“ሴቲቱም፡- ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ ብላ ስለ መሰከረችው ቃል ከዚያች ከተማ የሰማርያ ሰዎች ብዙ አመኑበት ። የሰማርያ ሰዎችም ወደ እርሱ በመጡ ጊዜ በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት፤ በዚያም ሁለት ቀን ያህል ኖረ ። ስለ ቃሉ ከፊተኞች ይልቅ ብዙ ሰዎች አመኑ” /ዮሐ. 4፥39-41/።
ሴቲቱ ከምሕረቷ ተነሥታ ኃጢአቷን ስትመለከተው ቀለላት ። ድሮ ስለ ኃጢአቷ መከላከያ የምታቀርበው አሁን ግን በገዛ አፏ መናገር ጀመረች። ኃጢአትን በነበር ሲያወሩት ደስ ይላል ። ምስክርነትም ነው ። የሰማርያ ሰዎች ያመኑበት ይህችን ሴት ስላጋለጠ በትክክልም አውቋታል በሚል ስሜት አይደለም ። ሕይወትን የሚለውጥ ኃይል ከሆነ ለእኛም ያስፈልገናል በማለት ነው ። በዓለም ላይ ብዙ ሸክሞች አሉ ። ከሸክም ሁሉ የሚከብደው ግን የኃጢአት ሸክም ነው ። ይህን ሸክም የትም ማውረድ አይቻልም ። በራስ አቅምም ማውረድ አይቻልም ። የኃጢአትን ሸክም አውርዶ ዕረፍትን የሚሰጥ እግዚአብሔር ብቻ ነው /ማቴ. 11፥28-30/ ።
የሰማርያ ሰዎች በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር ለመኑት ። ለአንድ ቀን ዕረፍት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ለቀጣይም ከእኛ ጋር ሁን አሉት ። ቤታቸውን ሳይሆን ከተማቸውን ከፍተው ግባ አሉት ። ከከተማቸው በራፍ ላይ ሀብት ቆሞ ቢያገኙት ወደ ከተማችን ግባ ሳይሆን ወደ ቤቴ ግባ ይሉታል ። ሀብት ስስት ነውና ። ጌታችን ግን ለሁሉ ይበቃልና ወደ ከተማው ጋበዙት ። በዚያች ከተማ የቆየው ሁለት ቀን ነው ። ግን ተዘግቦልናል ። ንጉሣዊ ግብዣ አጭር ነው ። ግን ታሪክን የሚለውጥ ውሳኔ ይተላለፍበታል ። በከተማቸው ሁለት ቀን ያህል ቆየ በልባቸው ግን ለዘላለም ይኖራል ። ሳይለያቸው ይሄዳል። ሳይርቅ መጣ ይባላል ። እንደ እርሱ የተመሰገነ ማን አለ ?
ጌታችን በቆይታው ሁሉ ያለ ማቋረጥ ያስተምራቸው ነበር ። ከፊተኛው ይልቅ ብዙዎች በእርሱ አመኑ ። የሰዎች ምስክርነት የራቁትን ሊያቀርብ ይችላል ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የሚተክለው የእግዚአብሔር ቃል ነው ። እግዚአብሔር በእኛ ሕይወት ውስጥ ያለውን ዓላማ መረዳት እርሱ በቤቱ ይተክላል ። መጽሐፉ ፡- “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል” ይላል /ሆሴዕ. 4፥6/ ። ሕዝቡ ተአምራት ከማጣት ወይም በረከት ከማጣት የተነሣ አልጠፋም ። የጠፋው እውቀት ከማጣት የተነሣ ነው ። ጌታችን ለሳምራውያውን ሰዎች ቃሉን ነገራቸው ። ቃሉ ያላመኑትን ወደ አሚነ ሥላሴ ሲያመጣ ፣ ያመኑትን ደግሞ በአሚነ ሥላሴ ያጸናል ። የእግዚአብሔር ቃል ኅብረት ነውና ይወልዳል ፣ ወተት ነውና ያሳድጋል ፤ አጥንት ነውና ያጸናል ። ረቂቁ ቃል ግዙፉን ሥጋ ሲዋሐድ ጽድቅ ይፈጸማል። እንዲሁም “ቃል ሥጋ ሆነ” ተብሏል /ዮሐ. 1፥14/ ። ቃል ያለ ተዋህዶ አይሠራም ። ለዚህ ነው ፡- “ዳሩ ግን የሰሙት ቃል ከሰሚዎቹ ጋር በእምነት ስላልተዋሐደ አልጠቀማቸውም”የሚለው /ዕብ. 4፥2/።
ከሲካር ምንጭ አጠገብ ተቀምጦ ከተማይቱ በር እስክትከፍትለት የሚጠብቀው ጌታችን አሁን በጋበዙት ጊዜ በደስታ ወደ ከተማይቱ ገባ ። የእርሱ መግባት የሰላም ፣ የፍቅር መግባት እንጂ ተራ መግባት አይደለም ። ወደ ከተማይቱ እንዲገባ ለመኑት ። እኛ ያረከስናትን ከተማ አንተ ቀድሳት ማለታቸው ነው ። እኛ ከተማይቱን ለቀን ይኸው ወጥተናል ። ስንመለስ ግን አንተን ይዘን እንግባ ። የወጣነው እኛ ብንመለስ ለውጥ የለም ። አንተን ይዘን ብንመለስ ግን ለውጥ አለ ። ያላንተ ካሳለፍነው ዘመን ካንተ ጋር የምናሳልፈው ሁለት ቀን ዋጋ አለው እባክህ ወደ ከተማችን ግባ ብለው ለመኑት ። ሲለምኑት ተለማኝ ነውና ግብዣቸውን አክብሮ ወደ ከተማይቱ ገባ። በከተማይቱ በገባ ጊዜ ማን ቤት አርፎ ይሆን ? ቤት ውስጥ የሚታረፈው ከተማው የሌሎች ከሆነ ነው ። ከተማው ለክርስቶስ ከገበረ ከተማው ቤት ሁኗል ማለት ነው ። ጌታችን ከተማይቱን ቤት ፣ ጨረቃን መብራት አድርጎ አረፈ ።
ጌታችን በዚያች ከተማ ሁለት ቀን ያህል ኖረ ይላል ። ሁለት ቀን ለእኛ ቆየ የምንልበት እንጂ ኖረ የምንልበት አይደለም ። ሁለት ቀንም ግን መኖር ነው ። ያለ ክርስቶስ ስንኖር በዓመት እንቆጥራለን ። ከክርስቶስ ጋር ስንሆን ግን እያንዳንዱ ቀን ዋጋ አለው ። ሁለት ቀንም መኖር ነው ። እስከ መጨረሻው መኖር አለመቻል አለመታደል ነው ። የበሽታ ድምፅ ስንሰማ ወዲያው ተስፋ እንቆርጣለን ። በሽታው የዛሬ አሥር ዓመት ይገድለኛል የሚል ጭንቀት ይይዘናል ። ከቀኑ በፊት በጭንቀት እንሞታለን ። አንድ ሰው ታምሞ ሐኪም ቤት ይሄዳል ። ሐኪሙም የዕድሜ ልክ መድኃኒት አዘዘለት ። ታማሚውም “ዕድሜ ልኬን ? ” ብሎ ደነገጠ ። ሐኪሙ ግን ፡- “የእኔና የአንተ ዕድሜ ልክ መቼ ነው ? ዛሬ ማታም ሊሆን ይችላል” አለው ። አዎ ዕድሜ ልክ ሩቅ ይመስለናል ። ዕድሜ ልካችን ግን ዛሬ ማታም ሊሆን ይችላል ። ያ ታማሚ ይኸው 15 ዓመታት አለ ። አንድን ቀን መኖር መታደል ነው ። አንድ ቀንን በዕረፍት መዋል ፣ የሚያውኩንን መስመሮች ዘግቶ ማረፍ መታደል ነው ። አንዳንዴ ጊዜ ጭንቀት መስማት ሱስ ይሆናል። ማወክና መታወክ ያስደስተናል ። ምክንያቱ ምንድነው? ስንል ትኩረት የምናገኘው በዚህ ስለሚመስለን ነው ። ጭንቀትን የመስማትና የማሰማት ሱስ ውስጥ ስንገባ የደስታ ዜናዎች እየረበሹን ይመጣሉ ። ልቅሶ ቤት እየፈለጉ ማልቀስ ፣ በትንሽ በትልቁ መበሳጨት ፣ ከሰዎች ፍጹምነትን በመፈለግ ጠብ መለኮስ ፣ ያለፈውን መጎዳት እያስታወሱ ከተዳፈነበት አውጥቶ መንደድ ይከሰታል ። እባካችሁ አንድ ቀን እንኳ ዕረፉ ። በጸጥታ ፣ በጸሎት ፣ ተፈጥሮን በማድነቅ ፣ የከበባችሁን የምስጋና ርእስ በመቊጠር ደስ ይበላችሁ ።
መነጽራችሁ ከቆሸሸ የምታዩት ቆሻሻውን ነው ። ወዳጃችሁን ፣ በፊታችሁ የቆመውን ማየት አትችሉም ። ንጹሕ ልብ መስተዋቱ መጠረጉን ያበስራል ። እምነትም ንጹሕ ልብ ላይ ሁኖ ጌታውን ያያል ። ጌታን ማየት አንድ ቀን የመኖርን ዕድል ያቀዳጃል ። ያ አንድ ቀን መቼ ነው ? የሳምንቱ መጨረሻ ቀን ? የወር መባቻው ? የዓመት ዕረፍት ? የጡረታ ዕድሜ ? ወዳጆቼ መደሰት ምርጫ ነው ። የሚያሳዝናችሁም ይኸው በፊታችሁ አለ ፣ የሚያስደስታችሁም ክርስቶስ ይኸው በፊታችሁ አለ ። መደሰት ምርጫ ነው። ደስታ የማሰብና የመቊጠር ውጤት ነው ። እግዚአብሔርን ስናስብና ያደረገልንን መቊጠር ስንጀምር ደስ ይለናል ። ቀይ ባሕርን መሻገር ዮርዳኖስን ለመሻገር ዋስትና ነው ። የሚበልጠውን ማለፍ የሚያንሰውን ለመናቅ ይረዳል ። አዎ ከበጋ በኋላ ክረምት ፣ ከውሽንፍር በኋላ ጮራ ይፈነጥቃል ። በምንም መንገድ ከትላንቱ የባሰ ቀን አይመጣም ። ወደ ተሻለች ነገ እየሄዳችሁ ነው ። ደስ ይበላችሁ ። ዛሬ በተስፋ ፣ ነገ በፍጻሜው ደስ ይበላችሁ ። እግዚአብሔር ድርብ ደስታን ሊሰጠን ስለ ወደደ ተስፋን ሰጠን ።
ጌታ ሆይ ከዛሬ ቀን በፊት አይቻት የማላውቃትን ዛሬን አይቼ አዲስ ነገር የለም እላለሁ ። የዛሬን አዲስነት በማሰብ መደሰትን ስጠኝ ።