የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ንስሐ

“ሴቲቱ፡- ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ አለችው” /ዮሐ. 4፥15/ ።
ሴቲቱ ስለ ሕይወት ውኃ ፣ ስለማያስጠማው እርካታ በሰማች ጊዜ ከሥጋ ድካም ማረፍ ፈለገች ። ምድራዊ ውኃ በቧንቧ እቤቷ ድረስ የሚመጣ መሰላት ። የማያልቅና የማያደክም ውኃን ፈለገች ። ጌታችን ግን የነገራት የማያስጠማውን የሕይወት ውኃ ነው ። ዶሮ ብታልም ያው ጥሬዋን ነውና እርስዋም ያሳስባት የነበረው ሕይወቷ ሳይሆን ኑሮዋ ነው ። ጌታችን ግን ስለ ሕይወቷ ግድ አለው ። ብልጦች በብልጥነት ያልያዙት ነገር መንፈሳዊነት ነው ። ራስ ወዳዶች ለእኔ ያላሉት የዘላለም ሕይወትን ነው ። ስለ ሆዳችን የሚያስቡት ወላጆች ያልሰጡን ሰማያዊውን ነገር ነው ። ጌታ ብቻ የነፍስን መጠማት ያውቃል ። ቀሳውስት በሚመገቡበት በደጀ ሰላም የተማረውም ያልተማረውም ፤ ሌሊት በቁመት ያደረውም ሲነጋ የመጣውም እኩል ሲመገብ ያዩ አንድ ቄስ፡- “ተማሩም ለእንጀራ አልተማሩም ለእንጀራ” አሉ ይባላል ። በሥራ የምንደክመውም ፣ በሃይማኖት የምንሮጠውም ለዚሁ ለሥጋ ብቻ ከሆነ ጥቅም የለውም ። ያመነውም ያላመነውም የሚሻው ይህን ብቻ ከሆነ ልዩነት እያጣ ይመጣል ። በአገራችን የነበረው የእምነት አስተሳሰብ ሰው እግዚአብሔርን ሲከተል ብዙ ፈተናና መከራ ይደርስበታል ግን በመጽናት ይባረካል የሚል ነበር ። አሁን ግን የሚሰማው ትምህርት እግዚአብሔርን ካመንህ ድሃ አትሆንም አትቸገርም የሚል ነው ። በርግጥ ይህ ትምህርት የአፍሪካ ወንጌል ይባላል ። ለድሃ ሕዝብ ማባበያ ነው እንደ ማለት ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ ግን ስለ ትንሣኤ ሙታንና ስለሚመጣው ሕይወት በተናገረበት ክፍል ፡- “በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን” ብሏል /1ቆሮ. 15፥19/ ።
ጌታችን ለዚህች ሴት በመስጠት ንግግሩን ቢጀምር ኑሮ ትሸሸው ነበር ። በመለመን ስለጀመረ መሸሽ አልቻለችም ። ንግግሩንም የከፈተው በሚያግባባው ርእስ በውኃና በርግጥም ጠምቶት በመሆኑ ሴቲቱ የምትቀበለው ነው ። ስለ ሕይወት ውኃ ሲነግራትም አንተ ከአባታችን ከያዕቆብ ትበልጣለህን ? ስትለው ጌታችን የመጀመሪያ ንግግሩን ወደ መተርጎም ሄደ እንጂ መልስ አልሰጣትም ። አዎ እበልጣለሁ ቢላት ትታው ትሄድ ነበር ። ኋላ የምንናገረውን አሁን ብናዘገየው እየዋሸን አይደለም ። ሰዎች የመለያያ ጥያቄ ያቀርባሉ ። ከጌታችን ግን የተማርነው ቀስ እያልን ማሳደግን ነው ። ወንጌል መስበክ መርዳት እንጂ መንዳት አይደለም ። ወንጌል በፍጹም ጨዋነት የሚነገር እንጂ የድፍረትና የስድብ ደግሞም የትችት መልእክት ያለበት አይደለም ። ዛሬ ብዙዎች የጠሉት ክርስቶስን ሳይሆን ክርስቲያኖችን ነው ። አንዳንዶቹ ክርስቶስን አይመስሉትምና።
ጌታችን የሴቲቱን እምነት አሳደገ ። እርሱን የይሁዳ ሰው ከማለት ጌታ ሆይ ወደ ማለት ከፍ አለች ። ከጕድጓድ ውኃም የሕይወትን ውኃ ወደ መፈለግ መጣች ። ይህን ውኃ እፈልጋለሁ ካለች የሚገኝበት መንገዱ እምነት ነው ። እምነት ሁለት ክፍል አለው ። የመጀመሪያው ኃጢአተኛ መሆናችንን ማመን ሲሆን ሁለተኛው ከኃጢአት የሚያድነውን ክርስቶስ ማመን ነው ።
“ኢየሱስም፦ ሂጂና ባልሽን ጠርተሽ ወደዚህ ነዪ አላት” /ዮሐ. 4፥16/ ። የሕይወት ውኃን ፈልጋለችና ጌታችን ወደ ጓዳዋ ወደ ሕይወቷ ምሥጢር መጣ ። “ሴቲቱ መልሳ፡- ባል የለኝም አለችው ። ኢየሱስ ፦ ባል የለኝም በማለትሽ መልካም ተናገርሽ ፤ አምስት ባሎች ነበሩሽና፥ አሁን ከአንቺ ጋር ያለው ባልሽ አይደለም፤ በዚህስ እውነት ተናገርሽ አላት” /ዮሐ. 4፥17-18/ ። ይህንን ምሥጢር እርስዋ ብቻ የምታውቀው ነው ። ባሎችዋ እንኳ ራሳቸውን እንጂ እርስ በርስ አይተዋወቁም ነበር ። አንዱ ሲወጣ አንዱ ስለሚገባ ደግሞም ከቀን ይልቅ የምሽት ወዳጆች ነበሩና እርስ በርሳቸው አይተዋወቁም። ለዘመናት የደበቀችውን የሕይወቷን ትርምስ ጌታችን ገለጠላት ። ለንስሐ ጋበዛት ። አምስቱን ባሎች ሸኝታ ፣ ስድስተኛውን እቤት አስቀምጣለች ። ባል ሲሞት ሌላ ማግባት ይቻላል ። ሞት ባመጣው ችግር ከሁለትና ሦስት በላይ ማግባት ግን አልተለመደም ። ይህች ሴት ግን እርስዋ ታገባቸዋለች ፣ እርስዋ ታባርራቸዋለች ። በሕሊናዋ ሲሞቱባት ይባረራሉ ። ይህ ያለ መርካትም ችግር ነው ። ከኃጢአት ዕረፍትን የሚመኝ ሰው አንዱን ሞክሮ ሲያቅተው ወደ ሌላ ይሄዳል እንጂ መቆሚያ የለውም ። ኃጢአት ራሱን የማሳደግ ባሕርይ አለው ። በጽድቅ ትይዩ ስላለ ጽድቅ በየጊዜው እንደሚያድግ ኃጢአትም እያደገ ይመጣል ። እስካሁን የተነገሩት እርስዋን የማይነኩ አጠቃላይ ጥሪዎች ናቸው ። አሁን ግን እየቀጠነ ወደ ጓዳዋ መጣ። ንስሐ የሰውዬውና የእግዚአብሔር ግንኙነት ነው ። የጸጋ መጎናጸፊያ ይዞ ለሚጠብቀው አምላክም መራቆት ነው ።
ሴቲቱ በቀጥታ እርስዋን የሚለከተውን ይህን ጥሪ አቅጣጫውን ማዞር ፈለገች ። ከራስዋ ጋር መተያየትና ለአፍታም ቢሆን ኑሮዋን አስባ መጸጸት አልፈለገችም ። በንስሐ ውስጥ ያለውን ቅዱስ ሕመም ማምለጥ ፈለገች ። መፍትሔ ያለውን ጸጸት ጠላች ። ራሳቸውን ለማየትና በንስሐ ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የሚያደርጉትን የሃይማኖት ክርክር አነሣች ። ሃይማኖታዊ ክርክር ንስሐን ለሚጠሉ ሰዎች የዘመናት መደበቂያ ነው ። ለሃይማኖታቸው መኖር የማይፈልጉ ሰዎች ለሃይማኖታቸው መሳደብና መደባደብ ይፈልጋሉ ። ራሳቸውን የማይጠይቅ ከሆነ ምንም ለማድረግ ፈቃደኛ ናቸው ። እግዚአብሔር ግን ንስሐ ያልቀደመበትን አገልግሎት አይወድም ። ሰዎች ዛሬም ለንስሐ ሲጋበዙ ፣ ከራሳቸው ጋር ሊገናኙ ሲሉ “እኛ እኮ የቱን እንደምንሰማ ግራ ገባን እንዲህ የሚባሉ መናፍቃን መጥተዋል ይባላል ፣ ሃይማኖታችንን ማስነካትማ የለብንም” ይላሉ ። ለዚህ ነው እየሰረቁ አስራት ማውጣት ፣ እየሰከሩ ጠበል መጠጣት ፣ እየገደሉ ቤተ ክርስቲያን ማሳነጽ ፣ ወንድምን እየጠሉ መዘመር እየበዛ የመጣው ። ሃይማኖትን የሚገልጡ ልብሶችን መልበስ ፣ ማስታወቂያዎች መለጠፍ ይቻላል ። ትልቁ ነገር ግን ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር መታረቅ ነው ። ሰማዕትነትም ሰማዕትነት የሚሆነው ለኖርንለት ሃይማኖት ስንሞት ነው ።
“ሴቲቱ ፡- ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ፤ እናንተም፡- ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው”  /ዮሐ. 4፥19-20/ ።
ሴቲቱ የይሁዳ ሰው ፣ ጌታ ሆይ ከሚለው አጠራሯ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ ወደሚል አጠራር አድጋለች ። ራሷን የሚመለከተውን የንስሐ ጥሪ ግን መሸሽ ፈለገች ። የሸሸችው ደግሞ ማለቂያ ባጣው የሃይማኖት ክርክር ውስጥ ነው ። ሳምራውያን በገሪዛን ተራራ መቅደስ ሠርተው ያመልካሉ ። አይሁዳውያንም በኢየሩሳሌም ባለው መቅደስ ያመልካሉ ። ሳምራውያን በታሪክም በትእዛዝም የገሪዛን መስገጃ ቀዳሚ ነው ። አብርሃምም ሙሴም ያዕቆብም አሉበት ። የኢየሩሳሌም መቅደስ ግን በኋላ ዘመን በሰሎሞን የተሠራ ነው ይላሉ ። አይሁዳውያንም አብርሃም ልጁን የሠዋበት በዚሁ በሰሎሞን መቅደስ አቅራቢያ ነው ፣ በእግዚአብሔር ትእዛዝ የተገነባ ነው ስለዚህ ማንም ሰው ጸሎቱ ተሰሚ ፣ መሥዋዕቱ ሥሙር የሚሆነው በኢየሩሳሌም ባለው መቅደስ ነው ይላሉ ። ይህ ሃይማኖታዊ ክርክር ጦርነትን ጭምር አስነሥቶ በገሪዛን ያለው መቅደስ እንዲፈርስ አድርጎታል ። ሳምራዊቷ ሴትም ማዶ ይህን የፈረሰ መቅደስ ለጌታችን እያሳየች ፡- “ጌታ ሆይ፥ አንተ ነቢይ እንደ ሆንህ አያለሁ ። አባቶቻችን በዚህ ተራራ ሰገዱ ፤ እናንተም፡- ሰው ሊሰግድበት የሚገባው ስፍራ በኢየሩሳሌም ነው ትላላችሁ አለችው”  /ዮሐ. 4፥19-20/ ።
በትልቁ ያስጨነቃት ይህ ሃይማኖታዊ ክርክር ሳይሆን ራሷን ለመደበቅ ዋሻ መፈለጓ ነው ። ጌታችን ለንስሐ የጋበዛት መጀመሪያ መፍትሔውን በመናገር ነው ። እርስዋ ግን ፈቃደኛ አልነበረችም ። ሰዎች በተለያየ ምክንያት ከንስሐ ይዘገያሉ ። ከምክንያታቸው አንዱ ለእኔ ኃጢአት መፍትሔ የለውም ብለው ማሰባቸው ነው ። ዛሬም ስለ ኃጢአታቸው ንስሐ መግባት የማይፈልጉ ሰዎች በሃይማኖት ሙግት ውስጥ ግን ዋነኛ ናቸው ። ንስሐ ከገቡ በኃጢአት ምክንያት የሚመጣው የገንዘብ ገቢያቸው የሚቀርና የሚቸገሩ ስለሚመስላቸው እምቢ ይላሉ ። እግዚአብሔር ግን በረከትን እንደሚሰጥ ሊያስቡ ይገባቸዋል ። ብዙ ተከራካሪዎች ከእውቀቱም ፣ ከሃይማኖቱም ፣ ከሥርዓቱም የሉበትም ።
በአቡነ ቴዎፍሎስ ዘመነ ፕትርክና ነው ይባላል ። ሁለት ሰዎች በገና ጾም ሥጋ ለመብላት ወደ ሥጋ ቤት ይሄዳሉ ። ሲሄዱም የሚያወሩት የገና ጾም ሊቀነስ ነው አሉ የሚለውን ሐሜታ ነው ። ወደ ሥጋ ቤቱ ሲገቡ አንድ የሚያውቁት ሰው ሥጋውን በአፉ በእጁ ቢላዋ ይዞ እየገዘገዘ ነው ። እነርሱም፡- “አንተ የገና ጾም ሊቀነስ ነው አሉ” ይሉታል ። እርሱም ሥጋውን በአፉ እንደያዘ ቢላውን እየገዘገዘ ፡- “እንሞታታለን እንጂ አባቶቻችን የሠሩልን የገና ጾም አይቀነስም” አለ ይባላል ። ራሱ ያፈረሰውን ሌሎች እንዲጠብቁለት ይፈልጋል ። ለማይኖሩለት ሃይማኖት እንሞታለን ማለት ጥቅም የለውም ። ሃይማኖትን ማወቅ ንስሐ መግባት ፣ በቅዱስ ቁርባን መጽናት ፣ በአገልግሎት መሠማራት ያስፈልጋል ።  ሳምራዊቷ ሴት ዋሻ ውስጥ ገባች ። አዳምና ሔዋን በጫካ ፣ ቃየን የሚያውቀውን አላውቅም በማለት እንደ ተደበቁ እርስዋም በሃይማኖት ሙግት ውስጥ ተደበቀች ። እኛስ ቀላሉ ንስሐ ከብዶን ይሆን ? ለሃይማኖት መቅናታችን መልካም ነው ። በቆሸሸ ገላ ሽቱ ቢቀቡ መቆሸሹን ያጎላዋል እንጂ አይቀንሰውም ። እንዲሁም ንስሐ ባልገባ ማንነት ብንደክም መቆሸሹን ያጎላዋል ። ከሽቱው ዋጋ የውኃው ዋጋ ትንሽ ነው ። ንስሐም በጣም ቀላል ነው ። የሚቀድመውን እናስቀድም። ሒሳብ ሳይተሳሰብ ይቅር የሚል ጌታ ይኸው ቆሞ እየጠበቀን ነው ። ካለበት ሊወስደን ካለንበት ቦታ መጥቷል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ