የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሚበልጥ ምስክር

“እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል ። እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም ፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ ። እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ ፥ ይህ የማደርገው ሥራ ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና።” /ዮሐ. 5፡33-36/
ከተማ ከሚያውደለድል ይልቅ በረሃ የገባ ሰው ሹሞችን ያስደነግጣል ፡፡ ዮሐንስ መጥምቅም የአባቱ የዘካርያስን ቦታ የሊቀ ካህንነትን መዐርግ ትቶ በበረሃ መቀመጡ የአይሁድን አለቆች አሳስቧቸዋል ፡፡ ከእኛ ርቆ የእኛን ችግር እንዴት ሊያውቅ ይችላል እንዳይሉ ክርስቶስ ሰርግ እየተጠራ ፣ ልቅሶ እየደረሰ መጣ ፡፡ እንዴት እኛ የምንበላውን እየበላ እኛ በምንኖርበት እየኖረ እንዳይሉና እንዳያቃልሉ ዮሐንስ መጥምቅ ከምድረ በዳ መጣ ፡፡ ሰውን ምክንያት የለሽ አድርጎ ሊያድነው ስለ ፈቀደ ጌታችን በከተማ ፣ ዮሐንስ በምድረ በዳ አስተማሩ ፡፡ የመጀመሪያው ፍርድና ቁጣ የመጣው በምክንያት ነውና ከምክንያት ሊያድነን ይህን አለ ፡፡ የአይሁድ አለቆችና ሹማምንት ዮሐንስ ዘንድ መልእክተኛ ልከው ነበር ፡፡ እርሱ ግን ስለ እውነት ተናገረ ፡፡ ዮሐንስ የተናገረው እውነት ምንድነው?
·       የሊቃነ ካህናት የቅምጥልቅ ኑሮ ይብቃ ፡፡
·       የፈሪሳውያን ማስመሰል ፣ ዘመን ያለፈበት ነው ፡፡
·       የሮማውያን ግፍ እስከ መቼ ይቀጥላል ?
·       የጭቁኖች መብት መከበር አለበት ፡፡
እነዚህ ሁሉ የዚያ ዘመን እውነት ናቸው ፡፡ ዮሐንስ ግን የመሰከረው ኢየሱስ ክርስቶስ እውነት መሆኑን ነው ፡፡ ብዙ ሰዎች እውነት ምንድነው ? በሚል ጥያቄ ተወጥረናል በማለት ይናገራሉ ፡፡ እውነት መልስ ያላገኘ ጉዳይ ነው ይላሉ ፡፡ ለዚህም ጲላጦስ “እውነት ምንድርነው?” በማለት ጠይቋል /ዮሐ. 18፡38/ ፡፡ ይህ ጥያቄ ዛሬም እንደ ቀጠለ ነው ፡፡ እውነት ማለት አንጻራዊ ነው ፡፡ ያንተ እውነት ላንተ ፣ የእኔ እውነት ለእኔ እውነት ነው ይላሉ ፡፡ ሕይወት ያለ እግዚአብሔር የማያባራ ጥያቄ ናት ፡፡ እግዚአብሔር ስለ እውነት የሚናገር ሳይሆን ራሱ እውነት ነው ፡፡ ዮሐንስ የመሰከረው እውነትም ክርስቶስ ነው ፡፡ የጌታችን ስሙም መታወቂያውም እውነት የሚል ነው ፡፡
አዎ ጲላጦስ እውነት ምንድርነው ? ያለው ስለ እውነት ተጨንቆ አልነበረም ፡፡ የእውነት አሰሳ ያደከመው ሰውም አይደለም ፡፡ ያ ቢሆን ኑሮ ንጹሑን ክርስቶስ ለሞት አሳልፎ መስጠት አልነበረበትም ፡፡ እውነትን እየቀበሩ እውነት ምንድነው ? ማለት በፈላስፋ ሒሳብ ለመታሰብ ከመፈለግ ያለፈ አይደለም ፡፡ ዛሬም እውነት ምንድርነው ? የሚሉና እውነት አንጻራዊ ነው በማለት የሚናገሩ ሰዎች አጠገባቸው ያለውን ጉድለት ላለመሙላት በዚህ የስንፍና ንግግር ይያዛሉ ፡፡
ጌታችን በዮሐንስ ምስክርነት ኮርቶ መናገሩ አልነበረም ፡፡ ምክንያቱም እርሱ ከባሕርይ አባቱ በአደባባይ ምስክርነትን ተቀብሏልና ፡፡ ነገር ግን ይድኑ ዘንድ ሁሉንም መንገዶች እያሳያቸው ነው ፡፡ መንገዶቹ ሁሉ ግን ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ ናቸው ፡፡ ሰዎች ሁሉ ይድኑ ዘንድ የእርሱ መልካም ፈቃድ ነው ፡፡ ጌታችን የሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛን ለማዳን ደቂቃዎች አልፈጁበትም ፡፡ የነፍስ በሽተኞችን ለማዳን ግን ብዙ ግብግብ ገጠመው ፡፡ ምክንያቱም ሰዎች በሥጋ ሲታመሙ አሞኛል ይላሉ ፡፡ የነፍስ በሽታቸውን ግን አያውቁትም ፣ አይረዱትም ፡፡ አንዱ የእውቀት መንገድ ሁኖ ይሰማቸዋል እንጂ በጨለማ ግዛት እንዳሉ አይገነዘቡም ፡፡
እግዚአብሔር ጸጋውን የሚያስታጥቀው ቆርጦ ለወጣው የእምነት ወታደር ነው ፡፡ ሰይጣንም የሚፈራው የሚፎክረውን ሳይሆን የቆረጠውን አማኝ ነው ፡፡ ፉከራ ምን ማለት መሆኑን ትልቁ ፎካሪ ሰይጣን በራሱ ያውቀዋል ፡፡ ስለዚህ ዮሐንስ ቆርጦ ዓለምን በመናቁና በምድረ በዳ በመቀመጡ የአይሁድ ትልቅ ሸንጎ ሰው በመምረጥ እንዲያናግረው ወሰነ ፡፡ ይህ ውሳኔ በዓለሙ ሁሉ የተሰማ ነበር ፡፡ ለካ በበረሃ ተቀምጦ ፣ የግመል ጠጉር ለብሶ አንበጣና ማር ተመግቦ ፣ ንግግርን ሰይፍ አድርጎ ማንቀጥቀጥ ይቻላል ? ለቆረጠ አማኝ እግዚአብሔር ጸጋውን ያፈስለታል ፣ ሰይጣንም ይፈራዋል ፡፡ እግዚአብሔር የሚያግዘው ምኞታችንን ሳይሆን ውሳኔአችንን ነው ፡፡ ጌታችን ስለ ዮሐንስ ሲናገር ፡- “እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ ።” አለ ፡፡ መንደድ በውስጥ መቃጠልና ዘይትን መጨረስ አለው ፡፡ መንደድ ግን እዚያ ለቆመው መብራት ነው ፡፡ አንዱ ይነዳል ፣ አንዱ ይበራለታል ፡፡ በርቶልን ከሆነ የነደዱልን አሉ ማለት ነው ፡፡ እየነደድን ከሆነ የሚበራላቸው አሉ ፡፡ መንደድ በሌለበት ማብራት የለም ፡፡ ማብራት የመንደድ ውጤት ነውና ፡፡ ዮሐንስ እውነትን ዋጋ ከፍሎ ያስተማረ ነው ፡፡ ዮሐንስ ወታደሮችን ፣ ነገሥታትን በግልጽ ሲገስጽ የአይሁድ ሊቃውንት የፈሩትን ስለ ደፈረላቸው ደስ ብሏቸዋል ፡፡
ሴትዬዋ ሰባኪው ስለ ሌብነት ሲያስተምር የጎረቤቷ ሌባ ልጅ ትዝ እያላት “በልልኝ ፣ ንገረው” ትላለች ፡፡ ሰባኪው መለስ ብሎ እርሷ የምትሠራውን ኃጢአት እየገሰጸ ሲያስተምር “ደሞ ጀመረው” አለች ይባላል፡፡ አይሁድም ነገሥታትን የሚነካውን የባሕታዊ ዮሐንስን ስብከት በልልኝ እያሉ ሰምተዋል ፡፡ እነርሱን የሚነካውን ሲናገር ግን ደሞ ጀመረው ብለዋል ፡፡ ለጥቂት ጊዜ በተግሣጹ ብርሃን ደስ ቢላቸውም ለዘለቄታው ግን ጠልተውታል፡፡ በዮሐንስ ላይ የነበራቸውን የወረት ፍቅር ጌታችን ነቀፈ ፡፡
 ስለ ጌታችን አልሰማሁም ማለት ከባድ ነው ፡፡ በሰማይ እግዚአብሔር አብ ፣ በምድር ዮሐንስ መጥምቅ መስክረውለታል ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ማዕከላዊ አሳብ ብቻ ሳይሆን የቅዱሳን ማዕከላዊ ርእሳቸው እርሱ ክርስቶስ ነው ፡፡ ጌታችንን ማዕከል ያላደረገ ስብከትም ሕይወትም አስጊ ነው ፡፡ በመቀጠል ጌታችን ፡- “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ ፥ ይህ የማደርገው ሥራ ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና።” አለ ፡፡ ጌታችን በንጉሣዊ ክብሩ አንጻር ወርዶ ማስረዳት አይጠበቅበትም ፡፡ እርሱ እንኳን በልዕልናው ሁኖ በትሕትና ወርዶ ቢናገረንም ልንረዳው አልቻልንም ፡፡ የአብ ምስክርነት ከሁሉ በላይ ነው ፡፡ ቅዱሳን ሁሉ ስለ ጌታችን ቢመሰክሩም የአብን ምስክርነት አያህልም ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የሚታወቀው በእግዚአብሔር ነውና አብ ስለ ወልድ የመሰከረው ሙሉ ነው ፡፡ ስለ ክርስቶስ ለማስረዳት ብዙ መጻሕፍትን ብንጠቅስም በዮርዳኖስና በደብረ ታቦር ከተሰማው ከአብ ምስክርነት አይበልጥም ፡፡ የምወደው ልጄ ነው እርሱን ስሙት ብሏል ፡፡ አባት ልጁን መውደዱ መነገር የማያስፈልገው ይመስለናል ፡፡ ነገር ግን የአብና የወልድ ፍቅር መግለጫ የሌለው ምሳሌ የማያስረዳው ነው ፡፡ ልጄን ስሙት የሚል አባት ብዙ የለም ፡፡ አብ ግን እኩያ ልጁን ስሙት አለ ፡፡ ስለዚህ ወልድን አለመስማት ስሙት ያለውን አብን መቃወም ነው ፡፡ ወልድን አለማመን አብን አለማመን የሆነው በዚህ ምክንያት ነው ፡፡
ጌታችን፡- “አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ ፥ ይህ የማደርገው ሥራ ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና።” አለ ፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነ ሥራ ማስረጃው ምን እንደሆነ እየተናገረ ነው ፡፡ ከእግዚአብሔር የሆነ ሥራ ፡-
1-  ከራስ የመጣ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ምክር የፈለቀ ነው ፡፡
2-  በጅምር የሚቀር ሳይሆን የሚፈጸም ሥራ ነው ፡፡
3-  ክብርን ሁሉ ለላከው የሚሰጥ እንጂ ምስጋናው መንገድ ላይ የሚቀርበት አይደለም ፡፡
ተግባራችን ከእግዚአብሔር የተሰጠን ሥራ እንደሆነ በዚህ መንገድ መፈተሽ ይቻላል ፡፡ የተሰጠን ተግባር አንዳንድ ጊዜ የእኛ ምኞት መሐል ላይ ይገባበታል ፡፡ ምልክቱ በትዕቢት መሞላት ፣ ለመታወቅ እንጂ ለሰዎች መዳን አለመጨነቅ ነው ፡፡
አብ ከላከው ሥራ አንዱ የመጻጉዕ መዳን መሆኑ ይገርማል ፡፡ እንደ ትኋን ከአልጋ ጋር የተጣበቀ ፣ ከኑሮ ይልቅ ምነው በሞተ የሚባል ፣ እንደገና እንደሚጀምር ተስፋ የተቆረጠበትን አባቱ አድን አለው ፡፡ ይህን ያህል ዝቅ ያለ ሰው ፣ ከቆሙት በታች ከሞቱት በላይ የሆነ ማንነት ፣ ከሰው ልብ የወጣ ፣ ስቃዩ የተለመደ ሰውን እግዚአብሔር ያስበዋል ፡፡ የመጻጉዕ ስለ ተጻፈልን ነው ፡፡ ያልተጻፈላቸው ብዙ ተፈዋሾች አሉ ፡፡ በእውነት እግዚአብሔር ማንንም አይንቅም ፡፡ እርሱ ለሁላችንም እቅድ አለው ፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ