የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመጻሕፍት ምስክርነት

“እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው ፤ ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም።” /ዮሐ. 5፡39-40/ ።
አይሁድ የዘላለም ሕይወትን ይፈልጋሉ ፣ የሚፈልጉት ግን ያለ መንገዱ ነበር ። ሰዎች የዘላለም ሕይወትን በመንገዱ ይፈልጋሉ ፣ ይህ እምነት ነው። ያለ መንገዱ ይፈልጋሉ ፣ ይህ አለማወቅ ነው ። በራሳቸው መንገድ ይፈልጋሉ ፣ ይህ እልከኝነት ነው ። መፈለግ ከመንገዱ ጋር ካልተገናኘ አይጠቅምም ። ሰዎች እግዚአብሔር ለዘረጋው የመዳን መንገድ ግዴለሽ ሁነው በራሳቸው መንገድ ግን የዘላለም ሕይወትን ይፈልጋሉ ። ዋጋ የሚሰጡት እግዚአብሔር ላዘጋጀው መንገድ ሳይሆን እነርሱ ለሚከፍሉት ጥቂት ዋጋ ነው ። ከእኛ ፍቅር የእግዚአብሔር ፍቅር ፣ ከአገልግሎታችን እርሱ በሥጋ መጥቶ ማገልገሉ ፣ ከፍለጋችን እርሱ እኛን መፈለጉ ይበልጣል። አንድ ታማሚ መዳን ቢሻና በመረጠው መድኃኒት መዳን ቢፈልግ አይሆንም ። ያለ መድኃኒቱ ከበሽታው አይድንም ። ሐኪሙ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ያዘዘውን መድኃኒት በሽተኛው በመውሰዱ እንጂ በሽተኛው የምፈልገው መድኃኒት ይህንን ነው ማለቱን አይደለም ። አይሁድም በራሳቸው መንገድ መዳንን ይፈልጉ ነበር ።
በቤተ አሕዛብ የተነሡ ግኖስቲኮች የሚባሉ ወገኖች ነበሩ ። እነዚህ ሰዎች መዳን በእምነት ሳይሆን በእውቀት ነው ብለው ያስተምሩ ነበር። ክርስትናው በብሔረ አሕዛብ ለተነሣበት ትግል ዋነኛው ይህ የግኖስቲኮች አስተሳሰብ ነበር ። ብዙ በማወቅ ነፍስ ከሞት እንደምታመልጥ ያስቡ ነበር። እውቀት ሰውዬውን ማዕከል ያደረገ ሲሆን እምነት ግን እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ ነው ። ይህ በብሔረ አሕዛብ የነበረው አስተሳሰብ በአይሁድም ዘንድ በከፊል ታይቷል ። በመጻሕፍት እውቀትና ምርምር ብቻ የዘላለም ሕይወት እንዳላቸው ያስቡ ነበር ። መጻሕፍት ግን የዘላለም ሕይወት መንገዱን የሚያሳዩ ቀስት እንጂ ራሳቸው የዘላለም ሕይወት የሚሰጡ አልነበሩም። አይሁድ መጻሕፍት ላይ ቀርተዋል ። መጻሕፍት ላይ መቅረት ሊቅ ሲያደርግ መጻሕፍትን ሰምቶ መታዘዝ ግን አማኝ ያደርጋል ። አንድ መምህር የተሰጠው የትምህርት ዓይነት ላይ ይዘጋጃል ፣ ያነባል ፣ ያስተምራል ። የሚያስተምረው ትምህርት ግን ከሕይወቱ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድና የለውም ። ትምህርቱ በሕይወቱ ላይ ከእንጀራ በቀር ደስታና ዕረፍትን የሚያመጣ ላይሆን ይችላል ። አይሁድም መጻሕፍትን ለእውቀትና ለኑሮ እንጂ ለእምነት አልረዱአቸውም ነበር ። እምነት የሌለበት የመጻሕፍት እውቀት ስሜት አልባ ሕይወትን ያመጣል ። ሊቅ ተብሎ በሰው ዘንድ ለመከበር እንጂ በጌታ ፊት ሞገስ ለማግኘት አይረዳም ። አዋቂ ተብሎ ከሕይወት ከመቅረት አላዋቂ ተብሎ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የተሻለ ነው። እውቀት ያለ እምነት ደረቅ ነው ። ሥጋዊና መንፈሳዊ ፈውስን ሊያመጣ አይችልም ። እውቀት አልባ እምነት ተሳዳቢ ፣ እምነት አልባ እውቀት ትዕቢተኛ ያደርጋል ።
አይሁዳውያን ለዛሬ ንባብ አይደለም ለወደፊት ዓይናችን ደክሞ ማንበብ እንዳያቅተን ብለው ይጨነቃሉ ፣ ለዓይናቸውም ጥንቃቄ ያደርጋሉ ። ሲቀመጡ ፣ ሲቆሙ ፣ በመንገድ ሲሄዱ ያለማቋረጥ ያነባሉ ። በምናየው ነገር አስተያየት እንዳንሰጥና እግዚአብሔርን እንዳናሳዝን ብለውም እየጸለዩ ይጓዛሉ። ብሉይ ኪዳንን በንባብ የሚዘልቁት ገና በለጋ ዕድሜአቸው ሲሆን በትርጓሜ ደግሞ በዘመናቸው ሁሉ ያጠኑታል ። መጻሕፍት ግን ቀስት ናቸው ፣ ወደ ክርስቶስ ካላደረሱ ምልክትነታቸው ከንቱ ይሆናል ። አንድ ሰው ስለ አንድ መድኃኒት ምንነት በትክክል አውቆ መድኃኒቱን ካልወሰደ እንደማያድነው ሁሉ ፣ መጻሕፍትም ስለ ክርስቶስ የሚናገሩትን አውቆ በእርሱ ካላመኑ ሕይወት አይሰጡም ። የመጻሕፍቱም ልፋት ከንቱ ይሆናል ።
የአይሁዳውያን እውቀት አይጠረጠርም ። ጌታ የት እንደሚወለድ ለሄሮድስ ተናግረው ነበር ። እርሱ ለመግደል ሲሄድ እነርሱ ግን ለመስገድ አልሄዱም ። ለሚገድለው ሄሮድስ ሲናገሩ ለሚሰግዱለት ምእመናን ግን አልተናገሩም ። ትንቢቱን በቦታ ፣ ሱባዔውን በዘመን ቢያስተነትኑም ወደ ክርስቶስ ግን መድረስ አልቻሉም ። በትንቢት የናፈቁትን በሥጋ ሲመጣ ተቃወሙት ። የትንቢት ዝምድና ፣ የፍጻሜ ጠላትነት ሆነ ። አንዳንድ ሰዎች ወዳጃቸውን በጣም ይናፍቁና ካልመጣህ ይላሉ ፣ የመጣ ቀን ግን ነገር ቆስቁሰው ይጣላሉ ። እንዲሁም በተስፋ ፣ በትንቢትና በሱባዔ ክርስቶስን ናፍቀው ሲመጣ ግን ተጣልተዋል ።
መጻሕፍት ተግባራዊ ካልሆኑ ወደ ክህደትና ወደ ጭካኔ ያደርሳሉ ። በእግዚአብሔር ቤት ብዙ መጻሕፍትን የሚመረምሩ ሰዎች ወደ እምነትና ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ካላደጉ ክርስቶስን የሚጋርዱና ለአዳዲስ አማንያን ድፍረትን የሚያሰለጥኑ ደግሞም በፌዘኝነትና በዋዛ የሚደሰቱ ይሆናሉ ።
ጌታችን መጻሕፍትን መመርመር ኃጢአት ነው እያለ አይደለም ። ግቡን ካልመታ ግን የልብ ድንዳኔ እንደሚያመጣ እየገለጠ ነው ። ሁልጊዜ መስተዋት ላይ የሚውል በመስተዋቱ ግን ያየውን ቆሻሻ የማያነሣ ሰው ምንም ጥቅም አያገኝም ። መስተዋት የሚታየው አፍንጫዬ በርግጥ አለ ወይ ለማለት ሳይሆን በአፍንጫ ላይ ያረፈ ባዕድ ነገርን ለማንሣት ነው ።  መጻሕፍትም የተሰጡት የባሕርያችን ያልሆነውን ኃጢአት ፣ ያረፈብንን ባዕድ ነገር በሃይማኖተ ክርስቶስ ለማንሣት ነው ። የመጻሕፍት ምርመራ ብቻውን ወደ እግዚአብሔር አሳብ አያደርስም ። መጽሐፉ ለነቢያት የተሰጠው በምርመራ መንገድ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት ነው ። መጽሐፉንም ለመረዳት የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ በጽኑ መለመን ያስፈልጋል ። መጽሐፍ ቅዱስን በተጻፈበት መንገድ ካልሆነ በሌላ አንጻር መረዳት አይቻልም ። የመንፈስ ቅዱስ መምህርነት በጣም ያስፈልጋል ።
መጻሕፍት ስለ ክርስቶስ የሚመሰክሩ ናቸው ። በሌላ ስፍራም ፡- “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው።”  ብሏል /ሉቃ. 24፡44/ ። የብሉይ ኪዳን አጠቃላይ መጠሪያ ሕግና ነቢያት የሚል ነው ። ጌታችንም ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በመላው ብሉይ ኪዳን ስለ እርሱ የተነገረው እንደ ተፈጸመ ተናገረ ። መላው ብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ የሚናገር ከሆነ አይሁድ መጻሕፍት መመርመራቸው ከንቱ ነው ። “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” እንዲሉ አልተገናኙም ። የሚከስሩት መጻሕፍትንም ክርስቶስንም ነው ። ዛሬም ድረስ በክርስቶስ ያላመኑ አይሁዳውያን በታላቅ ጥያቄ ውስጥ እየገቡ ነው ። ብሉይ ኪዳን የመሰከረለት ክርስቶስ መቼ ነው የሚመጣው በማለት ይጠይቃሉ ። አንዳንዶችም የመጣውና በጰንጤናዊው በጲላጦስ ዘመን የተሰቀለው እርሱ እውነተኛው መሢሕ ነው ወደ ማለት ደርሰዋል ።
ጌታችን በመቀጠል ፡- “ነገር ግን ሕይወት እንዲሆንላችሁ ወደ እኔ ልትመጡ አትወዱም” አለ ። መጻሕፍት በራሳቸው ሕይወት አይሰጡም ፣ መጻሕፍት የሚናገሩለትን ክርስቶስ ማመን ግን ሕይወት ያስገኛል ። ሕይወት በአማራጭ የትም አልተቀመጠም ። ሕይወት ወደ ክርስቶስ በእምነት በመገስገስ ብቻ የሚገኝ ነው ። ሰዎች ሕይወትን የሚያጡት ባለመውደድ እንጂ በመቸገር አይደለም ። እናምነው ዘንድ ክርስቶስ ሕይወት ሁኖ ወደ ዓለም መጥቷል ። የመጻሕፍት ግብ ሕይወት ነው ።
ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን ይዘው በክርስቶስ ላያምኑ ይችላሉ ። ይህ በአይሁዳውያን የታየ ነው ። ዛሬም መጽሐፍ ቅዱስን እየጠቀሱ በክርስቶስ ግን የማያምኑ አያሌ ናቸው ። እግዚአብሔር ለሁሉም ብርሃኑን ይላክልን ። አወቅሁ ብለን እንዳንራቀቅ ፣ አላወቅሁም ብለን እንዳንሰቀቅ ክርስቶስ ዕረፍት ይሁነን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ