የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰባቱ ነገሮች

እግዚአብሔር የማያውቃቸው ሰባት ነገሮች አሉ ይባላል ። ማዕምረ ኅቡዓት /የተሰወረውን የሚያውቅ/ እግዚአብሔር አያውቅም ተብሎ የተነገረለት ነገሮች ምንድናቸው ?
1-  እግዚአብሔር አይቻልም የሚለውን ቃል አያውቅም ።
2-  እግዚአብሔር ሊመለስ የማይችል ጸሎትን አያውቅም ።
3-  እግዚአብሔር የፈጠረውን አስቀያሚ ሰው አያውቅም ።
4-  እግዚአብሔር ሊፈወስ የማይችል ቊስልን አያውቅም ።
5-  እግዚአብሔር ይቅር ለማለት የማይችለውን ኃጢአት አያውቅም ።
6-  እግዚአብሔር ሊያድን የማይችለውን ኃጢአተኛ አያውቅም ።
7-  እግዚአብሔር ከአሁን የተሻለ ጊዜ አያውቅም ።
በእነዚህ መመዘኛዎች ሳምራዊቷን ሴት እስቲ እንመልከታት ። የዚህችን ሴት ታሪኳን ፣ ሕይወቷን ፣ ኑሮዋን ፣ ስምዋን መቀየር ለሰው አይቻለውም ። ሁሉን የሚችለው ጌታ ግን ታሪኳን ቀይሮ ሰባኪ ፣ ሕይወቷን ቀይሮ ያረፈች ፣ ኑሮዋን ቀይሮ የተከበረች ፣ ስምዋን ቀይሮ የተለወጠች አደረጋት ። እርሱ የላይ ቁመናችንን ያህል የነፍሳችንን ጉስቁልና ያውቃል ። ይህን እያወቀ ግን የጀመረው “ውኃ አጠጪኝ” በማለት ነው ። ለመስጠት እንጂ ለማሳጣት/ጠበቅ ተብሎ ይነበብ/ ገስግሶ አያውቅም ። ለማጥፋት ኃይልም ሕጋዊ ምክንያትም እያለው እርሱ ግን ኃይሉን እኛን ለማዳን ያውለዋል ። ምሕረቱም ሕጋዊ ይሆን ዘንድ ራሱን ስለ እኛ በመስቀል ላይ ሰጥቷል ። በሕይወታችን ለእኛ ያልተቻሉን ነገሮች ለእርሱ ይቻላሉ ።
ሳምራዊቷ ሴት በየዕለቱ እያዘነች እያጉረመረመች ውኃ ለመቅዳት ወደ ያዕቆብ ጉድጓድ ትመጣ ነበር ። ጌታችን መከፋቷን ያለ ነጋሪ ፣ ኀዘኗንም ያለ አሳሳቢ አወቀ ። ላልፈለጉት የሚገለጥ ፣ ላልጠየቁት የሚገኝ ጌታ ፈልጎ ተገለጠላት /ኢሳ. 65፥1/ ። ጎደለኝ የምትለውን ሳይሆን ያላወቀችውን ጉድለቷን ሞላላት ። የችግሯን ቅርንጫፍ ሳይሆን ሥሩን ነቀለላት ። ወራጁን ሳይሆን ምንጩን ደፈነላት ። በልቧ አደባባይ ላይ ያለውን ብሶት ጸሎት ብሎ አነበበላት ። ከእግዚአብሔር አቅም በላይ የሆነ ጸሎት የለም ። እርሱ እንኳን አቅርቦ ፈጥሮም መስጠት ይችላል።
ሳምራዊቷ ሴት ሁሉ የጠላትና የተጸየፋት ሴት ነበረች ። የእግዚአብሔር ብልሹ ፍጥረት ተደርጋም ተቆጥራ ነበር ። በዚያ ባሕል አምስት ባሎች አግብቶ መፍታት አልተለመደም ። በባሕል ነውር ፣ በሃይማኖት ውጉዝ ፣ በሕግ ወንጀል ነበረ ። ከምንጯ የደፈረሰች ተደርጋም ሳትታይ አትቀርም ። ብልሹ ሰው እንዳልፈጠረ እርግጠኛ የሆነው እግዚአብሔር ፣ በልጅነት ንጽሕና የጀመረውን የዚያችን ሴት የዘመናት አቧራ ሊያነሣላት መጣ ። ሁሉ ሲጥል ዕዳው የእኔ ነው ብላ መድኃኔዓለም ይመጣል ። እርሱ ከአቅሜ በላይ ነው ብሎም ለማንም አሳልፎ አይሰጥም ። የፍጥረቱ የመጨረሻው ተጠያቂ እርሱ ነው ። የቀራጮችና የኃጢአተኞች ወዳጅ ተብሎ መከሰስ የማይፈራ እርሱ ብቻ ነው ። ከሕሊና ከሕግ በላይ ሁኖ የሚምር እርሱ ብቻ ነው ። እርሱ የፈጠረውን አስቀያሚና ብልሹ ሰው አያውቅም ። በፊቱም ትልቅ ኃጢአት የማትረባ ብሎ ሰውን መስደብ ነው ። እግዚአብሔር የማይረባ ሰውን አልፈጠረም ። ሰውን የማይረባ ብሎ መስደብ እግዚአብሔርን የማይረባ ያስቀመጠ ብሎ እንደ መሳደብ ነው ። እግዚአብሔር ተስፋ ባልቆረጠበት ላይ ተስፋ መቊረጥ አይገባም ።
ሳምራዊቷ ሴት ሥጋዋ ዕረፍትን ፣ ነፍሷ ምሕረትን ፣ መንፈሷ አምልኮን ይፈልጋል ። ሥጋዋ በኑሮ ፣ ነፍሷ በኃጢአት ፣ መንፈሷ በአምልኮ ጥማት ቆስሏል ። የሁሉም ፈውስ ያለው እግዚአብሔር ጋ ነው ። ለሶምሶን ኃይል ሥጋዊን ፣ ለዮሐንስ መጥምቅ ኃይል መንፈሳዊን ያስታጠቀ እርሱ ነው። እግዚአብሔር ራሱን በራሱ በኃጢአት ጦር ለወጋው ፣ የኑሮ ጉዳትም ላቆሰለው ፣ የምሕረት ጥማትም ላንከራተተው መልስ አለው ። እነዚህ ቊስሎች በምድራዊ አዋቂ የሚፈወሱ ሳይሆን የሚታወቁም አይደሉም ። እግዚአብሔር ግን ሕልሙም ፍቺውም ለጠፋቸው ሕልሙንም ፍቺውንም ይሰጣል ።
ሳምራዊቷ ሴት ለእኔ ኃጢአትስ ምሕረት የለውም ብላ ተስፋ የቆረጠች ፣ ሰዎችም ምሕረት አይገባትም ብለው የፈረጇት ልትሆን ትችላለች ። የሃይማኖት ነገር ሲነሣም ገብስ ገብሱን መጫወት የፈለገችው ከዚህ ተስፋ መቊረጥ በመነሣት ሊሆን ይችላል ። ጌታ ግን ጓዳዋን ጠቅሶ ነገራት ። ቤትዋ ባል የተባለ አለ ። እርሱን ጠርተሽ ነይ አላት ። ከአንድ ከሁለት በላይ ባል ሙከራ እንጂ ደስታ እንደማይሆን የታወቀ ነው ። ዕረፍት ሳይሆን ብቀላ ነው ። ስለዚህ ይህች ሴት የነበረባት የውኃ ጥማት ብቻ ሳይሆን የዕረፍት ጥማትም ነው ። ሕይወቷ በማያቋርጥ ሙከራ ውስጥ ያልፍ ነበር ። ሙከራ ውጤት ከሌለው ያደክማል ። የምትሞክረው በቤተ ሙከራ ሳይሆን በሕይወቷ ላይ ነውና የምትከፍለው ዋጋ የላቀ ነበር ። የዚህ ሁሉ መፍትሔው ግን እግዚአብሔር ይቅር የማይለው ኃጢአት እንደሌለ ማወቅ ብቻ ነው ። በርግጥም የእግዚአብሔርን ምሕረት የሚፈታተን ከባድ ኃጢአት የለም ።
ሳምራዊቷ ሴት ከዚህ የውድቀት ኑሮ ወጥታ የእግዚአብሔር ሎሌ ትሆናለች ተብሎ አይጠበቅም ። እግዚአብሔር ግን የፈረሰ ሕይወትን በመሥራት የታወቀ ነው ። በፊቱ እንዳለ ያለ ማንም ሰው የለም ። ምሕረቱ ደግፎ ያቆመው ግን እጅግ ብዙ ነው ። እኔን በሥራዬ ፣ እገሌን በምሕረትህ አስበው ማለት አይቻልም ። አልታይ እያለን እንጂ ሁላችንም ጉደኞች ነን ። የሰው ትልቅ ሞኝነቱ የሌላውን ኃጢአት ማውራቱ ነው ። ያለፈውን እየረሳ ወደፊት መዘርጋት የሰው ክብር ነው ። ጳውሎስ ያለፈውን ቢያስብ ነፍሰ ገዳይ ነው ። ጴጥሮስም ያለፈውን ቢያስብ ከሃዲ ነው ። እግዚአብሔር ግን ያለፉትን ሺህ ዓመታት እንደ አሁን ያውቃቸዋል ያስታውሳቸዋል ። ቅድም የተናዘዝነውን ኃጢአት ግን አያውቀውም ። ታዲያ እግዚአብሔር የረሳውን ለምን እኛ እናስታውሰዋለን ? እንዴት እኔ ይህን አደረግሁ ? እንላለን ። እንዴት እኛ ያንን አናደርግም ? ሌሎች ያደረጉትን ሁሉ ያላደረግነው ምሕረቱ ጋርዶን እንጂ ያንን የማያደርግ ሥጋ ስለተሸከምን አይደለም ። የሌሎችን ያህል ብንፈተን እንደ እኛ ብልሹ አይኖርም ነበር ። እግዚአብሔር ከአቅሜ በላይ ነው የመለሰው ኃጢአተኛ የለም ። ዕድሜን የንስሐ ዕድል አድርጎ የሰጠ ጌታ እንዴት ቡሩክ ነው ።
    ጌታችን ለሳምራዊቷ ሴት ከዛሬ የተሻለ ቀን እንደ ሌለ አወቀላት ። አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሕይወቷን ከፈውስ አገናኘላት ። እግዚአብሔር በርግጠኝነት የሰጠን ቀን ዛሬ ነው ። ከዛሬ የተሻለ ምቹና የእኛ ቀን የለም ። ስለዚህ በፊቱ በንስሐ እንውደቅ ። አገር የሚያውቃትን ያችን ሴት ጌታችን አገር ሁሉ እንዲቀበላት አደረገ ። ኃጢአቷ ከተማው ያወቀው ስለነበር ምሕረቷንም ከተማው እንዲያውቀው አደረገ ። በእርሷና በከተማው መካከል የነበረው ልዩነት ሕዝቡ በጨለማ ፣ እርሷ በገሀድ መበደላቸው ብቻ ነው። ምክንያቱም የእርሷን ያህል ክርስቶስ እንዳስፈለጋቸው እናያለን ። ካላዳናቸው በቀርም መድኃኔዓለም ብለው አይጠሩትም ነበር /ዮሐ. 4፥42/ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ