የሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛ
“አንዳንድ ጊዜ የጌታ መልአክ ወደ መጠመቂያይቱ ወርዶ ውኃውን ያናውጥ ነበርና፤ እንግዲህ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ የገባ ከማናቸው ካለበት ደዌ ጤናማ ይሆን ነበር” /ዮሐ. 5፡4/፡፡
የእግዚአብሔር መላእክት አገልግሎታቸው ብዙ ነው ፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለብሥራት ፣ ለፈውስ ፣ ለማጽናናት ፣ የምሥራችን ለመንገር ፣ ጻድቃንን ከጠላት ለማዳን ፣ …ይላካሉ ፡፡ እነዚህ መላእክት የእግዚአብሔር ወዳጆች ናቸው ፡፡ በምርጫ ነጻነታቸውም እግዚአብሔርን መርጠው በሰማይ የቀሩ ናቸው ፡፡ ትልቁ መዐርጋቸውም በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙ መሆናቸው ነው ፡፡ መላእክት የእግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን የሰው ልጆችም ወዳጆች ናቸው ፡፡ እያንዳንዱን ሰውና ፍጥረት እንዲጠብቁም ከእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው ፡፡ በሰው ልጆች ንስሐ መግባትም የሚደሰቱ ናቸው ፡፡ ተፈጥሮአቸውም ኃይልን የተሞላ ነው ፡፡ ቁጥራቸውም በሰው የመቁጠር አቅም የሚለካ አይደለም ፡፡ እነዚህ መላእክት ከበውናልና ደስ ይለናል ፡፡ የከበቡን ቅዱሳን ናቸውና ልባችን ሐሤት ያደርጋል ፡፡ እነዚህ መላእክት አንድ ጊዜ ከተፈተኑ በኋላ ዳግመኛ ፈተናና ውድቀት አልገጠማቸውም ፡፡ ምክንያቱም የመላእክት ተፈጥሮ አንድ ጊዜ በነገሮች እንዲያልፉ ነውና ፡፡ መድገም ወይም ዳግመኛ የሚለው ዕድል ያለው ለሰው ብቻ ነው ፡፡ ለምሳሌ መላእክት አንድ ጊዜ ተፈጠሩ ፡፡ ሰው ግን አንድ ጊዜ ተፈጥሮ በልደት ይገለጣል ፡፡ መላእክት አንድ ጊዜ ተፈተኑ ፡፡ ሰው ግን በየጊዜው ይፈተናል፡፡ የአእምሮአቸውና የኃይላቸው መጠን ከፍ ያለ ነውና ከአንድ ጊዜ በላይ ዕድል አልተሰጣቸውም ፡፡ ከእነዚህ መላእክት አንዱ የቤተ ሳይዳን ውኃ ያናውጥ ነበር ፡፡
የቤተ ሳይዳ ውኃ ይናወጥ የነበረው አንዳንድ ጊዜ ነው ፡፡ በሽተኞቹ ይጠብቁ የነበረው ይህንን መናወጥ ነው ፡፡ እግዚአብሔር ውኃውን ካላናወጠው ፈውስ አልነበረም ፡፡ ይህ መናወጥ መቼ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ በሽተኞቹ ግን ነቅተው ይጠብቁ ነበር ፡፡ እግዚአብሔር ካላናወጠ ፈውስ የለም፡፡ እነዚህ በሽተኞች የውኃውን መናወጥ ሲጠብቁ ፡-
1- የራሳቸውን የሕመም ስሜት ይረሳሉ ፡፡
2- እግዚአብሔርን በተስፋና በትዕግሥት ይጠባበቃሉ ፡፡
እግዚአብሔር ካላናወጠ ፈውስ የለም ፡፡ የባሕር ውኃ በነፋስ ይናወጣል ፡፡ ስለዚህ ሕይወትነቱንና መዓዛውን ይጠብቃል ፡፡ የቤተ ሳይዳው የኩሬ ውኃ ግን መልአኩ ሲያናውጠው ሕይወትና መዓዛ ያገኛል ፡፡ ማናወጥ ማንቀሳቀስ ነው ፡፡ የቆሙ የዓይን ብሌኖች ፣ የቆሙ እግሮች ፣ የሰለለ እጆች በዚህ መናወጥ ይንቀሳቀሳሉ ፡፡ እነዚህ በሽተኞች በራሳቸው ለማናወጥ አሳብ የላቸውም ፡፡ በራሳቸው ቢያናውጡት ከልጆች ጨዋታ አያልፍም ፡፡ እግዚአብሔር ግን እንዲያናውጠው በእምነት ይጠባበቃሉ ፡፡ ዛሬም በአገልግሎታችን እግዚአብሔር እንዲያናውጠው ሕይወትና መዓዛ እንዲሰጠው መጸለይ ፣ በጽሞና መሆን ያስፈልጋል ፡፡ እግዚአብሔር ካላናወጠው ፈውስ ሊኖረው አይችልም ፡፡ ቤተ ሳይዳ ቤተ ሕሙማን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን መጠበቂያ ወይም የጸሎት ማማ ነበር ፡፡
በሽተኞች ፣ ዕውሮች አንካሶች ሰውነታቸው የሰለለ ሁሉ ይጠባበቁ ነበር፡፡ ለችግራቸው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ጉልበት ሰጥተው ይጠብቁ ነበር ፡፡ ዛሬ የዓይን ብርሃናቸውን ያጡ ፣ የሚያነክሱ ፣ ሰውነታቸው የሰለለ እፈወሳለሁ ብለው ይጠብቃሉን ? የእነዚህ ሰዎች እምነት ላቅ ያለ ነበር ፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ አንዳንድ ጊዜ ወርዶ ያናውጥ ነበር ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ወርዶ ሲያናውጥ የሚፈወሰው መጀመሪያ የገባው ሰው ነው ፡፡ ይህ የሚያሳየን ፈውስ በእግዚአብሔር ፈቃድና ጊዜ መሆኑን ነው ፡፡ ያለ መዘናጋት የሚጠብቁት እነዚያ የቤተ ሳይዳ ሕሙማን በእውነት ትጉህ ናቸው ፡፡ መልአከ እግዚአብሔር ወርዶ ሲያናውጥ መጀመሪያ የገባው ከማናቸውም ደዌ ይፈወስ ነበር ፡፡ የደዌው ዓይነት በእግዚአብሔር ፊት ከቁጥር አይገባም ፡፡ በእግዚአብሔር ዓይን ሁሉም ነገር ቀላል ነውና ፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን የመጣው መጨረሻ የቀረውን ሰው ሊያድን ነው ፡፡ እርሱ ከመጨረሻው የሚጀምር አምላክ ነው ፡፡
“በዚያም ከሠላሳ ስምንት ዓመት ጀምሮ የታመመ አንድ ሰው ነበረ፤ ኢየሱስ ይህን ሰው ተኝቶ ባየ ጊዜ፥ እስከ አሁን ብዙ ዘመን እንዲሁ እንደ ነበረ አውቆ፡- ልትድን ትወዳለህን? አለው።” /ዮሐ. 5፡5-6/ ፡፡ ሰውዬው ይህን ድምፅ መስማት አይደለም ማሰብ አይፈልግም ፡፡ ከሠላሳ ስምንት ዓመት በኋላ እፈወሳለሁ የሚል አሳብ አልነበረውም ፡፡ የጌታችን ድምፅ የተኛውን ልብ የሚቀሰቅስ ነበር ፡፡ ይህን ሰው ዛሬ የሚያየው ታማሚ እንደሆነ እንጂ ምን ያህል ዘመን እንደ ታመመ አያውቅም ፡፡ በሰውነቱ መጎሳቆል አይታወቅም ወይ ቢሉ ሰው በአንድ ቀን ሕመምም ሊረግፍ ሌላ ሰው ሊመስል ይችላል ፡፡ የሰው ልጅ ለመርገፍ የአንድ ቀን ትኩሳት በቂው ነው ፡፡ ሠላሳ ስምንት ዓመት መታመም ሲያወሩት ቀላል ነው ፡፡ ሲኖሩት ግን ከባድ ነው ፡፡ ምነው እኔም በሽታ ከጀመረኝ ሃያ ዓመት አለፈኝ አይደለም ወይ እንል ይሆናል ፡፡ ነገር ግን ቆመን እየሄድን ፣ የእፎይታ ጊዜ እያገኘን ነው ፡፡ ይህ ሰው በእኛ ዘመን ቢኖር ኑሮ ብዙ መንግሥታትን መኝታው ላይ ሁኖ አሳልፏል ፡፡ በየአራት ዓመቱ መሪያቸውን በሚመርጡ አገራት ይህ ሰው ዘጠኝ መሪዎችን አሳልፎ አሥረኛው ለምርጫ በሚወዳደርበት ዕድሜ ላይ ነው ፡፡ አንድ ልጅ ተወልዶ አድጎ ፣ ተድሮ ልጅ የሚወልድበት ቢያንስ የአሥራ ሰባት ዓመት ልጅ የሚያደርስበትን ዕድሜ በአልጋ ላይ አሳልፏል ፡፡ ሰዎች የልጅ ልጅ በሚያደርሱበት ዕድሜ በአልጋ ላይ ፈጅቶታል ፡፡ ዘመንን የሚክስ ጌታ ባያገኘው ዘመኑን በምን ይክሰው ነበር ፡፡ ጌታችን ማግኘት ግን ከኖሩበት ዘመን በላይ ነው ፡፡
ጌታችን በሽታውን ብቻ ሳይሆን ያን ያህል ዘመን እንዳሳለፈ ምን ያህል እንደ ተጎዳ አወቀ ፡፡ ሥጋውን ሲጠግን ከነፍሱ ጋር ነበር ፡፡ የሰዎችን ውጫዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ውስጣዊ ስብራት የሚያውቅ እርሱ ብቻ ነው ፡፡ አእምሮ የሌላቸው ለአእምሮ አይጨነቁም ፡፡ ትልቁ ጉዳት ግን የውስጥ ነው፡፡ ይህ ሰው ምን ያህል ዘመን እንደማቀቀ ጌታችን አውቆ ያቀረበለት ጥያቄ አስደናቂ ነው ፡፡ ልትድን ትወዳለህን የሚል ነው ፡፡ ይህ ሰው ምናልባት ችግሩን ረስቶት ችግሩን የገቢ ምንጭ አድርጎት ይሆናል ፡፡ ጌታችን ግን የጠየቀው ለመዳን ተስፋ የቆረጠውን ልቡን ለመቀስቀስ ነው ፡፡ ልቡ ካልተንቀሳቀሰ አካሉ አይንቀሳቀስምና ፡፡ ጌታችን የዚህን ሰው ፈቃዱን እንጂ እምነቱን እንኳ አልጠየቀም ፡፡ አምኖ ሳይሆን የተደረገለት ፤ ከተደረገለት በኋላ ነው ያመነው ፡፡
“ድውዩም፡- ጌታ ሆይ ፥ ውኃው በተናወጠ ጊዜ በመጠመቂያይቱ ውስጥ የሚያኖረኝ ሰው የለኝም ነገር ግን እኔ ስመጣ ሳለሁ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል ብሎ መለሰለት።” /ዮሐ. 5፡7/፡፡ ይህ ሰው ጌታ ሆይ ያለው በአክብሮት እንጂ በእምነት አልነበረም ፡፡ ጌታችን ስለ በሽታው መረጃ የሚጠይቀው እንጂ የሚፈውሰው መሆኑን አላወቀም ፡፡ እርሱ ያለ መረጃ ችግሩን አውቆለታል ፡፡ ይህ ሰው ብሶቱን ተናገረ ፡-
– ሰው የለኝም
– ጉልበት ያለው ይቀድመኛል አለ፡፡
ጌታችን ግን የመጣው ሰው ሁኖ መሆኑን አልተረዳም ፡፡ እርሱ ሰው የለኝም ለሚሉ ለዘመናት ብሶተኞች ሰው ሁኖ መጥቷል ፡፡ ተቀድሜአለሁ ለሚሉት ድል ሁኖ መጥቷል ፡፡ ዘመን የማያልፍበት ነውና ዘመኔ አለፈ ለሚሉት ዘመናቸውን ሊቀድስ የታሪክ አባል ሁኗል ፡፡ ሰው የለኝም የሚል ብሶት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ እየበዛ ነው ፡፡ ሁሉም ነገር በዘመድ ይመስል ይሆናል ፡፡ የክርስቶስ ዘመድነት ግን ከሁሉ ይበልጣል ፡፡ ሰዎች ለመሥራትም ለማገልገልም ሰው የለኝም እያሉ ነው ፡፡ እግዚአብሔር አለኝ ካላሉ ግን ምንም ዓይነት ጅምርና ፍጻሜ ሊኖር አይችልም ፡፡ ከጅምራችን በፊት ያለው አልፋ ያስጀምረናል ፤ ከፍጻሜአችን በኋላ ያለው ዖሜጋ ያስፈጽመናል ፡፡
“ኢየሱስ፦ ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው። ወዲያውም ሰውዬው ዳነ አልጋውንም ተሸክሞ ሄደ።” ይህ ሰው አልጋ ተሠርቶለት ከሆነ እዚያ በመኖሩ ታምኖበት ነው ፡፡ ክረምትና በጋውን እዚያ ያሳልፍ ዘመን አልጋ ሠሩለት ፡፡ የጌታችን የሥልጣን ቃል ሲነገር ለአእምሮው አንታዘዝም ብለው ብዙ ዘመን የሆናቸው ጡንቻዎቹ ለጌታ ታዘዙ ፡፡ አጥንቶቹ መጠነካከር ፣ ሥጋውም ማገገም ሳያስፈልገው አልጋውን ተሸክሞ እንዲሄድ ታዘዘ ፡፡ ይህ ሰው ምናልባት በጤነኝነት ዘመኑ አልጋውን መሸከም የማይችል ሰው ይሆናል ፡፡ አሁን ፈውስ ብቻ ሳይሆን ኃይልም ወደ እርሱ ስለመጣ በረታ ፡፡ የጌታ ፈውስ ከችግሩ በፊት ወደ ነበረው አቅም ሳይሆን ከዚያ ወደሚልቅ ኃይል ይመልሳል ፡፡ ይህን ያህል ጊዜ የተኛ በሽተኛ ቢድን እንኳ እስኪያገግም ብዙ ጊዜ ይወስዳል ፡፡ የጌታ ፈውስ ግን ማገገም የለበትም ፡፡