የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የቀናዎች ዓይን

“ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የስምዖን ጴጥሮስ ወንድም እንድርያስ፡- አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል ? አለው ።” ዮሐ. 6 ፡ 8 ።
እየመጣ ላለው ሕዝብ በጌታና በፊልጶስ መካከል የነበረው ምክክር አሁን እንድርያስን ጨመረ ። ቀጥሎ ደግሞ መላውን ደቀ መዛሙርት ምግቡን በማደል ያሳትፋል ። ስለ ሌሎች አሳብ እንዲኖረን እግዚአብሔር ሸክም ይሰጠናል ። እግዚአብሔር ይሠራል ፣ በሰው በኩል ይሠራል ። ሰውን በሰው መደገፍ ይፈልጋል ። የሰው ወገኑ ሰው ነውና ። በአንድ ሰው የተጀመረ ራእይ ብዙዎችን ያስከትታል ። ራእይ በአንድ ሰው ይጀመራል ፣ በብዙዎች ይፈጸማል ። እግዚአብሔር ስለ ሌሎች ያለንን አሳብ እንጂ ያለንን አቅም አያይም ። መሻት የሰው ፣ አቅም የእግዚአብሔር ነው ።
እንድርያስ የቤተ ሳይዳ ሰው ነው ። አስቀድሞ የዮሐንስ መጥምቅ ደቀ መዝሙር ነበረ ። ዮሐንስ መጥምቅ ቀና አመለካከት ያላቸውንና መሢሑን የሚናፍቁትን ወደ ክርስቶስ እንዲሄዱ አመልክቶ ነበር ። ከእነዚያ አንዱ እንድርያስ ነበረ ። ከዮሐንስ ደቀ መዛሙርት እስከ ዘለቄታው መሢሑን መቀበል ያልቻሉ ፣ ከፈሪሳውያን ጋር ሁነው ክርስቶስንና ሐዋርያትን የሚከስሱ ነበሩ ። ዮሐንስ ግን ቀናዎቹን ወደ ጌታ አመለከታቸው ። እንድርያስ ቀና አመለካከት ያለውና መሢሑን የሚናፍቅ ሰው ነበረ ። ይህ ብቻም ሳይሆን መሢሑን ካገኘ በኋላ ያረፈና የተረጋጋ ደቀ መዝሙር ነበረ ። እንድርያስ ከዓሣ አጥማጅነትን ሰውን ለማጥመድ የተጠራ ነው ። በትጋት ዓሣን ማጥመድም ለደቀ መዝሙርነት ለመታጨት መስፈርት ነው ። እግዚአብሔር ለላቀው ሥራ የሚያጨን ባነሰው ድርሻ ታማኝ መሆናችንን ካረጋገጠ በኋላ ነው ። የጴጥሮስ ወንድም ሲሆን ጴጥሮስን ከክርስቶስ ጋር ያስተዋወቀ ነው ። እኔ አስተዋውቄ ጴጥሮስ እንዴት ስመ ጥር ሆነ አላለም። እግዚአብሔር ለሁሉ ስለሚበቃ በቤተ ክርስቲያን ቅንዓት የለም ። ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በአዲስ ኪዳን 155 ጊዜ ያህል የተወሳ ሲሆን እንድርያስ ግን ስሙ የተነሣው ለ12 ጊዜ ያህል ነው ። በአደባባይ የሚታዩትን የሚያመጡ የማይታዩ ናቸው ። ዝነኞችን የሚወልዱ ዝና የሌላቸው ሰዎች ናቸው ። ሙሴን ከጡት ጋር ስለ አገር ፍቅር የነገረችው ስሟ እንኳ በቅጡ ያልተጻፈልን እናቱ ነበረች ። በ127 አገሮች ላይ ንግሥት እንድትሆንና አይሁድን ከመደምሰስ ያዳነች አስቴር ያሳደጋትና ለዚህ ክብር እንድትበቃ ደጀን የሆነላት ድንጋይ ላይ የሚቀመጠው መርዶክዮስ ነው ። ዛሬም ዙፋን ላይ ለማስቀመጥ ድንጋይ ላይ የተቀመጡ ፣ የሚታዩትን የወለዱ የማይታዩ ሰዎች በዓለም ላይ  አሉ ። በእውነት ለእነዚህ ሰዎች አድናቆት ይገባቸዋል ። እንድርያስ ስመ ጥር የሆነውን ጴጥሮስን ወደ ክርስቶስ ያመጣ ነው ። ሚሊየኖችን ማምጣት ለሁሉም የተሰጠ አይደለም ። ሚሊየኖቹን የሚያመጣውን አንድ ሰው መርዳትና ማገዝ ግን ለአንዳንድ ሰው የተሰጠ ጸጋ ነው።  ራእይ ዱላ ቅብብሎሽ በመሆኑ ድሉ የጋራ ነው ።
ቤተ ሳይዳ የብዙ ደቀ መዛሙርት መገኛ ናት ። የተናቀችና ታናሽ መንደር ብትሆንም የከበሩ ሐዋርያትን አስገኝታለች ። መንፈሳዊ ነገር እንዲህ ነው ። ከሚጠበቁ ቦታዎች ፣ ሰዎች ፣ ሁኔታዎችና ጊዜ ውጭ የሚሠራ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው ። እንድርያስ ፀጥና ዝግ ያለ ነው ። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው እንዲሉ ከተናጋሪውና ከዕረፍት የለሹ ጴጥሮስ ጋር በፍጹም አይመሳሰሉም ። የእናት ሆድም አንድነት አይሰጥም ፣ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ዓይነት መልክ ያጎናጽፋል ። የሥጋ ወንድሙ ጴጥሮስ ቢሆንም እንድርያስ ግን የፊልጶስ የቅርብ ወዳጅ ይመስላል ። ፊልጶስና እንድርያስ የሚያመሳስል ጠባይ አላቸው ፡-
·        ሁለቱም ከቤተ ሳይዳ ከአንዲት መንደር የተገኙ ናቸው ።
·        ሁለቱም ዓሣ በማጥመድ ሥራ ላይ የኖሩ ናቸው ።
·        ሁለቱም የሚወዷቸውን ወደ ክርስቶስ ያመጡ ናቸው ። እንድርያስ ጴጥሮስን ፣ ፊልጶስ ናትናኤልን አምጥተዋል ።
·        ሁለቱም በብርቱ ጉዳይ ላይ ይፈላለጉ ነበር ። ይህ መፈላለግም በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻና የግሪክ ሰዎች ኢየሱስን ልናይ እንወዳለን ባሉ ጊዜ ተገልጧል ። ዮሐ. 6 ፡ 8 ። 12 ፡ 22 ።
ፊልጶስ ስለሚገዛ እንጀራ ሲያስብ እንድርያስ ደግሞ አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በመካከላቸው እንዳለ ተናገረ ። ያ ብላቴና ማነው ? አምስት የገብስ እንጀራና ሁለት ዓሣ አስታቅፈው ይህን ሕጻን ወደ ክርስቶስ ልከውት ነበር ። ወላጆቹ ይህን ልጅ ለክርስቶስ ለመስጠት አልሳሱም ። ዛሬ ብላቴናዎችን ጎበዝ ተማሪ እንጂ ጎበዝ ክርስቲያን እንዲሆኑ ወላጆች እየተመኙ አይደለም ። ክርስቶስ የሌለበት ጉብዝና ወንዝ አይሻርም። የገብስ እንጀራ ለአንድ ብላቴና አንዱ የቀን ምግብ ነው ። ብላቴናው ለቀጣይ አምስት ቀናት ከክርስቶስ ጋር እንዲሰነብት ወላጆቹ ልከውታል ። የላኩት ክርስቶስ ጋር ነበርና ስጋት አልገባቸውም ። ክርስቶስ ጋ የተቀመጠ አይባክንምና ። ይህ ሕጻን ስለ ክርስቶስ ነጻነት ያገኘ ነበር ። ነጻነቱን ግን ሰፈር ለመዋል ፣ ከልጆች ጋር ለመጫወት አላደረገውም ። ብላቴናውም ገና በጠዋቱ በክርስቶስ ፍቅር የነደደ ነበር ።
ከአምስት ሺህ መካከል በዚህ ብላቴና የተገረመ እንድርያስ ነበር ። ብላቴናነቱን ሳይንቅ ቀረበው ። ወላጆቹ አጠገቡ እንደሌሉ ሕጻኑ በክርስቶስ ራሱን እየመራ መሆኑ እንድርያስን ይበልጥ ሳበው ። እንድርያስ ስለዚህ ሕጻን የማወቅ ጉጉቱ እየጨመረ መጣ ። ሕጻኑን ጓደኛው አደረገው ። አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ እንደ ያዘ ገባው ። ሕጻኑ ምን እንዳለው ለማወቅ ሕጻኑን ያከበረው የእንድርያስ ቅንነት ይደንቃል ። ለብዙዎች የሚበቃ በረከት እንደ ያዘ አወቀ ። ብላቴና ነው ፣ የመባረክ ምክንያት ነው ። ብላቴናዎች የያዙትን አይለቁም ፣ አምስቱን እንጀራና ሁለት ዓሣ አምጣ ቢባል ማንኛውም ብላቴና ይጋደላል እንጂ እሺ አይልም ። እንድርያስ ግን ብላቴናው ደግ መሆኑን ያውቅ ነበር ። ገና በጠዋቱ በፍቅር የተቀባ ነበር ። አምስት ሺህ ሰው ደርሶ ለመመለስ ስለ መጣ ምግብ አልያዘም ነበር ። ሕጻኑ ግን ለመሰንበት ስለ መጣ ስንቁን ይዞ ነበር ።
ፍቅር ከሚቀበል ሕጻን ፍቅር ይሰጣል ፣ ደግነት ከሚሻ ብላቴና ደግነት ይገኛል ተብሎ አይጠበቅም ። በታናናሾች ውስጥ የተቀመጠውን ታላቅ ጸጋ ለማወቅ የእንድርያስ ዓይን ያስፈልጋል ። ትንሹ ሕጻን ትልቁ እግዚአብሔር የላከው መልእክተኛ ነው ። ባጠረው ቁመቱ ፣ በጠበበው ደረቱ ማንነቱ አይለካም ። ትንሹን ብላቴናነት ፣ ትንሹን ስንቅ እግዚአብሔር ሲባርከው ለአእላፋት ጥጋብ ይሆናል ። ውስጣዊ መነጽራችንን እናነጣጥራለን ፡-
·        የብላቴናው ቤተሰቦች ቅንነት ፡- ልጃቸውን እስከ ሩቅ ዳርቻ ያመኑት ለክርስቶስ አሳልፈው ስለሰጡት ነው ። ዛሬ መውለድና ፍርሃት አብረው ያሉ ይመስላል ። ልጅን በክርስቶስ ፍቅር ማሳደግ ሩቅ ቦታ ለመልቀቅ ዋስትና ነው ። እስከ ሰማይም ለመልቀቅ ክርስቶስ ድፍረት የሚሰጥ ነው ። ልጆቻችን የእኛ ከሆኑ እናጣቸዋለን ፣ የክርስቶስ ከሆኑ እናገኛቸዋለን ። ምእመናን ልጆቻቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመላክ የትምህርት ጥናታቸውን ፣ የመጫወቻ ጊዜያቸውን ፣ የዘመድ መምጣትን ሰበብ ያደርጋሉ ። በጠዋቱ ወደ እግዚአብሔር እቅፍ ያልገባ ብላቴና እስከ ሽበት ያስለቅሰናል ። ለክርስቶስ የሰሰትናቸው ለምንም አይሆኑም ።
·        የብላቴናው ቅንነት ፡- ዓይኖቹ በክርስቶስ ላይ ተተክለዋል ፣ ከጠቢባን የተሰወረው ምሥጢር የእርሱን ትንሽ ልብ ያፈራርሰዋል ። የያዘውን ምግብ ሳይበላው በክርስቶስ ትምህርት ጠግቧል ። እንድርያስን ከአምስት ሺህ ሕዝብ መሐል የሳበው ይህ ብርሃናዊ ፊትና ጌታን የተጠማች ነፍስ ናት ።
·        የእንድርያስ ቅንነት ፡- ከትልቆች ትልቅ ይገኛል የሚል ቅንነት አይደለም ። እግዚአብሔር እንዳይመኩ ብሎ ትልቅ ነገርን ትንሽ የሚባሉ ሰዎች ጋ አስቀምጧል ። በሚያድጉ ሕጻናት ውስጥ ያለውን ራእይና ቅንዓት መገንዘብ መቻል ትልቅነት ነው ።
እግዚአብሔር የሚፈልገው ትልቅ ነገራችንን ፣ ብዙ ገበታችንን አይደለም ። ትንሽነታችንን ለትልቅነቱ ፣ አምስት እንጀራችንን ለተአምራቱ ይጠቀምበታል ። እኛስ ብላቴናዎች ምን እንደያዙ እናውቅ ይሆን ? የዛሬ መነሻቸው ላይ ሆነን መድረሻቸውን ማየት ችለን ይሆን  ? ይህንን ማየት የቻሉ የሙሴ እናት ፣ መርዶክዮስ ፣ እንድርያስ ለብዙዎች መዳን ምክንያት ሁነዋል ። ልጆች ራእያቸውን እንዲያወጡት ወደ ክርስቶስ መምጣት አለባቸው ። ትንሹ አስተሳሰባቸውን ክርስቶስ እንደሚያበረክተውም ማመን አለብን ። እኛ የምንመኝላቸውን ሳይሆን እግዚአብሔር ለዓለም እንዲሰጡት የላከውን ነገር እንዲያወጡት መርዳት አለብን ።
ቤተ ክርስቲያን የእንድርያስን አገልግሎት በጣም ልትይዝ ይገባታል ። ብዙ የወንጌል አገልጋዮች ሕጻናት ጋ የተመደብነው በግፍ ፣ በቅንዓት ነው በማለት የሕጻናት አስተማሪ መሆንን እንደ ቅጣት ይመለከቱታል ። በሙሉ ልብ የሚሰሙን ግን እነርሱ ናቸው ። አዋቂው ከሚሰማው የሚያልፈው ይበዛል ። በትሕትና የሚቀበለውም ጥቂቱን ነው ። ሕጻናት ግን በእምነት የሚሰሙና የሚፈጽሙ ናቸው ። ወላጆችን ለመያዝ ተብሎ የሚደረግ የሕጻናት አገልግሎት የትም አይደርስም ። ሕጻናት ለክርስቶስ እንደሚያስፈልጉት ማመን ያስፈልገናል ። ይህ ሁሉ ጳጳስና መነኩሴ የተገኘው በሕጻንነት ወደ ቤተ ክርስቲያን ስለመጡ ነው ። የእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ፓትርያርኮች ፣ የእነዚህ ሁሉ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወላጅ የሆኑትን ዛሬ እናደንቃለን ። በሕጻንነታቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን ባያመጧቸው ኑሮ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ሁሉ እረኞች አጥታ ነበር ። ሕጻናትን ማገልገል መጪውን ሰባና ሰማንያ ዓመት ማገልገል ነው ።
ፊልጶስ ሁለት መቶ ዲናር እንጀራ ቢገዛ ብሎ አሰበ ። እንድርያስ ደግሞ አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ የያዘ ብላቴና በመካከላችን አለ ነገር ግን ለዚህ ሁሉ ሕዝብ ምን ይበቃል አለ ። ዋናው ከሩቅ ገበያ የሚመጣው እንጀራ ሳይሆን በመካከላችን ያለው ፣ ብላቴናው የያዘው ምን አለ የሚል ነው ። ሁለት መቶ ዲናር ከፍ ያለ ተመን ነው ። ከፍ ያለ ዋጋ ቢወጣም ሕዝብን የሚያጠግብ ነገር ማምጣት አይቻልም ። በመካከላችን ያለውን ስንጠቀም ግን እግዚአብሔር ክብሩን ይገልጣል ። የመኖር ምሥጢር ያለው በትልቅነት ሳይሆን በታማኝነት ውስጥ ነው ። በብዛት ሳይሆን በበረከት ነው ። ለዓይን የማይገቡ ሰዎች የያዙትን ትልቅ ነገር ወደ ክርስቶስ ካቀረብነው ብዙ ሕዝብ የሚያጠግብ ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ