የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት በሁለት ታላላቅ ክፍሎች ይከፈላል ፡-
ከቊጥር 1-45 ስለ ሳምራዊቷ ሴት
ከቊጥር 46-54 ስለ ሁለተኛው ምልክት
 የዮሐንስ ወንጌል የኢየሩሳሌም ወንጌል በመባል ይጠራል ። ጌታችን በኢየሩሳሌም ስላደረገው ውሎና ትምህርት የሚናገር ወንጌል በመሆኑ ነው ። የዮሐንስ ወንጌልን የኢየሩሳሌም ወንጌል የሚያሰኘው ቀጥሎ ያለውን በመመልከት ነው ።
ከምዕ. 1፡1-52
 ምዕ. 2፡13-3፡36
 ምዕ . 5፡1-47
 ምዕ. 7፡1-20፡31 በኢየሩሳሌም ስለተፈጸመው ተአምርና መከራ እንዲሁም ትምህርት የሚናገር ነው ። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ስለ ገሊላ የሚናገረው ምዕ. 2፡1-12 ዳግመኛም ምዕ. 4፡46-54 እንዲሁም ምዕራፍ 6 እና ምዕራፍ 21 ነው ። ስለ ሰማርያ ምዕ. 4:41-45 ይናገራል ። ከኢየሩሳሌም ውጭ ያለው ትረካ በምዕራፍ ሲቀመጥ ከሦስት ምዕራፍ አይበልጥም ። በሌላ አገላለጽ የዮሐንስ ወንጌል 880 ቊጥሮች ያሉት ሲሆን ስለ ኢየሩሳሌም ያለው ዘገባ 717 ቁጥሮች ያህል ነው ፡፡ ስለዚህ የኢየሩሳሌም ወንጌል መባሉ እውነት ነው ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የዮሐንስ ወንጌል የጥቂት ቀን ውሎና ትምህርት የያዘ መጽሐፍ ነው ። ይኸውም የ19 ቀናት ውሎና ትምህርት በጥቂቱ የሰፈሩበት ነው ፡፡ ወንጌላዊው በመዝጊያው ላይ፡- “ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ይመስለኛል” ብሏል /ዮሐ. 21፡25/፡፡ ሐዋርያው ግምት አያውቅም እንዳንል ሰማይን ያየ የዘመናት ምሥጢር የተብራራለት ነው ፡፡ ደግሞም የ19 ቀናት ውሎና ትምህርት የዮሐንስ ወንጌልን ወልዷል ፡፡ በርግጥም ጌታችን ያደረገውና ያስተማረው ቢጻፍ ምድር አይበቃውም ነበር ፡፡ ለመዳናችንና ለምክር የሚሆነው ግን በበቂ ሰፍሯል፡፡
ጌታችን ከኢየሩሳሌም ውጭ በሰማርያ ያደረገው ጉብኝት ምዕራፍ አራት ላይ ሰፍሯል ፡፡ በዚያም አድራሻ ያደረገው አንዲት ሴትን ነው ፡፡ ሳምራውያን በራሳቸው የተናቁ ናቸው ፡፡ የተናቁት ሳምራውያን የናቋት ሳምራዊቷን ሴት ለማግኘት ጌታችን ግድ ሆነበት ፡፡ ከንቀት ወለል በታች ያለችውን ፣ የተናቁት የናቋትን ሴት ጌታችን መፈለጉ አስገራሚ ነው ፡፡ እርሱ የትኛውም ታሪካችን ወደኋላ አይመልሰውም ፡፡ የትኛውም የወደቅንበት ወለል አይርቀውም ፡፡ ከፍ ሊያደርገን ዝቅ ይላል ፡፡ እርሱ ከፍ ካደረገን በኋላ ማንም ሊንቀንና ሊገፋን አይችልም ፡፡ እርሱ ዋጋችን ነውና ፡፡ ሳምራዊቷ ሴት ሁሉ የናቃትና የጠላት ብትሆንም ክርስቶስ ካከበራት በኋላ ግን መላው ከተማ በአንድ ድምፅ የሚሰማት ሆነች ፡፡ መናቋ ፣ ሴትነቷ ሳይገድባት ስንቱን ወገን ለክርስቶስ አሰለፈች ፡፡ ሰዎች ወንጌልን ለመስበክ ብዙ መላ ያበጃሉ ፡፡ የሚታወቀው ታሪካቸው እስኪረሳ ይጠብቃሉ ፡፡ ይህች ሴት ግን ጥዋት የሸሻት ወገን ከሰዓት በኋላ ተከተላት ፡፡ ብዙ ሰዎች ወንጌልን ለመስበክ የተሻሉ አዳራሾችን ያስባሉ ፣ እግዚአብሔር ከተማውን ሲሰጥ ግን አዳራሽ አይችለውም ፡፡
በምዕራፍ አራት ላይ ሁለት ዓይነት ክስተቶች ተከናውነዋል ፡፡ አንዱ የሳምራዊቷ ሴት ሕይወት መለወጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የቅፍርናሆሙ ሹም ልጅ መፈወስ ነው ፡፡ ጌታችን ድውያነ ነፍስን በትምህርት ፣ ድውያነ ሥጋን በተአምራት ፈውሷል ፡፡ ሳምራዊቷ ሴት ከራሷ ጋር እንድትገናኝ በብርቱ ትዕግሥት አገዛት ፡፡ በኃጢአት በዓመጻ ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጋቸው ትምህርትና ንስሐ ነው ፡፡ ኃጢአትን እንደ በሽታ ቆጥሮ በፈውስ ጸጋ አስለቅቃለሁ ማለት እየበዛ ነው ፡፡ በርግጥ እግዚአብሔር የኃጢአትን ሥር ይቆርጣል ፡፡ ከፊት ለፊቱ ግን ትምህርት ፣ ንስሐና ጥልቅ ፍላጎት አለው ፡፡ ትምህርት በቃሉ ራስን ማየት ነው ፡፡ ያለ ቃሉም ራስን ማየት አለ ፡፡ ያ ግን ወደ በለጠ ኃጢአት እንጂ ወደ ንስሐ አይመራም ፡፡ ንስሐ ላለፈው ተግሣጽ ለአሁኑ ንጹሕ ልብ መቀበያ ነው ፡፡ ጥልቅ ፍላጎትም አስፈላጊ ነው ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ከምንወደው ኃጢአት አያላቅቀንምና ፡፡ ይህንን መርህ የሚከተለውን ኃጢአት በፈውስ አስለቅቃለሁ ማለት ተገቢ አይደለም ፡፡ ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት ብዙ ጉልበት ከሚጨርስ የዝሙት መንፈስ ብሎ ቢገስጽ ከእኛ ይልቅ ለእርሱ ይቀለው ነበር ፡፡ ነገር ግን መንገዱን ጠብቆ የሚሠራ አምላክ ነው ፡፡ አዎ ጌታችን ድውያነ ሥጋን በተአምራት ፣ ሲፈውስ ድውያነ ነፍስን በትምህርት ሲፈውስ እናያለን ፡፡ ምዕራፍ አራት ይህን ይነግረናል ፡፡
ደዌ ነፍስና ደዌ ሥጋ ልዩነት እንዳለው ሁሉ ድውያነ ነፍስና ድውያነ ሥጋም ይለያያሉ ፡፡ ደዌ ነፍስ ንስሐ ይፈልጋል ፣ ደዌ ሥጋ ግን ተአምራት ይፈልጋል ፡፡ ደዌ ነፍስ ባለቤቱ በቀጥታ መገኘት አለበት ፣ ደዌ ሥጋ ግን በሌሎች ጸሎትም መዳን ይቻላል ፡፡ ደዌ ነፍስ አሁን መዳን ቢገኝበትም መላቀቁ ግን ሊዘገይ ይችላል ፡፡ ይቅርታው ቅጽበታዊ መለወጡ ግን በጊዜ ውስጥ ነው ፡፡  ደዌ ሥጋ ግን አልጋን ተሸክሞ መሄድ ነው ፡፡ በደዌ ነፍስ የእግዚአብሔር ፍቅር ይታያል ፡፡ በደዌ ሥጋ ደግሞ የእግዚአብሔር ብርታት ይታያል ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በኃጢአት ለተያዙ ብትጸልይም ዋነኛ አገልግሎቷ ለንስሐ ማብቃት ነው ፡፡ ለደዌ ሥጋ ግን የፈውስ ጸጋን በመጠቀም ትፈውሳለች ፡፡
ጌታችን በሰማርያ ካደረጋቸው ተአምራት አንዱ በሳምራዊቷ ሴት ሕይወት ያበራው የጽድቅ ብርሃን ዘመናትን ተሻግሮ ዛሬም ያበራል ። እርሱ የሥጋችንም የነፍሳችንም ፈዋሽ ነው ። የሥጋችንም የነፍሳችንም ፈጣሪ እርሱ ነውና ለሥጋችንም ሆነ ለነፍሳችን ጥያቄ ሙሉ መልስ አለው ። ጌታችን ዳግም ልደትን ለኒቆዲሞስ ሲገልጥ መንፈሳዊውን አምልኮም ለሳምራዊቷ ሴት ገለጠ ። ታላላቅ ምሥጢሮችን በጉባዔ ሳይሆን በስውር ፣ ለብዙዎች ሳይሆን ለግለሰቦች ገለጠ። ምንም እንኳ ኒቆዲሞስና ሳምራዊቷ ሴት ግለሰቦች ቢሆኑም ልዩነት ግን አላቸው ። ጌታችን ግን ማንንም አይንቅም ። ቅድስናችን ወይም ግድፈታችን ሳይሆን ከጌታ የሚያገናኘን እሺታችን ነው ። እሺ ስንለው ሺህ ይሆንልናል ። ሳምራውያን ቅይጥ ሕዝብ ናቸው ።
በ722 ዓመት ቅድመ ክርስቶስ አሦራውያን መጥተው ይህችን ሰማርያን ወረሩ ፡፡ ያደረጉት ነገር አገር ማፍረስ ፣ ቅጥር ማውደም ፣ ሕዝብ እየነዱ መውሰድ አልነበረም ፡፡ ከአሦር ያሉት የታወቁ ወንበዴዎች አምጥተው በሰማርያ ላይ አፈሰሱ ፡፡ ከሰማርያ ደግሞ ሽማግሌዎችንና የተከበሩ ሰዎችን ማርከው ወደ አሦር ወሰዱ ፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎችና አዋቂዎች ሥነ ምግባር የሚያስተምሩ የአገር ሚዛን ናቸው ፡፡ ሚዛኑ ከጠፋ ልኩ እንደሚጠፋ አሦራውያን በትክክል ያውቃሉ ፡፡ ስለዚህ አገሩን ሽማግሌ አልባ አደረጉትና እርስ በርስ ሆነ ፡፡ የእርስ በርስ ዕድር የተለየ እውቀት የማይገኝበት ነው ፡፡ መከባበርም ስለሌለው ስላለፈው ተግሣጽ ፣ ስለሚመጣው ምክር የማይሰማበት ሁሉም የተነፈሰውን አየር መልሶ የሚስብበት ፣ የተቃጠለ አየር የሚለዋወጥበት ነው ፡፡ ሰማርያ ከአሦር ወንበዴዎች ጋር በማይፈታ ቋጠሮ በጋብቻ ተሳሰረች /2ነገሥ. 17፡24/፡፡ ባሕሏን ሃይማኖቷን ማንነቷን አጣች ፡፡ ስለ ስህተት የሚነግራት የለምና ለመመለስ እንኳ ተስፋ የማትደረግ ከተማ ሆነች ፡፡ እነዚህ ሳምራውያን ከነቢያትና ከሽማግሌዎች ተለያዩ ፡፡ ስለዚህ ቅይጥ ናቸውና ከሁሉም ቅምሻ ቅምሻ የሚይዙ ሆኑ ፡፡ በዚህም ምክንያት ሳምራውያን ኦሪትን እንጂ ነቢያትን አይቀበሉም ነበር ፡፡ በደቡብ የሚኖሩ አይሁዶች ወደ ባቢሎን በ586 ዓመት ቅድመ ክርስቶስ ተማርከው ሰባ ዓመት በግዞት ቆይተው ሲመለሱ ሁለተኛውን መቅደስ በመገንባት ሂደት ሳምራውያን መጥተው ነበር ፡፡ የተከለሱ ዘሮች በመሆናቸው ግን አባረሩአቸው /ዕዝ. 4፡1-4/ ፡፡ በዚህ ምክንያት በደብረ ገሪዛን መስገድ ጀመሩ ፡፡ እንደውም ደብረ ገሪዛን የበረከት ተራራ ነውና ኢያሱ መሠዊያ የሠራበትም ነውና በዕድሜ ከኢየሩሳሌሙ መቅደስ ይበልጣል በማለት መከራከሪያ አነሡ ፡፡ ጌታችን እስኪመጣ ድረስ ስግደት ትክክል የሚሆነው በገሪዛን ነው ወይስ በኢየሩሳሌም የሚል ሕዝባዊ ሙግት ነበረ ፡፡ ጌታችን ግን ለሳምራዊቷ ሴት በሰጠው ምላሽ ከሁለቱም የተለየ የስግደት መንገድ እንደ መጣ ገለጸ፡፡ እርሱም በመንፈስና በእውነት ለእግዚአብሔር መስገድ ነው /ዮሐ. 4፡24/፡፡
ሳምራውያን ምንም የተናቁ ቢሆኑም የተመረጡ ሰዎች ተገኝተውባቸዋል፡፡ ሳምራዊቷ ሴት አንዷ ተጠቃሽ ናት ፡፡ ጌታ ከፈወሳቸው 10 ለምጻሞች አንዱ ለምስጋና ሲመለስ ዘጠኙ ወደ ኋላ ሳይሉ ውለታ በላ ሆነው ሄደዋል ፡፡ ያ የተመለሰው ሰው ግን ሳምራዊ ነበር /ሉቃ. 17፡16/ ፡፡ በኢያሪኮ መንገድ በወንበዴዎች እጅ ለወደቀው ሰው የራራውና ያከመው የተናቀው ሳምራዊ ነው /ሉቃ. 10፡33/፡፡  ሳምራዊው ዓለም ለናቀው ለእግዚአብሔር ልጅ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር፡፡ እግዚአብሔር በሁሉ ቦታ ሰው አለው ፡፡ ከተናቁት መሐልም ለእግዚአብሔር ውድ ገንዘቦች አሉት ፡፡ እግዚአብሔር የወደቀውን በማንሣት የክብር ዕቃ ማድረግ ክብሩም አሠራሩም ነው፡፡ ምናልባት ቤተሰብ የናቀኝ ሞኝ ነኝ አሊያም ሰው ሁሉ የጠላኝ ስደተኛ ነኝ ደግሞም ማንም ወድቀህ ተነሥ የሚለኝ የሌለኝ ብቸኛ ነኝ ትሉ ይሆናል ፡፡ እግዚአብሔር ግን በመብራት የሚፈልገው እናንተን ነው ፡፡ እርሱ የሞኞች ጠበቃ ፣ የተጠሉት አለኝታ ፣ የብቸኞች መከታ ነው ፡፡ እኛም አይተነዋል ፡-
–    ዕውራንን ሲፈውስ
–    ለምጻሞችን ሲፈታ
–    መካኒቱን ባለ ልጅ ሲያደርግ
–    ማቅ ቀዶ ወርቅ ሲያለብስ
–    ምስኪኑን ከጉድፍ ሲያነሣ
–    ብኩኑን ሲሰበስብ
–    የተናቀውን ሲያከብር
–    አለቀለት ለተባለው ዘመን ሲጨምር
–    በረሀብ ዘመን ሲያጠግብ
–    ጉልበት በዛለ ቀን ሲያጠነክር
–    ከተዛተ አይደለም ከተወረወረ ሲያድን
–    ቀንበርን ሰብሮ ቀና ሲያደርግ
–    እስራትን ፈትቶ ነጻ ሲያወጣ
–    የኃጢአተኞች ወዳጅ ሲሆን
–    የሙት ልጅን ሲያሳድግ
–    ሽማግሌውን ሲጦር
–    ልጆቹ ለከዱት ልጅ ሲሆን
–    ቤቱ የፈረሰውን ሲያስጠጋ
–    የተራቆተውን ሲያለብስ
–    ኢያሪኮን ሲያፈርስ
–    ባሕሩን ሲከፍል
–    ድንጉጡን ሲያረጋጋ
–    ምስኪኑን ሞገስ ሲያለብስ
–    ለሕጻናት ጥበብ ሲሆን
–    ሽማግሌዎችን ሲያባብል
–    ቀሳውስትን ሲያጽናና
–    መነኮሳትን አገር ሲያወርስ
–    ባሕታውያንን ሲያለመልም
–    ደንቆሮዎችን ሲያስጠብብ … እኛም አይተነዋል ፡፡
      እንደ እኔ ውለታ ያለባችሁ ዝም አትበሉ ፡፡ ደቦ ለሥራ ፣ ጂጊም ለእርሻ ይጠራል ፡፡ ለምስጋና ደቦ እንጥራ ፡፡ እናቶቻችን፡- “እኔን የሰማ እናንተንም ይስማ ስእለት አለብኝ አግዙኝ” በማለት “ኧረ እሰይ አማኑኤል” እያሉ እንደሚዘምሩ እኛም ምስጉኑን ልናመሰግን ፣ ቡሩኩን ልንባርክ ይገባል።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ