የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ማጠቃለያ/2/

መጻጕዕ ከበሽታው ጋር ሠላሳ ስምንት ዓመት ቆየ ። ሰው ከትዳሩ ጋር እንኳ ይህን ያህል ዓመት ላይቆይ ይችላል ። የመጻጕን የተጸውዖ ስም አናውቅም ። ጌታ ያደረገለትን ግን እናውቃለን ። በየዓመቱ እናስበዋለን ። ከዐቢይ ጾም ሳምንታት አራተኛው መጻጒዕ ይባላል ። መጻጉዕ በሚሠራበት ዕድሜ ያልሠራ ሰው ነው ። ጌታ የሠራለት ግን እስከ ዛሬ ይወራል ። ባንሠራም የተሠራልን አለ ። ዘመኖቻችን ያለ ወዳጅ ፣ ያለ ሥራ ያልፋሉ ። የማይካስ ዘመን ብለንም እንጠራቸዋለን ። እነዚህን ጉዳቶች ግን የእግዚአብሔር ሥራ ይክሳቸዋል ። የእግዚአብሔርን ሥራ በሚመለከት ሦስት ነገሮች አሉ ፡-
1-  እግዚአብሔር ይሠራልናል – ሥራችንን
2-  እግዚአብሔር ይሠራብናል – በእኛ በኩል ሌሎችን ይነካል
3-  እግዚአብሔር ይሠራናል – ሕይወታችንን ይለውጣል
ከሁሉ የሚያስደስተው እግዚአብሔር ሲሠራን ነው ። እግዚአብሔር መጻጕዕን ሠራው ለክብሩም አቆመው ። የተሠራ ሰው መሥራት ይችላል ። በሰባራ ቅል ውኃ መቅዳት እንደማይቻል ያልተሠራ ሰውም ሊሠራ አይችልም ። እግዚአብሔር በተአምራቱ ብቻ ሳይሆን በመከራም ይሠራናል ። የዘመናት ርዝማኔ ጸሎታችንን አያስረሳውም ። ለዚህም ምስክሩ መጻጕዕ ነው ። የተሰማው ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ የጸለየው ጸሎት ሳይሆን  የመጀመሪያ ቀን የጸለየው ጸሎት ነው ። የሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛን ጌታችን ወደ አልጋው ቀርቦ፡-  “ልትድን ትወዳለህን ?” አለው ። ምናልባት በሽታው የገቢ ምንጭ ሁኖት ይሆናል ። ሰዎች እንዲያዝኑላቸው በፈቃዳቸው የሚታመሙ ወይም አመመኝ የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ ። ይህ የሰዎችን አትኩሮት ለመሳብ ይረዳ ይሆናል ። የጌታ ፈውስ ግን ከሰው ኀዘኔታ በላይ ነው ። መጻጕዕ ራሱ እግዚአብሔር መጥቶ የዳሰሰው ነው ። ወደ ውኃው ለመውረድ አቅም ፣ ዘመድ የለውም ። ስለዚህ ጌታ ወደ አልጋው መጣ ። ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ላቃታቸው ጌታ ካሉበት ድረስ ይፈልጋቸዋል ። ጌታችን እስንመጣ ቢጠብቀን ኑሮ እስካሁን ዓለም አይድንም ነበር ።
 አዎ ስንሠራ ጎበዞች ነን ፣ እግዚአብሔር ሲሠራብን ግን አገልጋዮች ነን ። ጌታ የሚሰጠን የልመናችንን ያህል አይደለም ። ከለመነው በላይ ነው። የመጻጕዕ የልመናው ልክ መዳን ነበረ ። ጌታ ግን አልጋውን ተሸክሞ እንዲሮጥ አደረገው ። አልጋን መሸከም የጤነኞች እንኳ ስጋት ነው ። የጌታ ፈውስ ግን ጤንነት ብቻ ሳይሆን የተሸከመንን የመሸከም አቅም ነው ። በርግጥ ተፈውሰን ከሆነ የተሸከሙንን እንሸከማለን ። ወላጆቻችንን ፣ መምህራኖቻችንን እንሸከማለን ። ወላጆች በተሸከሙን ዘመን ልጄ መች ባደገልኝ ብለው ሳለ እኛ ግን በተሸከምናቸው ዘመን መች በሞቱ ካልን አስቸጋሪ ነው ። አገራችን ተሸክማናለች ። ካላት ጥቂት አቅም በነጻ አስተምራናለች ። እኛም ልናገለግላት ይገባል ። መሸከም የማይፈልግ ሰው ለመጣላትና ለመሄድ ሰበብ ይፈልጋል ። የተሸከመንን የመሸከም ዕድል ማግኘት ቀላል አይደለም ። ሕይወትን አስደሳች የሚያደርጋትም ለደከሙልን ስንደክምላቸው ነው ። በሰማይ የበጎ ሥራ ሽልማት እንጂ በጎ የመሥራት ዕድል የለም ። ከሞት በኋላም ንስሐ የለም ። አሁን መልካም ማድረግ ይገባናል ። ይልቁንም የክፉ ቀን ወዳጆቻችንን ዛሬ ከምናውቃቸው ሰዎች ጋር ማወዳደር አይገባንም ። መምህራኖቻችንም በዛሬው እውቀታችን አይለኩም ። ያለ እርካብ ፈረስ ላይ አይወጣም ። ትንሹ እርካብ ግን ትልቁ ፈረስ ላይ መውጫ ነው ። የዛሬው ትልቅ መሆን የብዙ ትንንሽ አስተዋጽኦዎች ውጤት ነው ። ዕዳ ይዞ መኖር በኅሊና ፣ ዕዳ ይዞ መሞት በእግዚአብሔር ያስጠይቃል ። ያልከፈልነውን መክፈል አለብን ። ያለፈውን ዘመን አብረውን የቆሙትን ማሰብ ተገቢ ነው ። ትላንት የዛሬ ውጤት ፣ ዛሬ የነገ መሠረት ናት ። ዛሬ ለትላንት መኸር ፣ ለነገ አዝመራ ናት ። የትላንትን ዛሬ እናጭዳለን ፣ የነገውን ዛሬ እንዘራለን ።
መጻጕዕ ፈውሱን በትክክል እንዲያረጋግጥ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው ። ለሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛ ማገገሚያ ጠቦት እንኳ መታረድ አለበት ። ፀሐይን መላመድ ያስፈልገዋል ። መጻጕዕ ግን የዳነ ቀን አልጋውን እንደ ዣንጥላ ዘርግቶ ወጣ ። መቅደስም ተገኘ ። እስረኛ ብዙ ዓይነት ነው። እንደ መጻጕዕ የአልጋ እስረኛ አለ ። የፍርሃት እስረኛም አለ ። እስረኛ መምጣት አይችልም ። ካልሄድን አናገኘውም ። እስረኛ ሁሉንም ነው ። ጌታ በመጨረሻው ቀን የሚጠይቀንን ጥያቄ በሙሉነት የጠቀለለ እስረኛ ነው ። በመጨረሻው ቀን ጌታ ብራብ አብልታችሁኛል ? ይላል ። እስረኛ ረሀብተኛ ነው ። እስረኛ ጥማተኛ ነው ። እስረኛ በለበሰው ልብስ ዕድሜ ልክ የተፈረደበት የታረዘ ነው ። እስረኛ በወዳጅ ክዳት የታመመ ነው ። እስረኛ ከቤቱ የራቀ እንግዳ ነው ። እስረኛነት ከባድ ነው ። እስረኛን ስንጠይቅ ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን አሟላን ማለት ነው ። መጻጕዕም እስረኛ ነበር ። ጌታ ሲጠይቀው ተፈታ ፣ ጠገበ ፣ ረካ ፣ ለበሰ ፣ ወገን አገኘ ፣ ተፈወሰ ።
ያ ሁሉ ጠበለተኛ መጻጕዕን ሲያይ ምን ይል ይሆን ? በታማሚዎች የተቆረቆረው ያ መንደር ዛሬ ምን ይል ይሆን ? ታላቁ ተአምር ግን ታላቅ ክስ አመጣ ። ዓለም እንደምናስበው አይደለም ። መጻጕዕን ሲተኛ የሚወዱት ሲነሣ ጠሉት ። ከሰው ፍቅር የጌታ ፈውስ ይበልጣል ። መጻጕዕን አልጋ ተሸክሞ ስታዩ ቤት እየቀየረ አይደለም ። ፈውሱን እያወጀ ነው ። ለእኔም ቀን አለኝ ብለው ብሶተኞች በዚህ ሕያው ምስክር ሲጽናኑ እንዲውሉ ነው ። አልጋው በመጠኗ ባለ ርስት አድርጋዋለች ። አልጋውን ሲሸከም ግን ያችንም ርስት አጣ ። ከታሠረ ባለ ርስት የተፈታ ስደተኛ ይሻላል ። ለውስጣችን ክብር ካለን የመንፈስ ነጻነትን እናስቀድማለን ። በእውነት ልቅሶአችን ትክክለኛ አልቃሽ ሲያገኝ ደስታችን ግን ትክክለኛ አጋር አያገኝም ። ዓለም ርግጠኛ ጠላቶችና አጠራጣሪ ወዳጆች ያሉባት ናት ። እውነተኛ ወዳጆች በመዳናችን የሚደሰቱ ናቸው ። መጻጕዕ ፈውሱን ብቻ ሳይሆን አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለውንም ትእዛዝ ተቀብሏል ። ያዳነን ካዘዘን እናደርጋለን ። ከእርሱ በላይ ለማን እንታዘዛለን ?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ