የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የእግዚአብሔር ሕይወት

“አብ ሙታንን እንደሚያነሣ ሕይወትም እንደሚሰጣቸው፥ እንዲሁ ወልድ ደግሞ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣቸዋል።” /ዮሐ. 5፡21/፡፡
ጌታችን በአብ ክብር ያለ መሆኑን እየተናገረ ነው ፡፡ አብ በሚሰጠው ሕይወትና ወልድ በሚሰጠው ሕይወት መካከል ምንም ልዩነት የለም፡፡ በአንዲት መለኮታዊ ሥልጣንና ክሂል አንድ ሕይወትን ሦስቱም የሥላሴ አካላት ይሰጣሉ ፡፡ አይሁድ እግዚአብሔርን አንድ ገጽ ፣ አንድ አካል ብለው ያምናሉ ፡፡ እግዚአብሔር ግን ሦስት ገጻትና ሦስት አካላት ያሉት ነው፡፡ በምድር የተገለጠውን ወልድን ለመቀበል የቸገራቸው በሰማይ ላለው አብ ጥብቅና መቆማቸው ነው ፡፡ የማይታየውን አብ ተቀብለው በትሕትና የተገለጠውን ወልድን መቀበል አቃታቸው ፡፡ ወልድ በምድር ላይ የተገለጠው የሥላሴን ፈቃድ ለመግለጥ ድኅነትን ለመፈጸም እንጂ ማነስ ገጥሞት አይደለም ፡፡ ስለዚህ የተላከውን ወልድን አለመቀበል ላኪውን አብን አለመቀበል ነው፡፡ አይሁድ ወልድን ሲያጡ አብንም ያጣሉ ፡፡ ጌታችን ከአባቱ ጋር ያለውን ዋሕድነት ወይም አንድነት እየተመካበት ሳይሆን መንግሥተ ሥላሴን እየገለጠ ነው ፡፡ “የበላችው አንቋታል በላይ በላይ ያጎርሳታል” እንዲሉ ተአምሩ ለቆረቆራቸው እግዚአብሔርነቱን ገለጠላቸው ፡፡ የማይበሉትን በግ በቀራንዮ እንዳረዱ ፣ የማያርፉበትንም ጥያቄ ጠየቁት ፡፡ በጉ ለዓለም ጥጋብ ሆነ ፣ የጥያቄውም መልስ ለሥላሴ ትምህርት መሠረት ሆነ፡፡
ሕይወትን መስጠት የሚችለው የሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለችው ሕይወት አንዲት ናት ፡፡ ያችን ሕይወት ለመስጠትም እግዚአብሔር መሆን ያስፈልጋል ፡፡ ጌታችን በዚህ ክፍል ላይ አብን ወልድን እንዲሁም ሕይወት በማለት መንፈስ ቅዱስንም እየገለጠ ነው፡፡ ጌታችን ሙታንን ስለ ማንሣት ለምን ተናገረ ስንል ያ በሽተኛ አካሉ በደዌ ፣ ነፍሱ ተስፋ በመቁረጥ የሞተች ነበረች ፡፡ ሁለንተናዊ ቁመና መስጠት ሥጋንም ነፍስንም መደገፍ እንደሚችል እየተናገረ ነው ፡፡ ይህ በሽተኛ የተነሣው ሕይወትም ያገኘው በአብም በወልድም ሥልጣን ነው፡ አብን ዘላለማዊ አባት ብለው ቢያምኑ ኑሮ ወልድን ዘላለማዊ ልጅ ብለው ይቀበሉ ነበር ፡፡ ልጅ በሌለበት አባት መባል የለምና ፡፡ “ወልድ ሲነካ አብ ይነካ” እንዲሉ ወልድን መንካት አብን መንካት ነው ፡፡ ጌታችን እንደ ገለጠው ለሙታን ሁለት ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ይደረግላቸዋል ፡፡ የመጀመሪያው መነሣት ነው ፡፡ ሁለተኛው ሕይወት ማግኘት ነው ፡፡ በአልዓዛር መቃብር ላይ ጌታችን “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” ብሏል ፡፡ መነሣት ሞትን ማሸነፍ ሲሆን ሕይወት ደግሞ የመኖር አቅም ነው ፡፡ ሰዎች በሥጋ ተነሥተው በነፍስ ግን ሊሞቱ ይችላሉ ፡፡ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ግን ትንሣኤና ሕይወት ነው ፡፡ ብዙ ሰዎች በሥጋ ተነሥተዋል ፡፡ ረሀባቸው በጥጋብ ፣ ውርደታቸው በክብር ፣ ጭቆናቸው በሥልጣን ተተክቷል ፡፡ ነገር ግን በነፍስ ሞተዋል ፡፡ ገንዘብ እውነትን ፣ ሥልጣን ርኅራኄን ፣ ዝና መነሻቸውን አስረስቷዋል ፡፡ ከእግዚአብሔር የሚገኘው ግን የተሟላ ሕይወት ነው ፡፡ በሥጋ መነሣት ብቻ ሳይሆን በነፍስም መኖር ነው ፡፡
መቃብር ብዙዎችን አስገብሯል ፡፡ ዓለምን የገዙ ነገሥታትን መቃብር አሸንፏል ፡፡ የቤተ መንግሥት ደጆች በሞት ተከፍተዋል ፡፡ ሞትን በትንሣኤ ለመለወጥ ደፍሮ ተስፋ የሰጠ ማንም የለም ፡፡ ጌታችን ግን በሞት ላይ የበረታ ፣ ሞትንም በሞት የቀጣ ነው ፡፡ ሞት ቀጪ አጥቶ ይፋንን ነበር ፡፡ ሞት፣ ሞት የለብኝም ብሎ በገዳይነቱ ይኩራራ ነበር ፡፡ ለሞት ሞትን የከፈለው ሥልጣነ እግዚአብሔር ፣ ሕይወተ መንፈስ ቅዱስ ነው ፡፡ የሞቱት መነሣት የተነሡትም መኖር ይችላሉ ፡፡ እግዚአብሔር በመንበሩ የሚሠራው ድንቅ ችሎታው ነው ፡፡ ሙታንን ማስነሣት ሕይወትንም መስጠት እግዚአብሔር በመንበሩ የሚገለጥበት ግብሩ እንጂ ወቅታዊ ሥራው አይደለም፡፡ ሞት ብዙ ዓይነት ትርጉም አለው ፡፡ የሞት ትንሹ ትርጉሙ መቃብር መውረድ ነው ፡፡ ሞት ግን ከእግዚብሔርና ከመንፈሳዊ ጠባያት መራቅ ነው ፡፡ ሰዎች ኖረው በሥጋ ሊሞቱ ይችላሉ ፡፡ በመንፈስ ሞተውም በሥጋ ሊሞቱ ይችላሉ ፡፡ ልባቸው በጥላቻ የሞተባቸው የፍቅር ትንሣኤና የርኅራኄ ሕይወት ማግኘት እንደሚችሉ ጌታችን እየተናገረ ነው ፡፡  እኛ ከእንቅልፍ የምንቀሰቅሳቸውን ልጆቻችንን እንጀራ እናቀርብላቸዋለን ፡፡ እግዚአብሔር ግን ከሞት የሚቀሰቅሳቸውን ልጆቹን ሕይወት ይጋብዛቸዋል ፡፡
ጌታችን ሕይወት ስጦታ መሆኗን ተናገረ ፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ሕይወት ትልቅ ርእስ ነው ፡፡ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እውነት ፣ እምነትና ሕይወት በመደጋገም ተጠቅሰዋል ፡፡ በርግጥም እውነት ወደ እምነት እምነትም ወደ ሕይወት ያደርሳል ፡፡ የእውነትና የእምነት ግብ ሕይወት ነው፡ እውነትና ሕይወት የእግዚአብሔር ገንዘብ ሲሆን እምነት ግን የሰው ምላሽ ነው ፡፡ ጌታችን በዚህ ክፍል ላይም ሕይወት ስጦታ መሆኑን ተናገረ ፡፡ እግዚአብሔር ሕይወትን የሚሰጥበት መንገዱን ጌታችን ሲገልጥ ፡- “ለሚወዳቸው” የሚል ቃል ተናግሯል ፡፡ ጌታችን ማንን ይጠላል ብንል ለፈቀደላቸው ማለቱ ነው ፡፡ መውደድ መፍቀድ ነውና ፡፡ ሕይወት የሰውን ፈቃደኝነትና የእግዚአብሔርን ፈቃደኝነት የሚጠይቅ ነው ፡፡ በሞት ቀጠና ውስጥ ያለው ሰው ሕይወትን ከመፈለግ ውጭ ምንም አማራጭ የለውም ፡፡ ከሰው ፈቃድ ይልቅ ዋጋ የሚሰጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ፡፡ ሰው ፈቅዶ እግዚአብሔር ባይፈቅድ ምንም መፍትሔ አልነበረም ፡፡ ዘወትር ማድነቅ የሚገባን እኛ እግዚአብሔርን ስለ መውደዳችን ሳይሆን እግዚአብሔር እኛን ስለ መውደዱ ነው ፡፡
የሥላሴ ሕይወት መንፈስ ቅዱስ ነው ፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሕይወት ሲሆን ልብና ቃል ያለው ሕይወት ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወትም ወደ እኛ ሲመጣ ማስተዋልና ተግባር ይኖረናል ፡፡ ማስተዋል መነሻ ሲሆን ተግባርም መድረሻ ነው ፡፡ ማስተዋልና ተግባር የሌለው ሕይወት ወይም ህልውና የትም አይደርስም ፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ሲኖረን ሰጪ ብቻ ሳንሆን ተቀባይም መሆናችንን እንረዳለን ፡፡ እንደውም አንድ ስንሰጥ ሁለት እንደምንቀበል በማሰብ ከሌሎች ጋር በመገናዘብ እንሠራለን ፣ በአንድነት እንኖራለን ፡፡
በልጅነቴ አንዲት አውቶብስ ልብ የለሽ እየተባለች ስትጠራ አስታውሳለሁ ፡፡ የአንድ መጠጥ ፋብሪካ ንብረት ናት ፡፡ ሠራተኞችን ማድረስና መመለስ ተግባሯ ነው ፡፡ ሠራተኛው መጠጥ ቀምሶ ነው የሚገባባት፡፡ ሲመጡም እየጨፈሩ ነው የሚመጡት ፡፡ ወደ ቤታቸውም አይገቡም በዚያው ወደ መጠጥ ቤት ይገባሉ ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን እናቴን “ለምንድነው ልብ የለሽ የተባለችው” አልኳት ፡፡ ያን ጊዜ አልገባኝም ዛሬ ግን መልሱ ገባኝ ፡፡ “ልብ ቢኖራት ልብ የለሾችን ጭና አትመጣም ነበር” አለችኝ፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ወደ እኛ ሲመጣ ልብ አለው ፡፡ ማስተዋል ምክር አለው ፡፡ ጥንቃቄ ተስፋ አድራጊነት አለው ፡፡
ዘመነ ብሉይ ዘመነ አብ ፣ ዘመነ ሥጋዌ ዘመነ ወልድ ፣ ዘመነ ቤተ ክርስቲያን ዘመነ መንፈስ ቅዱስ ይባላል ፡፡ ይህ ማለት አካላተ ሥላሴ የዘመን ገደብ አለው ማለት አይደለም ፡፡ እግዚአብሔር አብ ልብ ነውና ልብም አሻግሮ ያያልና በነቢያት ትንቢት ማናገሩን ለመግለጥ ነው ፡፡ በእግዚአብሔር ቃልና በተግባር መካከል ምንም ልዩነት የለም ፡፡ ስለዚህ ዘመነ ሥጋዌ መዳን የተፈጸመበት ነው ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያን አድሮ የሚሠራበት ይህ ዘመን ደግሞ ዘመነ ቤተ ክርስቲያን ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ሕይወት ሲኖረን ስለ ሌሎች መዳን እንተጋለን ፡፡ ስለ ሌሎች መዳን ከመትጋታችን በፊት ግን በውስጣችን ተስፋ ማድረግ በተግባራችን መርዳት ከፊት ለፊቱ አለው ፡፡ እጅ የሌለው ወንጌል የወደቁትን አያነሣም፡፡
ጌታችን ለአይሁድ እያስተላለፈ ያለው መልእክት ምንድነው ስንል የእግዚአብሔር ሕይወት ቢኖራችሁ ኑሮ ይህ በሽተኛ በመፈወሱ ትደሰቱ ነበር፡፡ ይህን ሕይወት ለመቀበል ደግሞ አብና ወልድን መቀበል ያስፈልጋል፡፡ እናንተ ግን አልተቀበላችሁም ፡፡ ሙታን ሲነሡ ከማየት ውጭ ትንሣኤ የላችሁም ፡፡ በሌሎች ማረፍ ከመበሳጨት ውጭ ለሌሎች የሚቆረስ ሕይወት የላችሁም እያላቸው ነው ፡፡ እኛስ ? ሲሰክሩ ዝም ያልናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነቡ እንቃወማቸው ይሆን ? ሲዘፍኑ ያለፍናቸውን ሲዘምሩ እንነቅፋቸው ይሆን ?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ