የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መድኃኔዓለም እንደ ሆነ እናውቃለን

“ሴቲቱንም፡- አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር” /ዮሐ. 4፥42/ ።
ከዚህች ሴት ጋር የጽድቅ ንግግር ሲነጋገሩ ይህ የመጀመሪያ ቀናቸው ነው ። ስለ ምድራዊ ውኃ እንኳ ከእርስዋ ጋር መነጋገር የሚፈልግ አልነበረም። አሁን ስለ ዘላለም ሕይወት መነጋገር ጀመሩ ። ይህች ሴት ለዘመናት ጆሮ ተነፍጋ ነበር ። ስለዚህ አፍ እያላት ዲዳ ነበረች ። ዛሬ ግን ለከተማው ተናገረች ። ከተማውም በሙሉ ሰማት ። ከተማው እንደ አንድ ሰው ሆነላት ፣ ከተማውም እንደ ብዙ ሰው አከበራት ። የተገለጠ ሥራዋን በመናገር ያደረግሁትን ሁሉ የነገረኝን ያንን ሰው ኑና እዩ እንጃ ክርስቶስ ይሆንን ? በማለት ያመነችውን ጌታ አብራ ለማመን አነሣሣቻቸው ። “እመን አንተና ቤተሰቦችህ ትድናላችሁ የሚለውን የወንጌል ሰፊ እሳት ለዚህች ሴት ቀይረን ብንሰማው “እመኚ አንቺና ከተማሽ ይድናል” ብንል ያስኬዳል ። እነርሱም የሚያውቁትን ታሪኳን ከገዛ አፏ ሰሙ ። እንዲህ ያሉ ኑዛዜዎች ሊያንጹ ይችላሉ ። የማይታወቁ የሕይወት ገጽታዎች ግን ለሕዝብ ኑዛዜ ሁነው ሲቀርቡ ብዙዎችን ያሰናክላሉ ። ኑዛዜዎች ለማይመለከታቸው ሲቀርቡ፡-
1-  እንዲህ ያለ ኃጢአት ለካ አለ በማለት የኃጢአት ትምህርት ይሰጣሉ።
2-  ደካሞች ሲሰሙ በኅሊናቸው ያ አሳብ እየመጣ ይፈትናቸዋል ።
3-  ለመሥራት የፈሩ ካሉ ለካ ይቻላል ብለው ያደርጉታል ።
4-  የሠሩ ካሉ ለካ ብቻዬን አይደለሁም በማለት ይደፍሩበታል ።
5-  በትንሽ ጽድቃቸው የሚመኩ ለካ እኔ እሻላለሁ በማለት ከንስሐ ይለያሉ ።
6-  ዓለማውያን የሆኑ ሰዎች ሲሰሙ ይታዘባሉ ።
7-  ሊቃውንት ሲሰሙ ቦታው አልነበረም በማለት በሰሙት ነገር ስለ ተናጋሪውና ስለ ሕዝቡም ይሸማቀቃሉ ። እጅግም ግልጽነት እብደት ነው ። ራሱን ለመሸፈን ልብስ የለበሰ ሰው ቤቱን ለመሸፈን ዝምታን የማይለብሰው ለምንድነው ? ኃጢአት ማለት ትልቅ አጥንት ነው ። አንደኛው በዚህ በኩል ሲግጠው ሌላኛው በዚያ በኩል ይግጠዋል ። የአቅጣጫው ጉዳይ እንጂ የማይበድል የለም ። አጥንት ለጥንካሬ ኃጢአት ለልብ ድንዳኔ እንጂ ለጥጋብና ለደስታ አይሆንም።
ኑዛዜ ማለት እንደ ሕክምና ነውና ጥንቃቄ ይጠይቃል ። ሐኪሙን ብቻ ማግኘት ይጠይቃል ። ከሐኪሙ ውጭ ያለ ሰው በፍቅር በሽታውን ቢሰማም የተሳሳተ መድኃኒት ሊያማክር ይችላል ። ከልምዱ ተነሥቶ እኔ እንዲህ ያደርገኝ ነበር በማለት እርሱ የወሰደውን መድኃኒት ይጠቁማል ። መድኃኒት በልምድ አይታዘዝም ። የአንዱ በሽተኛ መድኃኒት ለሌላው በሽተኛ አይረዳም ። መድኃኒት በሐኪሙ ብቻ ይታዘዛል ። በሽተኛው ደሙንና ተዛማጅ ናሙናዎችን ሲሰጥ በታላቅ ጥንቃቄ ነው ። በሽታው ሌሎችን እንዳይጎዳ የተለየ መንገድ አለው ። ኃጢአትም እንደዚህ ነውና በታላቅ ጥንቃቄ በቦታው መፍትሔ ሊያገኝ ይገባዋል ።
የሰማርያ ሰዎች የሚያውቁትን ታሪኳን ሲሰሙ እርስዋን ያዳነ እኛንም ያድነን ብለው ከከተማው ውጭ ሊፈልጉት ወጡ ። ብዙ ዘመን የእርስዋን ኃጢአት ሲናገሩት ኑረዋል ። ይህ ግን ሐሜት ነው ። አንድ ቀን እርሷ ብትናገረው ግን ንስሐ ሆነላት ። እርስዋም በሽታዬ ተገኘ ደስ ይበላችሁ በሚል ስሜት መሰከረች ። የሰማርያ ሰዎችም ጌታችንን ወደ ከተማቸው ጋብዘውት ሁለት ቀን ያህል አብሮአቸው ከቆየ በኋላ ይህችን ሴት ፍለጋ ሄዱ። ምክንያት የሆነቻቸውን ሴት መርሳት አልፈለጉም ። እንኳን አማኒ ጥሩ አስተዳደግ ያለውም ወደ ኋላ ዘወር ይላል ። አንገት የተፈጠረው ወደ ኋላ ዞር ለማለትም ነውና ። የመሰከረችላቸው ሰዎች ሊመሰክሩላት መጡ ። መልሳ ስትሰማ እንዴት ደስ ይላት ይሆን ? ሦስት ቀናት የቤት ሳይሆን የከተማ ደስታ ይንቦገቦግ ነበር ።
ያችን የጽድቅ ምስክር ፣ መድኃኔዓለምን አግኝተው የተጠቀሙባትን ብርሃን እንዴት ይርሷት ? እንኳን የሕይወትን መንገድ ያሳየ ፣ የፒያሳ መንገድ በዚህ በኩል ነው ያለ ሰውም ውለታው አይረሳም ። እጮኝነት ሲጀምሩ ያማከረ መምህር ፣ ሲያገቡ ቆሞ የዳረ ወላጅ ፣ ሲወልዱ ያጠመቀ ካህን ፣ ሲጣሉ ያስታረቀ ሽማግሌ ፣ ንስሐን የተሸከመ ከባቴ አበሳ ፣ ሲታመሙ የጸለየ ነቢይ ፣ ሲሞቱ አፈር ያለበሰ እንደራሴ ፣ ሞተው እንኳ ስም የሚያነሣ ጥሩ ሰው ፣ …ኧረ ያ አገልጋይ ፣ ያ ካህን እንዴት ይረሳል ??? በአንድ ጊዜ ብዙ ድርሻ ያለው ስመ ብዙው መንፈሳዊ አባት እንዴት ይዘነጋል ??? ወላጆቻችሁ ያልሰጧችሁን ሕይወት ያካፈለ ፣ ትዳራችሁ የማያውቀውን ምሥጢር የተሸከመ ያ የክርስቶስ አርበኛ እንዴት ይረሳል ???
 “ሴቲቱንም፡- አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር” /ዮሐ. 4፥42/ ። እነዚህ ሰዎች ምን እያሉ ነው ? አንቺን ለማስደሰት ብለን አይደለም ፣ ሊይዙት የሚገባውን ጌታ ነው ያስጨበጥሽን ። እርሱ እውነተኛ ነው ። አንቺ ስታገኚው የራስሽ መድኃኒት እንደሆነ ነገርሽን ። እኛ ስናገኘው የከተማው ፈውስ መሆኑን አየን ። ሁለት አብረነው ስንቆይ የዓለም መድኃኒት መሆኑን አወቅን በሚል ስሜት ተናገሯት። ሌላውን ላለማስቀየም መንፈሳዊ ነገርን የያዙ ሰዎች አሉ ። ያልገባቸውን አዎ ፣ አዎ የሚሉ የራሳቸው ጩኸት የሌላቸው አያሌ ናቸው ። ቀምሰው ያረጋገጡ ግን የሚድኑ ናቸው ። ለዚህ ነው፡- እግዚአብሔር ቸር እንደሆነ ቅመሱ የተባለው /1ጴጥ. 2፥2/ ። ወንጌል በስማ በለው አይሆንም።
ዐጼ ቴዎድሮስም ሆኑ ዐጼ ዮሐንስ ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ የነበሩ ሚስዮናውያንን የሚናገሩት አንድ ቃል አለ ። ለምን መጣችሁ ሲሉ ? ሚስዮናውያኑ ወንጌል ለመስበክ ነው ይላሉ ። ነገሥታቱ ግን እንደ አንድ ልብ መካሪ ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሁነው ፡- “የአይሁድን አገር እስራኤልን፣ የእስላምን አገር ምድረ ዐረብን አልፋችሁ እኛ በወንጌል ያመነውን ለመስበክ እንዴት ትመጣላችሁ?” ሲሉ ሚስዮናውያኑ ፍጥጥ ይላሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በጣም እየተስፋፋ ያለ ንግግር አለ ። ይህንን እሰማለሁ ። እኔም ላይ ይደርሳል ። “ክርስቲያን ናቸው ወይስ ኦርቶዶክስ?” የሚል ንግግር በሚስዮናውያኑ እየበዛ መጥቷል ። “እናቴ አታምንም ኦርቶዶክስ ናት” የሚሉ ምስክርነት ተናጋሪ ሰዎችን እየሰማን ነው ። ቢያንስ በእጃቸው የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ቅዱስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ያቆየችው ደግሞም ተርጉማ ያቀረበችው መሆኑን ምነው ታሪክ አጥንተው ባወቁ ? እኛም እንደ ሰማርያ ሰዎች “አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን” እንላለን /ዮሐ. 4፥42/ ። ኢየሱስ ክርስቶስን መድኃኔዓለም ብሎ የሚያምን ሕዝብን አያምንም ማለት ነውር አይደለም ወይ ?
ዘወትር በቅዳሴያችን እንዲህ እንላለን፡-
“አምናለሁ አምናለሁ አምናለሁ ። እስከ መጨረሻዪቱም እስትንፋስ እታመናለሁ ፤ በሁለት ወገን ድንግል ከምትሆን ከሁላችን እመቤት ከቅድስት ድንግል ማርያም የነሣው የጌታችንና የመድኃኒታችንም የኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋው ደሙ ይህ እንደሆነ ያለ መቀላቀል ያለትድምርት ያለመለዋወጥና ያለመለየት ከመለኮት ጋራ አንድ ያደረገው ፤ በጰንጤናዊ በጲላጦስም ዘመን ባማረ ምስክርነት ምስክር የሆነ ፤ ስለ እኛና ስለ ሁላችንም ሕይወት አሳልፎ የሰጠው ። አሜን ። …” /ቅዳሴ ሐዋርያት ቊ. 101/።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ