የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቦኪም

ቦኪም
“በእነዚህ ውስጥ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ በሽተኞችና ዕውሮች አንካሶችም ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ሕዝብ ይተኙ ነበር” /ዮሐ. 5፡3/፡፡
ቤተ ሳይዳ ማለት የምሕረት ቤት ማለት ነው ፡፡ ቤተ ዛታም ሊባል ይችላል ፡፡ ብዙ በሽተኞች ፈዋሹን አምላክ ደጅ የሚጠኑባትና ፈውሳቸውን ተቀብለው የሚሄዱባት ፣ የካርድ የማይከፈልባት ፣ በተለቀቀ መኝታ ተረኛው የሚገባባት የሁሉ ስፍራ ነበረች ፡፡ ርስትን የሚሻማው የሰው ልጅ ሲፈወስ በቃኝ የሚለውና ለተረኛ የሚለቀው ርስት ቢኖር የሐኪም ቤት መኝታን ብቻ ነው ፡፡ በሐኪም ቤት ኑሮዬ ይበቃኛል ይታወቃል ፡፡ አንድ ነገር ብቻ ይለመናል ፡፡ እርሱም ፈውስ ነው ፡፡ የቤተ ሳይዳ መጠመቂያ የሁሉ ስፍራ ነበረች ፡፡ አንድ ኩሬ ስትሆን ወደ እርስዋ ለመውረድ ግን አምስት መመላለሻዎች ነበሯት ፡፡ መግቢያዋ ብዙ ቢሆንም ምንጩ ግን አንድ ነበረ ፡፡ በዚህች መጠመቂያ ስፍራም ከእግዚአብሔር የሚላከውን ፈውስ ሰዎች ተቀብለው ይሄዱባት ነበር ፡፡ ለመግባትም ለመውጣትም አለቃ አልነበረም ፡፡ የስፍራው ጠባቂ ፈሪሃ እግዚአብሔር ብቻ ነው ፡፡  የሰው አጥማቂም አልነበረም ፡፡ መልከአ እግዚአብሔር ወርዶ ውኃውን ያናውጠው ነበር ፡፡ ቀድሞ የገባም ይፈወስ ነበር፡፡
እንዲህ ያሉ ነጻ ቀጠናዎች እጅግ አስፈላጊ ናቸው ፡፡ የደከመው ከድካሙ ዐረፍ የሚልበት ፣ ሆድ የባሰው አምላኩን የሚያዋይበት ፣ ብቸኝነት የተሰማው ቃለ እግዚአብሔር የሚያደምጥበት ፣ ማልቀስ የፈለገ በነጻነት ዕንባውን የሚያፈስበት ቦታዎች ወይም ቅዱሳት መካናት በጣም ያስፈልጋሉ ፡፡ ቤቱን የጠላው በሽተኛ ከሌሎች በሽተኞች ጋር ሁኖ አምላኩን ሲለምን ይጽናናል ፡፡ የባሰውን ሲያይ ያመሰግናል ፡፡ ማንም የሌለውን ሲያይ ቤተሰቦቹን ማማረር ያቆማል ፡፡ አዳዲስ ወዳጆችን ያተርፋል ፡፡ እውነተኛ ሰዎች ሲመጡ ያያል ፡፡ በሐኪም ቤት ሊመጡ የሚችሉ እውነተኛ ሰዎች ናቸውና ፡፡ እውነተኛነታቸው ምንድነው ስንል ነገም የእኔ ዕጣ እንዲህ ይሆናል ብለው የሕይወትን እውነት የተቀበሉ ፣ ራሳቸውን በተጎዳው ሰው ቦታ ላይ ያስቀመጡ ሰዎች መሆናቸው ነው ፡፡ በሐኪም ቤትና በጠበል ስፍራ ያለ ፍቅር ሌላ ቦታ አይገኝም ፡፡ የመከራ ጓድ አይረሳም ፡፡ ደስታ ብዙ አጃቢዎች አሏት ፤ መከራ ግን ጥቂት ወዳጆችን የምታስቀር ጠባብ በር ፣ የማጣሪያ ወንፊት ናት ፡፡
በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት በዘመነ መሣፍንት ቦኪም ተብሎ የተጠራ ስፍራ አለ /መሳ. 2፡1-5/ ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ውለታ የረሱትን የትላንቱን ለማየት አንገት ያጡትን እስራኤላውያንን ሲወቅሳቸው ልባቸው ተነካ ፡፡ በፍቅር አለቀሱ ፡፡ የንስሐ ዕንባ አፈሰሱ ፡፡ ቦታውንም ቦኪም ብለው ጠሩት ፡፡ ማልቀሻ ማለት ነው ፡፡ የትም አይለቀስም ፡፡ እንኳን እንባን የሚያብስ ወዳጅ የሚያለቅሱበት ቦታም ባለውለታ ነው ፡፡ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያለቀሱበትን ያን ስፍራ ቦኪም በማለት ጠሩት ፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ቦኪም ናት ፡፡ የስንቱ ዕንባ ይፈስባታል ፡፡ አገልጋዮችም ቦኪም ናቸው ፡፡ የስንቱን ኀዘን ይሰማሉ ፡፡ በነጻ የሚያማክሩ ፣ የተጠላን የሚያስታርቁ እነዚያ ሽማግሌዎች እነዚያ ቦኪሞች ዛሬ እየጠፉ ነው ፡፡ ካህናት ቢጣሉ ይታረቃሉ ፡፡ የቤተሰብ ጠብ ነውና አይከፋፉም ፡፡ ምእመናን ጣልቃ ሲገቡበት ግን መጀመሪያ ቦኪም የሚሆን ስፍራና ሰው ያጣሉ ፡፡ ስንቱ ማልቀሻውን አፈረሰ ፡፡
ሰውዬውን ከመንገድ ጎትተው እቤታቸው አስጠግተው ያኖሩታል ፡፡ መማር አለበት ብለውም እንደ ወላጅ እየተቆጡ እየመከሩ ያስተምሩታል ፡፡ ችግሩ አልፎ ትምህርቱ ተፈጽሞ ራሱን ችሎ ወጣ ፡፡ እነዚያን ሰዎች ግን ረሳቸው ፡፡ ስለ እነርሱ ሲወራ ደግም ክፉም መመለስ አይፈልግም ፡፡ በመንገድ ሲያያቸው ይሸሻል ፡፡ አንድ ቀን በጠባብ መንገድ ተገናኙ ፡፡ ጠባብ መንገድ ያወቃቅሳል ፣ ያስታርቃልና ምነው እንዲህ ጠፋህ አሉት ፡፡ እርሱ ግን እናንተን ሳይ የረሳሁትን ኑሮዬን እንዳላስታውስ ነው የጠፋሁት አላቸው ፡፡ ከጥፋቱ ምክንያቱ በለጠ ፡፡ የችግር ቀን ወዳጅ ያን ችግር ቀን መስሎ የሚሰማው ባለጌ ብቻ ነው ፡፡ በርግጥ መልካም ያደረጉ ሰዎችም ያን ቀን መርሳት አለባቸው ፡፡ ዛሬን ብቻ መጨዋወት አለባቸው ፡፡ ሰውዬው ከፈለገ ያንሣው ፣ ያመስግን ፡፡ ዛሬ እነዚያ ዳቦ የቆረሱልንን ረስተናል ፡፡ ደብተር ገዝተው ብዕር ቀርጸው ያስተማሩንን ትንሽ ቃላቸውን ይዘን ተቀይመናቸዋል ፡፡ ቦኪም የሚሆኑ ያስፈልጋሉ ፡፡ የቤተ ሳይዳ መጠመቂያ የሁሉ ማልቀሻ ናት ፡፡ በዚህ ስፍራ ላይ የትሕትና ጸሎት በየዕለቱ ያርጋል፡፡ ስለ በሽታ ፈውስ ብቻ ሳይሆን ስላላመሰገኑበት የጤንነት ዘመንም ይቅርታ ይጠየቃል፡፡ ታላቅ የንስሐ ቦታ ናት ፡፡ ሰው በበሽታ ሲሆን ለንስሐ ቅርብ ነው ፡፡
በሽተኞቹ ቀኑን በሙሉ የሚጠመቁ አልነበሩም ፡፡ የውኃውን መንቀሳቀስ እየጠበቁ ወደ ውኃው ዘለው ይገቡ ነበር ፡፡ ፈውሱ የሚገኘው በሐኪም ወይም በመድኃኒት ሳይሆን መልአኩ ውኃን ሲያናውጠው የሚሆን ነው ፡፡ በዚህ የፈውስ ስፍራ ዕውሮች ይበራሉ ፡፡ ሰውነታቸው የሰለለ ቅርጽ ያገኛሉ ፡፡ አንካሶች ጠንክረው ይጓዛሉ ፡፡ እግዚአብሔር የሚታይ ፈውስን ያደርግ ነበር ፡፡ ዛሬ አሉ የሚባሉት ፈውሶች ማስጮህ የመጀመሪያው ተግባራቸው ነው ፡፡ አብዛኛው ሰው በጭንቀት እያለፈ ስላለ ይህንን ጩኸት ከአጋንንት መለየት አስፈላጊ ነው ፡፡ ይህንን ለመለየት ደግሞ የተማሩና መንፈሳውያን አባቶች ያስፈልጋሉ ፡፡ የዛሬ ፈውስ ሌላው ባሕርዩ ውጫዊ ነገርን አይመለከትም ፡፡ እግዚአብሔርን የውስጥ ደዌ ፈዋሽ ብቻ ያደረገ ይመስላል ፡፡ የውስጥም ሆነ የውጭ ፈውስ ቢኖር የዳኑት ፈዋሹን አምላክ ማክበር ካልቻሉ ፣ የሰው ማስታወቂያ ሠራተኞች ከሆኑ ትልቅ አደጋ ነው ፡፡ “ከእባብ ጉድጓድ አምልጦ ዘንዶ ጉድጓድ” ማለትም ይህ ነው ፡፡ ከበሽታ ድኖ በአምልኮቱ እግዚአብሔርን ማስቀየም አይገባም ፡፡ የፈውስ ጸጋ የሰውዬውን ብቃት አያሳይም ፡፡ ብቃት ከተጠቀሰ ጸጋ ፣ ጸጋ መሆኑ ይቀራል ፡፡ በፈውስ ጸጋ ውስጥ እግዚአብሔር ለበሽተኛው ያለውን ምሕረት የምናይበት ነው እንጂ የፈውስ ጸጋ ያለውን ሰው ብቃት የምናይበት አይደለም ፡፡ የፈውስ ጸጋ አንዱ ጸጋ እንጂ የበላይ ጸጋ አይደለምና ይህ ጸጋ አለኝ ተብሎ ከቤተ ክርስቲያን ተገንጥሎ የራስን ስፍራ ማቋቋም አይገባም ፡፡ እግዚአብሔር ጸጋን የሰጠው ለአካሉ እንጂ ለግለሰብ አይደለምና ፡፡
የቤተ ሳይዳ መጠመቂያ ተመላላሽ በሽተኞችን ሳይሆን አዳሪ በሽተኞችንም የያዘ ትልቅ መጠመቂያ ነው ፡፡ ዛሬም ይህ የፈውስ ቦታ በአሮጌዋ ኢየሩሳሌም ውስጥ ይገኛል ፡፡ ይጎበኛልም ፡፡ ወንጌላዊው በዚህ ስፍራ ላይ ስለሚጠመቁ ብዙ በሽተኞች የመጻፍ ዓላማ የለውም ፡፡ የወንጌላዊው ዓላማ ስለ ሠላሣ ስምንት ዓመት በሽተኛው መናገር ነው ፡፡ ይህ ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት በደዌ የደቀቀ ሰው ነው ፡፡ ምናልባት ወደዚህ መጠመቂያ ሲገባ ዘመድም ገንዘብም ይኖረው ይሆናል ፡፡ ገንዘብ ሲያልቅ ወዳጅም አብሮ ያልቃልና አሁን አልከዳ ካለው በሽታ ጋር ይኖራል ፡፡ ምነው እንደ ሰው በሽታውም ከዳተኛ በሆነለት ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በበጎች በር የመሥዋዕት መልክ ይዞ የመጣው ይህን በሽተኛ ለመፈወስ ነው ፡፡ ጌታችን በሽተኛን ለመጠየቅ አልመጣም ፡፡ ፈውስን ለመስጠት መጣ ፡፡ ሁሉ አልተፈወሱም ፡፡ አንዱን ሊፈውስ መጣ ፡፡ ይህ ሰው ቀና ብሎ ውኃውን ማየት በሚችልበት ርቀት ላይ ነው ፡፡ ወደዚያ ለመድረስ ግን ሠላሣ ስምንት ዓመት ፈጅቶበታል ፡፡ ጉልበትና ዘመድ ያለው ሲፈወስ እርሱ ግን ተመልካች ሁኖ ፣ በፈውስም ተስፋ ቆርጦ ይኖራል ፡፡ ሰዎች ራርተው ሳይሆን ይሉኝታ እንኳ ይዟቸው ይህን ሰው ቢያስቀድሙት መልካም ነበር ፡፡ ጌታችን የመጣው ፡-
1-  ሁሉ በራስ ወዳድነት የገፋውን ሰው ለማንሣት ነው ፡፡
2-  ሰው ለሌለው ሰው ሊሆንለት ነው ፡፡
እግዚአብሔር ብቻ ከወርዋሪዎች ጋር አብሮ ድንጋይ አይወረውርም ፡፡ ከሚጠሉንን ጋርም አብሮ አይጠላንም ፡፡  እርሱ በራሱ ፍቅር የሚያፈቅር ፣ በራሱ ክብር የሚያከብር አምላክ ነው ፡፡ በዓለም ላይ ሠላሳ ስምንት ዓመት ወረፋ የጠበቀ ሰው የለም ፡፡ እኔነት የሞላባቸው ሰዎች ግን ይህን ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት መንገድ አንለቅም ብለውታል ፡፡ መልአኩ የሚያናውጠውን ውኃ ቢከለክሉት መልአኩን የላከው ጌታ መጣለት ፡፡ ሰዎች በነሡን ነገር ውስጥ የሚሰጡን ትልቅ ነገር አለ ፡፡ የቤተ ሳይዳ መጠመቂያ ጉልበትና የሰው ወገንነት ይፈልጋል ፡፡ የጌታ ፈውስ ግን ፈቃደኝነትን ይፈልጋል ፡፡ ልትድን ትወዳለህን ያለው ለዚህ ነው ፡፡ ያ በሽተኛ ውኃውን ያየዋል ፣ መልአኩም ሲያናውጣው ለዘመናት ሰምቷል ፣ ሰዎች ሲፈወሱም ተመልክቷል ፡፡ በሽታዬ ካልተፈወሰ በሽታዬን መተዳደሪያዬ ይሆናል ብሎ የሚለምን ሰው ሳይሆን አይቀርም ፡፡  የመልአኩ ፈውስ ሁሉንም ለምን አልተመለከተም ብንል የጌታም ፈውስ ሁሉንም አልተመለከተም ፡፡ ፈውስ በእግዚአብሔር ጊዜ ነው ፡፡ የቤተ ሳይዳ መጠመቂያ የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ልትሆን ትችላለች ፡፡ አምስቱ ብሔረ ኦሪት መመላለሻዎቿ ናቸው ፡፡ ያንን ሕዝብ መልአክ እየመራው ከግብፅ ወጣ ፡፡ መዳኑም ጥቂት ሰዎችን ወይም አንድ ሕዝብን ያማከለ ነበር ፡፡ ሰዎቹ ወደ ውኃው መሄድ ነበረባቸው ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም መቅደስ ካልሄዱ ፈውስ አልነበረም፡፡ የጌታችን ፈውስ ግን የአዲስ ኪዳንን ገጽታ ያሳያል ፡፡
1-  ሰው ለሌላቸው ሰው ሁኖ መጣ
2-  ካሉበት ድረስ መጣ ፡፡
3-  ፈቃደኛነታቸውን እንጂ ጉልበትና ወገናቸውን አልጠየቀም ፡፡
4-  መሥዋዕት ማቅረብ ለማይችሉና ለሚችሉ መሥዋዕታቸው ሆነ ፡፡
5-  መዳንን በቅጽበት ሰጠ ፡፡
 የእኛስ ቦኪም የት ይሆን ? አክብረን እንያዘው ፡፡ ማልቀሻም ቦታ ይቸግራል ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ