የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ዐቢይ ርእስ ፣ ጭብጥ መልእክት

“የላከኝ አብም እርሱ ስለ እኔ መስክሮአል ። ድምፁን ከቶ አልሰማችሁም ፥ መልኩንም አላያችሁም ፤ እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም።” /ዮሐ. 5፡37-38/ ።
በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ላኪዎች አሉ ። ጌታ ባሪያውን ይልካል ። ጌታ ባሪያውን የሚልከው አክብሮ ሳይሆን ንቆ ሊሆን ይችላል ። በመካከላቸው የፍቅርም የክብርም ምክንያት ላይኖር ይችላል ። እንዲሁም አባት ልጁን ይልካል ። አባት ልጁን የሚልከው በዘመን ስለሚቀድም በክብር ስለሚበልጥ ነው ። በመካከላቸው ፍቅር ቢኖርም የክብርና የዘመን ብልጫ ግን አለ ። ንጉሥም አምባሳደሩን “እንደራሴ” አድርጎ ይልካል ። አምባሳደሩ የክብር መልእክተኛ ቢሆንም ፣ ከንጉሡ በዘመን አቻ ቢሆን አሁንም በክብር በትንሽ ይበላለጣሉ ። እግዚአብሔር አብ ግን ልጁን የላከው ፍቅርና ክብር እንደሌለው እንደ ባሪያ ፣ ፍቅር እንጂ የክብር እኩያነት እንደሌለው ልጅ ፣ ክብር እንጂ ፍቅር እንደሌለው እንደ አምባሳደር አይደለም ። እግዚአብሔር አብ በዘመንና በክብር የተካከለውን የፍቅር ልጁን ወደ ዓለም ላከ ። ዓለም እኩያነትን ያለ መታዘዝ ምክንያት አድርጋ ታቀርባለች ። እኩያነት መሐል መታዘዝ ካለ ምክንያቱ ፍቅር ብቻ ነው ። ይህንን በእግዚአብሔር አብና በእግዚአብሔር ወልድ አየን ። የአብ ላኪነት ፣ የወልድም ተላኪነት ልዩ ነው ። የተላከውን አልቀበልም ሲሉ ላኪው መጀመሪያ ይመሰክርለታል ፣ ቀጥሎ እንቢ ባዮችን ይቀጣል ።
የእግዚአብሔር አብን ድምፅ ሰምተዋል ፣ መልኩን ግን አላዩም ። ጌታ ግን ድምፁን አልሰማችሁም ፣ መልኩንም አላያችሁም እያላቸው ነው ። ምክንያቱም ድምፁ “ልጄን ስሙት” የሚል ነው ። የአብ ቃል ነውና ወልድን መስማት አብን መስማት ነው ። ወልድን ማየትም አብን ማየት ነው ። እርሱ በአብ ክብርና ሥልጣን ያለ ነውና ። ሰው ልጁን “መልኬ” ብሎ ቢሰይም ራሴን ይመስላል ማለቱ ነው ። ወልድም የአብ መልክ ነው ። እርሱ “እኔን ያየ አብን አየ” ሲል ስለ አካል አንድነት እየተናገረ አይደለም ፣ ምክንያቱም አብና ወልድ በአካል ልዩ ናቸውና ። የሥልጣንና የህልውና አንድነትን እየተናገረ ነው ። አብ የላከውን ክርስቶስን አለማመን የአብን ቃልና ድምፅ አለመቀበል ነው ። ትልቁ መልስ የሆነው ክርስቶስ ትልቅ ጥያቄ ሲሆን ክርስቶስ ተወለደ ብሎ መቆምና መስቀሉ ጋ አለመድረስ በእውነት ሥላሴን እንደ መካድ ነው ።
እግዚአብሔር አብ ስለ አብርሃም ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ፣ ለጌራራ ንጉሥ ለአቤሜሌክ ፣ ስለ ሙሴ ለአሮንና ለማርያም ደግሞም ለእስራኤል መስክሯል ። ስለ ልጁ የመሰከረው ምስክርነት ልዩ የሚያደርገው ምንድነው ስንል እኩያዬ ብሎ የመሰከረለት ፣ በቀኜ ተቀመጥ ብሎ በአንድ ዙፋን ያከበረው መሆኑ ነው ። ስለ ክርስቶስ ሐዋርያትም መስክረዋል ፣ ሰማዕታትም በቃልና በደም አትመዋል ። የእግዚአብሔር አብ ምስክርነት ልዩ የሚያደርገው በባሕርይ አባትነት የባሕርይ ልጄ ነው ብሎ መመስከሩ ነው ። ኢየሱስን ክርስቶስ ወይም ጌታ ብለው አማንያን መስክረዋል ፣ ልጄ ብሎ የመሰከረው ግን እግዚአብሔር አብ ነው ። የእግዚአብሔር ልጅ ነው ብለው ከመሰከሩት ይልቅ ልጄ ነው ብሎ የመሰከረው የአብ ምስክርነት ይበልጣል ። ምስክርነት የማየት ፣ የመስማት ውጤት ነው ። ሰው ስለ ቃሉ ቢመሰክር ግን ልዩ ምስክርነት ነው  ። እግዚአብሔር አብም ስለ ባሕርያዊ ቃሉ መሰከረ ። እግዚአብሔር አብ የመሰከረለትን ክርስቶስ ካልመሰከርንለት ከትልቅ ክብር እንጎድላለን ። እግዚአብሔር አብ የመሰከረለት ሊያከብረው ሳይሆን ክብሩን ለሌሎች ሊገልጥ ነው ። ምስክርነት የሚያግዘው ሰዎችን እንጂ ክርስቶስን አይደለም ። ነቢያትን በትንቢት ፣ አበው በተስፋ ፣ መላእክት በቤተ ልሔምና በጎልጎታ ፣ ሐዋርያት በአጽናፈ ዓለም የመሰከሩት ስለ ክርስቶስ ነው ። ሰማዕታት በደም ፣ ጻድቃን በገዳም የጸኑት ስለ ክርስቶስ ነው ። የመነኮሳት ቆባቸው የአክሊለ ሦኩ ምሳሌ ነው ። ካህናት በመቅደስ የሚያጌጡት በክርስቶስ ምሳሌዎች ነው ። አዎ ስለ እርሱ መመስከር ግድ ነው ። እርሱ ዛሬ በሐሰት ዓለም የመሰከሩለትን ፣ በእውነት አደባባይ ይመሰክርላቸዋል ፤ በሚያልፍ ዓለም ያፈሩበትን በማያልፈው ዓለም ያፍርባቸዋል ። እርሱ ዝቅ ብሎ “ወንድሞቼ” ብሎ ከመሰከረልን ፣ እኛ ቀና ብለን “ጌታ ነው” ብለን መመስከር ሊከብደን አይገባም ። ካሳፈረም ክርስቶስ በእኛ ቢያፍር ወጉ ነው ፣ ባላፈረብን ጌታ አናፍርም ።
እግዚአብሔር አብ ዝርዝር መመሪያዎችን ፣ ጥልቅ የነገረ መለኮት እውነታዎችን አልነገረንም ። ወደ ጥበብ ግምጃ ቤት ፣ ወደ እውቀት መዝገብ ወደ ክርስቶስ ብቻ እጁን ቀሰተልን ። “እርሱን ስሙት” አለ ። እርሱን ስሙት ሲል በዮርዳኖስ ለተሰለፉት ንስሐ ገቢዎች /ተነሣህያን/ አዳኛችሁ ነው ማለቱ ነው ። እርሱን ስሙት ሲል ለደብረ ታቦር እድምተኞች ምስክርነታቸውን ማለት “አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” የሚለውን ቃለ አሚን ሊያጸናላቸው ነው ። የእግዚአብሔር አብን ምስክርነት ተቀብለን ወደ ክርስቶስ ከመጣን የሰማይን ጓዳ እናያለን ። የሥላሴን ምሥጢር እንረዳለን ። ወደ ክርስቶስ መምጣት ብዙ ዋጋ አለው ። ጉዳቶች ሁሉ በክርስቶስ ይካሳሉ ፤ ክርስቶስን መክሰር ግን ካሣ የሌለው ጉዳት ነው ።
   “እርሱም የላከውን እናንተ አታምኑምና በእናንተ ዘንድ የሚኖር ቃሉ የላችሁም።” አለ ። ቃሉ ሀብት የሚሆነን ክርስቶስን ስናምን ነው ። በክርስቶስ ለማያምን ቃሉ ፍርድ ነው ። እግዚአብሔር አብ የመሰከረው ለግንዛቤ ማስጨበጫ ፣ አሊያም ለአእምሮ እብጠት አይደለም ። ለእምነት ነው ። ስናምንና በክርስቶስ ፍቅር ስንኖር የእግዚአብሔር ቃል የኅሊናችን ሀብት ሁኖ ይኖራል ። ቃሉ ግቡን ካጣ ግን ወደ መጣበት ይመለሳል ። መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የትርጓሜ መጻሕፍት ፣ መተርጉማን ሊቃውንት፣ መዝገበ ቃላት ፣ የዘመኑ ባሕልና ታሪክ አስፈላጊ ናቸው ። ቃሉን ለመረዳት ዋነኛው ቁልፍ ግን ሁለት ነው ። ክርስቶስና መታዘዝ ። የመጽሐፍ ቅዱስ ዐቢይ ርእስ ፣ ማዕከላዊ ጭብጥ ክርስቶስ ነው ። ያለ ማጠንጠኛው ሁሉም ነገር የተበተነ እንደሆነ ያለ ክርስቶስም መጽሐፍ ቅዱስ ብትን አሳብ ነው ። እንዲሁም ቃሉ የተሰጠን ለመታዘዝ ነውና ስንታዘዘው ይበልጥ እየገባን ይመጣል ።
ባሪያውን ሙሴን ያልሰሙ እነ ዳታንና አቤሮን መሬት ተከፍታ በቁም ወደ ሲኦል ካወረደቻቸው ክርስቶስን አለመስማትማ ቅጣቱ ምን ይሆን ? የአስታራቂነቱ ደም እስከ ምጽአት አደግድጎ ይቀበለናል ፤ ከምጽአት በኋላ ግን ፍርድ ይሆናል ። አዎ አንዱ ክርስቶስ የምሕረት ደም ያለው የፍርድ ቃልም ያለው ነው ። ዛሬ የምሕረት ዘመን ስለሆነ ስለ አስታራቂነቱ ይነገራል። እግዚአብሔር በሩን ከፍቶ ፍጥረቱን እየጠበቀ ነውና ። ስለ ፍርዱ ግን ስብከት ሳይሆን ብይን የሚተላለፍበት ቀን ይመጣል ። ዛሬ በደሙ ብንድን የኋላ ፍርዱ አያስፈራንም ። ደሙ ያስፈቅደናል ፣ ፍርዱ ግን ፈቃዳችንን አይፈልግም ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ