“ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው፥ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነው”
/ዮሐ. 3፡6/ ፡፡
ኒቆዲሞስ ስለ ሥጋዊ ልደት እያሰበ ነው ፡፡ የሥጋ ልደት ስለ ግዙፍ ነገር እንጂ መንፈሳዊ ነገርን ማየትና መውረስ እንደማይችል ጌታችን ነገረው ፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነው ፡፡ አስተሳሰቡ ፣ ምኞቱ ፣ የሚቆጥረው ድል ሥጋዊ ነው፡፡ ክበቡ አጭር ነው ፡፡ ከወንዙና ከአስተዳደጉ በላይ ማሰብ አይችልም ፡፡ የእኔ ለሚላቸው ካልሆነ ለሌላ ፍቅር የለውም ፡፡ በራሱ መንግሥት ክበብ ውስጥ ስላለ እንደ እግዚአብሔር መንግሥት ሰፍቶ ማሰብ አይችልም ፡፡ ኑሮው እንደ ልደቱ ነው ፡፡ በሥጋ የተወለደ የሚገለጠው በሥጋ ነው ፡፡ በመንፈስ የተወለደ ደግሞ የሚገለጠው በመንፈስ ነው ፡፡ የሥጋ ልደት ብቻውን ሊያስብ የሚችለው ስለ እውቀት እንጂ ስለ እምነት አይደለም ፡፡ ሥጋ ተጨባጭና የሚታይ ነገር ስለሚፈልግ እምነት ይርቀዋል፡ ራሱንም እንደ አምላክ ስለሚቆጥር ኢየሱስ ክርስቶስን በአምላክነቱ ማመን ይቸገራል ፡፡ ስሙን ቢጠራ ፣ እንደ ስምዖን ለምጻም በቤቱ ቢጋብዘውም ሥጋ አሁንም ብድር መመለስና ዝናን የሚያስብ ነው /ሉቃ. 7፡36/ ፡፡ ብድሩን ከመለሰና ዝናውን ካደራጀ በኋላ መልሶ ወደ ንቀት የሚገባ ነው ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን የሚያምን እርሱ ዓለምን ያሸንፋል ይላል /1ዮሐ. 5፡5/ ፡፡ ዓለም የሥጋ የሥራ ባልደረባ ናት ፡፡ የሚታይ ነገርን ማለት ጣዖትን የምትከተል ናት ፡፡ ሥጋም ግዙፍ ነገርን ማለት ዘመዱን ፈላጊ ነውና ከዓለም ጋር የማይፈታ ትዳር አለው ፡፡ ለዚህ ዓለም ሰውና ለሥጋዊ ሰው መንፈሳዊ ነገር ሞኝነት ነው ፡፡
ከመንፈስ የተወለደ መንፈስ ነው ፡፡ የሥጋ ልደት እንዳለ የመንፈስ ልደትም አለ ፡፡ ይህ የመንፈስ ልደት የራሱ መገለጫዎች አሉት ፡፡ መገለጫዎቹም ስሜት ሳይሆኑ ተግባር ናቸው ፡፡ ልደቱ የማይታይ ቢሆንም የሚታይ ሥራ ግን ይሠራል ፡፡
ጌታችን በመቀጠል ፡- “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ። ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” /ዮሐ. 3፡7-8/፡፡
ኒቆዲሞስ የተደነቀው እንዴት በሚለው በራሱ ጥያቄ እንጂ እግዚአብሔር በሚሰጠው ሥጦታ አይደለም ፡፡ የራሱን ጥያቄ እንደ ገደል ማሚቱ መልሶ እየሰማ ይደነቃል ፡፡ በራስ ማስተዋል፣ ፍልስፍናና በጥርጥር አሳቦች መደነቅ ወደ መድከም ያመጣል ፡፡ ምድርን ባለቤት አልባ ነገሮችን አምላክ የለሽ ማድረግ ሁሉንም ነገር ጨለማ ያደርጋል ፡፡ ሰው በእውነት ማረፍ ካልቻለ በሐሰት እንኳ ለመደለል ይሞክራል ፡፡ በእግዚአብሔር መደነቅ ግን አቅምን ይጨምራል ፡፡ መደነቅ ያደቃል ፣ መደነቅ ያነቃል ፡፡ መደነቅ እንዲሁ የሚታለፍ አይደለም ፡፡ ጉልበትን የሚያበረታ ጉልበትን የሚሰብር ነው ፡፡ ኒቆዲሞስ በእግዚአብሔር መቻል ሳይሆን እንዴት ይሆናል በሚል በራሱ አስተሳሰብ መደነቅ ጀመረ ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት እንዴት አይባልም ፡፡ እግዚአብሔር ለሞተው ሕይወት የሚሰጥ ፣ የሌለውንም እንዳለ አድርጎ የሚቆጥር ነው ፡፡
ጌታ ስለ መንፈሳዊው ልደት ባሕርይ ተናገረ ፡- “ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” /ዮሐ. 3፡7-8/፡፡ መንፈሳዊው ልደት በነፋስ ተመስሏል ፡፡ ነፋስ አይታይም፣ መንፈሳዊ ልደትም አይታይም ፡፡ ስሜታዊ ማረጋገጫዎች የሉትም ፡፡ በእምነት የሚቀበሉት እንጂ ሰዎች ለሰዎች የሚያረጋግጡትም አይደለም ፡፡ እንደ ውኃ ሽልስ ብሎ የሚቀዘቅዝ ፣ እንደ እሳት ቦግ ብሎ የሚያግል አይደለም ፡፡ ብዙ ሰዎች መንፈስ ቅዱስንና ዳግም ልደትን በዚህ የስሜት ማረጋገጫ ይጠብቁታል፡፡ ስሜታዊ ማረጋገጫዎች ካሉት እምነት መሆኑ ይቀራል ፡፡ ዳግም ልደት ከጌታችን ሞትና ትንሣኤ ጋር የተቆራኘ ነው ፡፡ በቀራንዮ ያማጠው እኛን ለሕይወት ለመውለድ ነው ፡፡ ይህንን በናሱ እባብ ትርጓሜ እናየዋለን /ዮሐ. 3፡14/ ፡፡
ነፋስ አይታይም ፡፡ በሥራው ግን ይታወቃል ፡፡ ዛፍ ሲያንቀሳቅስ ፣ ስጥ ሲበትን ፣ ቀላል ነገሮችን ተሸክሞ ሲሄድ ፣ ሰውየውን ሲያንገዳግድ ነፋስ በተግባሩ ይታወቃል ፡፡ ዳግም ልደትም በተግባሩ የሚታወቅ ነው ፡፡ የራሱ የሆኑ የኑሮ ፍሬዎች ፣ የምስክርነት ዋጋዎች አሉት ፡፡ እነዚህ ፍሬዎች ብዙ ናቸው ፡፡ በዳግም ልደት ያለ ሰው ውስጡ በፍቅር ኃይል መለወጥ ይጀምራል፡፡ ስለዚህ ከጭካኔና ሌሎችን ረግጦ ከመደሰት ይድናል ፡፡ እግዚአብሔርን አባት ብሎ ለመጥራት የኅሊና ነጻነትና የፍቅር ግለት ያገኛል፡፡ ዳግም መወለድ ከእግዚአብሔር ጋር በአምልኮ ኅብረት ለመገናኘት ይናፍቃል ፡፡ ለአንድ ተወዳጅ ልጅ ከደህና ቁርስ በላይ የሚያስደስተው አባቱን በማለዳ ማግኘት ነው ፡፡ ከእራቱ በፊትም አባቱን ይጠብቃል ፡፡ አባቱ ቢዘገይ እንኳ መጠበቂያው ወንበር ላይ ደክሞት ይተኛል ፡፡ እንዲሁም እግዚአብሔርን አባቴ ለማለት የተወለደ ምእመን በማለዳ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ይገናኛል ፡፡ ምሽቱንም ሳይጸልይ አይተኛም ፡፡ እግዚአብሔር የዘገየ ቢመስለው እንኳ በመጠበቂያው ማለት በጸሎት ማማው ላይ ሁኖ ይጠብቃል እንጂ ተስፋ ቆርጦ ሌላ አባት ፍለጋ አይሄድም ፡፡ ጥያቄው ያልተመለሰ ልጅ ያኮርፍ ይሆናል እንጂ የአባት ለውጥ አያደርግም ፡፡ ምእመንም ካለመጸለይ አኩርፎ ቢጸልይ መልካም ነው ፡፡ እግዚአብሔር በልዩ ፈገግታ ይቀበለዋል ፡፡
“ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል” ይላል ፡፡ በዳግም ልደት ላይ እኛ ለመወለድ ከመፈለጋችን በላይ እግዚአብሔር አባት ሊሆን መፍቀዱ ትልቅ ዋጋ ሊሰጠው ይገባል ፡፡ አንድ ሰው ከንጉሥ መዛመድ ከመፈለጉ በላይ ንጉሡ ፈቃደኛ መሆናቸው ዋጋ ይሰጠዋል ፡፡ ንጉሡ ብዙ አማራጭ አላቸው፤ ሰውየው ግን ምንም አማራጭ የለውም ፡፡ በድሮ የጡት አባት እየተባለ ከትልቅ ሰው ጋር መዛመድ ይፈለጋል ፡፡ ይህንን የሚጠይቀው ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖረው ወይም በዘመኑ መዐርግ የሌለው ሰው ነው ፡፡ ታዲያ መኳንንቱና መሳፍንቱ እንደ ንቀት ያዩት ነበር ፡፡ አንድ የታወቁ አዛዥ አንድ ሰው ይመጣና “የጡት አባት ይሁኑኝ” አላቸው ፡፡ እርሳቸውም ከፊት ለፊታቸው ደረቱና ጡቱ ያረጠረጠ አሽከር ነበራቸውና “ሂድ የእገሌን ጡት ጥባ “ አሉት ይባላል ፡፡ የጡት አባትነት በሰው ዓለም ውድ ከሆነ እግዚአብሔር እኛን ልጆቼ ብሎ ሊቀበለን መፍቀዱ በእውነት ክብር ሊሰጠው ይገባል ፡፡ እኔም ከመቀመጫዬ ተነሣሁ፣ ብዕሬን አስቀመጥኩና እንዲህ ብዬ መጸለይ ጀመርኩ ፡-
ጌታዬ ሆይ አመሰግንሃለሁ ፡፡ እኔን ልጅ ብለህ ልትቀበል ስለወደድህ አከብርሃለሁ ፡፡ በቀን ሦስቴ የምለዋወጠውን እኔን በማይለወጥ ፍቅር ስለወደድከኝ በእውነት አከብርሃለሁ ፡፡ እንደ እኔ ያለ ሰው አታጣም ፤ እንዳንተ ያለ አምላክና ወዳጅ ግን አላገኝምና አመሰግንሃለሁ ፡፡ ስናወጥ ብትናወጥ ስመለስ ባጣሁህ ነበር ፡፡ እኔን ወደ አንተ በልጅነት በእቅፍ በወጣትነት በመሳብ ላቀረቡኝ በረከትን አብዛላቸው ፡፡ ወርቅ የሰጠም አይረሳም ፡፡ የሰማይን መንገድ ያሳዩኝን አትርሳብኝ ፡፡ እኔንም ወደ አንተ ባቀረቡኝና ባስተማሩኝ ፣ ድካሜን ሰምተው በጸለዩልኝ ላይ ጠላት ሁኖ ከመነሣት አድነኝ በተወዳጁ ስምህ ለዘላለሙ አሜን ፡፡
“ነፋስ ወደሚወደው ይነፍሳል፥ ድምፁንም ትሰማለህ፥ ነገር ግን ከወዴት እንደ መጣ ወዴትም እንዲሄድ አታውቅም፤ ከመንፈስ የተወለደ ሁሉ እንዲሁ ነው” አለ ፡፡ ዳግም ልደት በነፋስ ተመስሏል ፡፡ የተለወጠ ልብን እንጂ የተለወጠ ፊትን ላያመጣ ይችላል ፡፡ የመንፈስ ከፍታን እንጂ የኑሮ ዕድገትን ላያስገኝ ይችላል ፡፡ ልደቱ የማይታይ ሀብትን የሚያስገኝ በሚታይ ፍሬ ግን የሚገለጥ ነው ፡፡ ነፋስ ከወዴት እንደ መጣ ወዴት እንዲሄድ አይታወቅም መባሉ ዳግም ልደትም እንደዚህ ነው ወይ? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን ፡፡ ሁለት ነጥቦችን ማስቀመጥ መልካም ነው ፡-
– የዘላለም ሕይወት በእግዚአብሔር እጅና በእኛ ልብ ውስጥ ያለ ነው ፡፡
– ምእመን ኑሮው ዓላማ፣ ሞቱ አድራሻ ያለው ነው ፡፡
ዳግም ልደት ልዩ ክስተት ነው ፡፡ ለዳግም ልደት የወለደን መንፈስ ቅዱስም ልዩ ነው ፡፡ ሰው አንድ ጊዜ ሲወለድ ዕለት ዕለት ግን ያድጋል ፡፡ የሚያድገው ግን ያው ትንሹ አካል ነው ፡፡ በማኅጸን የነበረው ያች ትንሽ እጅ እርሷ ታድጋለች ፡፡ ያቺ ትንሽ እግር እርሷ ታድጋለች ፡፡ እንዲሁም ስንወለድ የወረስነው መንፈሳዊ ማንነት እርሱ ወደ ዕድገት ያመራል ፡፡ መች በፍቅር እንደ ተለወጥን መች ከውስጣችን ያለ የኃጢአት ማንነት እንደ ወደቀ አናውቀውም ፡፡ አንድ ቀን ተለውጠን ራሳችንን እናገኛለን ፡፡ ይህ መንፈስ ቅዱስ ቀንና ሌሊት ሳይደክም ስለሚሠራን የሥራው ውጤት ነው ፡፡ የተወለደው ለማደግ ምግብ ያስፈልገዋል ፡፡ ምግብ ብቻ ሳይሆን ኅብረት ወይም የወላጅ ፍቅር ያሻዋል ፡፡ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ዕድገታችንን በቃሉና በአባቶች በኩል ያደርግልናል ፡፡ ዕድገቱ እንዲህ ከሆነ ልደቱም ልክ እንደዚህ ነው ፡፡ ከዚህ እስከዚህ አይባልም ፡፡ የዕድገታችን ጣራው ክርስቶስ ስለሆነ መቼም ብንቀደስ እርሱን በፍጹም መምሰል አንችልምና እስክንሞት በዕድገት ውስጥ ነን ፡፡ ልደቱ እንዴት እንደ ተከናወነ ወደየትኛው ልክ እንደሚሄድ አይታወቅም ፡፡ ግን ያለማቋረጥ መሠራት ይሆናል ፡፡ ምእመን ሆይ ሠሪው ሳይደክመው አንተ እንዳይደክምህ አስብበት ፡፡ ራስህንም ያለ ክርስቶስ ትኩር ብለህ አትየው ፡፡ ያለ መንፈስ ቅዱስም በራሴ ኃይል አሸንፋለሁ ብለህ አትግደርደር ፡፡ ኑሮህ እንደ ልደትህ ይሁን ፡፡ ስለዚህ ሰማይን እያየህ የሚታየውን የአሁን ኑሮ ናቀው ፡፡ መንግሥቱን እንደምትወርስ እያሰብህ የዛሬ መገፋትህን ቻለው ፡፡