ጌታችን የዮሐንስን ምስክርነት አነሣ ፡- “እናንተ ወደ ዮሐንስ ልካችኋል እርሱም ለእውነት መስክሮአል ። እኔ ግን ከሰው ምስክር አልቀበልም፥ እናንተ እንድትድኑ ይህን እላለሁ እንጂ ። እርሱ የሚነድና የሚያበራ መብራት ነበረ ፥ እናንተም ጥቂት ዘመን በብርሃኑ ደስ ሊላችሁ ወደዳችሁ ። እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ ፥ ይህ የማደርገው ሥራ ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና።” /ዮሐ. 5፥ 33-36/
ዮሐንስ የሊቀ ካህናት ዘካርያስ ልጅ ነው ። ዮሐንስ ወንበር ወራሽነቱን ትቶ ወደ በረሃ በመግባቱ አይሁድ ይጨነቁ ነበር ። ስለዚህ መልእክተኞችን በሸንጎ ወስነው ወደ ዮሐንስ ይልኩ ነበር ። ዓለም ሲሸሿት የምትከተል ጥላ ናትና ። በከተማ የሚያውደለድለውን መንግሥትም አይፈራውም ። ጫካ የገባው ግን ይፈራል ። በከተማ ያለው ክብርና ምቾት አደናቅፎ የሚጥለው ነው ። ለእርሱ ጉልበት ማባከን ዓለም አትወድም ። የምቾት እስረኛ ታደርገዋለች ። ዓለም የናቃትን “ምን ቢኖረው ነው ?” እያለች ትከታተለዋለች ። አጥቶ የናቀውን ሳይሆን ዕድሉ እያለው ዓለምን የገፋውን ይህች ዓለም ታስሰዋለች ። ዮሐንስን ያከበሩት ወንበራችንን አይነካብንም ብለው ነው ። ወንበሩን ከተወልን ጥቂት እንኳ ልንሰማው ይገባል ብለውም ነው ። ዮሐንስን ቢያከብሩማ የዮሐንስን አምላክ ክርስቶስን ያከብሩት ነበር ። ዮሐንስን ትልቅ አድርገው ሲያከብሩት ዮሐንስ ደግሞ የእኔ ትልቅ እርሱ ነው በማለት ወደ ክርስቶስ ያመለክታቸው ነበር ። እኛን ትልቅ ያሉ እኛ ትልቅ ነው ያልነውን ትልቅ አይሉምና ይገርማል ። እኛን ያከበሩ ያከበርነውን አምላክ ላያከብሩ ይችላሉ ። ጌታችን ይህንን የዮሐንስን ምስክርነት ያስታውሳቸዋል ። የእኔ ክብር ያለው በራሴ ነው ይላቸዋል ። የምነግራችሁ እንድትድኑ እንጂ በእናንተ ተቀባይነት ለማግኘት አይደለም ። ከምድር መጉደል ከሰማይ መጉደል አይደለም ። አልተቀበሉንም ማለት እውነት የለንም ማለት አይደለም ። ተቀብለውን ውሸታም ሳይቀበሉን እውነተኛ ልንሆን እንችላለን ።
ጌታችን የሕይወት እንጂ የእልህ ንግግር የለውም ። ሰዎችን ለማዳን እንጂ ለማስደንበር አልመጣም ። ያ ቢሆን በትንሣኤው ቀን ቀያፋ ግቢ ተገኝቶ “ይኸው ተነሣሁ” ባለ ነበር ። ዛሬ ያለው ስብከት በእርግጥ ሰውን ለማዳን ነው ? የመዳንን ቃል ለእልህ መጠቀም አይገባም ። ሥጋ ሊታለልና ወደዚህ ሊገፋን ይችላል ፣ እስከ መጨረሻው ግን መታለል የለብንም ። የሚያስመሰግነው ክፋትን አለ መጀመር ቢሆንም አለመጨረስም ያስመሰግናል። በመልካሙ ነገር ክፉ ሥራ እንዳንሠራ መጠንቀቅ አለብን ።
ጌታችን የዮሐንስ አገልግሎት በሰማዕትነት እንደሚጠናቀቅ እየተናገረ ነው ። ሊቃውንት በቀለም ሰማዕታት በደም ያስተምራሉ ። በብዕር የጻፉ ሊቃውንት ሃይማኖት ላይኖራቸው ይችላል ። በደም የጻፉ ግን በርግጥ አማንያን ናቸው ። ዮሐንስ የሚነድ የሚበራ ነበር ። ለመብራት መንደድ ያስፈልጋል ። ስሜታዊ አገልግሎት እንጂ በስሜት ማገልገል የሚፈለግ ነው ። ከሰል ጥቅሙም ጉዳቱም ያለው ሲነድ ነው ። ዮሐንስ ንስሐ ግቡ እስኪል ወደውታል ፣ ክርስቶስን ሲገልጥ ግን ጠልተውታል ። ዮሐንስን የወደዱ ሰዎች ኢየሱስ ሲወዳቸው መቋቋም አልቻሉም ። የሚወዱ ሰዎች ሲወደዱ መሸሽ ይጀምራሉ ። ዮሐንስ ንግግሩ ሰይፍ ነበር ፣ ጌታ ግን የተቀጠቀጠን ሸንበቆ የማይሰብር ፣ ድምፁ በአደባባይ የማይሰማ የተባለለት ነው ። ሰዎች ግን ሰይፍ የነበረውን ንግግር ወደዱ ። ግን አልተለወጡበትም ። ማጉረስ የሚወዱ መጉረስ ግን አልወድም ይላሉ ። ለመሥዋዕት የሚሆነውን የሚሰጡ መሥዋዕት መሆን ግን አይፈልጉም ። መሥዋዕት የሚሆን ይሰጣሉ ፣ መሥዋዕት የሆነላቸውን ጌታ ማመን ግን ይከብዳቸዋል ።
“እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ ምስክር አለኝ” ከቅዱሳን ምስክርነት በላይ ሥራዬ ይመሰክራል እያለ ነው ። ሰዎች እንኳን የደጎችን የክፉዎችን ምስክርነትም አይንቁም ። አጋንንት መሰከረልኝ እያሉ እንኳ የሚፈነጥዙ ሰባኪዎች አሉ ። ጌታችን ግን የደጎች ደግ የሆነው የአባቱ ምስክርነት እንዳለው ተናገረ ። ወንጌል ክርስቶስ ከሆነ ለክርስቶስም አስቀድሞ የመሰከረ አባቱ እግዚአብሔር አብ ነው ። ስለዚህ ወንጌል በዘላለማዊ ሥልጣን የምትሰበክ ናት ። ሰዎች ወንጌልን ሲያወግዙ እንበሳጫለን ፣ የሚሠራው ውግዘት ግን ወንጌል ብታወግዛቸው ነው ። ሰው ቢያወግዘን ከምኩራብ እንወጣለን ፣ ወንጌል ብታወግዘን ግን ከሰማይ እንወጣለን ። የሰውን የድጋፍ ድምፅ መፈለግ እግዚአብሔርን በሰው ማስገምገም ነው ።
ጌታችን መጻጕን በመፈወሱ ለተነሣው ግርግር መልስ እየሰጠ ነው ። ሰው የሚመርጠው የሚያሳርፈውን ሳይሆን የሚያስጨንቀውን ነው ። ለሰዎች ስንራራ ሰዎቹ “ያለ እኛ መኖር አይችሉም” ብለው ያስባሉ ። ጌታ ቢያድናቸው ሰቀሉት ። መልካም ነገር የኅሊና እንጂ የአካባቢ ነጻነት የለውም ። ስለዚህ ለማፍቀር ስንዘጋጅ ለመከዳት መዘጋጀት አለብን ። ለመራራት ስንነሣ ለመነከስ መዘጋጀት አለብን ። መንፈሳዊ ተግባር ያለ ምድራዊ ምላሽ የሚቀጥል ነው ። እግዚአብሔርን የማያይ ደግነት ዕድሜ የለውም ። ሰብአዊ ተግባር ምላሽ ሲያገኝ የሚቀጥል ነው ። ደግ የምንሆነው ባሉት ክፉዎች ላይ ተጨማሪ ክፉ ላለመሆንም ነው ። ደግ ስንሆን ክፋትን ብቻ ሳይሆን የክፉዎችንም ቊጥር እንቀንሳለን ። ደግነት የእግዚአብሔር መሆንዋ የሚታወቀው ከምድር ስትገፋ ነው ። ሰው ጥላቻ አመመኝ እያለ ፍቅር ግን አያስደስተውም ። የበደላቸው ፍርድ ቤት እየጎተቱት መልካም ያደረጉለትን ግን አመሰግናለሁ አይልም ። የበቀል በጀት አለን ፣ የፍቅር በጀት ግን የለንም ። ሰዎች በአብዛኛው የሚያላግጥባቸውን ነው የሚሰሙት ። የሚዘርፏቸውንም ይወዳሉ ። ፀጉር ጎንጉነን ወዮላችሁ ብንላቸው ወዮልን ብለው ይሰማሉ ።
አይሁድ የመጨረሻው ሞት ነው ብለው ሲያስቡ ጌታ ግን ትንሣኤን አወራላቸው ። ሊገድሉት ለተነሡ ሰዎች ጌታ የሚናገረው ስለ ትንሣኤና ሕይወት ነው ። በሰው የተገደሉ በእግዚአብሔር ይነሣሉ ። በእግዚአብሔር የተገደሉ ግን ትንሣኤ የላቸውም ።
የምናከብራቸው ጻድቃን ሰማዕታት ሁሉ የሚመሰክሩት ስለ ክርስቶስ ነው ። ክርስቶስን ለጣለ ቅዱሳንም ወዳጅ አይሆኑትም ። ክርስቶስን ለጣለ ሁሉም ነገር ኪሳራ ነው ። በክርስቶስ ከሰርኩ ፣ ያለ ክርስቶስ አተረፍኩ ማለት ሐሰት ነው ። ዮሐንስን የተጣሉት ዋናው መልእክት ጋ ሲደርስ ነው ። ጥላው ጋ ጠብ የለም ፣ አካሉ ጋ ሲደርስ ግን ችግር ይነሣል ። እየዋሸን እንኳ የታገሡን እውነት ስንናገር ይጠሉናል ። ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ሰው ስለ ክርስቶስ የተሟላ እውቀት ላይኖረው ይችላል ። ጌታ ከመጣ በኋላ ግን እውቀት ካጣ ይህ እልኸኝነት የወለደው ነው ። የማይታየው አብን የተረከው የሚታየው አምላክ ክርስቶስ ነው ። አብን ማወቅም በአብ መታወቅም በክርስቶስ ነው ። አብ ስለ ወልድ የመሰከረው አንድ መስመር የማይሞላ ነው ። “የምወደው ልጄ ይህ ነው ።” ሕይወት ያላቸው ቃላት ጥቂት ናቸው ። ለመኖር ግን ዘላለምን የሚፈልጉ ናቸው ። አጭር ቃል ብዙ ኑሮ የመንግሥቱ ፀባይ ነው ። የአብን መልክ ያላዩት ፣ ድምፁንም ያልሰሙት በክርስቶስ ባለ ማመናቸው ነው ። ራሳችንን ከራሳችን በላይ ማን ያብራራልናል ? አብንም ከወልድ በላይ ማን ያብራራዋል ? ኢየሱስ ስለ አብ ብቻ ሲናገር ስለ ራሱ እየተናገረ ነው ። ምክንያቱም ክብሩ ልክ እንደ አብ ነውና ። ወልድ የሆነውን አብ ፣ አብ የሆነውን ወልድ ነውና አንዱ ስለ አንዱ ቢመሰክር ስለ ራሱ እየመሰከረ ነው ። ኢየሱስን ስናይ እግዚአብሔርን ያለ ትንታኔ እንቀበለዋለን።
ዮሐ. 5፥39 ስናነብ ስለ መጻሕፍት ይናገራል ። መጻሕፍት በመፈጸማቸው እንጂ በመነበባቸው አያድኑም ። የመድኃኒት መመሪያዎችን ማንበብ በራሱ አያድንም ። መድኃኒቱን መዋጥ እንጂ ። የመታዘዝ መጻሕፍትን የጥናት ካደረግናቸው ራሳቸው ይፈርዱብናል ። የአጥሩን ድንበር ሁሌ የሚለኩ ሰዎች አጥረው ካልገነቡበት መወረሱ አይቀርም ። የራበው ሰው የሚጠግበው ዳቦ ሲልስ ሳይሆን ዳቦ ሲበላ ነው ። ብሉይን ሲያጠኑ መኖር ክርስቶስን በማግኘት ካልተፈጸመ ከንቱ ነው ። የምርመራ ሁሉ ማብቂያ እርሱን ማግኘት ነው ። ችግር መጥቶባቸው የሚቸገሩና ችግር ፈጥረው የሚቸገሩ ሰዎች አሉ ። ችግር ሲለምዱት ሱስ ይሆናል ። አይሁድ መጥቶባቸው ሳይሆን ፈጥረው እየተቸገሩ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ትምህርት አጥተው መሃይም የሆኑ እንዳሉ ሁሉ ፣ ተምረውም የደነቆሩ አሉ ። ትምህርት አጥተው የደነቆሩ በሐዋርያት ትምህርት ሲመለሱ ተምረው የደነቆሩ ግን ባለቤቱ ራሱ ቢናገራቸውም አልተመለሱም ። በእግዚአብሔር ፍቅር ካልገራ ትምህርት በራሱ የችግር አካል ነው ። ትምህርት ፈሪሃ እግዚአብሔር ከሌለው አነጣጥሮ የሚመታው ደግነትን ነው ። ይህም አውሬ ያደርጋል ። ከዚህ በኋላ የምናገኛቸውን ነገሮች ክርስቶስን ካልጨመርንባቸው ጎጂ ናቸው ። ክርስቶስ የሌለበት ዕድገት ለውድቀት ነው ። ጌታ የፈጠረን ለመፍትሔ ነው ። መፍትሔ ካልሆንን ችግር እንሆናለን ። ኢየሱስን ማየት ካልቻልን የሚጠሉንን ስናይ እንውላለን ።
ጌታችን ከሰው ክብርን አልፈልግም አለ /ዮሐ 5፥41-42 ። ጌታችን የእኛ ምስጋና በመቀበሉ ልናመሰግነው ይገባል ። የሰጠንን መልሰን ካልሰጠነው በቀር በእኛ አቅም ልናመሰግነው አንችልም ። አንድን ሰው ስንወደው ዙሪያውን ሁሉ እንወዳለን ። ኢየሱስንም መጥላት ከአብ ፍቅር መፈናቀል ነው ። የሲዖል ጉዳት እንኳ በክርስቶስ ተክሷል ። ኢየሱስን መጎዳት ግን በምንም አይካስም ። ሰው የመዳን አሳብ ከሌለው አያምንም ። አይሁድ አብን ብቻ ሳይሆን ሙሴንና መጻሕፍትንም እንደ ከሰሩ ጌታችን ተናገረ ። ያመኑ የሚመስሉና በእውነት ያመኑ የሚለዩበት ዘመን ይመጣል ። ጌታችን የሚታገሠን መካድ ያልፋል ፣ ፍርዱ ግን አያልፍም ብሎ ነው ። ስለዚህ የዘላለም ሕይወትን ሲነግረን የዘላለም ሞትን እያየ ነው ። ለዚህ ነው የሚታገሠን ። ምዕራፍ አምስትን ፈጸምን ። ወደ ምዕራፍ ስድስት እንገስግስ። መንገዱን ያቅናልን ።