“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና”/ዮሐ. 3፡16/።
በናሱ እባብ መሰቀል ምክንያት እስራኤል ተአምር ሆኖላቸዋል። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሞት ግን ሕይወት ሁኖልናል ። በተአምራት ሙት ቢነሣ ተመልሶ ይሞታል ፣ እሳት ቢወርድ ይጠፋል ። በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት የተገኘው ሕይወት ግን ዘላለማዊና የማይጠፋ ነው። የናሱን እባብ ያዩ በሕይወት ይኖራሉ ተብሏል /ዘኁ. 21፡8/። ክርስቶስን በእምነት የሚያዩም በሕይወት ይኖራሉ ። በሕይወት ለመኖር ማየት ወሳኝ ነው። የእስራኤል ልጆች የነደፋቸውን እባብ ቢያዩ በሕመም ላይ ጥዝጣዜ ይሰማቸው ነበር። የነደፉንን ማየት ይገድላል ። ያልበደለንን ጌታ ፣ እኛ አጥፍተን ሳለ እኔ ልቀጣ ያለውን ወዳጅ ማየት ግን በሕይወት ያኖራል። ሰው በአካል እየተንከላወሰ ውስጡ ግን በቂምና በቀል ስሜት ሊሞት ይችላል። እግዚአብሔርን ሲያይ ግን ውስጡ በአዲሱ የፍቅር አየር መሞላት ይጀምራል። ለመኖርም አቅም ያገኛል ። ያለቀ የመሰለው ነገር እንደገና ወደ ህልውና ሲመጣ ማየት ይሆንለታል ። በሕይወት ለመኖር የተሰቀለውን ማየት ይገባል ። እርሱ ያለበደለ ሳለ የእኛን በደል ተሸክሞ ሲሞት እኛ ግን የገዛ ጥፋታችንን ማመን ተስኖናል ። እርሱ ለጠላቶቹ ይቅርታ ሲለምን እኛ ግን ወዳጆቻችንን መውደድ አቅቶናል ። እርሱ ለማያምኑት ፀሐይን ሲያወጣ እኛ ግን የሠራተኞቻችንን ደመወዝ እንከለክላለን ። እርሱ ዘላለም ከእኔ ጋር ኑሩ ብሎ ሲጠራን እኛ ግን አሥር ዓመት አብረን ለመኖር ተቸግረናል ። የእኛ ፍቅር እንደ ጥዋት ጤዛ ሲረግፍ የእርሱ ፍቅር ግን እንደ ጸኑ ተራሮች ዛሬም ቀና ሲባል የሚታይ ነው ። ብዙ ወዳጆች ቀየርን ፣ እግዚአብሔርን ግን የሚተካ አላገኘንም ። ብዙ ደጆች ደርሰን ስንመለስ ተዘጉ ፣ እግዚአብሔር ግን በእኛ ላይ በሩን አልዘጋም ። በብዕር ፍቅሩን የሚገልጥልን ወዳጅ ተቸግረናል ፣ በደም ነጠብጣብ እወዳችኋለሁ የሚለንን ውድ ግን አግኝተናል።
“ጌታ ሆይ ምን ያህል ትወደኛለህ?” ብንለው አምስት ፊደሎችን ያሳየናል ። እነርሱም፡- የእሾህ አክሊል የደፋውን ራስ ፣ ችንካር የነደላቸውን እጆች ፣ በጦር የተማሰውን ጎኑን ፣ በአየር ላይ የተንጠለጠሉትን እግሮች ያሳየናል ። እኛስ እንወደዋለን ?
አባት ሦስት ልጆቹን አቁሞ፡- “ምን ያህል ትወዱኛላችሁ ?” አላቸው። አንዱ ልጅ ፡- “አባቴ ሆይ ፥ የዓባይን ርዝመትና ጥልቀት ያህል ላንተ ያለኝ ፍቅር እንደዚህ ነው” አለው ። ሌላኛው ልጅ ሲጠየቅ ፡- “የኪሊማንጃሮን ተራራ ያህል ግዙፍና ምጡቅ ነው” አለ ። ሦስተኛው ልጅ ግን ፡- “አባቴ በምትወደኝ ልክ እወድሃለሁ” አለ ። እግዚአብሔርም ከእኛ የሚፈልገው ፍቅር እንደ ወደደን እንድንወደው ነው ። አፍቃሪ ፍቅር ይፈልጋል ። እግዚአብሔርም እንድንወደው ይሻል ።
እግዚአብሔር ፍቅሩን በተለያየ ዓይነትና ጎዳና ሲገልጥ ኑሯል ። አንድ ልጁን ለእኛ ቤዛ አድርጎ በመስጠት ወሰን የለሽ ፍቅሩን ገለጧል። ልጁ በሞተ የእግዚአብሔር ፍቅር እንዴት ተገለጠ ይባላል ? ስንል እግዚአብሔር በፍቅር አንድ ስለሆነ ነው ። በዓለም ላይ ብንዞር ለበደለ ባሪያ አንድ ልጁን የሚሰጥ ጌታ ይቅርና ለጨዋ ባሪያ እንኳ አንድ ልጁን የሚሰጥ ጌታ አናገኝም ። እግዚአብሔር አብ ግን ለበደለ ለአዳም አንድ ልጁን በመስጠት ፍቅሩን ገለጠ። ይህ የፍቅር ዳርቻ የመውደድም ጥግ ነው ። እግዚአብሔር ማነው ? ስንል እግዚአብሔር ፍቅር ነው ። ፍቅር ሁሉ ግን እግዚአብሔር አይደለም ። የእግዚአብሔር ፍቅር ከራሱ የሚነሣ ፍቅር ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር ዘላለማዊና የጊዜ ተጽእኖን የሚቋቋም ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር አድልኦ የሌለው ኃጢአተኞችን የማያሳቅቅ ፍቅር ነው ። የእግዚአብሔር ፍቅር ከወዳጆች ፍቅር አልፎ የሚሄድ ነው ። በዓለም ላይ ያሉ ፍቅሮች እስከ መቃብር ናቸው ። እነዚህ ፍቅሮች ሲደነቁ ኑረዋል ። ከመቃብር ያለፈ አንድ ፍቅር ግን አለ ። እርሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ነው ። በመስቀል ላይ በተገለጠው ፍቅር ለጠላቶቹ የሞተው የወልድ ፍቅር ተደንቋል /ሮሜ. 5፡6-11/። ለበዳዮችም አንድ ልጁን የሰጠው የአብም ፍቅር ተደንቋል ። ፍቅሩን በልባችን ያፈሰሰው መንፈስ ቅዱስም ተደንቋል ። የወልድ ሰው መሆንና መሞት የአብ ስምረት ፣ የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ያለበት ነው። የሰው ልጆች ልባቸው ሰላም የሚሆነው የሰማይ ቤታቸው በርግጥም አስተማማኝ ሲሆን ነው ። እግዚአብሔር ለዚህ ማስተማመኛ አድርጎ የሰጠው ፍቅሩንና መንፈሱን ነው /ሮሜ. 5፡5/። ፍቅሩና መንፈሱ እውነተኛ ናቸው ። ፍቅሩ አይለወጥም ፣ ይህ ፍቅር አንድ ልጅን ካሰጠ መንግሥተ ሰማያትን ያውም ለእኛ የተፈጠረችውን እንዴት ያስከለክላል ? መንፈስ ቅዱስም አሁን ተስፋ የምናደርጋት መንግሥተ ሰማያት ችግር ቢገጥማት እንኳ አዲስ ዓለም ፈጥሮ ማውረስ የሚችል አምላክ ነው ። ሁላችንም እንደምናውቀው የ300 ብር ዕቃ አዝዘን የ400 ብር ቀብድ አንሰጥም ። ግማሹን ወይም ሩቡን ግን እንሰጣለን ። እግዚአብሔር ግን መያዣ አድርጎ የሰጠን መንፈስ ቅዱስን መሆኑ ከአእምሮ በላይ ነው ።
በእርሱ የሚያምን ሁሉ ይላል ። በማን የሚያምን ስንል በተሰቀለው ጌታ የሚያምን ማለት ነው ። እምነት ማለት በእግዚአብሔርና በተግባሩ ማመን ማለት ነው ። በእግዚአብሔር ስንል በአንድነት በሦስትነቱ ፣ በምልዐት በስፋቱ ፣ በእዘዝ በክብሩ ማመን ማለት ነው ። በተግባሩ ማመን ስንል ግን በአንድ ልጁ በሠራው የማዳን ሥራው ማመን ማለት ነው ። የሃይማኖት ሁለት ክፍሎች የምንለውም ይህን ነው ። ምሥጢረ ሥላሴ እግዚአብሔር በማንነቱና በህልውናው እንዴት እንደሚኖር የሚገልጥ ሲሆን ምሥጢረ ሥጋዌ ደግሞ እግዚአብሔር በለቢሰ ሥጋ ለእኛ ያደረገውን የምንማርበት ነው ። ሌሎቹ ምሥጢራት በሥጋዌ ሥር የሚገቡ ናቸው ። ስለዚህ እምነት ማለት በእግዚአብሔርና በተግባሩ ማመን ማለት ነው ።
እምነትን የማመን ትምህርት በዘመናችን እየተስፋፋ ነው ። እንዲህ ይሆናል ካልህ ይሆንልሃል ፣ ይህ ነገር የእኔ ነው በል ያንተ ይሆናል የሚል እግዚአብሔርን የሚጨምር የሚመስል ነገር ግን በቃል ኃይል የሚያምን ሰው ተኮርና ምኞት የበዛበት ትምህርት በዝቷል ። ቃሉ ግን ሁሉን እችላለሁ የሚለው በክርስቶስ መሆኑን ይነግረናል /ፊልጵ. 4፡13/። በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን በማለት ፍቅሩ ኃይላችን መሆኑን ወይም አፍቃሪያችን የማያስነካ መሆኑን ይነግረናል እንጂ በራሳችንና በቃላችን አንዳች ማድረግ እንደምንችል አይነግረንም /ሮሜ. 8፡37/። ይህ የፍልስፍናና የሩቅ ምሥራቆች ልምምድ ወደ ክርስትና ዘልቆ እየገባ ይመስላል ። የሚያመጣው ችግር ምንድነው ስንል ፡-
1- እምነታችንን በእምነታችን ላይ እንድናደርግ በማድረግ በእግዚአብሔር ላይ ካለን መደገፍ ይነጥለናል ።
2- በትዕቢት እንድናስብና ሌሎችን ረምርመን እንድንኖር ያደርገናል ።
3- ሥጋዊ ምኞትንና ምድራዊ ብልጽግናን የእምነት ጥግ ያደርግብናል ።
4- ቁሳቁስ ለሚያመጣብን መንፈሳዊ ድርቀትና የሕይወት ውድመት ይዳርገናል ።
5- በክህደትና ሁሉን ነገር በመጠራጠር ላይ ትቶን ይሄዳል ።
6- ምድር በምሕዋሯ ላይ መዞር ስትቀጥል ፣ የሕይወት ፕሮግራምም በታቀደለት መሠረት መጓዝ ሲጀምር ራስን ወደ መታዘብና ሌሎችን ወደ መንቀፍ ያደርሳል ።
7- ለራሱ የሚታዘንለት ሳለ ሌሎች አልገባቸውም በማለት ሌሎችን እንደ ተጎዱ መቊጠር ይጀምራል ። ባመኑትና ባላመኑት መካከል ልዩነት እስኪጠፋ ሁሉም የቁሳቁስ እስረኛ እየሆነ ይመጣል ።
8- ስለ ክርስቶስ መከራ መስቀል ለመሸከም የማይችል ተድላ ብቻ አፍቃሪ የሆነ ሰብእናን ይገነባል ። በዚህ ጊዜ ክርስቶስን በሰዎች ፊት መካድ ይከሰታል ።
9- ሥራን በመጥላት ቤተሰብን መበተን የያዙትን ሥራ ጥሎ መውጣትና ስንፍናን መሠረት ያደረገ ሱባዔ መግባት ይጀመራል ። በዚህም የአገር አቅም እየተጎዳ ይመጣል ።
10- ሌሎችንም ስለሚያስተባብር ስቶ ማሳት ይከሰታል ።
በክርስቶስ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው ። ዘላለም ካመኑበት ሰዓት አንሥቶ ያለው ፍጻሜ የሌለው ህልውና ነው ። የሰው ዕጣው የሚለየው በምጽአት ቀን አይደለም ። የምጽአት ቀን በጎችና ፍየሎች የሚለዩበት እንጂ በግና ፍየል የምንሆንበት ቀን አይደለም /ማቴ. 25፡32/። በጎች ሆነው የኖሩ ፍየሎች ሆነው ከኖሩት ይለያሉ ። ይህ ዓለም የመደባለቅ ዓለም ነውና ያ ቀን ግን ይለያል ። ክርስቶስ እንደ እረኛ ሁኖ ስለሚመጣ ይለያል ። ቀኑም እንደ ውድማ ነውና ገለባውና ስንዴው ይለያል ። በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት ይኖረው ዘንድ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷል ። እንዲሁ የተባለው ምንድነው ? በነጻ ማለት ነውን ? አይደለም ። እንደላይኛው ሙሴ እባብን እንደ ሰቀለው እግዚአብሔርም ልጁን ለሞት በመስጠት እንዲሁ ወደደን ። ፍቅሩ በነጻ ላይ የተመሠረተ ነው ማለት ሳይሆን በዋጋ ላይ የተመሠረተ ነው ማለት ነው ። እኛ ስንቀበለው ነጻ የሆነው እዚያ ጋ ዋጋ የተከፈለበት ነው ።
የዳግም ልደት አሳብ እስከዚህ ድረስ እየተተነተነ ነው ። ልደት ምጥ አለው ። እንዲሁም ክርስቶስ እኛን ለዘላለም ሕይወት ለመውለድ የመስቀል ምጥ አምጧል ። ልደት ዓለም ማያ ነው ። እንዲሁም ዳግመኛ ስንወለድ መንግሥቱን እናያለን ። ምጡ እንዲሰማን የሚያደርገው ነገር ምንድነው ? ስንል ጥምቀት ነው ። በውኃ ውስጥ ለሰከንዶች መዘፈቅ ሞትን አይቶ መምጣት ነው ። ይህ ሞቱን ያስታውሳል ። ከውኃው ሲወጣ ቅድም የማያውቀው እስኪመስል ስፍራውንና ዓለሙን ፈጥኖ ያያል ። እንዲሁም ከውኃና ከመንፈስ የተወለደው የሚመጣውን መንግሥት በእምነት ያያል ። ስለመንግሥተ ሰማያት ሲተረክለት ቢኖርም አሁን በልዩ ማሰብና መደሰት ይጀምራል ። የመንግሥተ ሰማያት የቅምሻ በረከትም በቤተ ክርስቲያን ዘወትር አለ ። እርሱም ምሥጢራት ፣ እረኝነትና ኅብረት ናቸው ። ዳግም ልደት ታላቅ ፍቅር የሚገለጥበት ነው ።