የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ንጉሡን ሊያነግሡት ፈለጉ

“ከዚህ የተነሣ ሰዎቹ ኢየሱስ ያደረገውን ምልክት ባዩ ጊዜ፡- ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው አሉ ። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ያነግሡት ዘንድ ሊመጡና ሊነጥቁት እንዳላቸው አውቆ ደግሞ ወደ ተራራ ብቻውን ፈቀቅ አለ ።” ዮሐ. 6 ፡ 14 – 15 ።
ጌታችን አያበድሩት ባለጠጋ ፣ አይሾሙት ንጉሥ ፣ አያልቁት ልዑል ነው ። ለባለጠግነቱ ክብር ፣ ለንጉሥነቱ መገዛት ፣ ለልዑልነቱ ቅዳሴ እናቀርባለን እንጂ ባለጠጋ ፣ ንጉሥና ልዑል አናደርገውም ። እነዚህ ሰዎች ንጉሡን ሊያነግሡ ፣ የአጽናፈ ዓለሙን አስተዳዳሪ የአጥቢያ ገዥ ሊያደርጉት እየፈለጉ ነው ። እርሱ ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው ፣ መድኃኒትንም ሊያደርግ በማዕከለ ምድር እስራኤል የተገኘ ነው ። መዝ. 73 ፡ 12 ። ከፍቅሩ ይልቅ ተአምራቱ ፣ ከጌትነቱ ይልቅ እንጀራ መጥገባቸው ማረካቸው። ያለ መነሻ የወደዳቸውን በመነሻ ሊያነግሡት ፈለጉ ። ስላለፈው ለማመስገን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ እያበረከተ ያበላናል ብለው ነው ። የዚህ ዓለም ሰዎች በስሌት እንጂ በእውነት አያምኑም ። ለዛሬ ጨርሰው ስለ ነገ ነፍሳቸው ሳይሆን ሆዳቸው ማሰብ ጀመሩ ። ዛሬም ነገም የሚኖሩት ለሆዳቸው ነው ። “ሆድ ከኋላ ቢሆን ኑሮ ፣ ገፍቶ ገደል በሰደደን ነበር” የሚባለው ለዚህ ነው ። መማር ለሆድ ፣ ማመንም ለሆድ ሲሆን ያሳዝናል ።
ነገ ለመኖራቸው እርግጠኛ አይደሉም ፣ ነገ ግን በእግዚአብሔር ፊት መቅረባቸው እርግጥ ነው ። ስለ እርግጠኛው ነገር ግዴለሾች ፣ እርግጥ ስላልሆነው ነገር ግን ስጉዎች ነበሩ ። ስላልመጣ ቀንም የሚያስቡት ምን እበላለሁ ? ብለው ነው ። ምን እሠራለሁን ? ትቶ ምን እበላለሁ ? ማለት ከባድ ነው ። የምንሠራው ካለን የምንበላው በግድ ይኖረናል ። እጅ አፉን ለማግኘት መብራት አይፈልግም ። ሆድና መብልም አይተጣጡምና ማመንን ለእምነት ማድረግ መልካም ነው ። “የእግዚአብሔር መንግሥት በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ደስታ እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችም” የተባለው ለዚህ ነው ። ሮሜ. 14 ፡ 17 ።

ከመጠን ያለፈ ምን እበላለሁ ? ምን እጠጣለሁ ? የሚል ስጋት አረማዊ ጠባይ መሆኑን ጌታችን ተናግሯል ። ማቴ. 6 ፡ 32 ። ወንጌላዊው “ከዚህ የተነሣ” ብሎ መጀመሩ በጣም የሚገርም ነው ። ሲጠግቡ ላንግሥህ የሚሉ በዘመናት ሁሉ ነበሩ ወደፊትም ይኖራሉ ። እነዚህ ሰዎች የጥቅማቸው እንጂ የእውነት ወዳጆች አይደሉም ። መለኪያቸው ታች ያለው ሆዳቸው እንጂ ላይ ያለው አእምሮአቸው አይደለም ። እግዚአብሔር የሆድን አቀማመጥ መሐል ላይ ማድረጉ ድንቅ ነው ። ከፍ ብሎ እንዳይገዛን ፣ ዝቅ ብሎም እንዳያሰንፈን መሐል ላይ አደረገው ። እንጀራን ማክበር መልካም ነው ። እንጀራ ብቻ ማለት ግን አደጋ አለው ። ማቴ. 4 ፡ 4 ። በሌላ አገላለጽ “ለመኖር መብላትና ለመብላት መኖር” ልዩነት አለው ።
አይተው የሚያምኑ እነዚህ የመረጃ ሰዎች እንጂ የሃይማኖት ሰዎች አይደሉም ። “ሃይማኖት ሳያዩ ማመን ነው ፤ ዋጋውም ያመኑትን ማየት ነው” ተብሏል ። /ቅዱስ አውግስጢኖስ/ ። ስላዩ የሚያምኑ ማረጋገጥ እንጂ መደሰት አይችሉም ። ይህ በእውነት ወደ ዓለም የሚመጣው ነቢይ ነው ካሉ በኋላ ሊያነግሡት ፈለጉ ። ነቢይ የእግዚአብሔር አፈ ንጉሥ እንጂ ምድራዊ ጌታ አይደለም ። የነገሥታት መካሪ እንጂ ንጉሥ አይደለም ። እነዚህ ሰዎች በማየት ብቻ ስለ ተወሰኑ ነቢይ ያሉትን ሊያነግሡት ፈለጉ ። እርሱ ግን የነቢያት ጌታ ነው ። ወደ ዓለም የሚመጣ አንድ መፍትሔ ሰጪ አንድ ሁሉን አዋቂ እንዳለ እየተናገሩ ነው ። ወደ ዓለም የሚመጡ ብዙ መፍትሔ ሰጪዎች የሉም ። ያለው አንድ ብቻ ነው ። እነዚህ ሰዎች ክርስቶስን ለማንገሥ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ሊነጥቁት ፣ ይዘው በሰረገላ አስቀምጠው ልብሳቸውን እያነጠፉ ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ሊሉ ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል ። ስሜት አሁን ላንግሠው ኋላ ልስቀለው ይላል ። ጌታ ፈቀቅ አለ ። እርሱ ለእውነት እንጂ ለስሜት ቦታ የለውም ። ስሜት መልካም ነው ፣ ስሜት ብቻ ግን አደገኛ ነው ። እነዚህ ሰዎች በጣም እየፈጠኑ ነው ። ሳያውቁት ክርስቶስን ከመስቀል ጉዞው ሊገቱት ነው ። እርሱ ብዙ ጊዜ ፈቀቅ እንዳለ ተጽፏል ።
·        ያለ ጊዜው ላለ መሞት ፈቀቅ አለ ።
·        ኀዘኑን ለመግለጥ ፈቀቅ አለ ። ማቴ. 4 ፡12 ።
·        ለመጸለይ ወደ ምድረ በዳ ፈቀቅ አለ ። ሉቃ. 6 ፡16 ።
·        ብዙ ሕዝብ እንዳያጋፋው ፈቀቅ አለ ። ሉቃ. 5 ፡ 3 ።
·        በሽተኛ ካዳነ በኋላ ፈቀቅ አለ ። ዮሐ. 5 ፡ 13 ።
·        ሊያነግሡት ሲፈልጉ ፈቀቅ አለ ። ዮሐ. 6፡15 ።
እኛም ከጌታ ፈቀቅ ማለት የምንማረው ነገር አለ ።
·        ሞት የማይቀር ቢሆንም በጊዜው ካልሆነ ፈቀቅ ማለት አለብን ።በዚህ ዓለም ላይ እያንዳንዱ ቀን የሞት መሰናክል አለው ። ፈቀቅ ካላልን ይህች አንድ ሕይወታችን ወይም አንድ መብራት ድንገት ትጨልማለች ። ለክለሳ ተመልሰን የማንመጣባት ባለ አንድ መንገድ ብትኖር ሕይወት ናት ። እያንዳንዱ ቀን ላይመለስ ይሄዳል ፣ ካየናቸው በኋላ ላይደገሙ ቀኖች እየመጡ ነው ።
ሰማዕትነት በግድ ሲሆን እንጂ እንዲሁ የምንሄድበት አይደለም ። ምክንያቱም ለእኛ ሰማዕትነት ሲሆን ለዚያኛው ወገን ግን ነፍስ መግደል ነው ። አንዳንድ ነገሮችን ፈቀቅ በማለት እናልፋቸዋለን ። ፈቀቅ ማለት ስልክን ማጥፋት ፣ ማኅበራዊ መገናኛዎችን መራቅም ሊሆን ይችላል ።
·        ኀዘናችንን መግለጥ ጤነኛ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ነው ። ስለ ወገኖቻችን ሞት የተሰማን ኀዘን እንደ ክርስቲያን በልኩ መገለጥ አለበት ። አሊያ ወንድነት የተነካ ወይም ስልጣኔ የፈረሰ  አሊያም እምነታችን ከንቱ የሆነ መስሎን ዝም ማለት ኋላ ጭንቀት ሊያመጣ ይችላል ። ያልተገለጡ ደስታዎች ኀዘን፣ ያልተገለጡ ኀዘኖች ጭንቀት ይሆናሉ ። ጌታችን እንደሚያስነሣው እያወቀ በአልዓዛር ሞት ማልቀሱ ስሜት አልባ ክርስቲያኖችን ለመፍጠር እንዳልመጣ ያሳየናል ። ብዙ ሰዎች ኀዘናቸውን የማይገልጡት አንድ ፍቅር ማጣት ነው ፣ ሁለት በክርስቶስ ያላመኑ የሚያስመስልባቸው መስሎአቸው ነው ። ሦስተኛ አረመኔ ስለሆኑ ነው ።
·        ለመጸለይ ጸጥተኛ ቦታን መፈለግ በዚያም ጽሞናን ማድረግ ተገቢ ነው ። ነገር ግን ፈቀቅ ማለትን ይጠይቃል ። ሰላማዊ አየር ለመተንፈስ ፣ ለቀጣዩ ሩጫ ኃይልን ለመሰብሰብ ፀጥታ እየታመነበት መጥቷል ። ራስን ለማየትና ለማሰላሰል ከግርግር ይልቅ ፀጥታ አስተዋጽኦ አለው ።
·        በመንፈሳዊ አገልግሎትና በእይታ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሕዝብ ፈቀቅ ማለት ያስፈልጋቸዋል ። በሚገኙበት ጊዜ እንደ ባሪያ፣ ሲርቁ እንደ ጌታ መኖር ይገባቸዋል ። መጋፋት ለቀጣዩ ሥራ ችግር ያመጣል ። “ከፍ ከፍ ያለ ማሽላ አንድም ለወፍ አንድም ለወንጭፍ” ይባላል ። ቀና ቀና ያለ ማሽላ እረኛ ወንጭፍ ይለማመድበታል ወይም ወፍ ይበላዋል ።
·        ታላላቅ አገልግሎቶች ከተፈጸሙ በኋላ ፈቀቅ ማለት ይገባል እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት አይገባም ። እንደውም ተሰውሮ መጸለይ የተሻለ ነው ። ጌታችን እንዳይገልጡት ያዝዝ ነበር ። ያለ ጊዜው መገለጥ ያሉበትን አድራሻ ለጠላት ማሳወቅ ነው ። ያለ ጊዜው መገለጥ ያልበሰለ ነገር ይዞ መቅረብ ነው ። ያለ ጊዜው መገለጥ በሚመጣው ፈተና ለመውደቅ ነው ። ዛሬ ግን ግለጡኝ አስተዋውቁኝ ተብሎ ገንዘብ ይከፈላል ። ውዳሴ ከንቱን ድል ያልነሣ አገልግሎት መንገድ ላይ እንደ ቀረ ወንዝ ነው ። መንገድ ላይ የቀረ ወንዝ አካባቢ ይበክላል ፣ የወባ መራቢያ ይሆናል ። ያልተፈጸሙ አገልግሎቶችም ለብዙዎች መዛል ምክንያት ፣ ክፉ አርአያም ይሆናሉ ።
·        ሊያነግሡን ሲፈልጉ አንድ ቀን ደግሞ ሊሰቅሉን እንደሚፈልጉ በማሰብ ፈቀቅ ማለት ይገባል ። ስሜት የሚጠየቅበት ሕግም ዳኝነትም የለም ። ሕዝብ ደግሞ አይከሰስም ። ያለፉት ሺህ ዘመናት ታሪክ የሚያስረዱት ይህን ነው ። ያወጣ ሕዝብ መልሶ ያወርዳል ። ዓለም ሲያዋርድ ሳይሆን ሲያመሰግን መፍራት የአስተዋዮች መገለጫ ነው ።
 ጌታችን ፈቀቅ ያለው ወደ ተራራ ፣ ወደ ምድረ በዳና ወደ ባሕር ነው። በምድረ በዳ ምቾት ፣ በተራራ ዕረፍት ፣ በባሕር ጸጥታ ላይኖር ይችላል ። ከዛሬው ምንጣፍ የምድረ በዳው አፈር ፣ ከዛሬው ማንገሥ የተራራው ከፍታ ፣ ከዛሬው ባሕር የምድረ በዳው ማዕበል የተሻለ ነው ።
ወንጌላዊው ዮሐንስ አሁንም ተአምራቱን ምልክት በሚል ስያሜ ይጠራዋል ። ተአምራት ምልክትነቱ ለነፍስ መዳን ነውና ። ምልክት መነሻ እንጂ መድረሻ አይደለምና ። ምልክቶች ያለ ቃሉና ያለ ውሳኔ ዘላቂ ወዳጅ አያደርጉም ። በምልክት የተመሰጡ ሰዎች ሁለት ነገሮች ይታይባቸዋል ፡-
1-  ማድነቅና
2-  እናንግሥህ ማለት
ማድነቅ ማመስገን አይደለም ። ማመስገን መቅረብ ይጠይቃል ።  ማድነቅ በሩቅ የሚነገር ለራስና ለሰዎች የሚወራ ትኩስ ዜና ነው ። አንዳንዴ ባለቤቱ ጋ ሊደርስ ይችላል ። ማድነቅ ግን ከሥራው ይልቅ ፣ ሥራውን ከፈጸመው አምላክ ይልቅ ለራስ መመሰጥ የሚከፈል ዋጋ ነው ። ማድነቅ የረጋ ሳይሆን ሌላም ይጠበቅብሃል የሚል ማበረታቻና ቀብድ ነው ። እናንግሥህ ማለትም በዓለም ላይ እንኳን ክርስቶስን በንግግር የማረኩንን የምንመርጥበት ምርጫ ነው ። ክርስቶስ በተግባር የታየ ነው ። ማንኛውም መንግሥት ከሚጠበቅበት ዋነኛ ነገር መሠረታዊ ፍላጎትን ማሟላት ነው ። ክርስቶስ ደግሞ በተአምራት የሚመግብ ነው ። ጥሩ ንጉሥ እንኳ አሳርፎ ሊመግብ አይችልም ። ሳይለፉ እንጀራን የሚሰጠው ክርስቶስ ከዚህ የላቀ ነው ። እነዚህ አድናቂዎች ትልልቅ ተአምራትን ሲቀበሉ ትልልቅ እውነቶችን ግን መቀበል አይችሉም ። ተአምር ፈላጊነት አንዳንድ ጊዜ በጠባቡ የሕይወት መስመር ላይ የእግዚአብሔርን ክንድ ለማየት መናፈቅ ሲሆን በሌላ ጊዜ ደግሞ ስንፍና የሚወልደው የሕይወትን ቋሚ መርሕ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆን የሚያስከትለው ነው ።
 ክርስቶስ ጌታችን ብዙ አድናቂዎች ሲኖሩት የሚያምኑት ግን ጥቶች ነበሩ ። ደቀ መዛሙርቱ የተከተሉት ሌላ ፈልገው ሳይሆን ያላቸውንም ጥለው ነው ። እንደ ማንኛውም እስራኤላዊ መሢሑ የሚመጣው ለምድራዊ ንግሥና ነው ብለው ቢያስቡም በርግጥ እርሱን የሚወዱትና ከእርሱ ጋር ለመሞት የቆረጡ ነበሩ ።
አምስት ዓሣና ሁለት እንጀራ አበርክቶ ሲመግባቸው ቀርበው ጌታ ሆይ ከእኛ ምን ትሻለህ ? ከማለት አድናቆት ማጉረፍ ጀመሩ ። ብዙ የሚያደንቁ ጥቂት እንኳ ላያምኑ ይችላሉ ። ክርስቶስን በአገሬ ላይ ንገሥ ማለት የተሻለ ኑሮ የሚፈልግ ሁሉ የሚለው ነው ። በልቤ ላይ ንገሥ የሚል ግን የእምነት ምርኮኛ ብቻ ነው ።
አድናቂዎች ፣ ማድነቅ ማወቅና ማመን ደግሞም መታዝዝ ስለሚመስላቸው በአደባባይ ቁመው መመስከር ፣ ችግር ካለ ጥሩኝ እናገራለሁ ማለት ጠባያቸው ነው ። ማድነቅ ጠባዩ እኔንም አድንቀኝ የሚል ነው ። ማድነቅ የራስንም ማስታወቂያ መሥራት ነው ። እምነት የሌለው ማድነቅ ከእውነት ይልቅ ለገበያ የቀረበ ነው ። ማድነቅ መልሶ ለመርገምም አይቸገርም ። ብዙ ወገን የተነገረውን ሰምቶ የሚጓዝ እንጂ እውነት ይሆንን ብሎ መመርመር ስለሚቸገር አድናቂዎች በቀላሉ ብዙ ሕዝብ ማስከተል እንደሚችሉ ያምናሉ ። በዚህም ይጽናናሉ ፤ ይደሰታሉ ። አድናቂነት ለጊዜአዊ ጦርነት እንጂ ለዘላቂ ጽሞና ላይረዳ ይችላል ። ጌታችን በዘመኑ እንዲህ ያሉትን አድናቆቶች አልተቀበለም ።
ከዚያ ባሻገር መልካም የሆኑ አድናቆቶች አሉ ። እነዚህ አድናቆቶች ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኙ የተባረኩ አንደበቶች መገለጫ ናቸው ። እግዚአብሔርን ከምንመስልበት ነገር አንዱ ማድነቅ ነው ። እግዚአብሔር ልጆቹን የሚያደንቅ አምላክ ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ የሚጀምረው በማድነቅ ነው ። “እግዚአብሔርም መልካም እንደሆነ አየ” ማለት ማድነቅ ነው ። መልካሙን መልካም ማለት ውዳሴ ከንቱ አይደለም ። መልካም ዓይን እንዳለን ማሳያ ነው ። መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን በአድናቆት የተሞላ መጽሐፍ ነው ። ቤተ ክርስቲያንን ክርስቶስ እንዴት እንደሚጠራት የሚያሳይ ነው ። እግዚአብሔር እንደ ጥብቅ ወዳጅ በቁልምጫ ስም የሚጠራ አምላክም ነው ። ይሹሩን ሆይ እያለ ያዕቆብን ሲጠራ እናያለን ። ለብዙ ወዳጆቹም ሁለተኛ ስም ያወጣላቸው ነበር ። ወዳጅ የራሱ መለያ የምትሆን ስም ያወጣል ። ይህ ስም የማሰብ ውጤት ሳይሆን የማፍቀር ውጤት ነው ። ያለንበት ዘመን ምክንያት የለሽ አድናቆቶች ለአንዳንዶች ፣ ምክንያት የለሽ ጥላቻዎች ለሌሎች በመስጠት የሰለጠነ ነው ። ዛሬም ተገቢ የሆኑ አድናቆቶች ያስፈልጋሉ ። ለአድናቆት የሚያስፈልገንና እንቅፋት የሚሆነንን መለየት ያስፈልጋል ። ለአድናቆት የሚያስፈልገን ፡-
·        መልካም ዓይን ነው ። መልካም ዓይን ከጉድለት ይልቅ ለተሠራው በጎ ነገር ዋጋ ይሰጣል ። ተደናቂውም የተደነቀውን ነገር እየጨመረ መሥራት ሲጀምር ያልተደነቀውን እየተወዉ ይመጣል ። ስለሆነው ነገር መናገር ስላልሆነው ነገር መናገር ነው የሚባለው ለዚህ ነው ።
·        ባስደነቀን ነገር ላይ የእኛንም ትንሽ ነገር ለመጣል ዝግጁ መሆን ነው ። ምናልባት ማዕዱ አልቆ ከሆነ የእኛ ድርሻ አሰልፎ መስጠት ሊሆን ይችላል ። መልካም አድናቂዎች ባለቀ ተግባር ላይ አሻራቸውን ለማኖር የታደሉ ናቸው ። አድናቂነት እጅ እግር አለው ።
·        እኔ ልሠራው የሚገባውን ነገር ያ ሰው ከሠራው የእኔን ሥራ እየሠራ ነው ። በማድነቅ ድሉን የጋራ ማድረግ ይቻላል ማለት እውነተኛነት ነው ።
ለማድነቅ እንቅፋት የሚሆነው ነገር ደግሞ፡-
·        ጉድለትን የሚያይ ዓይን ፣
·        ካደነቅሁ የእኔን ድርሻ ብጠየቅስ የሚል ስጋት ፣
·        እኔ ሳስበው የነበረውን እርሱ ሠርቶ እንድሳጣ አደረገኝ ፣ ደግሞም ክብሩን ሁሉ ብቻውን ወሰደው የሚል አመለካከት ነው ።
 ጌታችንን ያደነቁት ሰዎች ስለ ጠገቡ ያደነቁ ናቸው ። ሲጠግብ ያደነቀ ከራበው ይሳደባል ። “ያጣ ለማኝ ተሳድቦ ይሄዳል” እንዲሉ ። አድናቆታቸው ክርስቶስን ላገራቸው እንጂ ለሕይወታቸው የፈለገ አይደለም ። የተለወጡ አገራት ባልተለወጡ ሰዎች ይፈርሳሉ ። ያልተለወጡ ሰዎች እግዚአብሔር አገራቸውን እንዲለውጥላቸው ይፈልጋሉ ። የለውጥ ዘላቂነቱ የሕይወት መለወጥ ሲኖር ነው ። ግላዊ ሕይወትን ወይም አስተሳሰብን ችላ ያለ ለውጥ በድቡሽት /በአሸዋ/ መሬት ላይ የተሠራ ሕንፃ ማለት ነው ። ለጊው ቢቆምም አይጸናም ።
       ጌታችን ሊያነግሡት የፈለጉት ለምንድነው ብለን መጠየቃችን መልካም ነው ። ሮማውያን በአስገባሪዎች እያራቆቷቸው ፣ እየከፈሉ የሚደበድቧቸው ነበሩና የሚምር ንጉሥ ፈልገው ነው ። መሢሑ በተአምራት ከሮማውያን ነጻ ያወጣናል ብለዋልና ደግሞም ሕዝብን የሚመግብ ነውና ሊያነግሡት ፈለጉ ። እኛስ የፈለግነው ለምን ይሆን ?
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ