“ያም ቀን ሰንበት ነበረ። ስለዚህ አይሁድ የተፈወሰውን ሰው፡- ሰንበት ነው አልጋህንም ልትሸከም አልተፈቀደልህም አሉት።” /ዮሐ. 5፡10/፡፡
የእግዚአብሔር ፈውስ ጤንነት ብቻ አይደለም ፡፡ ከጤንነት በላይ የሆነ የልብ ደስታም ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ይቅርታ መንጻት ብቻ አይደለም ፣ ከመንጻት በላይ ማብራት መውዛትም ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ስጦታ ማግኘት ብቻ አይደለም ፣ ከማግኘት በላይም ትሑት መሆን ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ጥበብ ማወቅ ብቻ አይደለም ፣ ከማወቅ በላይም ማመን ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ምሕረት በነጻ መለቀቅ ብቻ አይደለም ፣ ላልተማሩት መራራትም ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ማዳን መትረፍ ብቻ አይደለም ፣ ለመሥዋዕትነት መጨከንም ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ጉብኝት ተስፋን ማደስ ብቻ አይደለም ፣ ለምስጋናም የሚያነቃ ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ተአምራት ከተፈጥሮ በላይ መሥራት ብቻ አይደለም ፣ አምላካዊ የሆነ ቃሉን የሚያስወድድም ነው ፡፡ የእግዚአብሔር መገለጥ ጨለማን የሚያስወግድ ብቻ አይደለም ፣ በፍቅር የሚመሰክርም ነው ፡፡ የእግዚአብሔር መዳሰስ ከአልጋ የሚያስነሣ ብቻ አይደለም ፣ አልጋን አሸክሞ የሚያዘምርም ነው ፡፡ እግዚአብሔር እጆቹ እንደ እኛ እጆች የተመጠኑ አይደሉም ፡፡ አትረፍርፈው የሚሰፍሩ ናቸው ፡፡ የለመነውን ያህል አይደለም ፣ ከለመነው በላይ አብዝቶ የሚሰጥ ነው ፡፡ ይህ ቸርነቱ ነው ዘማዊውን ድንግል ፣ ሌባውን መጽዋች ፣ ሽፍታውን ባሕታዊ ፣ ምስኪኑን ሰጪ የሚያደርገው ፡፡ ይህ ቸርነቱ ነው ደንቆሮን አስተዋይ ፣ ዓይነ ኅሊናው የተጋረደውን ጠቢብ የሚያደርገው ፡፡
ጌታ ሲፈውሳት በንዳድ ተይዛ ትሰቃይ የነበረችው የጴጥሮስ አማት ፍጹም መዳንን አገኘች ፡፡ ተነሥታም አገለገለቻቸው ፡፡ ጌታ የሥልጣን ቃል ሲናገር የሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ ፡፡ በጠበል ስፍራዎች አልጋ የለም ፡፡ የሚቆይ እንጂ የሚከርም የለምና ፡፡ ይህ ሰው ግን ዘመናትን ስላሳለፈ አልጋ ሠሩለት ፡፡ በሽታውን የሚያስታምምበት አልጋ የሠሩለት ፈውስ አንዲያገኝ ግን መንገድ አልለቀቁለትም ፡፡ ጎበዝ አስታማሚዎች ናቸው ፡፡ ፈውስ እንዳያገኝ ግን መንገድ ዘግተዋል ፡፡
ይህ ሰው የተፈወሰበትና አልጋውን ተሸክሞ የሄደበት ቀን አንድ ነው ፡፡ እግዚአብሔር የዘመናትን ጥያቄ በአንድ ቅጽበት ይመልሳል ፡፡ ይህ ሰው ፈውሱ የጌታውና የራሱ ደስታ ሲሆን ብዙዎችን ግን አስከፍቷል ፡፡ ምቀኝነታቸውን ግን ሃይማኖታዊ ካባ ማልበስ ነበረባቸው ፡፡ ሰዎች ምቀኛ መባልን አይፈልጉም ፣ መሆንን ግን አይጠሉም ፡፡ ይህ ሰው የሚታወቅበት ነገር ባይኖርም ዘመናትን ባስቆጠረው በሽታው ይታወቃል ፡፡ መፈወሱ የሚያስደስት ነበር ፡፡ ምክንያቱም የእርሱ በሽታውም ሆነ ፈውሱ የማንንም ጥቅም የሚነካ አይደለም ፡፡ አይሁድ ግን ተከፉ ፡፡ የችግሩ የበላይ ጠባቂዎች ይመስላሉ ፡፡ ጌታችን ከሞት እንዳይነሣ መቃብሩን ይጠብቁ እንደነበሩ ወታደሮች ፤ ሰው እንዳይነሣ ፣ እንዳያገኝ ዘብ የቆሙ አያሌ ናቸው ፡፡ እግዚአብሔር ካስነሣ ግን ማንም ሊይዝ አይችልም ፡፡ ሁልጊዜ መጸለይ ያለብን አንድ ብርቱ ጸሎት አለ ፡- “ጌታ ሆይ በሌሎች በጎ ዕድል ውስጤ እንዳይከፋ እርዳኝ” ማለት ይገባናል ፡፡ ምክንያቱም ምቀኝነት ነፍሰ ገዳይ ያደርጋል ፡፡ ቅንዓትና ምቀኝነት ማንኛውም መልካም ነገር ከእኔ ውጭ ለማንም አይገባም የሚልና ሌሎች ሲቸገሩ የደስታ ከበሮ የሚመታ ነው ፡፡ ቅንዓትና ምቀኝነት መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ በሽታ በመሆኑ መታከም ያስፈልገዋል ፡፡
አይሁድም ቅንዓትና ምቀኝነታቸውን በሃይማኖት ግምጃ መሸፈን ፈለጉ፡ ያ መላ አካላቱ በደዌ የታሰረ ሰው ዛሬ አልጋ ተሸክሞ ሲሄድ መደነቅ መደሰት ይገባ ነበር ፡፡ ነገር ግን በሃይማኖት ተከልለው ልቡን ሊያቆስሉት ፈለጉ ፡፡ ደስታ ባልንጀራ ይፈልጋል ፡፡ ይህ ሰው ግን የራሱ ልብና እግዚአብሔር ብቻ የደስታ አጋሩ ሆኑ ፡፡ እግዚአብሔር ብቻ አድርጎልን ይደሰታል ፡፡ ደስታቸው አጋር ያጣ ሰዎች በጣም ሲያዝኑ የመጣው ደስታቸውን ኀዘን ፣ እሴታቸው ባዶነት ፣ ማግኘታቸው የድህነት ያህል ሲሰማቸው ይታያል ፡፡ ነገር ግን ደስታ አጋር ሲያጣ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የቆየ ልማድ ነው ፡፡ ሰንበት እግዚአብሔር የሚከብርበት ፣ ሰው የሚደሰትበት ቀን ሳለ አይሁድ ግን የጭንቀት ቀን አደረጉት ፡፡ ያ ሰው ግን አልጋውን ተሸክሞ የሄደው ወደ ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ስለ ፈውሱ የእርሱ መደሰቻ ቦታ ቤተ መቅደሱ ነበር ፡፡ ፈውስን ነጥቆ የሚሮጥ አልነበረም ፡፡ በቤተ መቅደሱ ግን የነበሩት ሰዎች የእግዚአብሔርን ሥራ የሚቃወሙ እንጂ በአግዚአብሔር ሥራ ፣ በሰው መዳን የሚደሰቱ አልነበሩም፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ፍጥረትን ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ ፡፡ ድካም የሌለበት አምላክ ዐረፈ ተብሎ የተጻፈው ለእኛ አርአያ ለመሆን ነው ፡፡ ማረፍ ያስፈልገናል ፡፡ በእግዚአብሔር ቃል እናርፋለን እንጂ ከእግዚአብሔር ቃል አናርፍም፡፡ ሁሉ ቀን የጌታ ቢሆንም ሰንበት ግን ለእግዚአብሔር የምናወጣው የጊዜ አሥራት ነው ፡፡ የሰው ልጅ የሥጋ ሩጫውን ገታ አድርጎ፣ ከኅሊና መባዘን ወጥቶ ፣ መልካሙን ሥራ እየሠራ ይደሰት ዘንድ ሰንበት ተሰጥቶታል ፡፡ እግዚአብሔር ካዘጋጀልን ማረፊያ መስኮች ፣ መዝናኛ ደሴቶች በላይ ሰንበት ትልቅ የዕረፍት ቀን ናት ፡፡ የጭንቀት ቀን ያደረጋት የሰዎች ወግና ልማድ በሕጉ ላይ መጨመሩና ከሕጉ በላይም መከበሩ ነው ፡፡ ከሕጉ ጋር በቀጥታ መፋጠጥ ውጤታማ አያደርግም በማለት አስቀድመው አጥር ሠርተው ነበር ፡፡ ሰንበትን ለመጠበቅም እሳት አለመጫር ፣ ሸክም አለመሸከም ፣ የሰንበት መንገድ መሄድ የሚሉ ልማዶች ተጨምረው ነበር፡፡ በሰንበት ተግባረ ሥጋ እንዳይፈጸም ሲከለከል ተግባረ ነፍስን ለመፈጸም ነው፡፡ አይሁዳውያን እሳት ባለመጫር ፣ ዓለማውያን በኃጢአት ቀኑን ያሳልፉታል ፡፡ እውነተኛው የሰንበት ተግባር ግን በሽተኞችን መጠየቅ የተጎዱትን መርዳት ነው ፡፡ ጌታችን የሰንበት መሥራች ነው ፡፡ እርሱ የሰንበትን እውነተኛ ትርጉም በሽተኛን በመፈወስና አልጋውን በማሸከም አከበረው ፡፡
የተሸከሙንን መሸከም በእውነት የመፈወስ ምልክት ነው ፡፡ በጀርባቸው ያዘሉንን ወላጆች መጦር ፣ እኛን ለማስተማር የደከሙትን መምህራን መርዳት ፣ ከጥፋት የመለሱንን መንከባከብ ፣ መልካም ያደረጉልንን ማመስገን ይህ የመፈወስ ምልክት ነው ፡፡ በክርስቶስ መዳን ማለት መፈወስና የተሸከሙንን መሸከም ያለበት ነው ፡፡ መፈወስ ከአልጋ የሚያስነሣ ፣ ቀሊል ቀንበርን የሚያሸክም ነው ፡፡ የሞት ቀንበርን ጥሎ የፍቅር ቀንበርን የሚጭን አምላክ ምስጋና ለእርሱ ይሁን ፡፡