የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ አምስት ማጠቃለያ/3/

መጻጕዕ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ሲለው ገና መች አገገምኩና አላለም ። ለፈዋሹ ጌታ ታዘዘ ። እግዚአብሔር ሲያዝዘው የዘመናት እስራቱን አላሰበም ። የዘመናት እስራቱ ላይ ግን ሊጓደድ ተነሣ ። እግዚአብሔር ሲጠራቸው ማንነታቸውን ያዩ አያሌ ናቸው ። እግዚአብሔር ግን የሚጠራን አውቆን ነው ። እርሱ በባዶነታችን ሙላቱን ሊገልጥ ይጠራናል ። እግዚአብሔር ሲያዝዘን ለምን ሳንል መታዘዝ ትልቅ በረከት ያመጣል ። የእግዚአብሔር ሰዎች እግዚአብሔርን ያለ ማመንታት ታዝዘዋል ። አንድ ታሪክ በኢሳይያስ መጽሐፍ ጠቀስ ተደርጓል ፡- “በዚያ ዓመት እግዚአብሔር የአሞጽን ልጅ ኢሳይያስን፦ ሂድ፥ ማቅህን ከወገብህ አውጣ ጫማህንም ከእግርህ አውልቅ ብሎ ተናገረው ። እንዲህም አደረገ ፥ ራቁቱንም ባዶ እግሩንም ሄደ” /ኢሳ. 20፥2/። እግዚአብሔር ከጸጋ የተራቆቱትን ሕዝብ ለማስተማር ኢሳይያስን ራቁትህን ሂድ አለው ። ኢሳይያስም በመታዘዝ ሦስት ዓመት ራቁቱን ሄደ ። እግዚአብሔር ካዘዘን የምንመርጠው ትእዛዝ የለም ። መጻጕዕ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለው ። አልጋን መሸከም ትርጉም የማይሰጥ ይመስላል ። ዋናው ነገር “ያዘዘኝ ምን ዓይነት ትእዛዝ ነው ?” ማለት ሳይሆን “ያዘዘኝ ማን ነው ?” የሚለው ነው ። “ማን ነው ?” የሚለው ጥያቄ ሲመለስልን የምንድነው ? ጥያቄ ይመለስልናል ። መጻጕዕ ጌታ ሲያዝዘው ዝቅ ብሎ አልጋውን ተሸከመ ፣ መልሶ ተሸከመው ። አልጋ ይሸከማል እንጂ የሚሸከመው አግኝቶ አያውቅም ። አልጋህን ተሸከም ፡-
·       የተሸከመህን ተሸከመውና ዕዳህን ክፈል ነው ።
·       መዳንህ ጤነኛ ከመሆን በላይ ብርታት መሆኑን ተረዳ ማለት ነው።
·       የእግዚአብሔር ማዳን ቅጽበታዊ እንጂ ሂደታዊ እንዳልሆነ አስተውል ማለት ነው ።
 መጻጕዕ ጌታ ሲያዝዘው ራሱን አላየም ፣ እነዚያን የበሽታ ሎሌ የሆነባቸውን ዘመናት አልቆጠረም ። ሰው የሚያስታምመው በሽተኛ ቶሎ ተስፋ ይቆርጣል ። ብላ ጠጣ ፣ ተኛ ንቃ የሚለው ድምፅ ይረብሸዋል ። ራሱን የሚያስታምም ሕመምተኛ ግን ቶሎ ተስፋ አይቆርጥም ። እኛ እኛን ይቅር የምንለውን ያህል ሰዎች እኛን ይቅር አይሉንም ። ስለዚህ ሰዎች ጋ ከራሳችን ጋር እንደምንኖረው አብረናቸው ለመኖር መሞከር የለብንም ።
 መጻጕዕ ያዳነህ ማነው ? ብለው ጠየቁት ። ሊሰግዱለት አይደለም ፣ የእነርሱን እንቆቅልሽ እንዲፈታ ፈልገውም አይደለም ። ወርቅ ላበደረ ጠጠር፣ እህል ላበደረ አፈር ሊመልሱ እንጂ ። መጻጕዕ የዳነባት ቀን የምስጋና ቀን ልትሆን ይገባት ነበር ። ነገር ግን የሸንጎ ቀን ሆነች ። ፈውስ ጅረት ነውና ምንጩን ሊያደርቁ ፈልገው ማነው ? አሉ ። ፈውስን የናኘው ግን መጻጕዕ የማያውቀው መጻጕን ግን የሚያውቀው ጌታ ነው ። ስለዚህ ሊያሳያቸው አልቻለም ። መጻጕዕ ያለ ዛሬ አላየውም ። ጌታ ገና ሳይወለድ በማኅፀን ሳለ አይቶት ነበር ። ጌታችን በምድር ላይ የኖረው ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ነው ። መጻጕዕ ግን የታመመው ሠላሳ ስምንት ዓመት ነው ። ፈውስ የሚሆንልን እኛ ጌታን ስላወቅን ብቻ ሳይሆን እርሱ ስላወቀንም ነው ። ስለ ራሱ የሚያደርግልን ብዙ ነው ። ዛሬም ስሙ በእኛ ላይ ስለ ተጠራ አይተወንም እንጂ የእኛ ጭካኔማ ወደር የሌለው በአሕዛብም የማይገኝ ነው ። በርግጥ መጻጕዕ ጌታን በአካል ማወቅ አይጠበቅበትም ። ጌታን ማወቅ በእምነት ነውና ። በአንድ ስፍራ ላይ ወዳጅ ካለን ሥራውን ሁሉ ሠርቶ ለፊርማ ብቻ ይጠራናል ። የዘላለም ጉዳያችንን ጨርሶ ፊርማ ለተባለው እምነት የጠራን ክርስቶስ ነው ። መጻጕዕ ጌታን ማወቅ አልቻለም ፣ ጌታ ግን እንደገና ወደ እርሱ መጣ ። መጻጕዕ ከብዙ ሕዝብ መሐል ጌታን መለየት አቃተው ጌታ ግን ከብዙ ሕዝብ መሐል መጻጕን ለየው ። ሰው በዛብን ብለን ጌታን ገሸሽ እንላለን ። ጌታ ግን ጻድቃን በዙብኝ ብሎ እኛን ኃጢአተኞቹን አይተወንም ። ጸጥታ አጣሁ ብለን ጸሎት እናቆማለን ፣ ጌታችን ግን በሁከት ውስጥ የእኛን ጸሎት ይሰማል ። በእኛና በእርሱ መካከል ያለው ልዩነት ይህ ነው ። ኧረ እባክህ መጻጕዕ ልቀቀንና ወደ ምዕራፍ ስድስት ወደ ባሕሩ ዳርቻ እንሂድ ።
 ጌታችን መጻጕን አገኘውና ፡- “እነሆ ፥ ድነሃል ፤ ከዚህ የሚብስ እንዳይደርስብህ ወደ ፊት ኃጢአት አትሥራ አለው ።” /ዮሐ. 5፥14/። ይህ ሰው ወደ አልጋ የላከው ክፉ ነገር የነበረ ይመስላል ። ከኃጢአት የሚበልጠው ኃጢአት ግን የዳነውን ጌታ መተው ነው ። ከሠላሳ ስምንት ዓመት ደዌ የሚበልጥ ቅጣት አለ ። እርሱም የገሃነም ሞት ነው ። ሥጋዊ ፈውስ መንፈሳዊ ፈውስን አያመጣም ። ስለዚህ በዳነ ቀን ያዳነውንና ያስጠነቀቀውን ጌታ ከዳ ። እባብ የልቡን አይቶ እግር ነሣው እንደተባለው በአንድ ቀን እርምጃ ወደዚህ ከገባ ሠላሳ ስምንት ዓመት ቢራመድ ምን ያደርግ ይሆን ? እግዚአብሔር የሚነሣን ወይም የሚከለክለን ለካ ዕድሜአችንን ለማርዘም  ነው ። መጻጕዕ ያዳነውን አሳመመ ። ያዳነውን ለገዳዮች መጠቆም ትልቅ መርገም ነው ። ፈርቶ ነው እንል ይሆናል ። አዎ ሊሆን ይችላል ። ነገር ግን የሚመጣው ካሳለፈው አይበልጥም ። ሰዎች ከአልጋቸው ዘለው ወርደው ሰቃዮች ሊሆኑ ይችላሉ ። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያን መቅደም ያለበት የነፍስ ፈውስ ነው ። የነፍስ ፈውስ ለሥጋ ይተርፋል ፣ የሥጋ ግን ለነፍስ አይተርፍም ። ወደፊት የሚመጣው የበለጠ ክብር ብቻ ሳይሆን የበለጠ ውድቀትም ነው ። ትላንት ሕግን እንተላለፍ ይሆናል ፣ በዚያም በእግዚአብሔር ምሕረት እንድናለን ። ምሕረቱን ከተላለፍን ግን በምን እንድናለን ?
 ጌታችን የሠላሳ ስምንት ዓመት በሽተኛን በመፈወሱ ለተደነቁት ሰዎች ፡- “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ ብሎ መለሰላቸው ።” /ዮሐ. 5፥17/። ለመጻጕዕ የተደረገው ለዘመናት የሚደረግ ዛሬም እየተደረገ ያለ ነው ። ያንዱ መጻፉ የአንዱ አለመጻፉ ነው ። እግዚአብሔር የተአምራት አምላክ ነው ። ዛሬም ተአምር እየሠራ ነው ። ለእኔ ምን ሠራልኝ እያላችሁ ይሆን ? ዛሬን ማየታችሁ በራሱ ተአምር ነው ። እግዚአብሔር ከሚሊየን ተግባራቱ አንዱ ይህ ነው ። ገና ይቀጥላል አላቸው ። ለካ ቀኑ ያለ ተአምሩ አይውልም። ያለ ተአምሩ የመሸ ቀን የለም ። ጌታችንን ይህን የሥልጣን ቃል በመናገሩ ሊገድሉት ፈለጉ።
 መጻጕዕ ያለፈበት ጎዳና ለእርሱ ብቻ ነው የሚታወቀው ። ሞቶ ባረፈው የተባለለት ሰው ነው ። ሞቶስ ዕረፍት እንዳለው አረጋግጠዋል ? አሳራፊውን አምላክ ላልያዙ ሞት ዕረፍት አይደለም ። ሐዋርያው የተናገረው እንዴት ልብ ይነካል ፡- “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና።” /ፊልጵ. 1፥21/። ሞት ጥቅም የሚሆነው ክርስቶስ ሕይወት ለሆነለት ብቻ ነው ። ሞቶ ለማረፍ መስፈርቱ እምነት ነው ። በሽታ ስቃይ አለው ። ሰው ስለ ጤናውም ንብረቱን ሁሉ ያባክናል ። በሽታ አካላዊ ፣ ሥነ ልቡናዊ ፣ ማኅበራዊ ቀውሶችን የሚያመጣ ነው ። መጻጕዕን በእኛ ቦታ ቆመን ልንረዳው አንችልም ። በመጻጕዕ ቦታ መሆን ያስፈልጋል ። ሰዎችን መርዳት ያቃተን ለምንድነው ስንል በራሳችን ቦታ ቆመን ስለምናናግራቸው ነው ። አዎ የሥጋ ፈውስ ለነፍስ ፈውስ አምሮትን መቀስቀሻ እንጂ ዋስትና አይደለም ። በመጻጕዕ መፈወስ ጌታ ያተረፈው ጠላትነትን ነው ። ያውም ከመጻጕዕ ። በራሷ በመልካም ነገር ደስ ካላለን ሰዎች የሚሰጡን ምላሽ፣ የተደረገላቸው የሚያሳዩን ፊት እንድንጸጸት ያደርገናል ። ከእግዚአብሔር ጋር ጋር ባለን ግንኙነት ራሳችን ጠላት እንዳይሆንብን መጠንቀቅ አለብን ። እያንዳንዱ ሰከንድ የፈውስ ዕድል ነው ። በእያንዳንዱ ደቂቃ እግዚአብሔር በሥራ ላይ ነው ። በዚህች ሰዓት በሞት የሚወሰድ በልደት ወደዚህ ዓለም የሚመጣ አለ ።
ጌታችን እግዚአብሔር አብን አባቴ ነው በማለት እኩያነቱን ተናገረ ። ኋላም ለሞት የበቃበት ምክንያት ይህ ነው ። ከሳሾቹ የሚከስሱበት ሐሰት ቢያጡ በእውነቱ ከሰሱት ። የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል አሉ ። በርግጥም የእግዚአብሔር ልጅ ነው ። ክፋት የምስክር ወረቀት የለውም እንጂ በክፋት የረቀቁ ነበሩ ። ለቦታው በሚመጥን ክስ ከሰሱት ። ሃናና ቀያፋን ቱግ የሚያደርግ ሃይማኖታዊ ክስ ነውና እነርሱ ጋ ሲወስዱት “የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ” ይላል አሉ ። ሄሮድስን የሚያሳምመው ደግሞ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው ። “ንጉሥ ነኝ ይላል” አሉ ። በርግጥም ሳያምኑ መሰከሩለት ። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ፣ እርሱ ንጉሥ ነው ። ዓለም አዲስ የምትመስለው ታሪክ ያላነበበ ሰው ብቻ ነው ይባላል ። ዛሬ የሚሆነው ትላንት ሲሆን የነበረ ነው ።
 አብ ሳይሠራ የኖረበት ዘመን የለም አለ ። አብ ሲሠራ የነበረውን ሁሉ ወልድ አይቷል በማለት ተናገረ ። ይህ የሚያሳየን ወልድ ከአብ ጋር በዘመን እኩል መሆኑን ነው ። እኩልነት ብቻ ሳይሆን ጽኑ ኅብረትም አላቸው ። ለሰው ከልቡ የቀረበው እንደሌለ ለወልድም ከአብ የቀረበ የለም ። ለሰው ከቃል ይልቅ ፈጥኖ የሚላከው እንደ ሌለ ለአብ ከወልድ በላይ ፈቃዱን የሚፈጽም የለም ። ሁሉን ለማድረግ ፈቃድ ፣ አቅም ፣ ሥልጣን ያስፈልጋል ። ፈቃድ ያላቸው አቅምና ሥልጣን የላቸውም ። አቅም ያላቸው ደግሞ ፈቃድና ሥልጣን የላቸውም ። ሥልጣን ያላቸው ደግሞ ፈቃድና አቅም ላይኖራቸው ይችላል ። ሕዝብ ፈቃድ ፣ ሠራዊት አቅም ፣ ንጉሥ ሥልጣን አለው ። እነዚህ ሁሉ ካልተባበሩ ምንም ሊደረግ አይችልም ። በሥላሴ መንግሥት ግን ፈቃድ ፣ አቅምና ሥልጣን አንድ ነው ። ወልድም የአንድ ፈቃድ ፣ አቅምና ሥልጣን ተካፋይ ነው ። የአብና የወልድ የግንኙነቱ መሠረት ፍቅር ነው ። ሰዎች በዚህ ዓለም ላይ በሽርክና ሊገናኙ ይችላሉ ። ጥቅም እስካለ ድረስ አብረው ይጓዛሉ ። የአብና የወልድ ፍቅር ግን ይህን ዓለም አስገኝቷል ። ኅብረቱም ለዘላለም ጽኑ ነው ። የጀመረበት ጊዜ የለምና የሚቆምበት ጊዜም የለም ። የኅብረቱ መሠረት ፍቅር ባይሆን ኑሮ አብ በመላኩ ፣ ወልድ በመላኩ ባነሰ ነበር ። ላኪና ተላኪ መሆን ለፍቅር መንግሥት የፍቅር መግለጫ ነው ።
ዮሐ. 5፥21 ወልድ ለሚወዳቸው ሕይወት እንደሚሰጣቸው ይናገራል ። ሕይወትን የሚሰጥ ፍቅር ያለው እርሱ ብቻ ነው ። የማንም ሰው ፍቅር የዘላለም ሕይወትን መስጠት አይችልም ። አዳኝ ፍቅር ያለው ወልድ ብቻ ነው ። ሞት ለዚህ ዓለም ሰው የመጨረሻ ጥናቱ ነው ። ለጌታችን ግን የመጀመሪያ ሥራው ነው ። የእኛ መጨረሻ የእርሱ መጀመሪያ ባይሆን ኑሮ ሕይወት ባልቀጠለ ነበር ። አብ ፍርድን ሁሉ ለወልድ ሰጥቶታል ይላል ። ትልቁ የፍርድ አንቀጽ በሥጋ የመጣውን ክርስቶስ አለማመን ነው ። ስለዚህ ወልድ ፈራጅ ብቻ ሳይሆን የኵነኔም የጽድቅም አንቀጽ ነው ። አብ ስላልታየ ሁሉ ያከብረዋል ። ማየት ንቀት እንዳያመጣብን አብ አልታየም ። አለመታየት እግዚአብሔር ሩቅ ነው እንዳያሰኘን ወልድ ሥጋ ለበሰ ። ከባዱ አጠገብ ያለውን መውደድና ማክበር መሆኑን ከሰው ታሪክ እናያለን ። እውነተኛ እምነታችን የተለካው በልዑል እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን በትሑት እግዚአብሔር በማመንም ነው ። እግዚአብሔርን በኃይሉም በፍቅሩም አንችለውም ። እጅግ ታናናሾች ነን ። አብን ስላላዩት አከበሩት ፣ ወልድን ስላዩት ሰቀሉት ።  ያዩትን ወልድን መስቀላቸው አብ ቢታይ እንደሚሰቅሉት ማሳያ ነው ። ደግሞም ወልድን የጠላ አብን የጠላ ነው ። “ወልድ ሲነካ አብ ይነካ” እንዲሉ ። የሚያውቅ ይዳፈራል ፣ የሚታወቅ ይደፈራል ። የሚያውቅ ግን ማክበር ነበረበት ። “ቤተ መንግሥትንና ቤተ ክህነትን የሚደፍረው ውስጡን በሚያውቀው ነው” ይባላል ። በተዋወቅን ቍጥር መከባበር አስፈላጊ ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ