የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሲመሽ ይመጣል

“በመሸም ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ባሕር ወረዱ ፥ በታንኳም ገብተው በባሕር ማዶ ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር ። አሁንም ጨልሞ ነበር ፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር ፤ ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ ። ሀያ አምስት ወይም ሠላሳ ምዕራፍ ከቀዘፉ በኋላም ፥ ኢየሱስ በባሕር ላይ እየሄደ ወደ ታንኳይቱ ሲቀርብ አይተው ፈሩ ። እርሱ ግን፦ እኔ ነኝ ፤ አትፍሩ አላቸው ። ስለዚህ በታንኳይቱ ሊቀበሉት ወደዱ ፤ ወዲያውም ታንኳይቱ ወደሚሄዱበት ምድር ደረሰች ።” /ዮሐ. 6 ፡ 16-21/ ።
ጌታችን እስከ ምሽት ድረስ ቆይቶ ነበርና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ማዶ ተሻግረው ለማደር ፈለጉ ። ጌታችን ፈቀቅ ብሎ የነበረው የሥጋ ክብርን ሸሽቶ ነው ። የሥጋ ክብር ፈልገው የሚሄዱበት ሳይሆን ቢመጣ እንኳ የሚሸሹት ነው ።  ዓለም በመረቀ አፏ ሳትረግም እንቅልፍ አይዛትምና የሥጋ ክብርን መሸሽ ይገባል ። ትልቅ ሥራ እንጂ ትልቅ ዝና ለማንም ልከኛ ሰው አስፈላጊ አይደለም ። ትልቅ ዝና ሩቅ ሲሆን ትልቅ ሥራ ግን በየዕለቱ የከበበን ነው። ትልቅ ዝና ለአንዳንዶች ሲሆን ትልቅ ሥራ ግን ለሰው ዘር ሁሉ የተመደበ ነው ። ደቀ መዛሙርቱም ቀኑን በታላቅ ተአምር ላይ ቢውሉም ምሽት ላይ ግን ጌታ ወዴት እንደ ሄደ አላወቁም ። ትልልቅ ተግባራትን ካደረግን በኋላ መሸሸግ መልካም ነው ። ስሜት ሞገደኛ ያበዛልና እናንግሥህ የሚለው እልፍ ነው ። ስሜት ሲንጠፈጠፍ መውጣት ይገባል ። ታላላቅ ተግባራት ሲከወኑ ንግግርን ልከኛ ማድረግ ይገባል ፣ ግለቱ እንዳያስተን በጽሑፍ ብቻ የረቀቀ አሳብን ማንጸባረቅ በጣም ይጠቅመናል ። የብዙዎችን ስሜት ማሸነፍ ይከብዳልና እናንግሥህ ሲሉን ሰወር ማለት ይጠቅመናል ። እናንግሥህ ያለው ሕዝብ ይሰቀል እንደሚል የታወቀ ነው ። ደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ዳርቻ ሁነው ጌታን ይጠብቃሉ ። እነርሱ ንጉሥ መሆኑን እያወቁ ነው ፣ እናንግሥህ አይሉትም ። የነገሠን ማንገሥ አይቻልምና ። ሄሮድስ እንኳ ንጉሥ እንደ ተወለደ አውቋል ፣ በዓለም ላይ አልጋ ወራሽ እንጂ ንጉሥ አይወለድም ፤ ክርስቶስ ግን ንጉሥ ሁኖ የተወለደ ነው ። አይሾሙት ንጉሥ ፣ አያበድሩት ባለጠጋ የተባለለት ነው ።
ጌታችን ሁሉ እያለው ሁሉ እንደሌለው ሁኖ የመጣው ለዚህ ኃላፊ ዓለም እንዳንራኮት ሊያስተምረን ነው ። ሰው ከመሆኑ አንሥቶ ፣ በበረት መወለዱ ፣ በድህነት መኖሩ ፣ በመስቀል መሰቀሉ … ክብርን እንደናቀና አርአያ እንደሆነን እንረዳለን ። በልባቸው ላይ ሳይሆን በአገራቸው ላይ ሊያነግሡት ከሻቱ ፣ ስለ ቃሉ ሳይሆን ስለ እንጀራ ሰረገላ ካዘጋጁ ሰዎች ሸሸ። አድናቆቱን እውነተኛና ክቡር የሚያደርገው ምክንያቱ ነው ። ስለ ቃሉ አድንቀው ቢሆን ኑሮ ልባቸውን እንዲለውጥላቸው ይለምኑት ነበር ። የተለወጠ አገር እንጂ የተለወጠ ልብ አይፈልጉም ነበር ። የአገርን ለውጥ ዘላቂ የሚያደርገው የሕዝብ ለውጥ ነው ። ያልተለወጡ ሰዎች አገርን ለማፍረስ በቂ ናቸው ። ክፋት አቅም አይፈልግም ፣ አቅም የሚፈልግ ደግነት ብቻ ነው ። ጥፋት በቅጽበት ሲሆን ልማት ዘመናትን የሚያስቆጥር ነው ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሊያነግሡትና ሊነጥቁት የተጋጋሉትን ሕዝብ ሸሽቶ ፈቀቅ ብሎ ነበር ። እስከ ምሽት ድረስም ተሰወረ ። ደቀ መዛሙርቱም በመሸ ጊዜ በታንኳ ተሳፍረው ወደ ቅፍርናሆም ይመጡ ነበር ። ሊያነግሡና ነጥቀው ሰረገላ ላይ ሊያስቀምጡ የሚሹ ወገኖችን እስከ ምሽት ታገሣቸው ። እንዲህ ያሉ ወገኖች የምሽት ወዳጅ መሆን አይችሉምና ። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን እንኳ ሳይዝ ብቻውን ነበረ ። ደቀ መዛሙርቱም እንዲህ የተገለጠ ስሜት አይኑራቸው እንጂ ጌታ በዳዊት ዙፋን ነግሦ የቅርብ ባለሟል ያደርገናል ብለው ያምኑ ነበር ። በልባቸውም በስሜታቸውም ምድራዊ ንግሥናን ከሚሹት ጌታ እስከ ጊዜው ፈቀቅ አለ ። ስሜት አያድርምና ።
ወንጌላዊው ፡- አሁንም ጨልሞ ነበር ፤ ኢየሱስም ገና ወደ እነርሱ አልመጣም ነበር ፤ ብርቱ ነፋስም ስለ ነፈሰ ባሕሩ ተናወጠ” በማለት የገለጠው አስደናቂ ነው ።
ጌታችን ወደ እነርሱ ባለመምጣቱ ሁለት ነገሮች አስጨንቀዋቸው ነበር። ጽኑ ጨለማና ብርቱ ነፋስ ። ያሉበትን ሁኔታ ስናየው የረገጡት ባሕርን ነው፣ ዙሪያው ነፋስ ነው ፣ ሰማዩ ጨለማ ነው ። ይህ ብቻ አይደለም እስከ ምሽት መጠበቅ ባለመቻላቸው ጌታን ጥለው የራሳቸውን መንገድ ጀምረዋል ። ጌታ ግን ያረፈደ ቢመስልም እኩል ደርሰዋል ። የሰው ፍጥነት እርሱን አይቀድመውም ። እነርሱ በታንኳ ቢፈጥኑም ጌታ ግን ባሕሩን በእግር እየረገጠ ደረሰ ። ጨለማና ነፋስ እንዲሁም ነውጥ ጌታን እንደማንቀድመው ያስተምሩናል ። ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንዳለን እርግጠኛ መሆን ይገባል ። እርሱ እስኪመጣ ድረስ ጨለማውም ጨልሞ ፣ ነፋሱም አቅልሎ ነበር ። ባሕሩም በወትሮው ንውጽውጽታ ላይ ማዕበል ተጨምሮበት ነበር ። የራሳቸው ልምድ ደግሞም ጎበዝ ቀዛፊነት ችግሩን ማስወገድ አልቻለም ።
ደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ላይ ሳሉ አሁንም ጨልሞ ነበር ፣ ኢየሱስ አልመጣም ነበርና ይላል ። እርሱ የጽድቅ ፀሐይ እስኪመጣ ድረስ አሁንም ጨልሞ ነበር ። ጌታችን እስኪመጣ ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ነገሮች አስጨነቋቸው ። ጨለማና ነፋስ ። ጌታችን በዘመናት የተጠበቀውም እነዚህን ሁለት የሰው ልጆች ጠላቶች እንዲያስወግድ ነው ። የሞት ጨለማ በጌታችን መምጣትና መሞት ተገፏል ። አሁን የቀረው ነፋስ የተባለው ሽብር ደግሞ በጌታችን መምጣት የሚወገድ ነው ። የተቀየረ መዓት እንጂ የቀረ ክፉ ነገር እየሰማን አይደለም ። እንደውም እየባሰ ፣ የክፋት ውድድሩም እያየለ ነው ። ጌታችን ካልመጣ እነዚህን ነገሮች መቀነስ እንጂ መቅረት አይችሉም ። በመጀመሪያው ምጽአቱ ከጨለማ ያዳነን በዳግም ምጽአቱ ከነፋስ ያድነናል ።
ደቀ መዛሙርቱ ቢመሽም ጌታን መጠበቅ ነበረባቸው ። በእነርሱ ትዕግሥት ማጣት ግን ሁለተኛ ተአምራት አዩ ። የበረከት ንጉሥ ፣ የማዕበልም አዛዥ ነው ። ባለመታገሣችን ላይ ክብሩን እየገለጠ የበለጠ ወደ እቅፉ የሚስበን ጌታ እንዴት ምስጉን ነው ። ደቀ መዛሙርቱ የገጠማቸው የተፈጥሮ ጨለማ ብቻ ሳይሆን የሞትም ፍርሃት ነበረ ። በጨለማ ላይ ነፋስ ከባድ ነው ። የረገጡት ባሕር ፣ ዙሪያቸው ማዕበል ፣ ሰማዩ ጨለማ ነበር ። ጌታችን ታላቅነቱን የሚገልጡ ሦስት ነገሮችን ገለጠ ፡-
1-  በምድረ በዳ መገባቸው ፣ ምክንያት ሳይሻ መሥራት ይችላል ።
2-  በማዕበል ውስጥ ሰላምን ሰበከላቸው ። ማዕበሉን በፈሩበት መጠን የጌታን መምጣት ሲፈሩ አይዟችሁ እኔ ነኝ አለ ። ምጽአቱ የማዕበሉን ያህል ካስፈራን ጌታን አላወቅነውም ማለት ነው ።
3-  የማይቻለውን ይችላል ። ባሕርን መረማመጃው ያደርጋል ።
ደቀ መዛሙርቱ በባሕር ላይ በማዕበል ሲንገላቱ እነርሱ በታንኳ ሁነው ያቃታቸውን ማዕበል ጌታ በእግር እየተረማመደ በባሕሩ ላይ ይከተላቸው ነበር ። በልባቸው “ጌታን ጥለን በመምጣታችን ይኸው በሌሊት በማዕበል እንጨነቃለን” እያሉ ይሆናል ፣ የማይቀየመው ጌታ ግን እየተከተላቸው ነው። “ብቻችንን ከሞት ጋር ተጋፍጠናል” እያሉ ከሆነ ጌታ ግን ልትገለበጥ ያለችውን ታንኳ ደግፎ ይዞ ነበር ። በባሕሩ ላይ ከማዕበሉ ጋር የሚታገልላቸውን ፣ ገዳዩ እንዳይገድል የሚዋጋላቸውን ጌታ ማየት አልቻሉም። ባያዩትም እያያቸው ፣ ቢቀድሙትም እየተከተላቸው ነበር ። በመጨረሻ አይተውት በፍርሃት ጮኹ ። “እኔ ነኝ” ሲላቸው ተረጋጉና ወደ ታንኳው ቢጋብዙት ለካ መሬት ላይ ተቃርበዋል ። እነርሱም ከታንኳ ወረዱ፣ ጌታም ከባሕር ወረደ ። ባለማመን ላይ ታማኝነቱን የሚያሳይ አምላክ ስሙ ይመስገን ። ሲመሽ ይመጣል ። ትልቅ ተአምር አይተው ትልቅ መዓት ለገጠማቸው እግዚአብሔር መልስ አለው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ