የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የማይደክመው ደከመ

“ኢየሱስም መንገድ ከመሄድ ደክሞ በጕድጓድ አጠገብ እንዲህ ተቀመጠ፤ ጊዜውም ስድስት ሰዓት ያህል ነበረ” /ዮሐ. 4፥6/ ።
ጌታችን ከአርባ ኪ.ሜ. በላይ ተጉዞ ሰማርያ አውራጃ ፣ ሴኬም ከተማ ፣ ሲካር ቀበሌ ፣ የያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ መጣ ። እውነተኛው የሕይወት ውኃ ከውኃው ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ ። ጉድጓዱ ውኃ እንዲያወጣ ተቆፍሯል ፤ ጌታም ለእኛ የሕይወት እርካታ ለመሆን እጆቹ በችንካር ተነድለዋል ። ጎኑም በጦር ተወግቷል ። ጉድጓዱን የቆፈረው ያዕቆብ ነው ። ጌታንም የሰቀሉት የያዕቆብ ልጆች እስራኤላውያን ናቸው ። የጌታችን ቊስሉ በወዳጅ ቤት የቆሰለው ነው /ዘካ. 13፥6/ ። ሙሴ ዓለቱን በበትር ቢመታው ሚሊየኖችን የሚያረካ የውኃ ምንጭ ፈልቋል ። ክርስቶስም በመሰቀሉ ዓለም ድኗል ። እንደ ሕጉ በትር ዓለት ላይ ሲያርፍ ይሰበራል ። አሁን ግን ከሕግ ውጭ በትሩ ዓለቱን ሰበረው ። ደካማው በትር ብርቱ እንዲሆን ብርቱው ዓለት ደካማ ሆነ ። በጽናቱ ዓለት የሆነው ክርስቶስ በበትር ወይም በመስቀል ላይ ዋለ ። ዓለቱ ለበትሩ ካልተሸነፈ እስራኤል በጥማት ረግፈው ይቀሩ ነበር። ክርስቶስም ለመስቀል ሞት ባይታዘዝ ኑሮ ሞተን እንቀር ነበር ። በተአምራት ውኃን ከዓለት ያፈለቀ የእስራኤል ቅዱስ አሁን ለራሱ ውኃን ማፍለቅ አልፈለገም ። እርሱ በገዳመ ቆሮንቶስ ሲራብ ድንጋይን ዳቦ እንዲያደርግ ሰይጣን ሲፈትነው በተአምራት ድንጋዩን ዳቦ አላደረገም /ማቴ. 4፥3/ ። ነገር ግን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣን አበርክቶ አምስት ሺህ ሕዝብ መገበ /ማቴ. 14፥16-21/ ። አምላካዊ ኃይሉን ሌሎችን ለመርዳት ተጠቀመበት ። ተአምራትን አድርጎ ውኃን ለራሱ አፍልቆ ቢጠጣ ኖሮ ያችን ሴት የሚያነጋግርበት ርእስ አይኖርም ነበር ። እርሱ ከጥማቱ በላይ ጥማት ነበረው ። ከረሀቡም በላይ ረሀብ ነበረው ። ጥማቱና ረሀቡ የዚያች ሴት ማረፍ ነበር ። ለደቀ መዛሙርቱም ፡- “እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው” /ዮሐ. 4፥32/ ። በመቀጠልም ፡- “የእኔስ መብል የላከኝን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ሥራውንም እፈጽም ዘንድ ነው” አላቸው /ዮሐ. 4፥34/።
አዳምን በገነት ጫካ ፣ ቃየንን በተቅበዘበዘበት ስፍራ ፣ ሙሴን በተሰደደበት ኮሬብ ፣ ዳዊትን በዋሻው ፣ ጴጥሮስን በባሕሩ ፣ ጳውሎስን በደማስቆ ያገኘ ጌታ ይህችንም ሴት በሲካር ምንጭ አጠገብ አገኛት ። ሁሉንም የሚያገኘው በሕይወት ቀትር ላይ ነው ። አዳም ምርጫው ግራ አጋብቶት ፣ ቃየን ደም እየጮኸበት ፣ ሙሴ የፈርዖን ቂም እየታወሰው ፣ ዳዊት መረሳቱ እያዘመረው ፣ ጴጥሮስ የኑሮ ፍርሃቱ እየናጠው ፣ ጳውሎስ እልሁ እየተናነቀው ፣ ሳምራዊቷ ሴት መገፋቷ እያዋራት ሳለ አገኛቸው ። እርሱ ብቻ የቀትር ጓደኛ ፣ የእኩለ ሌሊት ወዳጅ ፣ የምድረ በዳ አነጋጋሪ ነው። ቀትር ክፉዎች የሚሰለጥኑበት ፣ የሰው ናላ በትኩሳት የሚዞርበት ፣  ለመጸለይና ለማመስገን አቅም የሚጠፋበት ነው ። ከአደጋ ጋርም ተመሳስሏል /መዝ. 90፥6/ ። እግዚአብሔር ግን ከአደጋና ከቀትር ጋኔን ያድናል ። ስንደክም ይበረታልናል ፣ ስንሰንፍ ይተጋልናል ።
እርሱ ብቻ የመጨረሻዋን ሰዓት ያውቃል ። በሰዓቱ ደርሶም ያድናል ። ያቺ ሴት የምትገኝበትን ቦታ ፣ የምትገኝበትን ሰዓት ያውቃል ። በቦታውና በሰዓቱ ተገኘ ። እኛ ሰዎቹ የሚገኙበትን ሰዓት ፣ ቦታና ሁኔታ ላናውቅ እንችላለን ። ለሚያውቀው ጌታ እንልቀቅለት ። ለእርሱም ቀን ቆራጭ ፣ ቦታ አመልካች ፣ ፍርድ አደላዳይ አንሁን ። እግዚአብሔር በልባቸው ካልነገራቸው የትኛውም ጩኸታችን ሰዎችን አይለውጥም ። ስለዚህ እርሱን እያስቀደምን እንናገር ። ራሳቸውን ሲበላቸው እግራቸውን እያከክን ስንቱን ከማስደሰት አሳመምነው ። በፍርድ ጀምረን በቅጣት የምንፈጽምበት ንግግራችን ስንቱን አስደነበረው ። ሕጉ የእኛ እስኪመስል ከማስተማር ተበሳጨን ። ለእግዜር ቀጪ እኔ ነኝ በሚል ስሜት ስንቱን አዋረድን ። ባለጌ ልጅ እናቱን ሲሰድባት አይሰማውም ። ሌላ ሰው ግን ኃይለ ቃል ሲናገራት ይደባደባል ። ለእግዜር የሚደባደቡለት እነርሱ በብዙ እንዳቆሰሉት ይረሳሉ ። ለማንም ሰው ስንናገር ክርስቶስ በእኛ ቦታ ቢሆን የሚናገረውን ልንናገር ይገባናል ። ይህን ብናስተውል ስብከት አሽሙር ፣ ተግሣጽም ስድብ ፣ ምክርም ማሳጣት ባልሆነ ነበር ። ስብከት ሰው ራሱን በክርስቶስ እንዲያይ ማድረጊያ ነው ። ራሱን ያለ ክርስቶስ ማየት ሰውዬው ራሱ ይችላል ። ተግሣጽም የፍቅር ቊጣ ነው ። ምክርም ሰውዬው ለራሱ ያለውን ግምት እንዲጥል ማድረጊያ በፍጹም አይደለም ። ስብከት አሽሙር ሲሆን ቂም በቀል ይበዛል ። ተግሣጽ ስድብ ሲሆን መካሰስ ይነግሣል ። ምክር ማሳጣት ሲሆን ተስፋ የሚቆርጥ ይበዛል ። አፈ ክርስቶስ ለመሆን ያብቃን ። አጥንት በሌለው ምላሳችን የስንቱን አጥንት ሰበርን ። እግዚአብሔር ሳይሰብረን የበደልናቸውን እንካስ ።
ጌታችን በብዙ ድካሙ ስለ ሌሎች ያስብ ነበር ። የዮሐንስ መጥምቅን ሞት በሰማ ጊዜ ብቻውን ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ ማለትና ማረፍ ፈለገ ። ብዙ ሕዝብ ግን ሲከተለው አዘነላቸው ። እነርሱንም ወደ ማገልገል ተመለሰ /ማቴ. 14፥13-21/። በመስቀል ላይ ሳለ የተናገራቸው ቃላት በሕማሙ እንኳ ለሌሎች ማሰቡን እንዳላቋረጠ ያሳያሉ ። አሁንም ደክሞ ሳለ ሳምራዊቷን ሴት ማነጋገር ፈለገ ። ከውኃ በላይ የጠማት ነገር እንዳለ ያም ጥማት በንስሐና በእምነት እንደሚመለስ ሊነግራት መጣ ። የአንድ ሰው ዋጋ በፊቱ ትልቅ ነው ። ከቆሻሻ አንሥቶ የክብር ዕቃ ማድረግ የሚችል አምላክ ነው ።
ጌታችን በለበሰው ሥጋ ደከመ ተባለ ። ደካሞችን ሊያበረታ እርሱ ደከመ ። የተጠሙትን ሊያረካ እርሱ ውኃ ለመነ ። የሕይወት ምድረ በዳ ላዛላቸው ብርታት ለመሆን እርሱ ወደ ምድረ በዳው መጣ ። ኑሮውም ሞቱም የእኛን ዘላለማዊ ጥያቄ የሚመልስ ነበር ። እኛ መድከም ቢገጥመን ለመድከም ፈቅደን አይደለም ። ጥማትም ቢገጥመን ለመጠማት ወስነን አይደለም ። እርሱ ግን የክብር ዙፋኑን ለቅቆ ስደተኛ የሆነው ፣ ሁሉ እያለው ሁሉ የሌለው የሆነው ፣ ሙሉ ክብር ካለበት ሰማይ ሙሉ ውርደት ወዳለበት ምድር የመጣው በፈቃዱ ነው ። በዙፋኑ ሳለ ቢያድነን ኃያል እንለው ነበር ፣ በመስቀል ቢያድነን ግን ፍቅር መሆኑን ተረዳን ። በዚያ በቀትር ደክሞት ከያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ ። ያልቀጠራትን ያችን ሴት እየጠበቃት ነው ። ቢቀጥራት ለመምጣት ፈቃደኛ ላትሆን ትችላለች ። ፍላጎቷ አጠገብ ሁኖ ጠበቃት ። ብቻዋን እያንጎራጎረች የምትመጣው ውኃ መቅዳት እንደ ግዞት አሰልቺ የሆነባት ያች ብቸኛ ሴት እስከ ዛሬ ሰው አይታ አታውቅ ይሆናል ። ዛሬ ግን የእግዚአብሔር ልጅ ከጉድጓዱ አጠገብ ጠበቃት ። በውኃ ጥም ዝሎ ቢሆንም ለመቅዳት ግን ማጥለቂያ አልነበረውም ። ሁሉ እያለው ሁሉ እንደሌለው ሆነ ።
“ከሰማርያ አንዲት ሴት ውኃ ልትቀዳ መጣች ። ኢየሱስም ፦ ውኃ አጠጪኝ አላት ፤ ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማ ሄደው ነበርና” /ዮሐ. 4፥7-8/ ። ይህች ሴት ብዙ ርቀትን አቋርጣ ወደዚህ የውኃ ጉድጓድ ትገሰግስ ነበር ። ይህ የውኃ ጉድጓድ የታወቀ ቢሆንም መንገደኞችና ምንጩን የሚያውቁት የሚፈልጉት ውኃ ነው ። ጌታችን ይህችን ሴት ለማነጋገር ደቀ መዛሙርቱን ወደ ከተማ ልኳቸው ነበር ። ወደ ሕይወቷ ጥልቅ ማንነት ስለሚገባ ኑሮዋንና ድካሟን እንዲሰሙ አልፈለገም ። ነገ የብዙዎች አማካሪ ቢሆኑም ዛሬ ግን ምሥጢሯን እንዲያውቁ አልፈቀደም ። እርሱ አክብሮ ለንስሐ የሚጋብዝ አምላክ ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ያመጡትን ምግብ ኋላ ላይ አልበላውም ። ይህ የሚያሳየን ምግብ ግዙ ብሎ የላካቸው ይህችን ሴት ለመጋረድ ነበር ። ዳግመኛም በዚህች ሴት መዳን መንፈሳዊ ጥጋብ እንደ ተሰማው ያሳያል ።
መንፈሳውያን አገልጋዮች የሌሎችን ምሥጢር መጠበቅ አለባቸው ። በሕይወት ውጣ ውረድ ፣ በሕመምና በኃጢአት ያሉትን ወገኖች በአደባባይ  ሊያነጋግሯቸው ፣ ሊያራቁቷቸው አይገባም ። እንኳን መንፈሳዊ አማካሪ የሥነ ልቡና አማካሪም የሌሎችን ምሥጢር የመጠበቅ የሕግ ግዴታ አለበት ። እኛ የምናምረው ለብሰን ስንታይ ብቻ ነው ። ያለ ሽፋን አናምርም ። ደግሞም ሁላችንም የራሳችን የሆነ ችግርና ድካም አለን ። በሌሎች ለመደነቅ እኛ ነጻ አይደለንም ። እንደውም በባሰ ጉዳይ ውስጥ ልንሆን እንችላለን ። የሌሎችን ምሥጢር የመዝናኛ ጨዋታ ፣ የስብከት ርእስ ማድረግ ትልቅ ጥፋት ነው ። በየአደባባዩ እንፈውሳለን ፣ እናስተምራለን እየተባለ የብዙ ትዳሮችን ምሥጢር የሚያወጡ አገልጋዮች ፣ የበሽተኞችን መልክ በቴሌቪዥን እያሳዩ የሚነግዱ ፈዋሾች በሕግ ሊጠየቁ ፣ በሃይማኖት ሊወገዙ ይገባል ። ወንጌልን እናስተምራለን የሚሉ ወደ ዘርዐ ክህነት የመጡ ወገኖች የሌሎችን ምሥጢር ስለመጠበቅ አጥብቀው ሊማሩ ይገባቸዋል ። የእግዚአብሔር አገልጋይ ለሰማው ምሥጢር አየሁ አላየሁም ፣ ሰማሁ አልሰማሁም የሚል እንጂ ስሙልኝ እያለ የሚለፍፍ ፣ ራሱን ጻድቅ ለማድረግ ሌሎችን የሚኰንን አይደለም ። አገልጋይ ምሥጢር አወጣ ማለት መቃብር አፍ አወጣ ማለት ነው ። ሳይማሩ ማስተማር ፣ ደቀ መዝሙር ሳይሆኑ መምህር መሆን የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ። ጌታችን የዚህችን ሴት ምሥጢር ጠበቀ። ነገ የቤተ ክርስቲያን አምድ የሚሆኑትን ሐዋርያት ዛሬ ተማሪዎች ናቸውና ምሥጢሯን እንዲሰሙ አልፈቀደም ።
ምሥጢርህን ለባዳ ለምን አዋየኸው ?
ወንፊት ውኃ ይዞ የት ሲደርስ አየኸው ?
ይባላል ። መንፈሳዊ አገልጋይ ግን ሰው ከትዳሩ ከቤተሰቡ የደበቀውን የሚያዋየው ትልቅ ዘመድ እንጂ ባዳ አይደለም ። ሲያምኑን ልንታመን ይገባል። አንዳንድ ምእመናን የቀሳውስቱን ምሥጢር መደበቅ አቅቷቸው እኔ እንደ ሰማሁ ዓለም ሁሉ ይስማልኝ እኔ እንዳየሁ ዓለም ሁሉ ይይልኝ ብለው ያዋርዳሉ ። የዘሩትን ማጨድ አይቀርምና ይኸው በሰው ንስሐ የሚነግዱ አገልጋዮችን እያተረፍን ነው ። በዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስና በንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ዘመን የሰው ንስሐን ያወጡ ቀሳውስት በሞት ተቀጥተዋል ። ሰውዬው ንስሐውን ከተናገረ በኋላ አገልጋዩ ተሸክሞታል ። ቢያወጣው የሚጠየቀው አገልጋዩ እንጂ ተነሣሂው አይደለም ። ገዳይ የለም እንጂ ሟችስ ብዙ ነበር እንዳለው ሰውዬ ዛሬ ዐፄ ቴዎድሮስና ንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ቢኖሩ ስንቱ በሞት ይቀጣ ነበር ። በሰው ንስሐና ምሥጢር መነገድ የጥፋት ጥፋት ነው ። ይህ ነገር አሳሳቢ እየሆነ ስለመጣ የሕግ ረቂቅ አሰናድተው ለማቅረብ የሞከሩ ወገኖች እንዳሉ ይታወቃል። በሌሎች አገራት ላይ የሚያስጠይቅ ወንጀል ነው ። ይልቁንም አገልጋይ የእግዚአብሔር ምስለኔ ነውና እግዚአብሔር ሸፋኝ እንደሆነ ሊሸፍን ይገባዋል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ