የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ትንሣኤ

“የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው። በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” /ዮሐ. 5፡27-29/ ።
ፍርድ የመለኮት የባሕርይ ገንዘቡ ነው ፡፡ በምድር ላይ ብዙ ፈራጆች ቢኖሩ እንኳ የውክልና እንጂ የባሕርያቸው አይደለም ፡፡ እግዚአብሔር ግን በባሕርዩ ጻድቅ ነውና ይፈርዳል ፡፡ በፍርድ ውስጥ ሽልማትና ቅጣት አሉ ፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ በሆነ ጊዜ ፍርድን ሁሉ ሰጠው ተባለ ፡፡ ምክንያቱም በተዋሕዶ ሥጋ የመለኮትን ሀብት ፣ መለኮትም የሥጋን ድህነት ገንዘብ ስላደረገ ነው ፡፡ ይልቁንም ቀዳማዊ አዳም በበደል ምክንያት ገዥነትን አጥቶ የምድር ገዥነቱን ለሰይጣን አሳልፎ ሰጥቶ ነበረ ፡፡ ሰይጣንም የምድር ገዥ ተብሎ ነበር /ዮሐ. 16፡11/፡፡ ጌታችን ግን ይህ ግዛት መመለሱን ከትንሣኤ በኋላ አረጋገጠ ፡- “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” አለ /ማቴ. 28፡18/፡፡ ቀዳማዊ አዳም ከበደል በፊት የምድር ገዥ ነበረ ፡፡ ከድኅነት በኋላ ግን የሰማይም ገዥ ሆነ ፡፡ ከበደል በፊት አራዊት እንስሳትን ይገዛ ነበር ፡፡ ከበደል በኋላ ግን በርኩሳን መናፍስትና በደዌያት ላይ ሥልጣን ተሰጠው ፡፡ በክርስቶስ ያገኘው ካሣ ቀድሞ ከመበደሉ በፊት ያልነበረውን ሥልጣን ነው ፡፡ አዎ አብ አይታይም ፣ ታይቶም በማንንም አይፈርድም ፡፡ ስለዚህ ታይቶ መግዛትንና ታይቶ መፍረድን ለወልድ ሰጠው ፡፡ ጌታችን ይህን ቃል ለአይሁድ የሚናገረው በዳኛ ፊት እየተናገሩ እንዳለ ተገንዝበው ለቃላቸው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ነው ፡፡ እርሱ በመጻጉዕ ደዌ ላይ ፈረደ ፡፡ ያሰረውን በሽታ አሰረው ፡፡ መንፈሳቸው የታሰረውንም በቃሉ ሊፈታቸው ፈቀደ ፡፡
ጌታችን በመጻጉዕ ፈውስ ምክንያት በተነሣው ተቃውሞ ስለ ሙታን ትንሣኤ እየተናገረ ያለው ለምንድነው ስንል ያ በሽተኛ ከሠላሳ ስምንት ዓመት በሽታው መፈወሱ እግዚአብሔር ሙታነ ኅሊናን በቃሉ ፣ ሙታነ ሥጋን በአዋጅ ድምፁ እንደሚያስነሣ ትልቅ ምልክት ነው ፡፡ ጤነኛ ሰው እንኳ አልጋውን ተሸክሞ ላይሄድ ይችላል ፡፡ ይህ በሽተኛ ግን ሲፈወስ አልጋውን ተሸክሞ መሄዱ ፈውሱ ከጤንነት አቅሙ በላይ መሆኑን ያሳያል ፡፡ በትንሣኤ የምንቀበለው አዲሱ አካልም እንዲሁ የታደሰና እርጅና የማይገጥመው የኃጢአት ተግባር ብቻ ሳይሆን አሳብም የሌለው ንጹሕ ልብስ ነው ፡፡ ዛሬ ተነሣሁ ስንል መልሰን በመውደቅ ፣ ተቀደስሁ ስንል መልሰን በመርከስ እናዝናለን ፡፡ ያ አካል ግን የእግዚአብሔር ልጅን የምንመስልበት ፣ በደልና ንስሐ የሌለበት ነው ፡፡ ዛሬ ግን እንደ መነቸከ ልብስ በጥቂቱ እየጸዳን እንኖራለን ፣ ያን አካል ስንለብስ ግን ፍጹም ክርስቶስን በቅድስና እንመስላለን ፡፡ እስከዚያው ድረስ ጽድቅን እያሰብን ኃጢአትን በመርገጣችን እናዝናለን ፡፡ ቆምን ስንል በመውደቃችን እንቃትታለን ፡፡ ትንሣኤ ሙታን የተዘጋጀው ይህንን የደቀቀ ስሜት ለመጠገንም ነው ፡፡
 “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” /ዮሐ. 5፡28-29/ ። በዚህ ክፍል ውስጥ ብዙ ዓይነት ትንሣኤ እንዳለ ተገልጧል ፡፡ በአጠቃላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ትንሣኤዎች ፡-
1-  የኅሊና ትንሣኤ ፡-
ኃጢአት ኅሊናን የመግደል አቅም አለው ፡፡ ሰው እስከ ተወሰነ ርቀት ድረስ ኅሊናው ይወቅሰዋል ፡፡ ኃጢአትን በደጋገመ ቁጥር ግን ኅሊናው እየሞተ ይመጣልና ውስጣዊ ወቀሳ አይሰማውም ፡፡ ኅሊናን ሁልጊዜ መለኪያ ማድረግ ተገቢ አይደለም ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ኅሊና ከግፍ ጋር ይተባበራል፡፡ ኅሊና ዝም አይልም የሚባለው እስከ ተወሰነ ርቀት ነው ፡፡ ኅሊና ዝም የማይለው በሕመም ዘመኑ ነው ፡፡ ሕመም ወደ ሞት ያደርሳልና ኅሊና ሲሞት ዝም ይላል ፡፡ ይህ ጊዜ ከባድ ነው ፡፡ ምክንያቱም እንደ ፈርዖን ልባችን ደንድኖ ለቅጣት የሚያመቻቸን ጊዜ ሊሆን ይችላል ፡፡ ጌታችን የኅሊና ትንሣኤን በቃሉ ይሰጣል ፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኛ ሲመጣ በክፉ ሥራችን ሕመም ይሰማናል ፡፡ ሰው በሕይወት ከሚቆይባቸው ነገሮች አንዱ የሕመም ስሜት ነው ፡፡ የሕመም ስሜት ማጣት ለከባድ አደጋ የሚያጋልጥ በሽታ ነው ፡፡ የሕመም ስሜት ከሌለን አእምሮአችን ስለሚደርስብን ችግር መልእክት ስለማይደርሰው እርዳታ ሊልክልን አይችልም ፡፡ ቃሉ የሕመም ስሜት እንዲሰማንና ላለፈው ንስሐ ለሚመጣው ረድኤት እንድናገኝ ያደርገናል ፡፡
2-  የልቡና ትንሣኤ ፡-
ትንሣኤ ልቡና በእምነት የምናገኘው ልጅነትን የሚያሳይ ነው ፡፡ ከትንሣኤ ኅሊና ቀጥሎ ትንሣኤ ልቡና እናገኛለን ፡፡ በትንሣኤ ኅሊና ስህተታችንን ማመን ሲሆን በትንሣኤ ልቡና የሚያድነንን ክርስቶስ እናምናለን ፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነትም በልጅነት ላይ የተመሠረተ ነው ፡፡ ይህ ልጅነትም ማፈርንና ፍርሃትን የሚያስጥለውን ፍጹሙን ፍቅር ይሰጠናል ፡፡ እግዚአብሔርን አባ አባት ብለን ለመቅረብና ለመጥራት ያስችለናል ፡፡ ይህ ልጅነት ከሌለ እግዚአብሔርን እየፈራን እንርቃለን ፡፡ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚባለው እግዚአብሔርን መቅረብ እንጂ መራቅ አይደለም ፡፡ አጋንንም ይፈራሉ ፣ ይንቀጠቀጣሉ ፡፡ ባሪያም ጌታን ይፈራል ፣ ያፍራል ፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች ፍርሃት ግን ከዚህ ይለያል /ሮሜ 8፡15፤ ያዕ. 2፡19፤ 2ጢሞ. 1፡7/፡፡
3-  የሥጋ ትንሣኤ ፡-
ይህ በተአምራት መንገድ የሚፈጸም ነው ፡፡ ኤልያስ የሰራፕታ መበለት ልጅን ፣ ኤልሳዕ የሱነም ሴት የሆነችውን ልጅ ከሞት አስነሥተዋል ፡፡ ጌታችም የዕለት ሬሳ ወለተ ኢያኢሮስን ፣ የአራት ቀን ሬሳ አልዓዛርን ከሞት አስነሥቷል ፡፡ እነዚህ ሙታን በሥጋ ቢነሡም የፊተኛ ኑሮአቸውን ለመቀጠል ተነሥተዋል ፡፡ እንደ ገናም ሞተዋል ፡፡ ለዚህ ትንሣኤ መሠረቱ ተአምራት ነው ፡፡
4-  ፊተኛው ትንሣኤ ፡-
ይህ ፊተኛ ትንሣኤ ከዋናው ትንሣኤ በፊት የሆነ ለእስራኤል ዓላማ ያለው ትንሣኤ ነው ፡፡ ይህ ትንሣኤ በቀዳማዊ አዳም መውደቅ ምክንያት ተሰናክሎ የነበረው የእግዚአብሔር እቅድ የሚፈጸምበት ነው /ራእ 20፡5-6/፡፡ በዚህ ትንሣኤ ላይ ዕድል ያላቸው የተወሰኑ ናቸው ፡፡ ይህ ትንሣኤ ልዩ የሚያደርገው ሁሉን የሚጠቀልል አለመሆኑ ነው ፡፡
5-  የሙታን ትንሣኤ ፡-
 ይህ ትንሣኤ ከአቤል ጀምሮ እስከ መጨረሻ ቀን ድረስ ያሉ የሰው ዘሮች የሚነሡበትና ፍርድን የሚቀበሉበት ታላቅ ቀጠሮ ነው ፡፡ ይህ ትንሣኤ ጻድቃንን ለክብር ፣ ኃጥአንን ለሐሳር የሚያበቃ ትንሣኤ ነው ፡፡ ትንሣኤ ሙታን የሚጠቅመው ትንሣኤ ልቡና ላገኙ ነው ፡፡ ትንሣኤ ልቡና የሌላቸው በዚህ ትንሣኤ ፍርድን ይቀበላሉ ፡፡ ከሃይማኖት አእማድ አንዱ ትንሣኤ ሙታንን ማመን ነው ፡፡ ትንሣኤ እንዳለን ማመን ክርስቶስ እንደ ተነሣ ማመን ነው ፡፡ ትንሣኤ ሙታን ብዙ ዓላማዎች ቢኖሩትም ዋነኛው ሁሉም ዋጋውን የሚቀበልበት አደባባይ መሆኑ ነው ፡፡
በትንሣኤ ሙታን በግርማው የሚመጣውን ጌታ አይሁድ አሁን በአጭር ቁመት ፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ አዩት ፡፡ ጌታችን ለአይሁድ እያስተላለፈው ያለው መልእክት ዛሬ በምሕረት ካላገኛችሁኝ ነገ በፍርድ አገኛችኋለሁ ፣ ምሕረት ፈቃደኝነትን ይጠይቃል ፤ ፍርድ ግን በእኔ ሥልጣን ይከናወናል እያላቸው ነው ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ