የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሁለተኛ ምልክት

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አራት ከቊ. 46-54 ስለ ሁለተኛው ምልክት ይናገራል ። የመጀመሪያው ምልክት በምዕራፍ ሁለት ላይ የተጠቀሰው የቃና ዘገሊላው ውኃ ወደ ወይን ጠጅ መለወጥ ነው ። ሁለተኛው ደግሞ የቅፍርናሆም ሹም ልጅ መፈወስ ነው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ገሊላ በመጣ ጊዜ በኢየሩሳሌም ያደረገውን ስላዩ የገሊላ ሰዎች ተቀበሉት ። በኢየሩሳሌም ያደረገው ምንድነው ? ስንል ቤተ መቅደሱን ማጽዳቱና ምልክቶችን መፈጸሙ ነው ። ይህንን የተመለከቱ ነበሩና ወደ ገሊላ ሲመጣ ተቀበሉት  ። ከዚያ በፊት ግን በገሊላ አውራጃ በቃና ቀበሌ ውኃውን ወደ ወይን ጠጅ መለወጡን አላስተዋሉም ነበር ። በገሊላ ስለፈጸመው ተአምራት ሳይሆን በኢየሩሳሌም ስለፈጸመው ተአምራት ተቀበሉት ። ለእነርሱ የተደረገውን እንደ መናኛ ነገር ቆጠሩት ። እግዚአብሔር በገሊላም በኢየሩሳሌምም በሰማርያም ተአምረኛ ነው ። ተአምር ያላደረገለት ማንም የለም ። የሌሎችን ተአምር እንጂ የራሳቸውን ተአምር መቊጠር የማይችሉ ሰዎች ብዙ ናቸው ። ዛሬን በተአምራት ቆመው ሌላ ተአምር የሚያምራቸው ፣ ብዙ ጋሬጣዎችን በተአምራት አልፈው እንዳልተደረገለት ሰው በሌሎች ተአምራት የሚቀኑ አያሌ ናቸው ። እግዚአብሔር ግን ድንቅ ያላደረገለት ከቶ ማን ነው ?
ጌታችን ለሁለት ቀናት ያህል ሰማርያ ከቆየ በኋላ ወደ ገሊላ ሄደ ። በሰማርያ ምንም ዓይነት ተአምራት አላደረገም ። በሰማርያ ግን ቃሉን አስተምሯል ። ብዙዎችም ለንስሐ በቅተዋል ። ቀጥተኛው ተልእኮ ይህ ነው። ቋሚው በረከትም ቃሉ ነው ። በየቀኑም የምንቀበለው ፈውስ የኃጢአታችን ስርየት ነው ። ለእስራኤል ልጆች በተአምራት መና ቢወርድም መና ግን የዘላለም ምግባቸው አይደለም ። ማረስና መዝራት በማይችሉበት ምድረ በዳ ላይ መና ወረደ ። ማረስና መዝራት በሚችሉበት ምድረ ከነዓን ደግሞ መናው ቆመ ። እግዚአብሔር የዘለቄታው በረከቱ የእጃቸውን ሥራ በመባረክ የሚገኝ ነው ። መዝራትና ማጨድም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና ።
ጌታችን ዳግመኛ ወደ ገሊላ መጣ ። ሁለተኛውንም ተአምራት በቃና ዘገሊላ ደገመ ። ዳግመኛ መምጣቱ ገበሬ ያረሰውን መሬት እንደሚያለሰልስ ነው ። ዘር ተቀባይ ምቹ ያደርገዋል ። ጌታችንም ለማጽናት እንደገና ተመለሰ ። የማጽናት አገልግሎት ወሳኝ ነው ። ገበሬ ተክል ተክሎ ተመልሶ ካላየው ያልተከለው አረም ይውጠዋል ። ሐዋርያት በአካል ተመልሰው ማጽናት ባይችሉ እንኳ መልእክቶችን ይጽፉ ነበር ። የዘራነውን መለስ ብሎ ማየት አስፈላጊ ነው ። አባትነት መውለድ ብቻ ሳይሆን ማሳደግም ነውና ። መውለድ የቅጽበት ማሳደግ ግን የዓመታት ነው ።
ጌታችን ወደ ገሊላ ቃና በመጣ ጊዜ በቅፍርናሆም ልጁ የታመመበት የንጉሥ ቤት ሹም አገኘው ። ቅፍርናሆም የነቢዩ የናሆም የትውልድ አገር ናት ። ቅፍርናሆም ወይም የናሆም መንደር ተብላ ተሰይማለች ። ይህ ሰው የንጉሥ ቤት ሹም ነው ። ልጅ ታሞበት ነበር ። በሥልጣኑ ሊያርቀው ያልቻለው አንድ ጉዳይ ገጥሞት ነበር ። ጌታችን የሁሉም አምላክ ነውና ይህን ሰው ሊረዳው መጣ ። በገሊላ አመጣጡ ስላደረገው ሌላ ነገር አናነብም። ይህን ሰው ግን እንደ ረዳው እናነባለን ። ጌታችን አንዲት የተጨነቀች ነፍስንም ችላ አይልም ። ሹም የሆነ ሰው የሚቸገር የማይመስለው አያሌ ነው። ለባለጠጎችና ለባለሥልናት የሚያዝን ሰው የለም ። በዚህ ዓለም ግን እንደ እነዚህ ወገኖች የተጎዳ የለም ። ሐሰተኛ ፍቅርን ፣ እውነተኛ ጥላቻን የሚያተርፉ ናቸው ። ፈተናቸው እንደ ከፍታቸው መጠን ነው ። የድሃ ፈተናው ዳቦ ነው ። ከበላ በደስታ ይተኛል ። የዚህ ዓለም ጥያቄ ግን ከዳቦ ያልፋል ። ተገዢዎች በቦታቸው ረክተው እንደውም የእገሌ ጠባቂ ነኝ እያሉ ይመካሉ ። የሚጠበቀው ንጉሥ ግን በፍርሃትና በጥርጣሬ ይኖራል ። የበላይና የበታች የሚበሉት እኩል ነው ። ጭንቃቸው ግን የተለያየ ነው ።
አንዲት እህት ኑሮዋ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያለ ነው ። እንደ ሰው አነጋገር። ታዲያ አንድ ቀን በቤቷ ጋብዛኝ አንድ ጥቅስ ከማዕድ ቤት እስከ መታጠቢያ ቤት ተሰቅሏል ። አንድ ቀን ስንመካከር የነገርኳት ነው ። እኔ ረስቼዋለሁ ። እርስዋ ግን የየዕለት መልሷ ነው ። “ከፍ ባሉ ቊጥር አየር ያጥራል” የሚል ነው ። ከፍታ የሚያመጣውን አለመርካት ካልተገነዘብን አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንገባለን ። የፈለግነውን አለማግኘትና በገደብ መኖር ዕድሜን ይጨምራል ። አንድ ነገር አጥተን እስክናገኘው ዕድሜ እንለምናለን። “ይህ ተፈጽሞ ምነው በማግሥቱ በሞትኩኝ” እንላለን ። ንጉሡ ጠንቋዩን ይጠራና “መቼ ነው የምሞተው?” አለው ። ጠንቋዩም ብልጥ ነበርና፡- “እኔ በሞትኩ በማግሥቱ” አለው ። ንጉሡም ከዚያን ቀን ጀምሮ ያ ጠንቋይ እንዳይሞት መንከባከብ ጀመረ ። ሞታችንን ስንሰማ መኖርን እንናፍቃለን ። መኖርን ብቻ አይደለም አብረውን የሚኖሩትንም መንከባከብ እንጀምራለን ።
ከፍ ባለን ቊጥር የሚያየን ሰው ብዙ ነው ። ከፍ ባልን ቊጥር እኛን በማዋረድ ትልቅ የሚሆኑ የሚመስላቸውን ብዙ ርካሾችን እናፈራለን ። ከፍ ባሉን ቊጥር ለወንጭፍ እንመቻቻለን ። ደማችን ሲፈስ ወተት የፈሰሰ ይመስላቸዋል ። ስናለቅስ ሐሰተኛ ማደናገር እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ ። እውነት ብንናገር የሚያስተባብሉ ይበዛሉ ። ጌታችን ግን በሁሉም ቤት ልቅሶ እንዳለ ያውቃል ። “ከፍ ያለ ማሽላ አንድም ለወፍ ፣ አንድም ለወንጭፍ” ይባላል ።
ይህ የቅፍርናሆሙ ባለሥልጣን በልጅ የተፈተነ ነበር ። የልጅን ችግር ምክንያት በማድረግ መርሳት አይቻልም ። ያማረ ቤት ሠርቶ ፣ ያማረ ምግብ አቅርቦ ሊሆን ይችላል ። ልጁ ግን ታማሚ ነበር ። ቤቱን ደጅ ፣ ምግቡንም እሬት የሚያደርግ ጉዳይ ገጥሞታል ። ሰላማዊ ትዳሮች በልጅ ምክንያት ይበጠበጣሉ ። ልጅ ባለመውለድ ብቻ አይደለም፣ በተወለደው ልጅ ጠባይ መበላሸት ትዳሮች ይናጋሉ ። ብዙ ወላጆች በልጃቸው ላይ የበላይነትን ካጡ መላው ዓለም አይሰማኝም የሚል ጭንቀት ውስጥ ይገባሉ ። አንድ የተከበሩ ባለሥልጣን ናቸው ። ያገኘኋቸው በእስር ቤት ውስጥ ነው ። አንድ ቀን ልጠይቃቸው ስሄድ እንዲህ አሉኝ፡- “ልጄ እኔ አሥራ ሁለት ልጆች ወልጃለሁ። አንዱም ልጄ ግን የእኔን አሳብ አያንጸባርቅም ። ሁለት መጽሐፍት ጽፌአለሁ ፤ እነርሱ ግን የእኔን አሳብ ያንጸባርቃሉ ። ልጅ እንደ ራሱ ነው ። መጽሐፍ ግን እንደ አንተ ነው ። ስለዚህ እባክህ ጻፍ” አሉኝ ። ልጅ የበሽታ ደግሞም የጠባይ ታማሚ ሆኖባችሁ ይሆን ? እግዚአብሔር እናንተን ሊጎበኝ ካላችሁበት ቅፍርናሆም ይመጣል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ