የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የተረፈ ያስፈልጋል

“ከጠገቡም በኋላ ደቀ መዛሙርቱን፡- አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ የተረፈውን ቍርስራሽ አከማቹ አላቸው ። ስለዚህ አከማቹ ፥ ከበሉትም ከአምስቱ የገብስ እንጀራ የተረፈውን ቍርስራሽ አሥራ ሁለት መሶብ ሞሉ።” ዮሐ. 6 ፡ 12 – 13
ጌታችን ሥራውን በምስክር የሚሠራ ነው ። ባደረገው ተደንቆ ሳይሆን የተደረገውን እንድናውቅ ይፈልጋል ። ለአንድ ቀን በተደረገው ሳይሆን ለሕይወት ዘመን የሚተርፍ መጽናናት እንድናገኝ ይወዳል ። በጎደለብንና ይህ ምን ይበቃል ? በምንልበት ነገር ያችን የተአምራት ቀን በማሰብ እምነታችንን ሊያነሣሣ ይፈልጋል ። እግዚአብሔር እንደሚያደርግልን የሚያሳምነን ከዚህ በፊት የተደረገልን ነው ። እግዚአብሔር ለአንድ ቀን የሚያደርገው ለዘመናት የሚተርፍ ነው ። የማይታለፍ የሚመስሉ ቀኖችን ስንጋጠም ቀይ ባሕርን የከፈለው ክንዱ ትዝ ይለናል ። ክስተቱ አንድ ቀን ነው ፣ መጽናናቱ ግን ለዘላለም ነው ። ድፍን ቅል የሆነ ጉዳይ ሲገጥመን ኢያሪኮን ያፈራረሰው ክንዱ ዛሬም አለሁ ይለናል ። የኢያሪኮ ግንብ የፈረሰው አንድ ቀን ቢሆንም ትምህርቱ ግን ለዘላለም ነው ። የወዳጅን ጦር ዘወር ብሎ ማሳለፍን ከዳዊት የሁለት ቀን ክስተት እንማራለን ። ቀኖቹ ያልፋሉ ትምህርቱ ግን ቋሚ ሁኖ ይኖራል ። ያበረከተውን ሁለት ዓሣና አምስት እንጀራ የተረፈውን እንዳይባክን ሰብስቡ አለ ።
እግዚአብሔር የጸሎትን መልስ ሲሰጥ አትረፍርፎ ነው ። ከለመነው በላይ በመስጠትም ብልጥግናውን ይገልጣል ። አለን ከምንለው ብዙ ነገር የእግዚአብሔር ትርፍራፊ ይሻላል ። የእኛ ነገር ፣ የሰዎችም ነገር ትራፊ የለውም ። የእግዚአብሔር ግብዣ ብቻ የተረፈ አለው ። አንድ እናት የልጃቸውን ሰርግ ሰርገው እቤቴ እደግሳለሁ ሲሉ በአዳራሽ ነው ብለው ልጆቻቸው ተቃወሟቸው ። በማግሥቱ ሳገኛቸው “እንዴት ነበር ?” ለሚለው ጥያቄዬ “ጠላን ፊልተር ይሁን ያለ ፣ ሰርግን ኮክቴል ይሁን ያለ ፣ ግብዣን ሆቴል ይሁን ያለ ርጉም ይሁን” አሉኝ ። እኒህ እናት የተረፈ የለውም ማለታቸው  ነው ። ጠላም ፊልተን ሲሆን ቅራሪ የለውም ፤ ሰርግም በአዳራሽ ሲሆን የተረፈውን ዱርዬ ቀምቶ ይበላዋልና “እንዳለሽ ፍርፋሪ” እያሉ ቤተ ዘመድ በማግሥቱ ሲመጣ የሚያቀርቡት አልነበራቸውም ። ስለዚህ ማፈሩ ስለበዛባቸው ጥያቄዬን ለመመለስ ከመቀመጫቸው ብድግ አሉ ፣ እጃቸውን መሬት ላይ አደረጉና ተራገሙ ፤ የእግዚአብሔር ግብዣ ግን የሚተርፍ አለው። ተረፈ የሚል ስም ስትሰሙ አንድ ነገር ታስተውላላችሁ ። ከዚህ በፊት ብዙ ባክኖ ይህ ግን ቀሪ እንደሆነ ትረዳላችሁ ።
የተረፈ ያጣንለት ብዙ ጉዳይ አለን ። እኛ እንደ እኒህ እናት ስሜታችንን መግለጥ ስላልቻልን ብዙ ጭንቀት ያራውጠናል ። ሀብታችን ፣ ፍቅራችን ፣ መልካችን ፣ ትዳራችን ፣ የነበረ እስከማይመስል የታረሰ መሬት ሁኗል ። ማጣታችን ከማግኘት ቀጥሎ የመጣ አይመስልም ፤ በልኩ ስለማንኖር በልኩ አንወድቅም ። ጠባችን ፍቅር የነበረው አይመስልም ። በጉርሻ ተቀያይመን አሁን ካልተጋደልን እንላለን ። መልካችን ቅሪት የነበረው አይመስልም ፤ የረዘመው አጥሮ ፣ የቀላው ጠቁሮ ፣ የጠቆረው አምድ ለብሶ ይታያል ። የፈረሰው ትዳራችን አንድ ቀን እንኳ አብሮ የኖረ አይመስልም ። እህትና ወንድም ሁኖ ለመቀጠል እንቸገራለን ። እስከ መጨረሻ መጣላት እንደ መብረቅ የወረደብን ጠባይ ነው ። እንደ እግዚአብሔር ሰው የተረፈ ቢኖረን መልካም ነው ።
እግዚአብሔር እንኳ የፈጠረው ፍጥረት እንደ ፈቃዱ አልሄድ ሲለው ማጥፋት እየቻለ ያኖረዋል ። ፈጥሮ እንዳልነበረ ሊያደርገው አይሻም ። አሁን ያለው ትውልድ ሲጣላም በልኩ አይደለም ። መገዳደል መጣላት አይደለም ። መገዳደል መጠፋፋት ነው ። ማጥፋትና መጠፋፋት ፣ መጣላትና መጠላላት ልዩነት አለው ። ይልቁንም በዛሬው ዘመን የምናየው የምንሰማው አብሮ የኖረ እስከማይመስል አንዱ አንዱን ሲያጠቃው ስናይ ሰው እንዴት የትላንቱን ዞር ብሎ የሚያይበት አንገት አጣ ያሰኛል ። እኛ ኢትዮጵያውን በጭካኔ እየተወዳደርን ነው ። በአገራችን ሁሉም ሃይማኖት በግለት ላይ ነው ያለው ። ሃይማኖት የሌለው ጥቂት ነው ። ሃይማኖት የማያስጥለው ጭካኔ ምንድነው ? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል ። አንድ የቆዩ ኢትዮጵያዊ “የአገራችን ክርስትና በአረመኔነት የተቀመመ ነው” ያሉት እውነት ይሆን ? ደጉ ፣ እንግዳ ተቀባዩ የሚባለው ሕዝብ እንዴት እዚህ ደረሰ?  ጥቂቶች አነሣሥተውት ነው ይባል ይሆናል ። አለመነሣት ይቻላል ። ውስጣችን የሌለውን ሺህ ጊዜ ቢያነሣሡን ሊነሣሣ እንዴት ይችላል ? ሺህ ጊዜ ቃለ እግዚአብሔር ሰምተን የለም ወይ ? ቃሉን የተቋቋመ ልብ ካለን ሌላውን መቋቋም በርግጥ እንችላለን ።
በሶሪያ መፈራረስ ከሁለት ሚሊየን በላይ ዜጎች ለስደት ተዳርገዋል ። ይህ ገርሞን ነበር ። ይህ ጽሑፍ በሚጻፍበት ጊዜ ከአንድ ክልል ወደ አንድ ክልል የተፈናቀሉ ሁለት ሚሊየን የሚጠጉ ፣ በገዛ አገራቸው የተሰደዱ ወገኖቻችን አሉ ። ትራፊ የሌለው ድግስ ማለት ይህ ነው ። የእኛ ሰው የሌለበት ክፍለ ዓለም የት ይገኛል ? በዓለም ጥግ ላይ በነጻነት ኢትዮጵያዊ እየኖረ በገዛ አገሩ ግን መኖር አለመቻሉ ያሳዝናል ። ቅራሪ የሌለው ድግስ ፣ የተሟጠጠ ፍቅር ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እየመጣ ነው ።
“አይቡን አይተህ አጓቱን ጠጣ” ይባላል ። አይቡ ጣፋጭ ነው ፣ አጓቱ ሆምጣጣ ነው ። አይቡ የሚያቃጥለውን ቀይ ወጥ ማብረጃ ነው ፣ አጓቱ ግን መልኩ ነጭ ግብሩ ቀይ ነው ። አጓቱ ሲጀምረው ወተት ፣ ሲቀጥል ቅቤ፣ ከዚያም አይብ ከዚያም አሬራ በመጨረሻ አጓት ሆነ ። የፊቱን ካላዩ የኋላውን መሸከም ይከብዳል ። ስለዚህ “አይቡን አይተህ ፣ አጓቱን ጠጣ” ተብሏል ።
ስንጀምር ሰው ነበርን ። ስንወለድ ሰው ተወለደ እንጂ እገሌ ዘር ተወለደ አልተባለም ። ስንጀምር ነጭና ጥቁር አልነበርንም ። ስንጀምር ዘር አልነበረንም ። የፊቱን እያሰብን የኋላውን መተው ይገባናል ። በርግጥ በመጨረሻው ዘመን ከሚታዩ ጥፋቶች አንዱ የዘር መለያየት ነው ። የትንቢት መፈጸሚያ ከመሆን እንዲጠብቀን መጸለይ ያስፈልጋል ። የሰይጣን ቀኝ እጅ የሆነው አውሬው ከሚያስፈጽመው ነገር አንዱ የዘርና የቋንቋ ስብከት ማጧጧፍ ነው ። ይህ የአውሬው መንፈስ እንዳይገዛን መጠንቀቅ ይገባናል ። “በነገድና በወገንም በቋንቋም በሕዝብም ሁሉ ላይ ሥልጣን ተሰጠው ” ይላል ። ራእ. 13 ፡ 7 ። ዘረኝነትን ባፋፋምን ቊጥር የአውሬው ጉዳይ አስፈጻሚ እየሆንን እንመጣለን ። አውሬው በቀጥታ በአጋጋንት አለቃ የሚመራ ሲሆን ዘረኞች የዲያብሎስ የልጅ ልጅ ይሆናሉ ማለት ነው ። በዘረኝነት ያልተለከፈ ሰው ካለ ዕድለኛ ነው ። ዘረኝነት የራስን ዘር መውደድ ማለት አይደለም ፣ የሌላውን መጥላት ነው ። የተረፈ ከሌለው ነገር አንዱ ዘረኝነት ነው ። የተረፈ ነገር ሲታሰብ ዋናውን ከማጥፋት እንድናለን ።
የጌታ ሐሔረር ለአነንደድ ቀነን ሐግብዣ የተረፈ ነበር ። በቅቷቸው ያቆሙት እንጂ አልቆ የተጠናቀቀ አልነበረም ። በልቷቸው የተረፈ እንጂ ስስት ያጠቃው አልነበረም። አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ ለአምስት ሺህ ሰው በቃ ። ለመሆኑ ማጠራቀሚያ ሌማት ፣ ዓሣ መያዣ ድስት ከወዴት አገኙ ። አንድ እንጀራ ሲያነሡ በተአምራት አንድ ይተካ ነበር ። አንድ ዓሣ ሲያነሡ አንድ ዓሣ ይመጣ ነበር ። በረከት ማለትም የሚበቃንን መኖር እንጂ በጎተራ መሙላት አይደለም ። አንዱን ስንጨርስ ሁለተኛው ይተካል ። አንዱን ስንጨርስም ሁለተኛው ይታየናል ። ጌታችን የተረፈውን አከማቹ አለ ።ሊያሳያቸው የፈለገው ነገር አለ ። ከዋናው እንጀራና ዓሣ ከጌታ ግብዣ የተረፈው እንደበዛ ለማሳየት ነው ። የእኛ ዋና ፣ ሁለት ዓሣና አምስት እንጀራ ለአንድ ቀን ፣ ለጥቂት ሰው አይበቃም ። የተነሣው አሥራ ሁለት መሶብ የተረፈ ነበር ። አሥራ ሁለት መሶብ የተረፈ ከመቶ ሰው በላይ የሚጋብዝ ነው ። የእግዚአብሔር በረከት ለኋላ ይቆያል ። የሆቴል ጥጋብ ለኋላ አይቆይም ፣ የቤት ጥጋብ ግን ለኋላ ይቆያል ። የተረፈውን አሙቀው ይበሉታል ። ጌታችን በመስክ ቢጋብዝም ግብዣው ግን የቤት ነበረ ። ለኋላ ይተርፋል ። እንዲተርፍ አድርጎ መጋበዝ ተገቢ ነው ። “የማይዘልቅ ማኅበር በጠጅ ይጀመራል” ይባላል ።
ያ ግብዣ የተለመደ ጣዕም የነበረው አይደለም ፣ የተለየ ጣዕምና መትረፍረፍ የነበረው ነው ። እስኪያጠግብ የሚጋብዝ እግዚአብሔር ነው ። ከቃና ዘገሊላው ግብዣ ትይዩ የሚቆም ነው ። የሰው ግብዣ ያልቃል ፣ የአምላክ ግብዣ ይተርፋል ። በቅዱስ መጽሐፍ ዕድሜን ጠግቦ እገሌ ሞተ የሚል ንባብ በብዛት ይገኛል ። እግዚአብሔር ዕድሜን የሚጋብዝ ባለጠጋ ፣ የሚያጠግብም የዘመናት ጌታ ነው ። ነቢዩ ዳዊት የሚያጠግብ አንድ ነገር አለ ይላል ክብሩን ማየት ። “እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ ክብርህን ሳይ እጠግባለሁ።” መዝ. 16 ፡ 15። እነዚህ ሰዎች የበሉት ዓሣና እንጀራ ብቻ አይደለም ፣ ፍቅርና ጸጋም ነው ።
ጌታችን በዚህ ወቅት ከሰጠው ታላላቅ ትእዛዛት አንዱ የተረፈውን ሰብስቡ የሚል ነው ። የተበላውን መሰብሰብ አይቻልም ። ሆድ ያየው እሳት ያየው ነውና ። የተረፈውን መሰብሰብ ግን ይቻላል ። ስለተበላው ለማወቅ የተረፈው ይረዳል ። የተረፈውን መሰብሰብ ዛሬም ትልቁ ትእዛዝና አማራጭ የሌለው ነው ። ትላንት ሙሉ ለሙሉ ደግ ፣ ዛሬም ሙሉ ለሙሉ ክፉ አይደለም ። ከትላንት የተረፈውን መንከባከብ ግን ይገባናል ። እንደ እርሾ ሁኖ ያቦካልናል ፣ እንደ ፍም ሁኖ ሌላውን ያቀጣጥልልናል ። የተረፈውን መሰብሰብ እስራኤልም የታዘዙት ነው ። አርባ ዓመት ከበሉት መና በመሶበ ወርቅ ቀንሰው እንዲይዙ ታዝዘው ነበር ። መናውን ያልበላ አዲስ ትውልድ ስለ መናው ሲነገረው እርግጥ መሆኑን እንዲያውቅ ይረዳ ነበር ። አሁንም ጌታችን ያንን ትእዛዙን እየደገመ ነው ። የተረፈውን ሰብስቡ ። ከፍቅር ፣ ከባሕል ፣ ከደግነት የተረፈው የቱ ነው ? እርሱን መሰብሰብ አለብን ። ደግነት አገራችን ላይ ጣር ይዞታልና ልንደርስለት ይገባል ። ከተረፈው መጀመር እንችላለን ። ጨርሶ ተስፋ የምንቆርጥበት ነገር የለም ። የተረፈውን ግን መሰብሰብ አለብን ።
ከተረፈው አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ ጌታ አዘዘ ። ምክንያቱም የእግዚአብሔር የበረከት እጅ ማሳያ ነውና ። የተረፈውን በማጥፋት ሥራ ከፖለቲከኞች ባልተናነሰ አብያተ ክርስቲያናት እየሠሩ ይመስላል ። ለፍቅር ለማኅበራዊ ትስስር የተሠሩ ብዙ ሐውልቶች በዘመናውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እየፈረሱ ይመስላል ። የሚፈርሱት ሐውልቶች ለእውነት መቆርቆር የሚመስሉ ነገር ግን የባሕል ወረራ ናቸው ። ለምሳሌ ያህል ጥቂት ለማሳያ ብንጠቅስ ፡- የአበ ልጅነት የተቋቋመው ለብዙ ዓላማ ቢሆንም አንደኛ ዓላማው ወላጆች ቢሞቱ ልጁ አሳዳጊ እንዲያገኝ ነው ። ይህ በዘመናት ሁሉ ሲሠራበት ኑሯል ። እንደውም ሲናዘዙ ለክርስትና ልጅም ኑዛዜ ያደርጉ ነበር ። ይህ ትልቅ የሆነ አሳብ የወለደውና ማኅበራዊ ቀውስን የሚታደግ ነበር ። ይህንን ትራፊ ለማጥፋት ግን ከሥሩ ተቆርጧል ። የሕጻናት ጥምቀት አያስፈልግም የሚል ትምህርት ብቅ ብሏል ። ዛሬ በዘመናውያን አብያተ ክርስቲያናት ያለው አለባበስ አንዳንድ ሆቴል እንኳ መግባት የማይቻልበት ነው ። የተረፈው ሥርዓት ግን ነጠላ ለብሶ መግባት ነው ። ይህን ብንይዘው መልካም ነው ። ነጠላ መልበስ አካል መሸፈን ብቻ አይደለም ፣ በቤተ ክርስቲያን የልብስ ውድድር እንዳይኖር የሚያደርግ ዩኒፎርም ነው ። ብዙ የተረፉ ነገሮች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይገኛሉ ። እነዚህን የተረፉ በረከቶች ለሃይማኖት ብቻ ሳይሆን ለፖለቲካውም ብንጠቀማቸው የሚያስከብሩን እንጂ የሚያዋርዱን አይደሉም ። የተረፈውን አንድ ስንኳ ሳይቀር ጥናት ቢደረግበት መልካም ነው ።
በዓለም ላይ ማስጣል ቀላል ነው ፣ ማስጨበጥ ግን ቀላል አይደለም ። ይልቁንም የዛሬው ትውልድ የገዛ ልብሱ የከበደው ነውና ጣል ብንለው ሁሉንም ይጥለዋል ።  መልሶ ማስጨበጥ ግን የማይቻል ነው ። ብዙ የወንጌል አገልግሎት የሚባሉት የባሕል ወረራ ሊሆኑ ይችላሉና መጠንቀቅ ያስፈልጋል ።
በየስፍራው ያለውን ቁርስራሽ በሰበሰቡ ጊዜ አሥራ ሁለት መሶብ ሞላ።በየስፍራው ያለው መልካም ነገር ምንድነው ? መሰብሰብና መጠናት አለበት።  ከአንድ ቦታ አንድ ቁራሽ ከሌላው ቦታ አንድ ቁራሽ ሲሰበሰብ መሶብ ይሞላል ። ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአንድ ቦታ ሳይነቃነቅ ለአምስት ሺህ ዓመታት ያሳለፈ ነውና ብዙ እውቀት ፣ ጥበብና የመድኃኒት ቅመማዎች አሉት ። መሰብሰብ ያስፈልጋል ። ሥነ ቃሉ ፣ ተረቱ ፣ እርቅ የሚፈጽሙበት መንገድ መሰብሰብ አለበት ።
ከትላንት የተረፉ አረጋውያን ዛሬ አንድ ስንኳ ሳይቀር ሊሰበሰቡ ይገባቸዋል።  አገራቸውን ያገለገሉ ሲጣሉ ስናይ ነግ ለእኛ እንዲህ መሆኑን ማወቅ አለብን ። አረጋውያንን ያገለለ መንገድ መጨረሻ የለውም ። አረጋውያን ይልቁንም በአፍሪካ ቤተ መጻሕፍት ናቸው ተብሏልና እንዲሁ ሳንጠቀምባቸው ይህ ቤተ መጻሕፍት ሊቃጠል አይገባውም ። ከአርባ ዓመት በላይ ያለ ማዳበሪያ ይሁን ማለት ይቀበር ሲሉ የነበሩ ወጣቶች በሙሉ አደባባይ ረግፈው ቀርተዋል ። ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአንድ ወቅት ወጣቶችን ሲመክሩ እንዲህ ብለዋል፡- “ሽምግልናችንን ያልናቀች ወጣትነታችን የተባረከች ናት” ብለዋል ። አረጋውያን ከትላንት የተረፉ ትላንትን የምናይባቸው መስተዋት ናቸው ። በሕጻናት ነገን ፣ በአረጋውያን ትላንትን እናያለን ። የዛሬ ሰው ብቻ ሁነን ሽማግሌዎችንና ሕጻናትን የጣልን ይመስላል ። “ማን ይናገር የነበረ ፣ ማን ያርዳ የቀበረ” እንደሚባለው ስለ ትላንት አረጋውያን የዓይን ምስክሮች ናቸውና ያስፈልጉናል ።
የተረፉት ሲሰባሰቡ መሶብ ይሞላሉ ። በየአገሩ ያሉት ከትላንት የተረፉት ፖለቲከኞች ፣ አማካሪዎች በጣም ያስፈልጉናል ። የፈረንጅ አማካሪን በሚሊየን ብር እያመጣን የእኔ ብለው በነጻ የሚያማክሩትን ግን የእስር ወረቀት ቆርጠንባቸው ወደ አገራቸው እንኳ ዞረው እንዳይተኙ አድርገናል ። የትም አገር ያለ ሕዝብ አዋቂውን ይጠቀማል ። አዋቂ የሚሰደደው በእኛ አገር ነው ። ይህ ግን ጊዜ የወለደው ጠባይ ነው ። እስረኞችን እንኳ አስረው እውቀታቸውን የሚጠቀሙ አገራት ብዙ ናቸው ። በጣም ውድና ጠቃሚ ነገሮች በእስር ቤቶች ይመረታሉ ። የተረፉትን እንሰብስብ ። የቀሩትም የቀናት ዕድሜ ያላቸው እስኪመስሉ ደክመዋል ። ማወቅ ዕዳ አይደለም ፣ ማወቅ ብርሃን ነው ። አዋቂዎቻችንን እናክብር ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ