የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል

“እንግዲህ፡- ኢየሱስ ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ያጠምቅማል ማለትን ፈሪሳውያን እንደ ሰሙ ጌታ ባወቀ ጊዜ፥ ይሁዳን ትቶ ወደ ገሊላ ደግሞ ሄደ፤ ዳሩ ግን ደቀ መዛሙርቱ እንጂ ኢየሱስ ራሱ አላጠመቀም” /ዮሐ. 4፥1-3/።
መንፈሳዊ አገልግሎት ቀጣይ የሚሆነው በደቀ መዛሙርት ነው ። ደቀ መዛሙርት ከመምህራቸው እግር ሥር ቊጭ ብለው የሚማሩ ናቸው ። ቀን ለራሳቸውና ለመምህራቸው የሚሆን ምግብ ሲለምኑ ይውላሉ ፣ ሌሊት ከመምህሩ እውቀትን ይቀስማሉ ። መምህራቸውን በሥጋ ያገለግላሉ ፣ መምህሩም በነፍሳቸው ያገለግላቸዋል ። የተመረጠውን ምግብ ሲያገኙ ይህ ለመምህሬ ይላሉና ደቀ መዛሙርት ከራሳቸው በላይ መምህራቸውን ይወዳሉ። መምህራቸውም በፈቃዳቸው ታስረው ፣ በጠባብ ጎጆ መንነው ፣ ዘመናቸውን ሰጥተው ፣ ጠላት ቢመጣ ፣ ራብ ቢነሣ ወንበሩን አላስደፍርም ብለው የሚሞቱ ሰማዕት ናቸው ። ይህ ተዋረድ ያለው ጉዞ ከዘመነ አበው የጀመረ ሲሆን በነቢያትና በሐዋርያት ቀጥሎ እኛ ዘመን ደርሷል ። በዚህ መንገድ ዮሐንስም ጌታችንም ደቀ መዛሙርት ያወጡ ነበር ። ጌታችን መላ የአገልግሎት ዘመኑን የፈጸመው ደቀ መዛሙርትን በማስተማር ነው ። መላውን ዓለም ግን ያገለገለው ግን በሞቱ ነው ። ለዚህ ነው አገልግሎቱ በምድረ እስራኤል ብቻ የተወሰነው። ደቀ መዛሙርቱ ግን እስከ ዓለም ዳርቻ ሄደዋል ። የማንደርስበትን ዳርቻ ለመድረስ ፣ የማንኖርበትን ዘመን ለማገልገል ደቀ መዛሙርት አስፈላጊ ናቸው ። በእግዚአብሔር መንግሥት አዳም ከተፈጠረ ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ያለው መርሐ ግብር የወጣ ነው ። ማንም ሰው ፈጽሞ ከሆነ ከእርሱ በፊት የጀመረ አለ ማለት ነው ። ጀምሮ ከሆነ ከእርሱ በኋላ የሚፈጽም አለ ። የፈጸመው አባቶቹን እንዳይክድ ፣ የጀመረው ደቀ መዛሙርትን እንዳይንቅ ማሰብ ያስፈልጋል ። በዓለም ላይ እኔ ጀምሬ እኔ ፈጸምኩት ማለት አይቻልም ። ራስን ጀማሬና ፈጻሚ ለማድረግ አምላክ መሆን ያስፈልጋል ። እኔ ብቻዬን ጨረስኩት ማለት ትዕቢትን ይወልዳል ፣ እኔ ብቻዬን እፈጽመዋለሁ ማለትም ድካምን ያመጣል ። ሃይማኖት ዘርዐ ክህነት ያለው ሰንሰለቱን ጠብቆ የሚቀጥል እንጂ ተቋርጦ ነበር እኔ ጀመርኩት የሚያሰኝ ነገር አይደለም ። ምክንያቱም የሃይማኖትን ሕያውነት የሚጠብቅ የሚታመነው እግዚአብሔር ነው ። አበው ለነቢያት ፣ ነቢያት ለሐዋርያት ፣ ሐዋርያት ለሊቃውንት ፣ ሊቃውንት ለአባቶች ፣ አባቶች ለእኛ ያቀበሉን ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፡- “ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ በቤተ መቅደስና በመሠዊያው መካከል እስከ ገደላችሁት እስከ በራክዩ ልጅ እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ የፈሰሰው የጻድቅ ደም ሁሉ ይደርስባችሁ ዘንድ” ብሏል /ማቴ. 23፥35/። ከአቤል እስከ ዘካርያስ ድረስ ማለት ከአዳም እስከ ክርስቶስ ማለት ነው ። ይህ 5500 ዘመናትን የሚጠቀልል ነው ። ጌታችን ለሐዋርያቱ ፡- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሏል /ማቴ. 28፥20/። ከክርስቶስ ጀምሮ እስከ ዕለተ ምጽአት ደግሞ በሐዋርያትና የሐዋርያትን ጎዳና በያዙ መምህራን ሃይማኖት ይቀጥላል ። ሃይማኖት መቋረጥ ገጥሞት አያውቅም ። ምክንያቱም ባለቤቱ ከአቤል እስከ ዕለተ ምጽአት ባለው ዘመን አገልጋዮችን ልኳልና ። ይህንን ማመን መቀበል የሚረዳን ለምንድነው ? ስንል ፡-
1-  እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ሥራውን በእቅድ የሚፈጽም እንድናውቅ ነው።
2-  ነገሥታት በሰይፍ ፣ አረማውያን በክህደት ፣ መናፍቃን በስህተት ሃይማኖትን ማጥፋት እንዳልቻሉ እንድንረዳና እንድንጸና ነው ።
3-  ሃይማኖት በእኛ ተጀመረ ብለው የሚያስቡ ሰዎችን አጥርተን እንድናይ ይረዳናል ። በዛሬው ጊዜ በየዕለቱ በሚበቅሉ የሃይማኖት ትምህርቶች የሚሰማው ነገር እግዚአብሔር ሥራውን በእኛ ጀመረ የሚል ድፍረት ነው ። ሃይማኖቱ ትምህርቱ ፍሰቱን ጠበቆ ፣ ከነቢያት ከሐዋርያት ጋር ያለውን ሐረግ አጥብቆ እንደያዘ መመርመር አለበት ።
 መጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ነበሩት ። ጌታችንም ደቀ መዛሙርት ነበሩት ። ጌታችን ግን ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ተብሎ ተወርቶ ነበር ። ጌታችን ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት የሚያደርገው እንዴት ነው ?
1-  መምህራን ተማሪ ለምኖ ያበላቸዋል ፣ ጌታችን ግን አበርክቶ ይመግባል። ።
2-  መምህራን ሁሉ ያዝዛሉ እርሱ ግን የመታዘዝ ጉልበት ይሰጣል ።
3-  መምህራን ሁሉ በሰሌዳ ያስተምራሉ ፣ እርሱ ግን በሕይወት እያሳለፈ ያስተምራል ።
4-  መምህራን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል በማለት ያስተምራሉ ፣ እርሱ ግን እኔ ግን እላችኋለሁ በማለት ያስተምራል ።
5-  መምህራን ሁሉ ይመጣል እያሉ ያስተምራሉ /ነቢያትም ይመጣል ብለዋል አሁን ያሉት መምህራንም ይመጣል ይላሉ/ እርሱ የመጨረሻው ነው ።
6-  መምህራን ሁሉ ስላስተማሩት ነገር በሰይፍ ስለት ፣ በእሳት ግለት ሰማዕታት ይሆናሉ ፣ እርሱ ግን ቤዛ ኩሉ ዓለም ሁኗል ።
7-  መምህራን ሁሉ በእርሱ ስም ያጠምቃሉ ፣ እርሱ ግን ልጅነትን ይሰጣል።
 ቢሆንም መምህራን በቃል ሲያስተምሩ እርሱ በልብ ያትማል ። መምህራን ሲያጠምቁ እርሱ ደግሞ በመንፈሱ ልጅነትን ይሰጣል ። በቃሉ “እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” ብሏል /ማቴ. 28፥20/። ሐዋርያው ጳውሎስም “እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር” ብሏል /1ቆሮ. 3፥6/ ። ከተካዮች ከሚያሳምኑ ፣ ከአጠጪዎች ከሚያስተምሩ ጋር ሁኖ የሚያሳድገው እግዚአብሔር ነው ። “የእግዚአብሔር እርሻ ናችሁ፤ የእግዚአብሔር ሕንፃ ናችሁ፤ ከእርሱ ጋር አብረን የምንሠራ ነንና” ብሏል /1ቆሮ. 3፥9/። ከእግዚአብሔር ጋር የሥራ ባልደረቦች ነን እያለ ነው ። በእርሻው ውስጥ አሳዳጊ እግዚአብሔር ነው ። ገበሬ ሊተክል ሊኮተኩት ይችላል ማሳደግ ግን የእግዚአብሔር ነው ። እንዲሁም ምእመናንን ወደ እግዚአብሔር ቤት ማምጣትና ማስተማር ይቻላል ። ማሳደግ ግን አንችልም ። የሚያሳድገውና የሚለውጠው እግዚአብሔር ነው ። በሕንፃው ውስጥ ድምድማቱን የሚሠራውና የሚኖረው እግዚአብሔር ነው ፣ አገልጋዮች ግን የሚራዱ ናቸው። ስለዚህ እግዚአብሔር በመምህራን ይሠራል ። ይልቁንም ግርማቸው እንደ እሳት ፣ ፍጥነታቸው እንደ ነፋስ በሆኑት በመላእክት ወንጌል አልተሰበከም ። ወንጌል የተሰበከው በደካማው ሰው ነው ። ለምን? ስንል ለሰው የተደረገውን መናገር የሚገባቸው ራሳቸው ሰዎች ስለሆኑ ነው ።
 አዎ ጌታችን ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዛሙርት ያደርጋል ። ደቀ መዛሙርቱንም ከጥሪአቸው እስከ አደራቸው ፣ ከአደራቸው እስከ ሰማዕትነት ቀናቸው እንዴት እንደ ረዳቸው ስናስብ በእርግጥም እርሱ ያሳድጋል ። ጥቂቱን ብናይ፡-
1-  ከተናቀው ሥራቸው ለከበረው ተግባር ጠራቸው ። ዓሣ አጥማጅነትና አናጢነት በዚያ ዘመን የከበረ ተግባር አልነበረም ።
2-  ያለ ምንም የሥራ ልምድ ቀጠራቸው ። ዓሣ የማጥመድ ልምድ ሰው የማጥመድ ልምድ አይሆንም ። ሙሴንና ዳዊትን ከእረኝነት ለንግሥና የመረጠ ደቀ መዛሙርቱንም ለሐዋርያነት ጠራ ።
3-  ተማሪነት በየትኛውም ዕድሜ ቢጀምሩት ልጅ ያደርጋልና የልጅነት ጠባያቸውን ወደደላቸው ። ከልጅነት ጠባይ አንዱ ቁመት መለካካት ነው ። ደቀ መዛሙርቱም ከመካከላችን ትልቅ ማነው እያሉ ቁመት ሲለካኩ በፍቅር አያቸው /ማቴ. 18፥1-4/ ።
4-  ምድራዊ ንግሥናን ፈልገው ቢከተሉትም እስኪገባቸው ድረስ ታገሣቸው። ምክንያቱም ከእከብር ባይ ልብ የሚያላቅቅ መንፈስ ቅዱስ ነውና ። ጌታችን ባረገ ቀን እንኳ ይህን ጥያቄ አቅርበዋል /የሐዋ.1፥6/። ከአሥር ቀን በኋላ ግን በመንፈስ ቅዱስ ይህ ጠባያቸው ተገረዘላቸው ።
5-  ሁሉንም እውነት አልነገራቸውም ። ምክንያቱም እውነትን ለመሸከም የመንፈስ ቅዱስ ትከሻ ያስፈልጋል ። “የምነግራችሁ ገና ብዙ አለኝ፥ ነገር ግን አሁን ልትሸከሙት አትችሉም” አላቸው /ዮሐ. 16፥12/። የሰጣቸውን እንደ ዋጡት ሲያውቅ ቀጥሎ ይጠቀልላል ። ወተትን ለሕጻንነታቸው ፣ ሥጋን ለማዕከላዊነታቸው ፣ አጥንትን ለምሉዕነታቸው አሰናዳ ።
6-  በፈተና ምሽት ክደውት ሲበተኑ እንደገና እንደሚያገኛቸው ተስፋ አደረገ ። እውነትን የቀመሰ የትም አይሄድምና ።
7-  በር ዘግተው ፈርተው ተቀምጠው ሳሉ ፡- “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ አለ” አላቸው /የሐዋ. 1፥8/። በር መክፈት ለፈራ ሰው እስከ ዓለም ዳርቻ ምስክር እንደሚሆን መንገር ቀልድ ይመስላል ። ጌታችን ግን የሆኑትን ሳይሆን የሚሆኑትን ነገራቸው ። አገልግሎትም በሥጋ ጉልበት ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ ረዳትነት መሆኑን አስረዳቸው ።
 ቅዱስ ጴጥሮስን እንኳ ብንመለከት ሦስት ዓይነት ስሞች ተጠቅሰውለታል፡-
1-  በመጀመሪያው ዘመናት የዮና ልጅ ስምዖን የሚል ነው ። የሚያስበው ገና በሥጋ ነበርና በአባቱ ስም ተጠራ ።
2-  በመካከለኛው ዘመን ስምዖን ጴጥሮስ ተብሏል ። ምክንያቱም መንፈሳዊነትና ሥጋዊነት በፈረቃ ይሠሩበት ነበርና ። በአንድ ምዕራፍ ላይ ተመስግኖ እንደ ገና ተወቅሷል /ማቴ. 16፥17 እና 22-23/።
3-  መንፈስ ቅዱስ ከወረደ በኋላ ግን ጴጥሮስ የሚለው ስም ብቻ ረግቷል ። ይህን ስም ገና በተጠራ ቀን ያወጣለት ጌታችን ነው ። ጌታችን በመካከል መፍረክረክና መካድ ቢኖርም የተናገረለት ግን የመጨረሻውን ነው ። ጌታችን የፍጻሜውን እንጂ የመሐሉን አይነግረንም  ። ለምን ስንል የመሐሉ ኃላፊ ነውና ስለሚያልፈው አይናገርም ። አዎ ጌታችን ከዮሐንስ ይልቅ ደቀ መዝሙር ያደርጋል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ