀ ይድናል ማር 16፤1 ከሚለው የክርስቶስ የተስፋ ቃል ጋር ምንም ግንኙነት አልነበረውም፡፡
ያመነ የተጠመቀ ይድናል ማር 16፤16 የሚለው ተስፋ ዮሐ 3፡5 በተሻለ የመተርጎም አቅም አለው፡፡
ስለ ዳግም ልደት
በውኃና በመንፈስ የሚደረገው ዳግም ልደት ሁለት ክፍል ያለው አንድ ልደት ነው፡፡ አንዱ ከውኃ መወለድ ሲሆን እሱም ጥምቀት ነው፤ በሰው ይከናወናል ( የሐ. ሥራ 22፡16 ) የዳግም ልደት ሁለተኛው ክፍል ከመንፈስ መወለድ ነው፡፡ እሱም የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ መቀበል ይባላል ፡፡ የሚከናወነው በእግዚአብሔር ነው፡፡
ዳግም ልደትን በተመለከተ የተነሣው ትልቁ ኑፋቄ፣ የመጀመሪያው ክፍል / የውሃ ጥምቀት ቢቀርም ላመነ ሰው ሁለተኛው ክፍል/ የመንፈስ ጥምቀት ይደረግለታል የሚል ነዉ ፡፡ ዮሐ 3፡5 ግን የመጀመሪያው ትርፍ ሁለተኛው በቂ መሆኑን አይነግረንም፤ የሁለቱንም አስፈላጊነት እንጂ፡፡ /ገባ ብሎ የተጠቀሰው ጀምስ ባርተን ኮፍማን ገለጻ ነው/