ታላቅ ጥጋብ
“ይህም ሲሆን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ፡- መምህር ሆይ፥ ብላ ብለው ለመኑት። እርሱ ግን፦ እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው ። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፡- የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ” /ዮሐ. 4፥31-33/።
ጌታችን ከከተማይቱ ወጣ ብላ ባለችው የውኃ ምንጭ አጠገብ ሳምራዊቷን ሴት ካነጋገረ በኋላ እርስዋ መልእክተኛ ሁኖ ወደ ሰማርያ ሄደች። እርስዋን ፍለጋ ያለችበት ድረስ የመጣ ጌታ የሰማርያ ሰዎችን ግን የውኃ ምንጭ ላይ ሁኖ ጠበቃቸው ። ከዚህ ውስጥ ብዙ ነገሮችን እንማራለን፡-
1- ሴቲቱን መልእክተኛ አድርጎ ላካት ። ይህች ሴት የሰዎችን ማንነት በደንብ ታውቃለች ። ሰዎች ቀንና ማታ የተለያዩ እንደሆኑ በሚገባ ትረዳለች ። ሐሰተኛ ፍቅርን በመጠጥ የሚያመጡ እውነተኛ ጥላቻን ግን ያለ መጠጥ የሚያራግቡ እንደሆኑ ከእርስዋ የተሰወረ አይደለም። የቀን ጌቶች የምሽት ሞዛዞች እንደሆኑ ይህች ሴት በዕለት ኑሮዋ ታውቃለች ። ጌታችን አውራዋን አድኖ እርስዋን መልእክተኛ አድርጎ ላካት ። ከሞት መነሣቱንም እንድትናገር የላካት የመጀመሪያዋ የትንሣኤ ምስክር መግደላዊት ማርያም ናት ።
2- ሳምራዊቷን ሴት ካለችበት ድረስ ገስግሶ አዳናት ። እነርሱን ግን ምንጩ አጠገብ ሁኖ ጠበቃቸው ። እነርሱ በመልእክተኛ እሺ የሚሉ ናቸው ። እርስዋ ግን እርሱ ራሱ ካልሄደ በጀ የማትል ናት ። የእርሱ ትዕግሥትና ፍቅር ካልሆነ ማንም ሊያተርፋት አይችልም ።
3- የከተማው ዳርቻ ላይ ሁኖ እስኪፈቅዱለት ጠበቃቸው ። ከፈቀዱለትና ካመኑበት በኋላ ገብቶ ሁለት ቀን ያህል ከእነርሱ ጋር ኖረ /ዮሐ. 4፥40/ ። እርሱ ካልከፈቱለት ሰብሮ አይገባም ። ፈቃድን የሰጠ ፈቃድን የሚያከብር አምላክ ነው ። ወደ ሕይወታችን ወደ ቤታችን ወደ ከተማችን እንዲገባ በሩን መክፈት ይገባል ። ከገባ ጸጋን ሲሰጥ አይጎድልበትም ።
ደቀ መዛሙርቱ ምግቡን ገዝተው ሲመጡ ሳምራዊቷ ሴት በጌታችን አምና ስለ አዳኝነቱ መስክራ መላ ሰማርያን ከኋላዋ እያስከተተች መጥታለች። የገዙትን ምግብ እንዲበላ ለመኑት ። ጌታችን ግን ምንም በለበሰው ሥጋ ቢደክመውና ቢርበው በውኃ ጥም ቢዝልም አሁን በዚህች ሴት መዳን ረካ ። በታላቅ ደስታም ጠገበ ። በኃጢአተኛው መመለስ እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን ቅዱሳን መላእክት እንኳ በጣም ደስተኞች ናቸው ። ይህንን የተማሩት ከእግዚአብሔር ነው ። ጌታችን እንዲበላ በለመኑት ጊዜ እናንተ የማታውቁት የምበላው መብል ለእኔ አለኝ አላቸው ። ደቀ መዛሙርቱ ገና ተማሪዎች ናቸውና ይህን መብል አያውቁትም ነበር ። በሰዎች መዳን የሚገኘውን ደስታና ጥጋብ ለማጣጣም ገና ናቸው ። ሐዋርያው ጴጥሮስ አንድ ቀን ተርቦ ሲጸልይ ሳለ አንድ ራእይ ወደ እርሱ መጣ ።
“ሰማይም ተከፍቶ በአራት ማዕዘን የተያዘ ታላቅ ሸማ የሚመስል ዕቃ ወደ ምድር ሲወርድ አየ ፤ በዚያውም አራት እግር ያላቸው ሁሉ አራዊትም በምድርም የሚንቀሳቀሱት የሰማይ ወፎችም ነበሩበት። ጴጥሮስ ሆይ፥ ተነሣና አርደህ ብላ የሚልም ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ጴጥሮስ ግን፡- ጌታ ሆይ፥ አይሆንም፤ አንዳች ርኵስ የሚያስጸይፍም ከቶ በልቼ አላውቅምና አለ።ደግሞም ሁለተኛ፡- እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው የሚል ድምፅ ወደ እርሱ መጣ። ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፥ ወዲያውም ዕቃው ወደ ሰማይ ተወሰደ” /የሐዋ. 10፥9-16/። ራእዩ የሚያመለክተው ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ቆርኔሌዎስንና ቤተሰቡን እንዳትንቃቸው ሄደህ አገልግላቸው ለማለት ነው ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም ይህን ሲተረጉም፡- “አይሁዳዊ ሰው ከሌላ ወገን ጋር ይተባበር ወይም ይቃረብ ዘንድ እንዳልተፈቀደ እናንተ ታውቃላችሁ፤ ለእኔ ግን እግዚአብሔር ማንንም ሰው ርኵስና የሚያስጸይፍ ነው እንዳልል አሳየኝ” ብሏል /የሐዋ. 10፥28/ ። መብል የሌሎች መዳን ነው ። ሌሎች ሲያርፉ ማየት ፣ ክርስትናን ሲቀበሉ መመልከት ጥጋብ ነው ። የራስን ጉዳትና ጥያቄ ሁሉ ያስረሳል ። የክርስቶስ ልብ ሲኖረን እንዲህ እንሆናለን ማለት ነው።
ደቀ መዛሙርቱ ጥጋብን የሚያውቁት በመብል ብቻ ነበር ። መብል ግን ብዙ ትርጉሞች እንዳሉት ሁሉ ጥጋብም ልዩ ልዩ ነው ። ጌታችን መብልን ብቻ ፈልገው ለተከተሉት ሰዎች የተናገረው ንግግር ይህንን ይፈታል። “ለሚጠፋ መብል አትሥሩ፤ ነገር ግን ለዘላለም ሕይወት ለሚኖር መብል የሰው ልጅ ለሚሰጣችሁ ሥሩ፤ እርሱን እግዚአብሔር አብ አትሞታልና”/ዮሐ. 6፥27/። ዘላለም የሚኖር መብል አለ ። የምድሩ ጥዋት ለቀትር የሚጠፋ ፣ መልሶ የሚርብ ነው ። ጌታችን አትሥሩ አላለም ። ለመብል ብቻ አትኑሩ ማለቱ ነው ።
ደቀ መዛሙርቱ የሚበላ አንድ ሰው አምጥቶለት ይሆናል ብለው አሰቡ። መንፈሳዊ ጥጋብን መረዳት አልቻሉም ። ጥጋብን በመብል ብቻ ይለኩ ነበር። ሰዎች ያላችሁን ተናገሩ ሲባሉ የሚናገሩት ንብረት የላቸውምና ይሸማቀቃሉ። አንድ ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፈልጌ ንብረት ምን አለህ ? ስባል “መድኃኔዓለም” አልኩኝ ። መልሱንም ሲሰሙ፡- “ከእርሱ የበለጠ ምን አለ ? የእኔም ተስፋ እርሱ ነው ። ከሕጻንነቴ ጀምሮ ተስፋ የማደርገው እርሱን ነው ። በእናቴ ሆድ ከፈሳሽ ያረጋኸኝ ፣ ሰው አድርገህ የፈጠርከኝ አንተ ነህ ። ሰማይን ያለ መደገፊያ ያቆምከው እኔንም ያለ ምክንያት ታኖረኛለህ” እለዋለሁ በማለት ተናገሩ ። ውስጣችንም ሆነ ዙሪያችን ምን አላችሁ ? ሲለን አንደኛ፣ እግዚአብሔር ሁለተኛ፣ እግዚአብሔር ሦስተኛ፣ እግዚአብሔር ልንል ይገባናል ። ሌላው ሁሉ አለኝ ባሉት ቅጽበት ማሳፈር ይጀምራል ። አለኝ ብለውት የማያሳፍር እግዚአብሔር ብቻ ነው ።
ደቀ መዛሙርቱ ሰው አንዳች መብል አምጥቶለት ይሆናል ብለው አሰቡ። እርሱ ግን ውኃ ለምኖ ውኃ ያጣ ። ውኃን ለነፈጉት ዘላለም ሕይወትን የሰጠ ነው ። ሰው ንፍገቱን ሲሰጠው እርሱ ደግሞ ቸርነቱን የሚሰጥ ነው ። ሳይበላ የበላ መሰላቸው ። አብረውት መንፈሳዊውን ደስታ ማጣጣም አልቻሉም ። እነርሱ የማያውቁት መብል አለ ። እንዲሁ ስንደሰት የሚያዩን ይገርማቸዋል ። የማያውቁት መብል አለ ። ሰዎች ስለተደሰቱ በልተዋል ማለት አይደለም ። ደስታ የመብል ውጤት ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነውና /ሮሜ. 14፥17/ ። ላልተጨማደደ ሰው መርዳት አይሆንልንም ። የምንረዳው ሰውን ሳይሆን ያዘነውን ስሜታችንን ነው ። እንዲሁ ብንሄድ ቀኑን በሙሉ ያን ሰው እናስበዋለን ። በሳንቲም ከኅሊናችን እንሰርዘው ዘንድ ብዙ ጊዜ ሳንቲም እንጥላለን ። አንድ ድራማ ላይ ስለ ፈንድ ለገበሬዎች ይነገራል ። ተናጋሪው ፡- “ፈንዱ ፣ ፈንዱ፣ ፈንዱ” እያለ ሲያወራ አንዱ ገበሬ ብድግ ብሎ “ካልፈነዳን አትሰጡንም ማለት ነው” በማለት መልሷል ።
“ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ፡- የሚበላው አንዳች ሰው አምጥቶለት ይሆንን? ተባባሉ” /ዮሐ. 4፥33/ ። አጠገባችን ላሉ ለሚያስቡልን ፣ ለሚወዱን ፣ ለሚጠነቀቁልን ያለን አመለካከት ምን ዓይነት ይሆን ? ልጆች እናት ምግብ የሚያስፈልጋት አይመስላቸውም ። ደቀ መዛሙርት መምህራን ተስፋ የሚያስፈልጋቸው አይመስላቸውም ። ወዳጄ ርቦት ይሆናል ብሎ የሚያስብ ፍቅር ብቻ ነው ። ፍቅር ከሌለን ሰዎች እንደ ጠገቡና ብዙ ገንዘብ እንዳላቸው ማሰብ እንጀምራለን ። ለእገሌ እገሌ ሰጥቶት ይሆናል እያልን ስንቶች በራብ ረግፈዋል ። እነዚያም የሚያስቡት እነርሱ አሉ ብለው ነው ። አንድ እናት ብዙ ጎበዝ ልጆች አሉአቸው ። ታዲያ ችግረኛ ናቸው ። ሌላው ሲረዳ እርሳቸው ይታለፋሉ ። “ልጆቼ ልመና ከልክል ሆኑብኝ” አሉ ። ሰዎች ጥሩ ልብስ ፣ መኪና ፣ ምቹ ወንበር ካዩ ሰው የቸገረው አይመስላቸውም ። ይልቁንም እነእገሌ ዝም አይሉትም ፣ አይሉአትም በማለት ወዳጆቻችንን መርሳት የለብንም ። እኛ መወጣት ያለብን የራሳችንን ነው ። ብዙ ወላጆች በመሐል ቤት ይራባሉ ። ትልቁ ልጅ ሀብታም ነው ዝም አይላትም እያለ ትንሹ ሲጨክን ፤ አብሮአት ነው ያለው እያለ ትልቁ በትንሹ ልጅ ሲጽናና ፣ አግኝታ ነው የለኝም የምትለኝ እያለ አንደኛው ሲያጉረመርም ይረሳሉ ። ወላጅን ለመርዳት መጠባበቅ ርግማን ነው ። የራስን ድርሻ መወጣት ብቻ ይገባል ። ደቀ መዛሙርቱ አንድ ሰው መብል አምጥቶለታል ብለው ያሰቡት ግምት እንጂ እውነት አልነበረም ። ግምታችንን አምነን የጠፋን ስንቶች እንሆን ? እግዚአብሔር የካሣ ዘመን ይስጠን ።