የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

                   ወልድ ሲነካ አብ ይነካ 

                                                                    
ሰዎች ሁሉ አብን እንደሚያከብሩት ወልድን ያከብሩት ዘንድ፥ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው እንጂ አብ በአንድ ሰው ስንኳ አይፈርድም። ወልድን የማያከብር የላከውን አብን አያከብርም”/ዮሐ. 5፡22-23/
ጌታችን በአብና በእርሱ መካከል ያለውን የፍቅር ቅርበት ፣ የሥልጣን እኩልነት እንዲሁም አብ እንደሚሠራ እርሱም እንደሚሠራ ፣ አብ ሕይወትን እንደሚሰጥ እንዲሁም ወልድም ሕይወትን እንደሚሰጥ ተናግሯል ፡፡ ወልድ ለሚወዳቸው ሕይወትን ይሰጣል የሚለውን ቃል ደግመን ማሰብ መልካም ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ፍቅሮች አሉ ፡፡ አንዱም ፍቅር ግን ሕይወት መስጠት ፣ ሞትን መቅዘፍ አይችልም ፡፡ የሚያድን ፍቅር የክርስቶስ ብቻ ነው ፡፡ እርሱ ሕይወትን የሚሰጠውም ችሎታውን ለማሳየት ሳይሆን ፍቅሩን ለመግለጥ ነው ፡፡ በዓለም ላይ ስጦታዎች ስጦታ ላይሆኑ ይችላሉ ፡፡ የእርሱ ስጦታ ብቻ ስጦታ ነው ፡፡ ከፍጡር እጅ የማንቀበለውን ሕይወት ከእርሱ ተቀብለናል ፡፡ ሕይወትንም የሚሰጠን ከባሕርዩ ነው ፡፡ ያ ሕይወትም ዘላቂ የሚሆነው ከእርሱ ጋር እስካለን ድረስ ነው ፡፡
እግዚአብሔር አምላክነቱን ከሚገልጥበትና የባሕርዩ መገለጫ ነው ከሚባሉት ነገሮች አንዱ ፍርድ ነው ፡፡ በዓለም ላይ ፈራጆች ቢኖሩ እንኳ በሚፈርዱት የሚፈርድ አንድ አምላክ አለ ፡፡ በዓለም ላይ ፈራጆች ቢኖሩ እንኳ በጽድቅ የሚፈርድ በርትዕ የሚበይን እግዚአብሔር ብቻ ነው ፡፡ ፊት አይቶ ፣ ጉቦ በልቶ የማያደላ እርሱ የሰማይ አምላክ ነው ፡፡ ምስክር ሳይሰማ ፍርድን የሚሰጥ ፣ ልብ ያመላለሰውን ኩላሊት ያጤሰውን የሚያውቅ እርሱ ብቻ ነው ፡፡ ሰዎች አትፍረዱ የተባሉት ፍርድ የእግዚአብሔር ስለሆነ ነው ፡፡ መፍረድ እግዚአብሔርን ዙፋን አልባ ማድረግ ነው ፡፡ ደግሞም ሰዎች በሰዎች የሚፈርዱት የራሳቸውን ስህተት ለመሸፈን ነው ፡፡ አሊያም ለራሳቸው ምሕረትን ፣ ለሌሎች ፍርድን በመቁረሳቸው ራስ ወዳድ መሆናቸው ነው ፡፡ የእግዚአብሔር ፍርድ ግን የተለየ ነው ፡፡ የዘገየ ቢመስል የማያረፍድ ፣ ዝም ያለ ቢመስልም የሚገደው ፈራጅ ነው ፡፡ እግዚአብሔር አንድ ነው ስንል በፍርድም አንድ ነው ፡፡ ስለዚህ አብ ፈራጅ እንደሆነ ወልድም ፈራጅ ነው ፡፡
አብን ባለመታየቱና በልዕልናው ሰዎች ሁሉ አክብረውታል ፡፡ ወልድ በመታየቱና በትሕትናው ደግሞ ሰዎች ሁሉ ንቀውታል ፡፡ ነገር ግን አብን ማክበር ማለት ወልድን ሲያከብሩ የሚገኝ አምልኮት ነው ፡፡ አብን ማክበር ማለት አንቱ ብሎ መጥራት ወይም እንደ ምድራዊ ከበሬታ ያለ አይደለም ፡፡ አብን ማክበር አብን ማምለክ ነው ፡፡ አብ አምልኮትን የሚካፈለው ከወልድ ጋር ነውና ወልድን አለማክበር አብንም አለማክበር ነው ፡፡ ስለዚህ አብ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠ ፡፡ የዘላለም ሕይወት ወልድን በማመንና ባለማመን የተመሠረተ ሆነ ፡፡ እግዚአብሔር ልዑል እግዚአብሔር ትሑት ፣ እግዚአብሔር የአርያሙ እግዚአብሔር የበረቱ ፣ እግዚአብሔር ባለመንበሩ እግዚአብሔር ባለመስቀሉ ብሎ የማያምን የዘላለም ሕይወትን አያገኝም ፡፡ የዘላለም ሕይወት እግዚአብሔርን ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን አዳኝ ብሎ ማመንም ይጠይቃል ፡፡
መጽሐፍ በወልድ ያመነ የዘላለም ሕይወት አለው ብሎ ሲናገር የማያምን ደግሞ አሁን እንደ ተፈረደበት ይናገራል /ዮሐ. 3፡16-18፤ ሮሜ. 8፡1/ ፡፡ መንግሥተ ሰማያት በመካከላችን እንደ ሆነች ሲኦልም በመካከላችን ናት ፡፡ መንግሥተ ሰማያት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንደሆነ ሁሉ ገሃነመ እሳት ማለትም ያለ እግዚአብሔር መኖር ነው ፡፡ ሰዎች አብን የሚያከብሩበት ክብር እውነተኛ የሚሆነው የወልድን ትሕትና አይተው እንደ ሰብአ ሰገል ሲሰግዱ ነው ፡፡ በኃይሉ ብቻ ሳይሆን በፍቅሩም ሲያምኑ ነው ፡፡ እንደዚህ ማመን የሚያስፈልጋቸው በሕይወታቸው ከፍቅር የበለጠ መሣሪያ እንዳይጠቀሙ ነው ፡፡ ሰው የሚኖረው የሚያምነውን ነውና ፡፡
ጌታችን ይህን ቃል እየተናገረ ያለው አምላክነቱን መቀበል ላቃታቸው ለአይሁድ ነው ፡፡ ለማይቀበሉት ይህን ያህል እንዴት ይናገራል ? ስንል ለአብ ተቆርቁረው ልጁን መግፋታቸውን እንዲገነዘቡት ነው ፡፡ አብ በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር የማፈቅረው ልጄ ይህ ነው እርሱን ስሙት ብሏል ፡፡ የአብ ቃሉ ነውና ወልድን መስማት አብን መስማት ነው ፡፡ በቀላል ምሳሌ ብንጠቀም አንድ መንግሥት አምባሳደሩን አልቀበልም ቢሉት አምባሳደሩን እንጂ እኔን አልቀበልም አላሉም አይልም ፡፡ ሙሉ በሙሉ እኔን አልተቀበሉኝም ብሎ ውሳኔ ይሰጣል ፡፡ አምባሳደር ላይ ክፋትና ጥፋት ለማድረስ የሚሞክር ማንም የለም ፡፡ አምባሳደር የመንግሥቱ ቃል ነው ፡፡ እንኳን ወልድን አገልጋዮቹን አለመቀበልም እግዚአብሔርን አለመቀበል ነው ፡፡ ጌታችን ይህን ሲናገር ፡-  “እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል” ብሏል /ማቴ. 10፡40/፡፡ እንኳን መግፋት አይደለም ምን እንደምናቀርብላቸውም ያያል ፡፡ ለቀዝቃዛ ውኃም ዋጋ ይከፍላል ፡፡
አብ ፍርድን ሁሉ ለወልድ መስጠቱ አስገራሚ አይደለም ፡፡ ወልድም ለአገልጋዮቹ ፍርድን ሁሉ ሰጥቷል ፡፡ ኤልያስ ሰማይ ጠልን ፣ ምድር ዘርን እንዳትሰጥ ገዝቷል /1ነገሥ17፡1/፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስም በምድር ያሰረው በሰማይ የታሰረ እንደሆነ ተነግሮታል /ማቴ. 16፡18/ ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስም በምድር ላይ በሚስማማው እግዚአብሔር በሰማይ እንደሚያጸድቀው ተናግሯል /ማቴ. 18፡19/ ፡፡ ሐዋርያትም እኛና መንፈስ ቅዱስ ወስነናል ብለዋል /የሐዋ. 15፡29/ ፡፡ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችሁላቸው ይቅር ተብሎላቸዋል በማለትም ሥልጣንን ሰጥቷል /ዮሐ. 20፡23/፡፡ እግዚአብሔር አዳምን ሲፈጥረው በምሳሌው ፈጥሮታል ፡፡ ምሳሌ ማለት ምስለኔ ልክ እንደ እኔ ወይም እንደራሴ ማለት ነው ፡፡ ታዲያ አብ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጠው ሲል አብ ሰጪ ወልድ ተቀባይ ሁኖ ሳይሆን ወልድን አለመቀበል አብን አለመቀበል እንደሆነ ፤ ክርስቶስ የጽድቅም የኩነኔም አንቀጽ መሆኑን የሚገልጥ ነው ፡፡
ሰዎች ሁሉ የተለማመዱት አንድ ክብር አለ ፡፡ የማይታየውን ፣ በልዕልናና በርቀት ያለውን ማክበር ሰዎች ሁሉ የለመዱት ክብር ነው ፡፡ ይህ ክብር ግን እውነተኛ እንዳልሆነ እያየን ነው ፡፡ እግዚአብሔር እጅግ ከፍ ያለ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር እጅግ የቀረበም ነው ፡፡ እርሱ ፈራጅ ብቻ ሳይሆን እርሱ አፍቃሪም ነው ፡፡ የብሉይ ኪዳን ጠባዩ ጭካኔ ፣ የአዲስ ኪዳን ጠባዩ ርኅራኄ ሳይሆን ሁልጊዜም መሐሪና ጻድቅ ነው ፡፡ እኛም በርቀት ያሉትን ስናከብር በቅርበት ያሉትን እየናቅን ይሆን ? የክብር መለኪያ ቅርበትና ርቀት ሳይሆን እውነት ነው ፡፡ በአጠገባችን ያሉትን ፣ ዝቅ ብለው የሚያናግሩንን እየኮነንን በርቀትና በገደብ ያሉትን እያከበርን ይሆን ? “የቅርብ ጠበል ልጥ መንከሪያ ይሆናል” እንደሚባለው ቅርቡን መናቅ ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል ፡፡ የቅርቡን ቅዱስ መናቅ የሩቁን ቅዱስ ማክበራችን ውሸት መሆኑን ያሳያል ፡፡ የቅርቡን አባት መግፋት የሩቁን አባት መሳባችን ሐሰተኛ መሆኑን ያወራብናል ፡፡ በሕይወት ያሉትን ጻድቃን እየገደልን የሞቱትን እናዘክራለን ብንል ሐሰተኞች ነን ፡፡
በርቀት ያሉ ክብር ሲመጣላቸው ያ ክብር በቅርበት ላለው እንደ ተሰጠ መጠየቅ አለባቸው ፡፡ የሚያውቀውንና የሚያየውን ትቶ የማያውቀውንና የማያየውን አከብራለሁ ቢል ሐሰተኛ ነው ፡፡ ሰውን ማየት በሰው ነውና እውነተኞች ክብር አቅራቢዎቻቸው እዚያ ጋ ሌላውን ንቀው እንዳልመጡ እርግጠኛ መሆን አለባቸው ፡፡ ጌታችንም እኛን በሰዎች ያየናል ፡፡ “ማንም፡- እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?” /1ዮሐ. 4፡20/፡፡ እግዚአብሔር አብ እንኳን በልጁ በወንድማችንም ይለካናል፡፡ የማይታየውን እግዚአብሔር መውደዳችን የሚታየውን ወንድማችንን በመውደዳችን ይመዘናል ፡፡ ሰንሰለቱ በአብና በወልድ ፤ በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል ጽኑ ነው ፡፡ ይህን ሰንሰለት የሚቆርጥ እምነትና ፍቅር ከንቱ ነው ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ