“አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና” /ዮሐ. 5፡26/፡፡
ጌታችን የመጻጉዕን መፈወስ ተከትሎ አይሁድ ላነሡት ተቃውሞና ጥያቄ የሰጠው መልስ ምሥጢረ ሥላሴን የሚያብራራ ነው ፡፡ አይሁድ የአንድ ገጽ ወይም የአንድ አካል አማኞች ናቸው ፡፡ እግዚአብሔር አንድ ነው ሲሉ አንድ አካልም ነው ማለታቸው ነው ፡፡ እኛ ግን እግዚአብሔር አንድ ነው ስንል ሦስት አካላት እንዳሉት በማመን ነው ፡፡ ስለዚህ አንድ ነው ስንል ከአይሁድ ፣ ሦስት ነው ስንል ብዙ አማልክትን ከሚከተሉ አሕዛብ እንለያለን ፡፡ አይሁድ ቢጠይቁም ጥያቄአቸው ለማወቅ የሆነ የትሕትና አልነበረም ፡፡ ጌታ ግን የመለሰላቸው በትሕትና ነው ፡፡ እግዚአብሔር አንድ ገጽ ወይም አንድ አካል ብቻ ሳይሆን ሦስት አካላት እንዳሉትም እየገለጠ ነው፡፡ ጌታችንን መቀበል የከበዳቸው ሥላሴን መቀበል ባለመቻላቸው ነው ፡፡ ስለዚህ ጌታችን እግዚአብሔር ከአንድ በላይ የሆኑ አካላት እንዳሉት ይገልጥና እነዚህ አካላት ደግሞ በአንድነት እንዴት እንደ ተገለጹ ያስረዳል ፡፡ አይሁድ መልሱን ባይቀበሉም ለእኛ ግን ምሥጢረ ሥላሴን ለማደላደል ጠቅሞናል ፡፡ አይሁድ የማያርፉበትን ጥያቄ ጠየቁ ፡፡ በቀራንዮም የማይበሉትን በግ አረዱ፡፡ ጌታችን እግዚአብሔር ከአንድ በላይ የሆኑ አካላት እንዳሉት እኔና አባቴ በማለት ሲገልጽ ሥላሴ አንድ የሚሆኑበትን ምሥጢርም ተናግሯል ፡፡
ጌታችን በዚህ ምዕራፍ ውስጥ በሥላሴ መንግሥት አካላት ልዩ መሆናቸውን አካላትን ደግሞ አንድ ስለሚያደርገው ህላዌ ፣ ህልውናና ፈቃድ እያስተማረ ነው ፡፡ እግዚአብሔር አባቴ ነው ማለቱም እኛ እግዚአብሔርን አባታችን ከምንልበት ጥሪ የተለየ ነው ፡፡ ከብርሃን የተገኘ ብርሃን ከእውነተኛ አምላክ የተገኘ አምላክ መሆኑን መናገሩ ነው ፡፡ ወልድ ከአብ መወለዱ አብን መስሎና አህሎ ነውና ፡፡ ይህ ንግግሩ አይሁድን ገብቷቸዋል ፡፡ አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም እሠራለሁ ያለውን ስናስብ በአብና በወልድ መካከል አንዲት መለኮታዊ ግብር እንዳለች ያሳያል ፡፡ ይህ መለኮታዊ ግብርም የቆመበት ጊዜ የለም ፡፡ እርሱ ከአባቱ ጋር የተካከለ ብቻ ሳይሆን አንድ የሆነም ነው ፡፡ የክብርና የዕድሜ ብልጫ የለውም ፡፡ በግብር ስያሜ አብ ወላዲ ወልድ ተወላዲ ስንል በምድር ላይ እንዳለው እንደ አባትና ልጅ አይደለም ፡፡ በኩነት ስያሜም አብ ልብ ፣ ወልድ ቃል ስንልም በእኛ ውስጥ እንዳለው ዝርው አሳብና ቃል ማለታችን አይደለም ፡፡ እግዚአብሔር ምድራዊ ምሳሌ የማይገልጠው ክብርና አኗኗር አለው ፡፡ ጌታችን ተአምራትን የሚያደርገው ስመ እግዚአብሔርን ጠርቶ ወይም በእግዚአብሔር ተማምኖ ሳይሆን እግዚአብሔር ሁኖ ነው ፡፡ የአብ ክሂልና ሥልጣን የእርሱም ክሂልና ሥልጣን ነው ፡፡ ያ ባይሆን ኑሮ መዳናችን ፍጻሜ አያገኝም ነበር ፡፡ ምክንያቱም በፍጡር ዓለም መዳን አይችልምና ፡፡ በፍጡር የሚምንም ርጉም ይሁን ተብሏልና እኛም በእርሱ በማመናችን ርጉማን በሆንን ነበር ፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ በፍጡር ማመን ጣኦት ማምለክ ነው ፡፡ ስለዚህ ክርስቲያንነት ጣኦት አምላኪነት በሆነ ነበር ፡፡ የጌታችንን አምላክነት የምንቀበለው መዳናችንን እውነተኛ ክርስትናችንንም ክቡር ለማድረግ ነው ፡፡ ነገር ግን ሰው በሆነው ቃል መዳናችን ተፈጸመ ፡፡
በአብና በወልድ መካከል ወይም በአካላተ ሥላሴ መካከል ያለውን አንድነት በዚህ ክፍል ላይ በሚገባ ገልጧል ፡፡ አካላት ለምን እንደማይጨፈለቁ መለኮትም ለምን እንደማይበተን አስረድቷል ፡፡ ሦስቱ አካላት ፡-
በመለኮታዊ ግብር አንድ ናቸው ፡፡ የአካላት ግብር ሦስት ሲሆን የመለኮት ግብር ግን አንድ ነው ፡፡ የአካላት ግብር ውስጣዊ ሲሆን የመለኮት ግብር ግን አፍአዊ ነው ፡፡ አፍአዊ ማለታችን ለፍጡር ያለውን ቸርነት የሚገልጥበት ነው ፡፡ ስለዚህ ወልድ ከአብ የተወለደው በውስጣዊ ግብር ነው ፡፡ በዚህም አብን ፣ አብ አሰኝቶታል ፡፡ የእኛ ልጅነት ግን አፍአዊ ነው ፡፡ ስለዚህ ከሥላሴ ተወልደናል ማለት ነው ፡፡ የእኛ ልጅነት አብን ፣ አብ አያሰኘውም ፡፡ የመለኮት ግብር መፍጠር ፣ ማዳን ፣ በቸርነት መቀበል ነው ፡፡ ይህ ተግባር ከሦስቱ አካላት በአንዱ ቢፈጸም በአንድነት የሠሩት በመሆኑ ይጠሩበታል ፡፡ ይህ ዓለም የተፈጠረው በወልድ ነው ፡፡ አብና መንፈስ ቅዱስ ፈጣሪ የተሰኙትም በዚህ አንድ የመለኮት ግብር ነው ፡፡ የሞተልንና ቤዛ የሆነልን ወልድ ነው ፡፡ መሞቱ በተለየ አካሉ በለበሰው ሥጋ ነው ፡፡ ማዳኑ ግን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በሚጋራው በአንድ መለኮታዊ ግብሩ ነው ፡፡ ስለዚህ በወልድ ቤዛነት አብና መንፈስ ቅዱስም አዳኝ ይባላሉ ፡፡ ወልድ በለበሰው ሥጋ በመሞቱ አብ ዓለምን አፈቀረ የተባለው ለዚህ ነው /ዮሐ. 3፡16/፡፡
እግዚአብሔር አብ ወልድን የሚወድበት ፍቅር መለኪያ የለውም ፡፡ የዘመን ጅማሬና ፍጻሜም የለውም ፡፡ ይህ የማይነገር ፍቅር ስላለ ነው አብ ላኪ ፣ ወልድ ተላኪ በመሆኑ መበላለጥ የሌለው ፡፡ ሕይወትን መስጠትም የአንድነታቸው ግብር ስለሆነ አብም ወልድም ሕይወትን ይሰጣሉ ፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለች ሕይወት አንዲት ናት ፡፡ ይህች ሕይወትም መቅደምና መከታተል የሌላቸውንም አካላተ ሥላሴን ትገልጣለች ፡፡ ይህች ሕይወት ለፍጡር ስትሰጥ የሥላሴ ገንዘብ ናትና በአንዲት ፈቃድ በአንድ ሕይወትነቷ ትሰጣለች ፡፡ አብና ወልድ ሕይወትን በመስጠት አንድ ናቸው ፡፡ አሊያ አብ የሚሰጠው ሕይወት ወልድ የሚሰጠው ሕይወት ልዩ ልዩ በሆነ ነበር፡፡
ፍርድን መስጠትም የአንድነታቸው ግብር ነው ፡፡ በወልድ ማመን በአብ ማመን የሆነው በመለኮት አንድ ስለሆኑ ነው ፡፡ በወልድ አለማመንም በአብ አለማመን ነው ፡፡ በአብና በወልድ መካከል ያለው ግንኙነት ሰው በቃሉ ቢናገርበት ፣ በእጁ ቢሠራበት ፣ በክንድ ቢመክትበት ማለት ነው ፡፡ ቃልም ከልብ ፣ እጅም ከክንድ ፣ ክንድም ከአካል ሳይለዩ እንደሚሠሩ ሁሉ አብና ወልድም አልተለያዩም ፣ አይለያዩም ፡፡ ስለዚህ አብ ፍርድን ሁሉ ለወልድ መስጠቱ ሥጋ በለበሰው ወልድ አለማመን በአብም አለማመን ስለሆነ እንጂ አብ ፍርድን ስለከሰረ አይደለም ፡፡
ትንሣኤ መስጠትም የአንድነታቸው ግብር ነው ፡፡ በዚህ ምዕራፍ ላይ የኅሊና ፣ የልቡና ፣ የአካል እንዲሁም የመጨረሻው ቀን የሙታን ትንሣኤ ተገልጧል ፡፡ የኅሊና መንቃት ነው ፣ የልቡና ልጅነት ነው ፣ የአካል የመጻጉዕ መዳን ነው ፡፡ የመጨረሻው ቀን ትንሣኤ ደግሞ ለሁሉ የሚሰጥ ነው፡፡ ጌታችን የዕለት ሬሳን ወለተ ኢያኢሮስን ፣ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ፣ የሺህ ዓመት ሬሳን በትንሣኤ ዘጉባዔ ያስነሣል ፡፡ ይህ ማስነሣት ግን የመለኮት ግብር ነው ፡፡
“አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና” /ዮሐ. 5፡26/፡፡ ይህች ሕይወት ከሦስቱ አካላት አንዱ በጥገኝነት የሚያገኛት ሳትሆን በአንድነቷ አካላተ ሥላሴ የሚካፈሏት ናት ፡፡ “በራሱ” የሚለው ቃል ወሳኝ ነው ፡፡ ጥገኝነትን የሚያጠፋ ነው ፡፡ “ሰጥቶታል” የሚለውም እኛ ሕይወትን እንደ ተቀበልነው ዓይነት አይደለም፡፡ የአብና የወልድ ሕይወት አንድ መሆኗን የሚገልጥ ነው ፡፡ ለየራስ የሆነ ሕይወት ቢኖራቸው ኑሮ የዘመን መቀዳደም በኖረ ነበር ፡፡ የሥላሴን አካላት አንድ የሚያደርጋቸው ይህ መለኮታዊ ግብር ነው ፡፡ አካላተ ሥላሴን የሚያስተሳስራቸውም ይህ አንድ ህልውና ነው ፡፡ አብ በወልድ ወልድም በአብ ውስጥ መሆናቸው ነው ፡፡ ህላዌውም አንድ ነው ፡፡ አካላተ ሥላሴን ዘላለማዊ የሚያደርገው ይህ ህላዌ ነው ፡፡ ይህንና ሌሎችን ክፍሎች ለመረዳት ለአካላት የተነገረውን ለአካላት መተርጎም ፣ ለባሕርይ የተነገረውን ለባሕርይ መተርጎም ግድ ይላል ፡፡ ለአካላት የተነገረውን ለባሕርይ መተርጎም አንድ የሆነውን የሥላሴን ባሕርይ ይከፍላል ፡፡ ለባሕርይ የተነገረውንም ለአካላት መተርጎም አካላትን ይጠቀልላል ፡፡ ለምሳሌ፡- በዮሐ. 10፡30 “እኔና አብ አንድ ነን” ያለው ለመለኮታዊ አንድነት የተነገረ ነው ፡፡ ይህን ለአካል ብንተረጉም እግዚአብሔር አንድ ገጽ ፣ አንድ አካል ነው እንደሚሉት እንደ ሰባልዮሳውያን ወይም እንደ ኦንሊ ጂሰሶች ስህተት ውስጥ እንወድቃለን ፡፡ የብዙ ኑፋቄዎች መገኛውም ይህ ፍልሰት ነው ፡፡
አዎ የነገረ ምሥጢራት መገኛ ነገረ ድኅነት ፣ የነገረ ድኅነት መገኛው ነገረ ሥጋዌ ፣ የነገረ ሥጋዌ መነሻውም ነገረ ሥላሴ ነው ፡፡ ስለዚህ ክርስቲያን የሆነ አስቀድሞ ምሥጢረ ሥላሴን መማር ይገባዋል ፡፡