የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

መዳን በሥላሴ

“ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና” /ዮሐ. 5፡19/፡፡
ቅዱስ አውግስጢኖስ ፡- “ዘላለማዊውንና የማይለወጠውን እውነት ማወቅ በሌለበት ስፍራ በመልካም ምግባር የተጌጠ ሕይወት እንኳ ሐሰት ሊሆን ይችላል” ብሏል ፡፡ እግዚአብሔር የለሾች የሚባሉ ብዙዎቹ ሰውን የማይነኩ ፣ የተቸገረ ሲገጥማቸው ኪሳቸውን አዋጥተው ብቻ ሳይሆን ቤታቸውን ሸጠው የሚሰጡ ናቸው ፡፡ ከክርስትና ርቀው ያለ የሩቅ ምሥራቅ እምነቶች ጨዋነታቸው መጠን የለሽ ነው ፡፡ እውነተኛ ምግባር ግን በእውነተኛው ሃይማኖት ላይ ይመሠረታል ፡፡ የአንድ አገር መንግሥት አለመቀበልና አለመገበር ወንጀለኛ ያደርጋል ፡፡ ይህ ሰው ጎረቤቱን ላይነካ ይችላል ፡፡ መንግሥቱን የማይቀበልና የማይገብር ከሆነ ግን ወንጀለኛ ነው ፡፡ እንዲሁም ለእግዚአብሔር አምላክነት የማይገዛ ፣ ለጌትነቱ የማይገብር ጨዋነት በተዘዋዋሪ ወንጀለኛነት ነው ፡፡ ከዐሥርቱ ትእዛዛት የመጀመሪያዎቹ ስለ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚናገሩ ናቸው ፡፡ ዐሠርቱ ትእዛዛት የሥነ ምግባር ሕግ ከሆነ ትልቅና የመጀመሪያው ሥነ ምግባር እግዚአብሔርን ማምለክ ነው ፡፡ ዐሠርቱ ትእዛዛት የፍቅር ሕግ ነው ካልን የፍቅር መነሻ እግዚአብሔርን መውደድ ነው ፡፡ እግዚአብሔርን ሳይወድ ወንድሙን የሚወድ ፍቅር ሐሰተኛ ነው ፡፡ ወይም መሠረት የሌለው ቤት ነው ፡፡ ስለዚህ በእውነት ላይ መመሥረት ሃይማኖትም ምግባርም ነው ፡፡
ጌታችን ከዚህ ጀምሮ ሥልጣኑን ይነግራቸው ነበር ፡፡ ቢያምኑ ይድኑበታል ፡፡ ባያምኑ ለፍርድ ይመቻቹበታል ፡፡ ጌታችን እውነት እውነት እላችኋለሁ ማለቱ አጽንኦትን ለመስጠት ነው ፡፡ አምላክነትን የተመኙ አምላክ ነን ብለው የተነሡ አያሌ ነበሩ ፡፡ እርሱ ግን በእውነት አምላክ ነው፡፡ አብ ከወልድ ተሰውሮ የሚያደርገው አንድም ነገር የለም ፡፡ አብ የሚያደርገውን ወልድ ያያል ያውቃል ፡፡ ወልድም የሚያደርገውን አብ ያያል ያውቃል ፡፡ የማይታየው አብና እንዲሁም ግብሩ ለወልድ ይታየዋል ፡፡ እንደውም በአንዲት መለኮታዊ ፈቃድ አንድ መለኮታዊ ግብር ያደርጋሉ ፡፡ እውር ማብራቱ ድውይ መፈወሱ የመጨረሻው ትልቅ ተግባር ለመሰላቸው አይሁድ ከዚህም የሚበልጥ ነገር እንደሚሠራ እየነገራቸው ነው ፡፡ በሥላሴ መንግሥት ያለው አንድነት ምንም ግርዶሽ የሌለበት ነው ፡፡ አብ የሚያደርገውን ወልድ ያያል ፣ ወልድም የሚያደርገውን አብ ያያል ፡፡
አንድነትን የምንማረው ከእግዚአብሔር ነው ፡፡ አንድነት ምንም ዓይነት የአሳብና የተግባር ግርዶሽ የሌለበት ሊሆን ይገባዋል ፡፡ አብ ያደረገውን ወልድ ያደረገው ነው ፡፡ ምክንያቱም የሚያደርጉት በአንዲት ፈቃድ ነውና አንድ ግብር ነው ፡፡ እውነተኛ አንድነት ሲኖረን በአሳብም በተግባርም አንድነት ይኖረናል ፡፡ የምናስበውን እንነጋገራለን ፡፡ የምናደርገውንም እንገልጣለን ፡፡ በርግጥ አብ የሚያደርገውን ወልድ የሚያውቀው ጠይቆ አይደለም ፡፡ ልቡ ነውና ያውቀዋል ፡፡ እንዲሁም ወልድ የሚያደርገውን አብ የሚያውቀው ጠይቆ አይደለም ፣ ቃሉ ነውና የተላከውን ያደርጋል ፡፡ ቃል ለልብ መልእክተኛ ሲሆን ድርሻ እንጂ ማነስን አያሳይም ፡፡ እንዲሁም በሥላሴ መንግሥት መላክና መላክ ፍቅርን እንጂ ደረጃን አያመለክትም ፡፡ ማንም በገዛ ቃሉ ቢናገር ልቡ አብሮት አለ ፣ ማንም በገዛ ክንዱ ቢጥል አካሉ አብሮት አለ ፡፡ ልብ የተለየው ቃል ፣ አካል የተለየው ክንድ የለም ፡፡ ወልድም የአብ ቃሉና ክንዱ ነው ስንል ባለመለየት አብሮት ይኖራል ማለታችን ነው ፡፡ አንድ ሰው መልካም ቢያደርግልን ይህን በአካሉ ይህን በክንዱ አደረገልን አይባልም ፡፡ አንድ ሰው ቢያጽናናን ይህን በልቡ ይህን በቃሉ አደረገ አንልም ፡፡ አንድ ግብር ሰጥተን እናመሰግናለን ፡፡ እንዲሁም በአብም በወልድም የሚደረገው ማንኛውም ተግባር ምሥጋናው ለአንዲት የሥላሴ መንግሥት የሚቀርብ ነው ፡፡ ጌታችን ድውይ በመፈወሱ አብም ከእርሱ ጋር እንዳለ ተናገረ ፡፡ ከዚህ የሚበልጠው ነገረ ድኅነትም የሦስቱ አካላት ተግባር አለበት ፡፡ ይህ ዓለም እንዲድን እግዚአብሔር አብ ዓለምን አፈቀረ ፣ ፈቀደ ፣ መከረ ፡፡ መንፈስ ቅዱስም ከጽንሰት ጀምሮ ሥጋን በማዋሐድ ፣ እመቤታችንን በመጋረድ ፣ እንዲሁም በትንሣኤው ከአብና ከወልድ ጋር ኃይልን በመግለጥ … ሥራውን ከወነ ፡፡ ነገረ ድኅነትን ስናነሣ አብና መንፈስ ቅዱስን እንዳንረሳ መጠንቀቅ አለብን ፡፡ ማዳን የአንዲት መለኮታዊ ግብር መሆኑንም ማሰብ አለብን ፡፡ ጌታችንም እያሳሰበ ያለው ይህን ነው ፡፡ በአሁን ዘመን አብና መንፈስ ቅዱስ በነገረ ድኅነት እየተረሱ ይመስላል ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በጸሎት መክፈቻ ፡- “የጌታችንን የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት እግዚአብሔርን እንማልዳለን” ማለቷ ፤ በጸሎት መዝጊያም ፡- “በአንድ ልጅህ በኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ያለ ክብር ጽንዕ ላንተ ይገባሃል ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ትክክል የሚሆን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን” የምትለው መዳንን ሥላሴያዊ ለማድረግ ነው ፡፡
ጌታችን ከገለጠው የሥላሴ ኅብረት የምንማረው ነገር አለ ፡፡ እውነተኛ አንድነት ሲኖረን ሳንነጋገር አንድ ነገር እናስባለን ፡፡ አንድ ነገርም እናደርጋለን ፡፡ በሌላው ሥራ ውስጥ እኛ አባል ፣ በእኛ ሥራ ውስጥ ሰዎች አባል እንደሆኑ ይሰማናል ፡፡ አንድነት ማለት የተግባሩን ምስጋና በጋራ መውሰድ ማለት ነው ፡፡ የአንድነት እንቅፋትም ከእኔ በእኔና ለእኔ የሚል አስተሳሰብ ነው ፡፡ አንድ ፈቃድና ግብር ሲኖር ምስጋናውም አንድ ይሆናል ፡፡ እግዚአብሔር በሰው ውስጥ ያሳደረው መልኩ ይህ አንድነቱም ነው ፡፡
በአብ ድርጊትና በወልድ ድርጊት መካከል የፈቃድም የኃይልም ልዩነት የለም ፡፡ ወልድ ሥጋ ለብሶ በምድር ላይ የሚያደርገውን አብ በሰማይ እውቅና ይሰጠዋል ፡፡ ወልድም በምድር ላይ ያለው በሰማይ ሳይታጣ ነውና ለአብ ተግባር እውቅና ይሰጠዋል ፡፡ አብ ሲያደርግ ያየውን ማለቱ ልክ እንደ አብ እሠራለሁ ማለቱ ነው ፡፡ ከራሴ ምንም አላደርግም ማለቱም እኔ በቃልነቴ ከዊን በወልድነቴ ግብር የማደርገውን ተግባር አብ በልብነቱ ከዊን መንፈስ ቅዱስም በእስትንፋስነቱ ከዊን አለበት ማለቱ ነው ፡፡ ልብ የሌለው ቃል የለም ፣ እንዲሁም ለወልድ አብ አለው ፡፡ አብ በልብነቱ የሚያስበውን እኔ በቃልነቴ አደርገዋለሁ ማለቱም ነው ፡፡
“አብ ወልድን ይወዳልና፥ የሚያደርገውንም ሁሉ ያሳየዋል፤ እናንተም ትደነቁ ዘንድ ከዚህ የሚበልጥ ሥራ ያሳየዋል።” የሥላሴ መንግሥት መታወቂያዋ ፍቅር ነው ፡፡ በአብና በወልድ መካከል ያለው ፍቅር ከዘላለም ነው ፡፡ ከጊዜ ውጭ ነውና ጊዜ አያደፈርሰውም ፡፡ የሰው ፍቅር በጊዜ ውስጥ ስለሆነ ትላንት የወደድነውን ዛሬ ጠልተነዋል ፡፡ ትላንት የመሰከርንለትን ዛሬ ክደነዋል ፡፡ ለምንወደው ሰው ከጥዋቱ ይልቅ አሁን ፍቅራችን ቀዝቅዟል ወይም ሞቋል ፡፡ አንዴ ወደ ላይ እየወጣ ሲያሳብደን ፣ አንዴ ወደ ታች እየወረደ ሲያስተክዘን ስሜት ፣ አልባ ሁነን ሲያስደንቀን የሚኖረው ተለዋዋጩ የእኛ ፍቅር ነው ፡፡ በእግዚአብሔር ፍቅር ፊት የሰው ፍቅር ከጥላቻ ትንሽ የሚለይ ይመስላል ፡፡ ፀሐይ ከወጣች በኋላ የወጣ አምፑል ከማብራት ይልቅ የራሱን ቆሻሻ ያሳያል ፡፡ ማታ ላይ ልዩ ብርሃን ነበረ ፣ አሁን ግን እንኳን ሊያሳይ የራሱ ደብዛዛነትና ቆሻሻነት ይታያል ፡፡ እኛ ፍቅር የምንለው አለመጥላትን ፣ ይቅርታ የምንለውም ንቆ መተውን ፣ ቸርነት የምንለውም የጉራ ወጪን ፣ በጎነት የምንለው ሽንገላን ፣ እምነት የምንለው በራስ መተማመንን ፣ ስብከት የምንለው መፎከርን ፣ መዝሙር የምንለው ቅላፄን ፣ ርኅራኄ የምንለው ሰውን እንደ ምስኪን መመልከትን ፣ እርዳታ የምንለው የበላይነታችንን ማስጠበቃችንን ፣ መንፈሳዊነት የምንለው መንፈሳዊ ቃላት መናገራችንን … ነው ፡፡ ፍቅራችን በፍቅሩ ፣ ቸርነታችን በቸርነቱ መፈተሸ አለበት ፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ሲመጣ የእኛ ፍቅር በራሱ ንጹሕ እንዳልነበር እንረዳለን ፡፡ የወደድነው ሰዎቹን ሳይሆን ሀብታቸውን ወይም መልካቸውን አሊያም ዝናቸውን ነው ፡፡ ሀብታቸው ሲሄድ ያስጠሉናል ፡፡ መልካቸው ሲከዳ እንከናቸውን እናበዛለን ፡፡ ዝናቸው ሲተንን ክስ እናበዛባቸዋለን ፡፡
ጌታችን አብ ወልድን ስለ መውደዱ መናገሩ በዚያ በሽተኛ መፈወስ ልባቸው የተከፋው ፍቅር አልባ ስለሆኑ እንጂ ስለ ሰንበት ስለ ገደዳቸው አልነበረም ፡፡ ፍቅር የሌላት ሰንበት ግን ዕረፍት የላትም ፡፡ ፍቅር ቢኖራቸው የዚያ በሽተኛ ፈውስ ከእግዚአብሔር መሆኑን ይረዱት ነበር ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለአፍቃሪዎችና ለትሑታን ራሱን በመግለጥ የታወቀ አምላክ ነውና ፡፡ በአብና በወልድ መካከል ያለው ፍቅር በግልጽነት ይታወቃል፡፡ እውነተኛ ፍቅር ባለበት መጋረጃ የለም ፡፡ ፍቅር ይተዋወቃል ፡፤ ይሸፋፈናል ፡፡ በእርግጥ እገሌን እወደዋለው ወይ ለማለት ቀላል መለኪያ ግልጽ ነኝ ወይ የሚል ነው ፡፡ ግልጽነት፡-
–    የፍቅርን ዕድሜ ያረዝማል ፡፡
–    ሸክምን በጋራ ለመጋራት ይረዳል ፡፡
–    ሦስተኛ ወገን ጣልቃ እንዳይገባ ያግዛል ፡፡
ግልጽነት መጋረጃን ማስወገድ ነው ፡፡ ነገር ግን አጥር ነው ፡፡ ጌታችን በእርሱና በአባቱ መካከል ያለውን ፍቅር በግልጽነት አብራራው ፡፡ ጌታችን ለአይሁድ እናንተንም ሥራውን እንዲያሳያችሁ ውደዱት እያለ ነው ፡፡ እግዚአብሔርን መውደድ እግዚአብሔር የፈጠረውን ሰው በመውደድ ይገለጣል ፡፡ ማንም አባት ልጁን ጠልተንበት ይወደኛል ብሎ አይቀበለንም፡፡ እንደውም “እኔን የወደደ ካንገት ፣ ልጄን የወደደ ካንጀት” የሚባለው ልጅ የፍቅር መለኪያ ስለሆነ ነው ፡፡ እግዚአብሔርም ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለጎረቤታችን ባለን ፍቅር ይለካዋል ፡፡    
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ