የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሁሉ ስለ እርሱ ይናገራሉ

“ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር ፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?”
                                       /ዮሐ. 5፥46-47/።
ሙሴ ለጌታችን ምሳሌ የነበረ ታላቅ መሪ ነው ። የመጀመሪያው የእስራኤል መስፍንና ሊቀ ነቢያት ተብሎ የተጠራም ነው ። በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ሦስት ሰዎች ጎልተው ይታያሉ ። በአባትነት አብርሃም ፣ በነጻ አውጪነት ሙሴ ፣ በንጉሥነት ዳዊት ናቸው ። ሙሴ የመጀመሪያው ነቢይ ነው ። ከአገልግሎቱና ከቀደምትነቱ የተነሣ ሊቀ ነቢያት ይባላል ። ሙሴ የመጀመሪያው የእስራኤል መስፍን ነው ። የመጀመሪያው ካህንም ነው ። ሊቀ ካህናት አሮን የተቀባው በሙሴ እጅ ነው ። እነዚህ ሦስት ታላላቅ መዐርጋት ማለትም ነቢይነት ፣ ካህንነትና ንጉሥነት ለአንድ ሰው በአንድ ጊዜ የሚሰጡ አይደሉም ። በታሪክ ውስጥ ግን አዳም ፣ ሙሴና ክርስቶስ ሦስቱን መዐርጋት ወርሰዋል ። ነቢያት ንግሥናን ሸሽተዋል ፣ ነገሥታትም ካህንነትን በመመኘታቸው እነ ዖዝያን ተቀጥተዋል ። ሦስቱ መዐርጋት በአንድ ጊዜ የተገኙት ለአዳም ለሙሴና ለክርስቶስ ነው ። አዳም በውድቀቱ ሦስቱንም መዐርጋት አጣ ። ሙሴ መስፍንነቱን ለኢያሱ ሲያስረክብ ፣ ነቢይነቱን ዐረፍተ ዘመን ሲገታው ፣ ካህንነቱን አሮንን ሲሾመው አበቃ ። ጌታችን ዳግማዊ አዳም ሁኖ ስለ መጣ አዳም ከበደል በፊት የነበረውን ስምና ክብር ሁሉ እንደ ገና ገንዘቡ አድርጓል ። ስም የሚያስጠራ ርስት የሚያስመልስ ልጅ ሁኗል ። አዳም ከነበረው በላይም በክርስቶስ ተዋሕዶ ከብሯል ።
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ራሱ ፡- “አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ መካከል ከወንድሞችህ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣልሃል እርሱንም ታደምጣለህ”ብሏል /ዘዳ.18፥15-16/። ይህ ትንቢት በክርስቶስ እንደ ተፈጸመ እናነባለን፡- “ሙሴም ለአባቶች፡- ጌታ አምላክ እኔን እንዳስነሣኝ ነቢይን ከወንድሞቻችሁ ያስነሣላችኋል፤ በሚነግራችሁ ሁሉ እርሱን ስሙት። ያንም ነቢይ የማትሰማው ነፍስ ሁሉ ከሕዝብ ተለይታ ትጠፋለች አለ።” /የሐዋ. 3፥22-23/። እንደ እኔ ያለ ማለቱ በብዙ መንገድ የጌታችን ታሪክና አገልግሎት ከሙሴ ጋር ተመሳሳይ ስለሆነ ነው ። ተካካይ ግን አይደለም ። ሙሴ ከአገሩ ውጭ የተወለደ ነው ፤ ጌታችንም በዚህ ምድር በሥጋ እንግድነት የመጣ ነው ። ሙሴ በእናቱ እጅ ያደገ ነው ፤ ጌታችንም ድንግልናዊ ወተትን እየጠጣ ያደገ በምድር አባት የሌለው ነው ። ሙሴ ፈርዖን ሕጻናትን በሚገድልበት ዘመን የተወለደ ነው ፤ ጌታችንም በተወለደ ጊዜ ሄሮድስ ሕጻናትን አስገድሏል ። የሙሴ እናት ሙሴን በማጥባቷ ከዓለም እናቶች ተለይታ የንጉሥ ደመወዝ ተከፍሏታል ። እመቤታችንም ጌታችንን በመውለዷና በማጥባቷ ወላዲተ አምላክ ተብላ ስትመሰገን ትኖራለች ። የሙሴ እናት የዓላማ ሴት ነበረች ፤ ጌታችንም የነፍስ ዓላማ ከነበራት ቅድስት ድንግል የተወለደ ነው ። ሙሴ ተወልዶ በወንዝ ዳር ተጣለ ፣ ጌታችን በበረት ተወለደ ። የሙሴ እናት የሕዝቡን ነጻ መውጣት የምትናፍቅ ሴት ነበረች ፣ እመቤታችንን የድኅነት ዓመትን ትናፍቅ ነበርና ገና ብሥራት በሰማች ቀን ታዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር ። ወትትኃሰይ መንፈስየ በአምላኪየ ወመድኃንየ ብላ አመስግናለች ። ሙሴ ስለ ወገኑ ባርነት ይቆጭ ነበር ፤ ጌታችንም ስለ እኛ ማወቅና መትረፍ የተቆጨልን ነው ። ሙሴ የፋሲካ በር አርዶ እስራኤልን ከግብጽ ያወጣ ነው ፣ ጌታችን የፋሲካ በግ ሁኖ የታረደልን ነው ። ሙሴ ባሕረ ኤርትራን ያሻገረ ነው ። ጌታችን ባሕረ ሞትን ያሻገረ ነው ። ሙሴ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት በደብረ ሲና ቆይቶ ሕገ ኦሪትን የተቀበለ ነው ፤ ጌታችንም ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጦሞ ከጸለየ በኋላ ሕገ ወንጌልን የሰበከ ነው ። ሙሴ በእጁ ከዓለት ውኃ ፈለቀ ፣ መና ከሰማይ ወረደ ። ጌታችን የሕይወት ውኃ ፣ የሕይወት ኅብስት ሁኖ ራሱን ለዓለም ሰጠ ። ሙሴ መቃብሩ አልታወቀም ፣ ጌታችንም መቃብሩ ባዶ ነው ።
ሙሴና ጌታችን የሚለያዩበት ፡- ሙሴ በቤተ መንግሥት አደገ ፣ ጌታችን በድሆች መንደር በናዝሬት አደገ ። ሙሴ ወደ ቤተ መንግሥት ተወሰደ ፣ በጌታችን ዘንድ ግን ነገሥታት ሊሰግዱለት ያለበት ድረስ መጡ ። ሙሴ የፋሲካን በግ አረደ ፣ ጌታችን ግን የፋሲካ በግ ሁኖ ታረደ ። ሙሴ ከሚያልፈው ባርነት ሕዝቡን ነጻ አወጣ ። ጌታችን ግን ከዘላለም ሞት አዳነን። ሙሴ ዓለቱን በመታ ጊዜ ውኃ ፈለቀ ፣ ጌታችን ግን ዓለት ኃይሉን ቢመቱት ደምና ውኃ ከጎኑ ፈለቁ ። ሙሴ ፍርድ የምታመጣ ሕግን በደብረ ሲና ተቀበለ ፣ ጌታችን ግን የምታድን ወንጌልን በቀራንዮ ገለጠ ። ሙሴ በልዑልነት አድጎ በመስፍንነት ሞተ ። ጌታችን ግን በባሪያ መልክ ኖረ ፣ እንደ ወንጀለኛም ተቀጥቶ ሞተ ።
ሙሴ ስለ ጌታችን በብዙ መንገድ ተናግሯል ። በትንቢት ፣ በምሳሌ አብራርቷል ። በሌላ ስፍራ ላይም ጌታችን ፡- “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው አላቸው ።” /ሉቃ. 24፥44/። በእያንዳንዱ ቀን በነበረው የሙሴ አገልግሎት ክርስቶስ ይታይ ነበር ። ስለዚህ ሙሴን መቀበል ማለት ክርስቶስ መቀበል ነው ። አይሁድ ክርስቶስን አለማመናቸው ሙሴ የተናገረውን አለማመናቸው ያመጣው ችግር ነው ። ለሙሴ የአፍ ወዳጆች ነበሩ ። ክርክራቸውን ለማስደገፍ ስሙን ይጠሩታል እንጂ በመራቸው መንገድ አይከተሉትም ነበር ። ሙሴ ያለው ስሙት ነው ።
ሙሴ ስሙት እንዳለ ሁሉ ፣ እግዚአብሔር አብም የምወደው ልጄ ነው እርሱን ስሙት አለ ። በሁለት ወገን ድንግል የምትሆን እመቤታችን ድንግል ማርያምም የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለች ። ቀስት ሁሉ ወደ ክርስቶስ ያመለክታል ። ምክንያቱም እርሱን የማትሰማ ነፍስ ትጠፋለችና ። ሙሴ የነጻነትን መልእክት ይዞ በመጣ ጊዜ ሕዝቡ አላመኑትም ነበር ። ጌታችንም ነጻ የምታወጣዋን ወንጌል ሲሰብክ ማንም አላመነውም ። ሙሴ በግሉ የፈርዖን ጽኑ አገዛዝ አይመለከተውም ነበር ። ጌታችንም ከክፋትና ከጥፋት ርቆ ያለ ነው ። ሙሴ ስለ ሕዝቡ መጀመሪያ ታማሚ ፣ ቀጥሎ ስደተኛ ኋላም ተከራካሪ ሆነ ። ጌታችንም ስለ ሕዝቡ የሕማም ሰው ሆነ ። በግብጽ ተሰደደ ፣ በምድረ እስራኤል ተንከራተተ ። ከገዳዩ ጋርም ተናነቀ ። ሙሴ ገና የነቢይነት አገልግሎቱን ሳይፈጽም ስለሚመጣው ነቢይ ተናገረ ። ለጊዜው ኢያሱን ይመለከታል ። ፍጻሜው ግን ጌታችን ኢየሱስን ያሳያል ። ኢያሱ ማለት መድኃኒት ማለት እንደሆነ ኢየሱስ ማለትም መድኃኒት ማለት ነው ። ኢያሱ ምድረ ርስትን እንዳከፋፈለ ጌታችንም በመንፈሳዊና በሰማያዊ በረከት የባረከን ነው ።
ክርስቶስን ለመግፋት ምክንያቱ ቅዱሳኑንና ቅዱሳት መጻሕፍት የተናገሩትን አለማወቅ ነው ። ከቅዱሳንና ከቅዱሳት መጻሕፍት የተጣላ የክርስቶስ ወዳጅ መሆን አይችልም ። እነዚህ ሁሉ ስለ ክርስቶስ ይናገራሉ ። ስለ እርሱ በመናገራቸውም ቅዱስ ተብለዋል ። የቅድስና ምንጭ ፣ እከብር አይል ክቡር ፣ እበደር አይል ባለጠጋ ፣ እደክም አይል ብርቱ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ቤተ ክርስቲያን ከመሠረቷ እስከ ጉልላቷ ያጌጠችው በክርስቶስ ነው ። ቋንቋዋን ለሚረዱ ቤተ ክርስቲያን ክርስቶስን ትሰብካለች ። ስለ ክርስቶስ የሚናገረውንም መጽሐፍ ቅዱስ ለሁለት ሺህ ዓመታት ጠብቃ ያቆየች ናት ።
የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ተፈጸመ ።   
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ