የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የሰማዩ እንጀራ

“የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና አላቸው ። ስለዚህ፦ ጌታ ሆይ ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት ።”ዮሐ. 6 ፡ 33-34 ።
ከዕለት እንጀራ ወደ ዘመናት መና እያሰቡ ያሉት ወገኖች ጌታ ሦስተኛውን እንጀራ አሳያቸው ። የበረከተው እንጀራ የዕለት መልስ ነበረ ። የተመኙት መናም የዘመናት መልስ ይሆናል ። ከሰማይ የሚወርደው እንጀራ ሕይወትን ይሰጣል ። የዕለቱም የዘመናቱም ከሞት አያድኑም ፣ ይህ እንጀራ ግን ሕይወትን ይሰጣል ። ይህ እንጀራ የራሱ የሆኑ ከፍታዎች አሉት ፡-
1-የእግዚአብሔር እንጀራ
ሁሉስ የእርሱ አይደለም ወይ ? ቢሉ ሁሉም የእርሱ ነው ፤ ነገር ግን ይህኛው እግዚአብሔር የሰጠን የመጨረሻው ጥጋብና ሁሉን የሚተካ ነው ። የእግዚአብሔር ያልሆነ እንጀራ አለ ወይ ? ቢሉ አዎ አለ ። ይህ እንጀራ ሰው በራሱ መንገድ ለራሱ ደግ የሚሆንበት ፣ እግዚአብሔርን ለመቅደም ሞክሮ ነገር ግን አዝኖ የሚቀርበት ነው ። ይህ እንጀራ ቢገኝም ጥጋብ የለውም ። መልስ ነው ሲባል መልሶ ጥያቄ ፣ ተጨበጠ ሲባል መልሶ ሕልም ይሆናል ። ይህ እንጀራ የአጋር እንጀራ ብንለው ያስኬዳል ። አብርሃም የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል መታገሥ አቅቶት ወደ አጋር በገባ ጊዜ እስማኤል ተወለደ ። የሚፈልገውን ልጅ ቢያገኝም ነገር ግን እርካታ አላገኘም ። ዘፍ. 16. ። መልሶ ልጅ የለኝም እያለ ያዝን ነበረ ። የአጋር እንጀራ ልብን አያሳርፍም ። በእቅፍ እንጂ በልብ አይሞላም ። እግዚአብሔር የሚሰጠው በረከት ብቻ ሳይሆን በእርሱ የታዘዘ መከራም ልብን ያሳርፋል ። እግዚአብሔር ወዳጆቹን ከሁሉ ያድናል ። አስቀድሞ ግን ከጥያቄ ያድናል ። የሰው እንጀራ የሙከራ ሕይወት ነው ። የሰው እንጀራ ቆስሎ መማር ነው ። የሰው እንጀራ ዓይኑ ብዙ ነው ። የሰው እንጀራ ክብ ነውና መልሶ እዚያው ነው ። የሰው እንጀራ ሰው ይሰበስባል ፣ ሲያልቅ ግን የተሰበሰበው ይበተናል። የሰው እንጀራ ያለማባያ ያለ መደለያ የማይበላ ኮምጣጣ ነው ። የሰው እንጀራ ቢጠግቡ የሚያንገሸግሽ ነው ። የሰው እንጀራ ሰውን ገፍቶ የሚመጣ ነው ።
አንድ ሕፃን ልጅን አስታውሳለሁ ። አባቱ ሲሞት የሦስት ዓመት ልጅ ነው ። አባቱን ቀብረው ሲመለሱ እናቱ ሞተች ። እርስዋን ቀብረው ሲመለሱ ለቀስተኛው “ኧረ ለዚህ ልጅ እንጀራ ስጡት” አለ ። እንጀራ ሲሰጡት እንጀራውን ብጥቅ አደረገና “እናንተዬ ይህ እንጀራ መራር ነው” ብሎ ጣለው። ኀዘነተኛው እንደገና አለቀሰ ። ከዚያች ቀን ጀምሮ ያች መራራ እንጀራ ይህን ልጅ ማስመረር ጀመረች ። ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት ማሰነ ። በመጨረሻ በመንግሥት ማሳደጊያ አደገ ። ኋላ ላይ ወደ ውትድርና ገብቶ ትልቅ መዐርግ ላይ እንደ ደረሰ በሶማሊያ ዘምቶ ሞተ ። እንጀራ ለአንዳንድ ሰው መራራ ነው ። አዎ የሰው እንጀራ ያለመደለያ ያለማስፈራሪያ መራራ ነው ። /ወጥ ማስፈራሪያ እየተባለ በትንሽ ይጨለፋል/ ።
የእግዚአብሔር እንጀራ የተባለው ከአብ አካል የተገኘ አካል ፣ ከአብ ባሕርይ የተገኘ ባሕርይ ፣ ልደቱ መለየት የሌለበት ፣ ልጅነቱ የዘመን ማነስ ፣ የክብር መቀነስ የሌለበት ነው ። እርሱም እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። ከውኃ ውኃ እንደሚገኝ ከአምላክም አምላክ ተገኝቷል ። ከሰው ሰው እንዲገኝ ከአብም የተገኘው እንደ አብ አምላክ ነው ።
2- ከሰማይ የሚወርድ
ከሰማይ የወረደ ብቻ ሳይሆን የሚወርድ ትኩስ መብል ነው ። ያደረ አይደለም ፣ ሰንብቶ የተበላሸም አይደለም ። መዓዛው ሂዶ አካሉ የቀረም አይደለም ። ከሰማይ የሚወርድ የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው ። ቀራንዮን መንበሩ ላይ ፣ ሰማይን ምድር ላይ ፣ ዕለተ ዓርብን ዛሬ ላይ የሚያመጣው ያ የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው ። እርሱ ከሰማይ የሚወርድ ነው ። ከሰማይ በመሆኑ መንፈሳዊ ማዕድ ነው ። የሚወርድ በመባሉ ደግሞ በኅብስቱና በወይኑ የምንዳስሰው ነው ። ከሰማይ የሚወርድ መባሉ እኛን አድራሻ አድርጎ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ። ከሰማይ የሚወርድ መባሉ የእኛን ፈቃድ እንጂ ብቃት እንደማይፈልግ የሚያስተምር ነው ። ከሰማይ የሚወርድ መባሉ በነጻ የተሰጠ እንደሆነ የሚያሳይ ነው ። ቀራንዮ ቀራንዮ ላይ የቀረባቸው ለታሪክ አዋቆች ነው ። ቤተ ክርስቲያን ግን በዕለተ ዓርብ ፍቅር በዕለተ ትንሣኤ ኃይል ፣ በዕለተ ዕርገት ክብር ፣ በየማነ አብ ርስት ውስጥ ናት ። መብል መጀመሪያ ሙቶ ቀጥሎ ሕይወት ይሰጣል ። የጌታ ሥጋና ደምም ለእኛ ተሠውቶ ሕይወትን ይሰጠናል ። ክርስቶስን ከመስማት አልፈን የምንመገበው በሥጋና በደሙ ነው ። ይህ እምነትን ተጨባጭ የሚያደርግ ትልቅ ሕይወት ነው ። ከሰማይ የሚወርድ መባሉ የወልደ እግዚአብሔር ሥጋና ደም መሆኑን የሚገልጥ ነው ። ከሰማይ ሲል መለኮትነቱን ፣ የሚወርድ ሲል ትስብእቱን ይገልጣል ። መለኮት ያለ ሥጋ ወረደ ፣ ሥጋም ያለ መለኮት ሰማያዊ መባል የለም ። ተዋህዶ አንዱ የአንዱን ገንዘብ የሚያደርግበት ነው ። መለኮት በሥጋ ታመመ ፣ ሥጋ በመለኮት ተነሣ ። የሞተውም የተነሣውም አንዱ ክርስቶስ ነው ። ከሰማይ የሚወርድ መባሉ ሰማይና ምድርን ያማከለ መሆኑን የሚገልጥ ነው ። ከእገዚአብሔር ጋር ኅብረት የምናደርግበት ፣ ማኅተመ ሥላሴን የምንቀበልበት ነው ። የሚወርድ መባሉም በየጊዜው የምንቀበለው መሆኑ ነው ። ዛሬ ቄሱ በመንበሩ ላይ በሚፈትተውና በቀራንዮ በተሰቀለው በክርስቶስ መካከል ምንም ልዩነት እንደሌለ በእምነት እንቀበላለን ። የፋሲካውን በግ የበሉ ከግብጽ ባርነት እንደ ዳኑ ይህንን እንጀራ የሚበሉም ከሲኦል ባርነት ነጻ ይወጣሉ ። የፋሲካው በግ አንድ ጊዜ በግብጽ ተሠውቶ በየጊዜው ደግሞ እንደሚሠዋ ክርስቶስም አንድ ጊዜ በመስቀል ላይ ውሎ በየጊዜው በቤተ ክርስቲያን ይሠዋል ። የፋሲካው በግ በየትም ቤት ቢሠዋ አንድ እንደሆነ የክርስቶስ ሥጋና ደምም አንድ ነው ። ይህን እንጀራ እንዳናቃልል ሰማያዊ መሆኑን ልናምን ይገባናል ። ይህንን የሚያከብርና ለእኛም እምነት ሰጥቶ ሕይወትን የሚያድለን መንፈስ ቅዱስ ነው ።
የእግዚአብሔር መባሉ ቀዳማዊ ልደቱን ፣ እንጀራ መባሉ በሥጋዌው የከፈለውን መሥዋዕትነት የሚገልጥ ነው ።
3- ለዓለም የተሰጠ
የበረከተው እንጀራ ለአምስት ሺህ ሰው ፣ መናው ለእስራኤል ወይም ለግማሽ ሚሊየን ሕዝብ ነበረ ። ይህ እንጀራ ግን ለመላው ዓለምና ዘመን የተሰጠ ነው ። ምክንያቱም ጌታችን ቤዛ ኩሉ ዓለም ሁኖ ሙቷልና ። ከእስራኤል ማኅበር ለማግባት በሥጋ ከአብርሃም ዘር መወለድ ያስፈልጋል ። ቤተ ክርስቲያን ግን ላመኑት ሁሉ የተሰጠች የምሕረት ደጃፍ ናት ። እግዚአብሔር አምላክ ለጻድቁ አብርሃም ዘርህን በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛዋለሁ ብሎት ነበረ ። ዘፍ. 22 ፡ 17 ። የባሕር ዳር አሸዋ የተባሉት በሥጋ ከእርሱ የተወለዱት ሲሆኑ የሰማይ ከዋክብት የተባሉት ግን ክርስቲያኖች ናቸው ። መንፈሳዊው እንጀራ ከሰማይ የወረደ ሲሆን ለሰማያውያን የተሰጠ ነው ። አባ ፍሬምናጦስ የመጀመሪያዋን ቤተ ክርስቲያን ሲመሠርት “ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት” በማለት ሰይሟታል ። ማኅበረ ጽዮን ምድራዊት የምታሳትፈው ከአብርሃም በሥጋ የተወለዱትን ብቻ ሲሆን ማኅበረ ጽዮን ሰማያዊት ግን በክርስቶስ ያመነውን ሁሉ ታቅፋለች ። አስቀድሞ ፡- በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና” የተባለው ለዚህ ነው ። ዮሐ. 3 ፡ 16 ።
ቤተ ክርስቲያን ከነገድ የተዋጀች በመሆኗ የሕዝቦች ልዩነት የለባትም። ከቋንቋ የተዋጀች ናትና በሀብተ ልሳን ተባርካለች ። ከወገን የተዋጀች ናትና በእያንዳንዱ ቤት መብራት ታበራለች ። ከሕዝብ የተዋጀች ናትና የአንድነት መቀነት ናት ። ራእ. 5 ፡ 9-10 ።
ክርስቶስን ማንም በግሉ ቢያምነውም እርሱ ግን የዓለም መድኅን ነው። እርሱ ከፍጥረቱ ጋር በመፍጠር ፣ በመግቦትና በማዳን ግንኙነት አለውና እግዚአብሔርን የእኔ ብቻ ማለት አይገባም ። በእርሱ ያገኘነው ሕይወትም ሌሎችን የምንወድበት እንጂ በሌሎች የምንመጻደቅበት አይደለም ። እርሱ የአጽናፈ ዓለሙ ገዥ እንደሆነ የዓለሙም አዳኝ ነው ። ብቸኛ አምላክ እንደሆነ ብቸኛ አዳኝም ነው ።
4- ሕይወትን የሚሰጥ
የበረከተው የዕለት እንጀራ ፣ የበረሃውም መና ጊዜያዊ እንጂ ዘላለማዊ ሕይወት የላቸውም ። ደመ ነፍስን እንጂ ሕያው ነፍስን የመደገፍ አቅም አልታየባቸውም ። ይህ እንጀራ ግን ሕይወትን የሚሰጥ ነው ። ጌታችን በሁለቱ እንጀራዎች ልባቸው የተያዘውን አንጋሾች ሦስተኛውን እንጀራ አመለከታቸው ። ሕይወት የሚገኘው ከሕይወት ነው ። ሕይወት ለበጎ ነገር መኖር ነው ። ነጻነትና ነጻ መሆን ልዩነት አለው ። ነጻነት የወደዱትን መምረጥ ሲሆን ነጻ መሆን ግን ሕግ የለሽ መሆን ነው ። ሕይወት በበጎ ነጻነት መራመድ ነው ። ሕይወት እንቅስቃሴ ነውና ከቀድሞ አድራሻ መራቅ ነው ። ሕይወት ለሕይወት ባለቤት መኖር ነው ። ከሰማይ የወረደው እንጀራ ሕይወትን የሚሰጥ ነው ። ሕይወት መጨረሻ የሌለው መጀመሪያ ነው ። ሕይወት ከዚህች ቀን እስከ ዘላለሙ የሚቆጥር የእግዚአብሔር ሰዓትና ሥርዓት ነው ። ሕይወትን የሚሰጥ ማንም የለም ። ይህ እንጀራ ግን ሕይወትን ይሰጣል ።
ጌታችን ፡- “የእግዚአብሔር እንጀራ ከሰማይ የሚወርድ ለዓለምም ሕይወትን የሚሰጥ ነውና” ሲላቸው እነርሱም፡- “ስለዚህ ፦ ጌታ ሆይ ፥ ይህን እንጀራ ዘወትር ስጠን አሉት ።” ዮሐ. 6 ፡ 33-34 ። እነዚህ ሰዎች የሚሰሙት የሚሰሙትን የጌታን ቃል ሳይሆን ምድራዊ አሳባቸውን ነው ። በሚሰሙትና በሚያስቡት መካከል ልዩነት ቢኖርም የሚሰሙትን ጥለው የሚያስቡትን ይሰሙ ነበር ። ይህ ደግሞ የተጠመዘዘ እውነትን ይወልዳል ። ጌታ ሆይ ያሉት በጌትነቱ አምነው አይደለም ፣ ለንግግር ማጣፈጫ ነው ። በዘመናት ሁሉ “ጌታ ሆይ ፣ ጌታ ሆይ” የሚሉት በአፋቸው እንጂ በተግባራቸው ያልተወዳጁት ብዙ ናቸው ። ማቴ. 7 ፡ 21 ። ይህን እንጀራ ከትላንቱ እንጀራና ከበረሃው መና ጋር ቀላቅለውታል ። ለጥጋብ ሳይሆን ለሕይወት ፣ ለቁንጣን ሳይሆን ለፍቅር የተሰጠ መሆኑን ደግሞም መንፈሳዊ ገበታ እንደሆነ አላስተዋሉም ። አሁንም በአገራቸው እንጂ በሕይወታቸው እርሱን ለመሾም አልፈቀዱም ፣ አሁንም ጉዳይ አስፈጻሚ እንጂ አባት አላደረጉትም ። ሰማያዊው እንጀራ ግን የፍቅር ምርኮኛ የሚያደርግ ፣ ምድራዊውን ሰው ሰማያዊነትን የሚያላብስ ነው ። ያለ እምነት የሚሰነዝሩት ወይም ያለ ጥማት የሚወረውሩት ጥያቄ ግን ትልቅ መልሶችን አምጥቷል ። አህያ ማር ብትሸከምም አትበላውም ። ወርቅ ብትጭንም አታጌጥበትም ። እግዚአብሔር የንዝህላሎችን አንደበት ተጠቅሞ አስተዋዮችን ያስተምራል ። አንዱን ጥያቄ እያስጠየቀ አንዱን ያሳርፋል ።
እነርሱ ባይጠይቁ ኑሮ ስለ ሰማያዊው እንጀራ አንሰማም ነበር ፣ ያረዱትን ጠቦት አልበሉትም ፣ እኛ ግን ጠገብነው ። የኒቅያ ፣ የቊስጥንጥንያ፣ የኤፌሶን ጉባዔያት ምክንያታቸው መናፍቃን ቢሆኑም ቤተ ክርስቲያን ግን ደልዳላና የነጠረ የነገረ መለኮት ትምህርትን እንድትቀርጽ ያደረጋት ነው ። “ምቀኛ ጎረቤት ዕቃ ያስገዛል” እንዲሉ ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ