የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ክርስቶስ ይመጣል

“ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች ለሰዎችም፡- ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች። ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር” /ዮሐ. 4፥28-30/።
ይህች ሴት በጣም ብልሃተኛ ሴት ናት ። የጌታችንን ማንነት በሚገባ ተረድታለች ። እርስዋ ወደ መንፈሳዊ አካለ መጠን እንዴት እንዳደገችና ከእውነቱ ለመሸሽ ስታደርገው የነበረውን ሙከራ አስታወሰች ። የተደረገላትን ለሰማርያ ሰዎች ስትደግም ትታያለች ። ንግግሯ ጥበብን የተሞላ ነው ። እርስዋ ኃጢአተኛ ሴት እንደሆነች ኃጢአተኞች ሁሉ ያውቃሉ ። የእርስዋ የተገለጸ ፣ የእነርሱ የተደበቀ መሆኑን እግዚአብሔር ያውቃል ። ሰዎች የሚጽናኑት በእግዚአብሔር ምሕረት ሳይሆን በሰዎች አለማወቅ ወይም ጻድቅ መስሎ በመታየት ነው ። ይህች ሴት ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን አለች ። ያደረግሁለትን አላለችም ። ከእኔ ምንም መልካም ነገር የለም ብላ የምታምን ናት ። ያደረግሁትን ስትል የሰማርያ ሰዎች ያውቋታልና ጆሮአቸውን ይከፍታሉ ። በዚህ ውስጥ ሁለት ነገሮችን ማየት እንችላለን፡-
1-  ይህች ሴት የምታወራው ለመላው ከተማ ነው ። ስትጮህ ስትሮጥ አይታያችሁም ? እኔ በጣም እያየኋት ነው ። ስለ ክርስቶስ ፍርሃትንና ይሉኝታን አሸንፋለች ። ደግሞም በደስታ ሰክራለች ። ቀድሞ የማትወደውን ሰው ለማቀፍ መስከር ነበረባት ። አሁን ግን የማታውቃቸውን ሰዎች ሕይወት ያስፈልጋችኋል ለማለት ክርስቶስ አስፈለጋት ። በተለያዩ ስፍራዎች መጠጥ የሚያገለግለው የማያውቁትን ሰው ለመውደድ ነው ። ሲነቁ ግን ያፍራሉ ። የማያውቁትን ሰው ለመውደድ ክርስቶስ በቂ ነው ። ፍቅሩም ቅዱስ ነው ።
2-  ንስሐዋን በአደባባይ እየተናገረች ነው ። እስከ ዛሬ የሰማርያ ሰዎች የራሳቸውን አስቀምጠው የእርስዋን ኃጢአት ይናገሩ ነበር ። እርስዋም እነርሱ ካወሩት ብላ እየጨመረችበት ትኖር ነበር ። እነርሱ ዝም ሲሉ እርስዋ መናገር ጀመረች ። ከምሕረትዋ ተነሥታ ስለምትናገር የዳነ ቊስልን እንደ ማውራት ነው ። እግዚአብሔር ይቅር ሲል በቅጽበት እንጂ በሂደት አይደለም ። ጌታችን በአጭር ቃል ኑሮዋን ሁሉ ነገራት ። አምስት ባሎች ነበሩሽ አሁን ያለውም ባልሽ አይደለም አላት ።
ይህች ሴት ክርስቶስ መሢሕ መሆኑን ካመነች በኋላ ዋጋ ስትከፍል ትታያለች ። የመጀመሪያው እንስራዋን ጥላ መሄዷ ነው ። ለዛሬ እንደሚጎድልባት እርግጥ ነው ። ያተረፈችው ግን ዘላለማዊውን ነው ። ከዕለት ኑሮ ወደ ዘላለም ሕይወት አደገች ። እግዚአብሔርን ሲከተሉ ከጉድለት ፍርሃት ወጥቶ መሆን እንደሚገባው በዚህ እንማራለን ። ስለ ክርስቶስ የሚጎዳንን ኃጢአት ብቻ ሳይሆን ጥቅም የሚመስለውን ነገርም መተው ይገባል ። ይህች ሴት በሁለተኛ ደረጃ እኔ እንደ ዳንሁ ሌላውም መዳን አለበት ብላ አሰበች ። በዚህም ክርስቶስ ከእርስዋ አልፎ ለብዙዎች እንደሚበቃ አምናለች ። ደግሞም ስስት የሌለበት ሰማያዊ ፍቅር አድሮባታል። አትሰማም ተብላ ተስፋ የተቆረጠባት ሴት ይህን ያህል በረከት ሲገኝባት እናያለን ። በርግጥም  ጌታችን በዚያ ቀትር የደከመው እንዲሁ አይደለም ። እውነት አትመክንም ። አገልግሎት እስከ የት ነው ? ስንል አያት እስኪሆኑ ድረስ ነው ። ጌታችን ይህችን ሴት አገለገለ ። ወዲያው ያገለገለችውን ሕዝብ አየ ። ሴቶች ላመኑበት ነገር ይሉኝታና ፍርሃት የላቸውም ። በዘመናት እግዚአብሔር ሠርቶባቸዋል ። ዛሬም እየሠራባቸው ይገኛል ።
እውነትዋን ነው ። የእርስዋ ኃጢአት የራስዋ ብቻ አይደለም ። አካባቢውም ያሳደረው ተጽእኖ ነበረው ። ቤትዋ በንጽሕና እንዲኖር አካባቢዋ መጽዳት አለበት ። ልብ አድርጉ ያላስተማሩት ሕዝብ ጠላት ነው ። ያስተማሩት ሕዝብ ግን ወዳጅ ነው ። ይህች ሴት ከዚህ ቀን በኋላ መላው ከተማ ጠባቂዋ ነው ። ከበደለችው በላይ በክርስቶስ ክሳለች ። ሰዎች ከበደሉት በላይ የሚክሱት ክርስቶስን ሲሰጡ ነው ። ሰማርያ ከሰባት መቶ ዓመታት በፊት ዝናብ አጥታ ተጨንቃ ነበር ። ሦስት ዓመት ከስድስት ወራት የጠፋው ዝናብ በአንድ ቀን ንስሐና እምነት ተለቀቀ /1ነገሥ. 18/። በዚያ ዘመን የነበረው ነቢይ ኤልያስ ነው ። ስሙም መዐርጉም ይታወቃል ። ዛሬ ግን ስም የለሽ የሆነችው ሴት የሕይወትን ውኃ ለተጠማው ሁሉ አዳረሰች።
ስለ ክርስቶስ የተናገረችው ንግግር ጥበብ የሞላበት ነው ። “ሴቲቱም እንስራዋን ትታ ወደ ከተማ ሄደች ለሰዎችም፡- ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ሰው ኑና እዩ፤ እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን? አለች። ከከተማ ወጥተው ወደ እርሱ ይመጡ ነበር” /ዮሐ. 4፥28-30/። ከራስዋ የኃጢአት ኑሮ ማለትም ከታወቀው መገለጫዋ ተነሥታ ስለ ክርስቶስ ተናገረች ። አሳቧ እኔን ያዳነ እናንተንማ ያድናል የሚል ነው ። ዳግመኛም እርስዋን የረዳ እኛንም ይረዳል የሚል አሳብን የሚቀሰቅስ ነው ። የዚህች ሴት አገልግልት ስብከት አልነበረም ምስክርነት ነው ። ምስክርነት አይቻለሁ ሰምቻለሁ ነው ። ይህን ለመናገር ኮሌጅ መግባት አያስፈልግም ። “ሴቲቱም፡- ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት” ይላል /ዮሐ. 4፥39/ ። በቀጥታ ክርስቶስን አገኘሁ ብትል እርስዋንም ይህ ስካርሽ እስከ መቼ አይለቅሽም ? ማለታቸው የማይቀር ነው ። ክርስቶስንም ሐሰተኛ ነው ብለው ይገፉት ፣ ሳያዩት ይጣሉት ነበር ። እርስዋ ግን እንጃ በሚለው የሚያጓጓ ንግግር ልባቸውን አነሣሣች ። መንገድ እንዳይዘጉ ወደ ቀጣዩ ሂደት እንዲሄዱ ነገሮችን ክፍት አደረገች ። ጌታችን እርስዋን ወደ ሕይወት ያደረሳት በዚህ መንገድ ነው ። እርስዋም የተደረገላትን ደገመችው ። ኋላ ላይ እነርሱም ፡- “ሴቲቱንም፡- አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር” /ዮሐ. 4፥42/ ።
ይህች ሴት ለዚያ ከተማ ስስ ርእስ ነበረች ። የእርስዋ ነገር ይገንን ነበር። ሰዎች በሁለት መንገድ ተጽእኖ ይፈጥራሉ ። የመጀመሪያው በደግ ሲሆን ሁለተኛው በክፉ ነው ። በደግ ተጽእኖ መፍጠር ሲያቅታቸው ወደ ክፉ የሚሄዱት በዚህ ምክንያት ነው ። በርግጥም ጌታችን መላውን ከተማ በማን ማግኘት እንዳለበት ያውቃል ። አብርሃምን ሲጠራው ዘሩን እንዳየ ይህችንም ሴት ሲጠራት ከተማውን በእርስዋ ውስጥ አይቷል ። በእናንተ ውስጥ ያየው ምን ይሆን ? ያየላችሁን ለማየት ያብቃችሁ ።
ስለ ክርስቶስ መሢሕነት ማስረጃ ያደረገችው የራሷን ሕይወት ነው ። እርሱ ክርስቶስ ባይሆን ከሚያጎብጠው ኑሮዬ አይገላግለኝም ነበር የሚል ስሜት ያዘለ ንግግር አደረገች ። እውነት ያልሆነ ነገር አያሳርፍም ። ክርስቶስ ይሆንን ? የሚለው ንግግር የክርስቶስን መምጣት ብዙዎች ይናፍቁት እንደ ነበር ያሳያል ። ክፋት በበዛ ቊጥር የመሢሑ መምጫ ቀርቧል ብለው ያምኑ ነበር ። ሊነጋጋ ሲል ይጨልማልና ። ያ ዘመንም በርግጥ መሢሑ እንደሚመጣ ሁሉም ሰው ተስፋ የሚያደርግበት ነበር ። ከሰው አልቋልና አሁን የቀረው የእርሱ ምጽአት ነው ብለው ያምኑ ነበር ። ያ ዘመን ሰዎች ራሳቸውንና ኑሮአቸውን ለመርሳት በማለዳ መጠጥ ላይ የሚሰየሙበት ፣ ከሚሠሩት የማይሠሩት የበዙበት ፣ በአእምሮ ጭንቀት በየስፍራው ጩኸት የበዛበት ፣ የሰው ሁሉ ፊት በኀዘን የጠቆረበት ፣ መጥፎ መርዶዎች የሚሰሙበት ፣ የቅኝ ገዥዎች በትር የጠነከረበት ፣ ነጻ እናወጣለን የሚሉ በትንሽ አቅማቸው ጫካ የገቡበት ፣ ካህናት ነጋዴዎች የሆኑበት ፣ ፈራጆች ፍትሕን እንደ ሸቀጥ የሚሸጡበት ፣ ተላላፊ በሽታዎች የተስፋፉበት ፣ ወጣቶች ተስፋቸው የጨለመበት ፣ ሕጻናት የሚፈልግ ቤተሰብ አጥተው አገር ካገር የሚጓዙበት ፣ ብዙዎች በመንፈሳዊው አገልግሎት ልባቸው የዛለበት ፣ የራስ ክብርና ጥቅም ብቻ ቅድሚያ የሚሰጥበት ፣ አገራዊ ስሜት የደበዘዘበት ፣ ሃይማኖት የካህናት ፣ አገር የፖለቲከኞች ጉዳይ የመሰለበት ፣ ሁሉ ለመሰደድ የቸኮለበት ፣ በምድረ እስራኤል ከነበረው እስራኤላዊ በደጅ ያለው እስራኤል የበለጠበት ፣ ነቢያት ከተነሡ አራት መቶ ዓመታት ያለፈበት ፣ ሐሰተኛ ክርስቶሶች ደግሞ ደጋግመው የመጡበት ዘመን ነበር ። ይህንን ዘመን ያዩና የዛሉ አሁንማ የክርስቶስ መምጫ ደርሷል ብለው ያምኑ ነበር ። አንድ ደስ የሚል ቃል አለ፡-
“ደጆቹ ተዘግተው ሳሉ፥ ኢየሱስ መጣ፤ በመካከላቸውም ቆሞ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው” /ዮሐ. 20፥19/ ። እርሱ መግቢያ መውጫው ደጅ ሲዘጋ ፣ ፍርሃት ነፍስ ውስጥ ገብቶ ሲንጥ ፣ ሁሉም ነገር ሲበላሽ ፣ ከካህናት ጽድቅ ፣ ከመኳንንት ፍርድ ሲታጣ … ይመጣል ። ዛሬም ዘመኑ ያንን ዘመን ይመስላል ። ጌታችን ግን ይመጣል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ