የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ወደ ውጭ አያወጣም

“አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል ፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም ፤ ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና ።” ዮሐ. 6 ፡ 37-38 ።
ጌታችን አማንያንን የአባቴ ስጦታ እያላቸው ነው ። ራሱንም እንደ ብርቱ ምሽግ ፣ እንደማይደፈር አምባ እየገለጠ ነው ። አንዳንድ አምባዎች አጥራቸው በዙሪያቸው ያለው ገደል ነው ። ከአምባው ከወጡ ያለው ሞት ብቻ ነው ። የነገሥታት ልጆች በተለያዩ አምባዎች ውስጥ ይታሰሩ ነበር ። በአምባ ማርያም ብዙ የነገሥታት ልጆች ፣ በኮረማሽ ቡልጋ ልጅ ኢያሱ ታስረዋል ። አምባው እንደ መሶብ የተቀመጠ ተራራ ሲሆን አንድ መንገድ ብቻ ያለው ነው ። በዚያ መንገድ መጥቶ በአምባው ላይ ማረፊያ ያገኘ ዙሪያውን እያየ ይደነቃል ። የነበረበትን ጥልቀትና ያለበትን ምጥቀት ያያል ።
ያ አምባ ወደ እርሱ የመጡትን ወደ ውጭ የማያወጣ ፣ ለነጣቂ ፣ ለገዳይ አሳልፎ የማይሰጥ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። እግዚአብሔር አብ ልጁን ለዓለም ሰጠ ፤ ምእመናንን ደግሞ ለልጁ ሰጠ ። ዮሐ. 3 ፡ 16 ፤ 6 ፡ 37 ። እግዚአብሔር አብ ወደ ልጁ እንዲመጡ ያመለክታል ፣ ልጁም ወደ እርሱ የመጡትን በዘላለም እቅፉ ያሳርፋል ። ወደ ክርስቶስ የምንመጣው በእኛ ፈቃድ ቢሆንም እግዚአብሔር ሲረዳንም ነው ።
ጌታችን ይህን ቃል የተናገረው አይተው ስላላመኑበት ሰዎች ነው ። ወደ እኔ ብትመጡ እንደ አባቴ ስጦታ እንከባከባችኋለሁ ፣ ደግሞም አውጥቼ አልጥላችሁም እያላቸው ነው ። ምክንያቱም ትላንት የበሉት ምግብ ዛሬ አልቋል ፣ የሚመኙት መናም የበሉትን ከሞት አላዳነም ። ስለዚህ እንጀራ ብቻ ፈልገው ለመጡት ሰዎች እኔን ብትሹ እንደ ስጦታ ልዩ ጥበቃ ፣ እንደ አምባ ልዩ ከለላ ታገኛላችሁ እያላቸው ነው ። ስጦታ ትንሽ ቢሆንም እንኳ የሰጪውን ትልቅነት ማሳያ ነው ። እናንተም ደካማ ብትሆኑ የሰጠኝ ግን አባቴ ነውና የከበራችሁ ናችሁ ። ስጦታ ከፍ ካለ ቦታ ይቀመጣል ፣ ዘወትርም ያዩታል ፣ እናንተም ወደ እኔ ብትመጡ በልጅነት ጸጋ ፣ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ትከብራላችሁ እያለ ነው ።
አምባዎች ሰው ሠራሽ ሳይሆን ተፈጥሮአዊ የሆነው አጥራቸው ገደሉ ነው ። የምእመናን አምባ ክርስቶስም ከተፈጥሮ በላይ የሆነ መዳኛ ነው ። በአምባ ላይ ያለ ጠላቱን ያያል እንጂ ጠላቱ አያየውም ፣ ክርስቶስን የተጠጉም የጠላታቸውን ክፋት ያያሉ ፣ እነርሱ ግን በዘላለም ምሕረት ይሰወራሉ ። በአምባ ላይ ያሉ ጠላታቸው የሚመጣባቸው በአንድ መንገድ ነው ። ክርስቶስን የተጠጉም ዋነኛ ጠላታቸው በክርስቶስ የሚመጣባቸው ነው። በአምባ ላይ ያሉ ባሻገር ያለውን አገር ያያሉ ፣ በክርስቶስ ያመኑም ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን በልባቸው ያኖራሉ ። በአምባ ላይ ያሉ ሁሉም ትንሽ ሁነው ይታያቸዋል ፣ በክርስቶስም የሚያምኑ ምእመናን በሰማያዊ ስፍራ ተቀምጠዋልና የምድሩን አሳንሰው ያያሉ ። በአምባ ላይ ያሉ ብርሃናቸው በሩቅ ላሉ ይታያል ። ስለዚህ ከሞት ያስመልጣሉ ።
ሰውዬው የሚኖረው በባሕር ዳርቻ ላይ ነው ። አንድ ቀንም ከመሸ ጀልባውን አሥነስቶ በባሕሩ ላይ መጓዝ ጀመረ ። ጨለማው እየገፋ መጣና የቤቱ አቅጣጫ ጠፋው ። ማዕበልም እየጠነከረ መጣና ተጨነቀ ። በዚያ በድቅድቅ ጨለማ ላይ በሩቅ አንድ ብርሃን አየና ወደዚያ መገስገስ ጀመረ ። ወደቡ ላይ ሲደርስ ልጆቹና ሚስቱ ተቀበሉት ። ቤቱ ግን ይነድ ነበር ። ምክንያቱን ሲጠይቃቸው “በባሕሩ ላይ አቅጣጫ እንደ ጠፋህ አስተዋልን ፣ ስለዚህ ወደ ቤትህ ትገባ ዘንድ ቤትህን ለኮስነው ። በቤትህም ቃጠሎ ብርሃን ይኸው በሰላም ደረስህ” አሉት ይባላል ።
በባሕር ዓለም ላይ ፣ በባሕር ሥጋዊነት ላይ አቅጣጫ ጠፍቶት ኮብልሎ የነበረውን አዳምን ለማዳን ቤት አልተቃጠለም ። የቤቱ ባለቤት ክርስቶስ ግን ራሱን መሥዋዕት አደረገ ። በዚህ የመሥዋዕትነት ብርሃን ተስበው የመጡ ሰዎች ወደቡ ላይ ሲደርሱ ክርስቶስ ምን ያህል እንዳፈቀራቸው ይረዳሉ ። አዎ እርሱ ከሩቅ ያሉት ፣ አቅጣጫ የጠፋቸው የሚኖሩበትን ከተማ መንገድ ያገኙበት ነው ። በጨለማ ላይ የወጣ ብርሃን ፣ በማዕበል ውስጥ የተገኘ ጸጥታ ነው ። ልክ እንደ እርሱ በትከሻው አምባ ላይ ያረፉ በጎችም ከሩቅ ይታያሉ። በብርሃናቸው ሁሉን ይስባሉ ።
ጌታችን ወደ እኔ የመጡትን ወደ ውጭ አላወጣም ብሏል ። የወደዱትን እንደማይጠላ ፣ ያመኑትን እንደማይከዳ ቃል ገብቷል ። ነገር ግን እርሱ ወደ ውጭ አያወጣም ፣ ራሳቸው ከፈለጉ ግን ይወጣሉ ። ወጥተውም ያሳዩን ይሁዳና ዴማስ አሉ ። እርሱ የሚያድነን በነጻ ፈቃዳችን ላይ ተመሥርቶ እንጂ አስገድዶን አይደለም ። ከአምባው የወጡ ራሳቸውን ለሞት አሳልፈው ይሰጣሉ ። በአምባው ውስጥ የትኛውም ጠላት ሊያወጣቸው አይችልም ፣ምኞታቸው ግን ሊያወጣቸው ይችላልና ምኞታቸውን ሊጠነቀቁ ይገባል ።
ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና ።”
ጌታችን ይህን ቃል የተናገራቸው በአብና በወልድ መካከል የክብርና የባሕርይ ልዩነት ያለ ስለመሰላቸው ነው ። አብና ወልድ በአካል ልዩ ናቸው፣ በመለኮት ግን አንድ ናቸው ። በዚህ ቃል ውስጥ አካላትን አጣፍተው አንድ የሚሉትን ሰባልዮሳውያንን ድል ይነሣል ። በዚህ ቃል ውስጥ የክብር መበላለጥ ፣ የዘመን መቀዳደም ያመጡትን አርዮሳውያንን ድል ይነሣል ። ጌታችን የራሴ ፈቃድ የለኝም ማለቱ ሥላሴ በፈቃድ አንድ ስለሆነ ነው ። አካላትን አንድ የምታደርግ አሐቲ ፈቃድ ናት ። ጌታችን እንደ ምድራዊ ሰው ተገልጾ ቢታይም ፈቃዱ ግን ሰማያዊ ነው ። የአብን ፈቃድ እያደረገ ከሆነ በዚህ ቅጽበት እንኳ ከአብ ጋር አልተለያየም ማለት ነው ። ከሰማይ ወርጃለሁ በማለቱም መለኮታዊነቱን እየገለጠ ነው ። በትሑት ሥጋ ውስጥ የተሰወረውን ልዑል መለኮት እያብራራ ነው ። ከሰማይ መውረዱ ድንቅ ነው። ወደ ሰማይ መውጣቱም እፁብ ነው ። መላእክት ለተልእኮ ከሰማይ ይወርዱ የለም ወይ ? ቢሉ አዎ መልአክ ብቻ ሁነው ይወርዳሉ ፣ ጌታችን ግን በሥጋ ተገልጧል ፣ የሰውን ባሕርይ ገንዘቡ አድርጓል ። መላእክት ቢወርዱ መልእክት ይዘው ነው ፣ ጌታችን ግን ባለ መልእክቱ ነው ። መላእክት ቢወርዱ ቤዛ ልሁን ብለው አያውቁም ፣ እርሱ ግን ለቤዛ ዓለም የወረደ ነው ። ወደ ሰማይ የወጣ መሆኑስ ድንቅ ነው ወይ ? መላእክት ተልእኮአቸውን ሲፈጽሙ ፣ ኤልያስ ከክፉ ዓለም ለመሰወር ወደ ሰማይ ወጥተው የለም ወይ ? ቢሉ መላእክት ወደ ሰማይ ቢወጡ መልአክነታቸውን ብቻ ይዘው ወጥተዋል ፣ እርሱ ግን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ሁኖ ወጥቷል። ኤልያስ ወደ ሰማይ ቢያርግ ሥጋን ብቻ ይዞ ነው ፣ ጌታችን ግን መለኮት የተዋሐደውን ሥጋ ይዞ ነው ። ኤልያስ ቢያርግ ተመልሶ መጥቶ ይሞታል ፣ ጌታችን ግን ዳግም ሞት ላይዘው በሰማያት ገንኗል ። መላእክት ከሰማይ ቢወርዱ ከሰው ጋር በልተው ጠጥተው አያውቁም ፣ እርሱ ግን ከእኛ ጋር በላ ጠጣ ። ልዕልናውን ከትሕትናችን ጋር አዋሐደ ። ለእርሱም ምስጋና እስከ ዘላለም ዘመን ድረስ ይሁን አሜን ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ