የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

እምነት

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና”/ዮሐ. 3፡16/።
      እምነታችንን ትክክለኛ የሚያደርገው ያመንበት ነገር ትክክለኛነት ነው። ሰው ከልቡ በጣዖታት ፣ በዛፍና በድንጋይ ሊያምን ይችላል ። ከልብ ማመኑ እምነቱን ትክክለኛ አያደርገውም ። ያመነበት ነገር ትክክለኛ መሆን አለበት ። ለዚህ ነው በክርስቶስ የሚያምን ያለው ። ሰው በብዙ ነገር ያምናል። በእምነቱ ያምናል ፣ በምግባሩም ያምናል ፣ በሰውም ያምናል ። በእምነቱ ሲያምን ራሱን እንደ ሁሉን ቻይ በመቊጠር የእግዚአብሔርን ረድኤት መጠየቅ ይሳነዋል ። በምግባሩ ሲያምን እንደ ፈሪሳውያን መመጻደቅና ሌላውን መናቅ ይጀምራል ። በሰውም ሲያምን ረሱኝ ፣ ከዱኝ በማለት ሞቱን ይመኛል ። ሰው እንኳን የመታመንን ይቅርና ፍቅርንም የመሸከም አቅም ያንሰዋል ። ባመኑት ልክ የሚገኘው መታመን ገንዘቡ የሆነው መድኃኔዓለም ነው ።
     አንድን ሰው አስቀድመን እናውቀዋለን ፣ ቀጥሎ እንወደዋለን ፣ ከዚያም እናምነዋለን ፣ ያመነውን ራሳችንን እንሰጠዋለን ። ስለዚህ እምነት ከፊቱ ሁለት ነገሮች አሉ ። እነርሱም፡- ማወቅና ማፍቀር ናቸው ። ከኋላው አንድ ነገር አለ ። እርሱም፡- ራስን መስጠት ነው ። እምነት በትክክለኛ እውቀት ላይ ይመሠረታል ። ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው”ይላል /ሮሜ. 10፡17/። ለማመን ግድ መስማት ያስፈልጋል ። የምንሰማው ነገር እንደሚያጠራጥረን ሁሉ የምንሰማው ነገርም ወደ እምነት ያመጣናል ። የምንሰማው ነገር ሁሉ ወደ እምነት ያመጣል ወይ ? ብለን ብንጠይቅ የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ወደ እምነት ያመጣል ። የእግዚአብሔር ቃል ስለ ክርስቶስ የሚነግረንን ማመን እርሱ እምነትን ያመጣል ። ስለ አንዱ አምላክ በአይሁድ ምኩራብ፣ በእስላም መስጊድ ይነገራል ። ክርስትናን ልዩ የሚያደርገው ስለ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ የሚናገር መሆኑ ነው ። ወንጌላት ሁሉ ልደቱን እንዲሁም ዕርገቱን አልዘገቡም ። ወንጌላት ሁሉ ግን ሞትና ትንሣኤውን ዘግበዋል ።የክርስትናው ዐቢይ ርእስ ስለሆነ ነው ። ወንጌል ስለ ክርስቶስ የሚነግረንን ሰምተን መቀበል እርሱ እምነት ነው ። ሐዋርያት በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንዲያጠምቁ ታዝዘው ሳለ በኢየሱስ ስም ያጠምቁ የነበረው አንዱ ምክንያት አይሁድ ስለ አንዱ አምላክ ጥያቄ አልነበራቸውም ። መቀበል ያቃታቸው ክርስቶስን ነው ። ጥምቀት ደግሞ በክርስቶስ በተሠራው ሥራ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ ግድ በኢየሱስ ማመን አለባቸው ።
      በክርስቶስ ማመን ማለት ምን ማለት ነው? ስንል እርሱን ካመኑት ቅዱሳን ሕይወት በመነሣት መረዳት እንችላለን ።
1-  ያለ ምክንያት የሚሠራ መሆኑን ማመን ነው ። ይህን ከእመቤታችን እምነት እንማራለን ።
2-  በበረት የተወለደው ሰማይ አገሩ ፣ ሌጣ የነበረው መላእክት ሠራዊቱ ናቸው ብሎ ማመን ነው ። ይህን ከእረኞች እንማራለን ።
3-  እግዚአብሔር ያዘጋጀው ብቸኛው መፍትሔና የኃጢአት ስርየትን የሚሰጥ ነው ማመን ነው ። ይህን ከመጥምቁ ዮሐንስ እንረዳለን።
4-  ባለቀ ነገር ላይ የሚቀጥል ነው ብሎ ማመን ነው ። ይህን በቃና ዘገሊላ ውሎ እንማራለን ።
5-  ለኃጢአት ይቅርታ የሚሰጥ ነው ብሎ መቀበል ነው ። ይህን ከማርያም ባለ ሽቱዋ እንረዳለን ።
6-  በትንሣኤም ቀን የሚያስነሣው ዛሬም ማስነሣት የሚችለው ያው እርሱ ነው ማመን ነው ። ይህን ከአልዓዛር እህት ከማርታ እንማራለን ።
7-  በሞት ላይ የገነነ የትንሣኤ አምላክ ነው ብሎ ማመን ነው ። ይህን ከሐዋርያት እንማራለን ።
        እምነት በትክክለኛ እውቀት ላይ ይመሠረታል ። “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት”ይላል /ዮሐ. 17፡3/። የዘላለም ሕይወት እውነተኛውን አምላክና መድኃኒት በማወቅ ይመሠረታል ። ያወቅነውን መውደድ ይገባናል ። የወደድነውን እናምነዋለን ። ያመነውን እንኖርለታለን ወይም ራሳችንን እንሰጠዋለን ።
       እምነት ማለት መስማማት ማለት ነው ። ከምን ጋር መስማማት ስንል ከእግዚአብሔር ዘላለማዊ አሳብ ጋር መስማማት ማለት ነው ። ለመስማማት መስማት ያስፈልጋል ። ሰዎች ትስማማለህ ? ሲሉን መጀመሪያ ልስማው እንላለን ። የምንሰማውና የምንስማማው ከወንጌል አሳብ ጋር ነው ። እምነት ሌላው ትርጉሙ መደገፍ ማለት ነው ። መስማማትና መደገፍ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ። መደገፍ መተማመን ፣ መደላደል ፣ አይጥለኝም ብሎ ማረፍ ነው ። እምነት መደገፍ ከሌለው ሙሉ አይሆንም ። እምነት ሌላው ትርጉሙ ማረፍ ነው ። ሸክምን ለእርሱ ጥሎ በእርሱ አባታዊ ፍቅር እፎይ ማለት ይህ እምነት ይባላል ።
      አንድን ሰው አምነዋለሁ ስንል መጨረሻ ላይ ይገድለኛል እያልን አይደለም ። ኧረ በፍጹም አይደለም ። አይጥለኝም ፣ አይተወኝም ፣ ለእኔ ያለው አሳብ መልካም ነው ማለታችን ነው ። እኛም በክርስቶስ እናምናለን ስንል በዚህ ዓለም ሸንግሎን በሰማይ ግን ገሀነም ይጥለናል ማለታችን አይደለም ። በእርሱ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው ። የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ሳይሆን ከእርሱ ጋር ለመገናኘት በአምልኮ በምግባር እንጸናለን ። በእርሱ ማመን ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር ነው ። አንድ ሰው ሊገድለው ከሚፈልገው ገዥ አምልጦ ወደ ሌላ ግዛት ቢሸጋገር እንደማይነካ ሁሉ እንዲሁም ከጨለማው ገዥ አምልጠን በክርስቶስ ግዛት ውስጥ መኖር እርሱ መዳን ይባላል /ዮሐ. 5፡24/ ። በርግጥ መዳን ተቦጭቆ እየተነገረ ነው ። መዳንን ስንናገር ወይም ትምህርተ ድኅነትን ስንናገር፡-
1-  ለመዳን የተደረገውን ጉዞ ነገረ ሥጋዌን መመርመር ይገባል ።
2-  መዳናችን እንዴት እንደ ተፈጸመ ማስተዋል ያስፈልገዋል ። ይህም ትምህርተ ድኅነት ነው ።
3-  የመዳናችን ግቡ መታየት አለበት ። ይህም በቅድስና ፣ በአምልኮና በምሥጢራት መጽናት ነው ። ክርስቲያናዊ ሕይወት ተብሎ የሚጠናው ይህ ነው ።
      ከመሐል ላይ መዳንን ብቻ ቦጭቀን የምናይ ከሆነ ከፊት መግቢያ ከኋላ መድረሻ ያጣል ። ያዳነንን ማንነት ማወቅ ለቅዱስ ፍርሃት ይረዳል ። መዳናችንን ማወቅ ለእምነት ዕረፍት ያበቃል ። በክርስቲያናዊ ኑሮ መገለጥ ረቂቁን እምነት ያጎላዋል ። ያመነው በልባችን ሲሆን የምንኖረው ግን በገሀድ ነውና ። ሰዎች በምናምነው ሳይሆን በምንኖረው ያውቁናል ። እግዚአብሔር ግን በምናምነው አውቆናል ። አንድ እስር ቤት ብንጎበኝ የቊጥር እስረኛን እናገኛለን ። ምናልባት ሃያ ዓመት ተፈርዶበት ይሆናል ። እንዲሁም የሞት ፍርደኛን እናገኛለን ። የቊጥር እስረኞች አንድ ቀን እንፈታለን ብለው ስለሚያስቡ ይማራሉ ፣ ከሰው ጋር ይተዋወቃሉ ፣ ይሠራሉ ፣ ገንዘብ ያጠራቅማሉ ፣ አመክሮ እንዲያዝላቸው ጠባያቸውን ያሳምራሉ ። የሞት ፍርደኞች ግን እነዚህን ሁሉ አያደርጉም ። ስለ ሞት የሚያጨካክን መጽሐፍ ማንበብ ይወዳሉ ። ቊጡዎችና የሚፈሩ ናቸው ። አንዱን ይዘው መሞት ለእነርሱ ምንም አይመስላቸውም ። ሰው መልካም የሚሠራው የመኖር ተስፋ ካለው ብቻ ነው ። ታዲያ ብዙ ጊዜ እንዳየሁት እነዚህ ሞት ፍርደኞች የሞት ፍርድ ተነሥቶላቸው ወደ ቊጥር ሲለወጥላቸው ወዲያ ትምህርት ይመዘገባሉ ፣ ሥራ መሥራትና ገንዘብ ማጠራቀም ይጀምራሉ ። ከተጣሉት ጋር ይታረቃሉ ። በጎ የሚያሠራ የመኖር ተስፋ ነው ። እንዲሁም ክርስትና በዘላለም ሕይወት ተስፋ የሚጀምር ነው ። ከክርስትና ሃይማኖት በቀር በዚህ ምድር ላይ የመዳንን ተስፋ የሚሰጥ ሌላ ሃይማኖት የለም ። ጌታችን ያገኘነው ዕለት ልጅነትንና የዘላለም ሕይወትን ይሰጠናል ። በመጀመሪያ ቀን የመጨረሻውን የሚሰጥ እርሱ ብቻ ነው  ። ለእርሱም ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብርና ምስጋና ይሁን ። አሜን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ