የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የመግደል ፍላጎት

የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሰባት
“ከዚህም በኋላ ኢየሱስ አይሁድ ሊገድሉት ይፈልጉ ስለ ነበር በይሁዳ ሊመላለስ አይወድም ነበርና በገሊላ ይመላለስ ነበር ።” ዮሐ. 7፡1 ።
ጌታችን የሕይወትን ወንጌል ይዞ ወደ ዓለም ሲመጣ ከአለማመን ውስጥ የሚፈልቁ የተለያዩ መስቀሎችን ተሸክሟል ። ሰዎች ልባቸውን አስቀምጠው በጆሮ ብቻ መስማታቸው ፣ ለምድራዊ ጥጋብ ብቻ ጌታን መከተላቸው ፣ ትምህርቱን መቃወማቸውና እውነትን ማስተባበላቸው … እነዚህ ሁሉ የመስቀሉ ክፍሎች ነበሩ ። ተቃዋሚዎች የመጨረሻው አቅማቸውና እርምጃቸው ጌታን ሊገድሉት መፈለጋቸው ነው ። ጌታችን መግደል ወደሚፈልጉት መሞት ፈልጎ አልሄደም ፣ የገዳይነት ዕድሜአቸውን ለማራዘም ወይም የማሰቢያ ጊዜ እንዲያገኙ ለመርዳት ጌታ በይሁዳ መመላለስን አልወደደም ። ለገዳይነታቸው አልተመቻቸም ። ዘወር በማለት በአሳብ ሳይሆን በተግባር ሊቀድሳቸው ፈለገ ። ክፉዎችን የምንረዳቸው ለክፋታቸው ባለመመቻቸት ነው ። ጊዜ ገዳዩን ጲላጦስ ሰማዕት ያደርጋልና ። ጌታችን የሸሸው ርምጃቸውን ሳይሆን ፍላጎታቸውን ነው ። ፍላጎት ወደ ተግባር ይለወጣል ። ያልተገረዘ ፍላጎት የጊዜ ጉዳይ እንጂ ነፍሰ ገዳይ ይሆናል ። ፍላጎትን ሊቀድስ ኃይል ያለው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ።
እውነትን ገሸሽ ማለት የሚጠናቀቀው በገዳይነት መሆኑን የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ስድስትና ምዕራፍ ሰባት ያስገነዝቡናል ። በምዕራፍ ስድስት እውነትን ለመስማት አቅም አጡ ፤ በምዕራፍ ሰባት ለመግደል አቅም አገኙ ። እውነትን ለመስማት ያልቻሉ ሰዎች መግደልን እንዴት ቻሉ ? ስንል እውነት ብርቱ አቅም እንደምትፈልግ ያሳያል ። እውነትን በሥጋ ትከሻ መሸከም አይቻልም ፣ እውነት በመንፈስ ቅዱስ የምንቀበላት አቅም ናት ። መግደል የሟቹን ደካማነት ሳይሆን የገዳዩን አቅም ማጣት የሚያሳይ ነው ። መታገሥ አለመቻል ፣ ማለፍ አለመቻል ገዳይ የሚያደርግ ከሆነ መግደልን የሚወልደው መቻል ሳይሆን አለመቻል ነው ። በገደለ ቅጽበት ሕሊናው ሲታወክ ስናይ ገዳይ የገዛ ሕሊናው ዘመድ እንደማይሆነው እናያለን ። ገዳዮች የባለ ራእዩ ንግግሩና ተግባሩ ብቻ ሳይሆን ህልውናው ሲረብሻቸው ከዚህ በኋላ ልንይዘው አንችልም ብለው ተስፋ ይቆርጣሉ ፤ ስለዚህ እንግደለው ይላሉ ። ገዳዮች ተስፋ የቆረጡ ናቸው ። እኔ በራሴ አልኖርም ፣ እኔ የምኖረው እገሌ ከሞተ ብቻ ነው የሚሉ ገዳዮች ለራሳቸው ክብር የሌላቸው ናቸው ። መኖር በእግዚአብሔር እንጂ በእነ እገሌ ሬሳ ላይ አይደለም ። ገዳዮች ግን እግዚአብሔር እንደሚያኖር አያምኑምና መግደል ከሀዲነት ነው ። ሰውን ገድሎ ከሰው ጋር ለመኖር ማቀድ በእውነት ገዳዮች ሞኝ እንደሆኑ ያሳያል ። በየካቲት 12 ቀን ጣሊያን የጨፈጨፋቸው ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሐውልታቸው ቆሟል ። የገዳዩ የግራዝያኒ  ሐውልት ግን ሲቆም በብዙ ሁከት ተነሥቷል ። ሟቾች ተሸናፊ ቢሆኑ ለተሸናፊ ሐውልት አይቆምም ። ገዳዮች ጀግና ቢሆኑ ኑሮ ሐውልት ይቆምላቸው ነበር ። ገዳዮች በሥጋ ጨርሰው በነፍስ የሚወቀሱ ፣ ክፋት የኋሊት እንደሚጥል ማስተማሪያ ናቸው ። በጀግናና በጨካኝ መካከል ያለው ልዩነት ጀግና በልኩ የሚዋጋ ሲሆን ጨካኝ ግን ቀጥሎ እንዲህ ቢያደርገኝስ እያለ ገድሎ እንኳ ዱላ የሚያበዛ ፣ ሬሳ የሚደበድብ ነው ። ነገሥታት እንኳን ባለ ራእይን ወንጀለኛንም የሚገድሉት ስለሚፈሩት ነው ። መግደል አቅም ማጣትና ተስፋ መቊረጥ የሚወልደው የመጨረሻው እርምጃ ነው ።
በዘመናት ሁሉ ባለ ዓላማዎች ተገድለዋል ፣ ዓላማን መግደል ግን አልተቻለም ። ባለ አሳቦች ይሞታሉ ፣ አሳብ ግን አይሞትም ፤ ባለ ራእዮች ያንቀላፋሉ ፣ ራእይ ግን ከመቃብር በላይ ይኖራል ። ገዳዮች የማይገነዘቡት ነገር ቢኖር የአንዳንድ ራእይ ልደት ያለው መቃብር ላይ መሆኑን ነው ። ሐዋርያው ጳውሎስ ፡- ይህንም በመስበክ እንደ ክፉ አድራጊ እስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ ፥ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም ።” /2ጢሞ. 2፡9/ ብሏል ። እኔ አልታሰርም አላለም ፣ እውነት ግን አትታሰርም አለ ።ጴጥሮስን የቁልቁሊት መስቀል ተችሏል ፣ እውነትን መስቀል ግን አልተቻለም።
አይሁድ ከብዙ ምልክቶችና ከብዙ ትምህርቶች በኋላ ጌታችንን ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር ። ተምሮም አይቶም ገዳይ መሆን አለ ። ገዳይነት ምርጫ ነው ። በዓለም ላይ የአምላክን ፍቅር ተቋቁሞ ገዳይ የሚሆን ከባድ ልብ ነው ። አብዝቶ የቀረበንን አብዝቶ መራቅ የሰውነት ዋጋችንን የሚያወርድ ነው ። ይንተገተግ የነበረውን የጌታችንን አገልግሎት በሞት ፀጥ ለማሰኘት ይፈልጉ ነበር ። አይሁድ ዓርብ ቀን የመግደል መሻት አድሮባቸው ዓርብ ቀን ጌታን አልሰቀሉትም ። የዓመታት ምኞታቸው ዓርብ ቀን ሞላላቸው ። ኃጢአት ዕድሜው ከጽንስ እስከ ልደት ነው ። ኃጢአት ሳይገለጥ በስውር ፣ ሳይወለድ በጽንስ ሊወገድ ይገባዋል ። ማንኛውም ነገር እርሱን የሚመስል ልደት አለው ። ያልዘሩት አይበቅልምና ። መፈለግ ለመልካምም ለክፉውም ተግባር መሠረት ነው ። አንዳንድ ራእይ ተወልዶ ያድጋል ። አንዳንድ ራእይ ሊገድሉት ሲሉ ይወለዳል ። በዓለም ላይ ያሉ የውቅያኖስ ውኆች ፣ የብዙ ክረምት ዶፎች የራእይን እሳት ሊያጠፉት አይችሉም ። ራእይን የሚያጠፋው ያው ባለ ራእዩ ብቻ ነው ። ጠላቶች ራእይን ማጥፋት አይችሉም ፣ በዚያው ተቃራኒም ራእይ ጠላትን ማጥፋት አይችልም ። ሁሉም በየራሳቸው ህልውናቸው ይቀጥላል ። ለመኖር ያለን ፍላጎት የሚጨምረው መኖርን የሚፈታተን ነገር ሲመጣ ነው ። ጠላቶች ነፍሳችንን ለመቀማት በሚያደርጉት ጥረት ለነፍሳችን ያለን ክብር ይጨምራል ። የፍጥረት ውበት ያለው ንቃት ውስጥ ነው ። አበቦች ሲነቁ ፣ ወፎች ሲነቁ፣ … ሁሉም ፍጥረት ሲነቃ ውበቱ ይታያል ። መንቃት የሚቻለው ጠላት ካለ ብቻ ነው ።
አይሁድ ጌታችንን ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር ። በመቻል ቢሆን መግደል እርሱ ይችል ነበር ። የቻልነውን ሁሉ የቻልነው ስለቻልን አይደለም ማለት ነው ። የሚችሉ በትዕግሥት ስላለፉን ነው ። እንደ ቻሉን ከገባን ክብር ይመጣል ። አሊያ ውርደት ይሆናል ። ትልቁ ትዕግሥት መግደል እየቻሉ መሞት ውስጥ ይገኛል ። በቃሉና በተአምራቱ ሕይወት የሰጣቸውን ጌታ ሊገደሉት ይፈልጉ ነበር ። ጌታችንን ሊገድሉት የሚፈልጉ ሃይማኖት አለን የሚሉ ሰዎች ሲሆኑ ሊገድሉት የሚፈልጉበት ቦታም ያው የሃይማኖት መዲና በነበረችው በኢየሩሳሌም ነው ። እስከዚህ የሚጨክኑ ሰዎች በሃይማኖት ቦታ የተደበቁ ጨካኞች ናቸው ። አንድ ሊቅ ተገፍተው እንደ እብድ ይዞሩ ነበር ። አንድ ቀን እንዲህ ብለው ቤተ ክርስቲያን ደጃፍ ላይ ጮኹ፡- “በቆብ ተሸሽጎ አጋሚዶ ሁሉ ፤ አገር ተቃጠለ እየጠፋ ውሉ ።” የሃይማኖት ሰው አጋሚዶ ወይም እሾህ ሲሆን ማን ይፈውሳል ? የሃይማኖት ሰው ወንበዴ ከሆነ ውሉ እየጠፋ አገር ይሰክራል ። በሃይማኖት ሥፍራ ያሉ ጨካኞች በሌላ ቦታ ላይ ላይገኙ ይችላሉ ። ይህ ብዙ ምክንያት አለው ። የመጀመሪያው እግዚአብሔር አልችልም ብሎ ማንንም የማይገፋ አምላክ ስለሆነ ነው ። ሁለተኛው በነፍሱ የጨከነ በማንም ይጨክናል ። ሦስተኛ የላይኛውን ጌታ የተዳፈረ ማንንም አያፍርም ። ሰው ሁሉ በሃይማኖት ይገዛል ፣ ሃይማኖት የማይገዛውን ምን ይገዛዋል ? ቀኑን በሙሉ ፍላት ሲወርድበት የማይበስል አንድ ጥሬ ባቄላ ይገኛል ። ከብዙ ብስሎችም መካከል አንድ ጥሬ ግድ ይገኛል ። የሚበዛው መልካም ነው ። ክፉዎች ስለሚጎሉብንና ስፍራ እየለቀቅንላቸው ስለምንሄድ የበዙ ይመስለናል ። ክፉዎች የማይሄዱት የትም ተቀባይ እንደሌላቸው ስለሚያውቁ ነው ።
አይሁድ ክርስቶስን ስላልዳኑበት ሊገድሉት ይፈልጋሉ ። ዛሬ ያልዳኑበት ነገ ይሰቅሉታል ። መዳን የሚያስፈልገን ገዳይ እንዳንሆንም ነው ። አምነው ያልዳኑበት ክደው ይሰቅሉታል ። ጌታችን ግን በይሁዳ ሊመላለስ አልወደደም ። ይሁዳ ደቡቡ ክፍል ሲሆን የሃይማኖት ሰዎች የሚገኙበት የሃይማኖት መዲና ነው ። ገሊላ ግን የሁሉ ሰብሳቢ የገበሬዎችና የልፋተኞች ቦታ ናት ። ልፋተኞች የሚበሉት እንጀራ ይጣፍጣቸዋል ። ምግቡና እነርሱም ይዋደዳሉ ። ምግቡም ከተመገቡት በኋላ እዚህ ነኝ አይልም ። በሙሉነት ይሐዳቸዋልና መጥፎ ቅርጽ የላቸውም ። ጓደኛቸው ሥራቸው ነው ። የላብ ኑሮ ደስ ይላል ። ሥራን የማያደማ ሰው በብዙ ነገር ሲደማ ይውላል ። ልፋተኞች ጊዜ ስለሌላቸው ስለ ሰዎችና ስለ ፖለቲከኞች አያቀነቅኑም ። የሃይማኖት ሰዎች ተግባረ ዕድንን አብረው ካልያዙ ሰፊ ጊዜ ስለሚያገኙ ነገር ሲሠሩ ይውላሉ ። ሰነፍ የሚዝናናው የሰውን ቤት እያፈረሰ ነው ። የትኛውም ጎበዝ ሰባኪ በቀን ከአንድ ሰዓት በላይ ሊሰብክ አይችልም ። ትርፍ ሃያ ሦስት ሰዓት ካለው አደገኛ ነገር ውስጥ ይገባል ። አገር ካገር ሲያራብሽ ይውላል ። ስለዚህ ተግቶ መማርና መጻፍ ፣ የሙት ልጆችን መጎብኘትና ሥራ መሥራት ይገባዋል ። ለሃይማኖት ሰዎች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ ይገባል ። ብቻውን የማይድን ብቻውን የማይሞት ነውና ። ወይ ገነት ወይ ሲዖል ተጅቦ የሚገባ ነው ።
ጌታችን ለገዳይነታቸው አልተመቻቸም ። ያለ ጊዜው ላለ መሞት ተጠነቀቀ ። ስለዚህ ከይሁዳ ራቀ ። በገሊላ በምእመናኑ አገር መመላለስ ጀመረ ። ካህን ሲያሳድድ ምእመንን ፣ ምእመን ሲያሳድድ ካህንን መጠጋት መልካም ነው ። የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ማብቂያ የለውም ። የዓለም ፖለቲካ ምርጫ የሚባል ነገር ይመጣና ዝም ይላል ። የቤተ ክርስቲያን ፖለቲካ ግን ምርጫ የለውምና ሁልጊዜ ትኩስ ወሬ አለ ። ጌታ እንኳ ዘወር ካለ ሁሉንም ፈተና በመጋፈጥ አናሸንፈውም ማለት ነው ። ዘወር በማለት የምናሸንፈው ፈተና አለ ።
የጌታችን ትምህርት እውነት ሲሆን እውነትን ራቁትዋንና እውነትን በካባ በሚፈልጓት መካከል ትንቅንቅ መጥቶ ነበር ። የሚሟገቱት ሰዎች ሙሉ ሐሰተኞች አልነበሩም ። ከፊል እውነትን የያዙ ነበሩ ። ከፊል እውነት ከሙሉ ሐሰት በላይ የሰይጣን ጉዳይ አስፈጻሚ ነው ። ቦግ ጭልም የሚል ነገር ሰይጣንን ይመቸዋል ። ጌታችን በሩቅ ሁኖ በአደባባይ ያስተማረ ሳይሆን ቀርቦ የእኛን ሥጋ ለብሶ ያስተማረ ነው ። የቱንም ያህል ቅርብ ብንሆን ከጌታችን በላይ ቅርብ መሆን አንችልም ። ሥጋዌው  እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሆነበት ትልቅ ምሥጢር ነው ። ኅብረታችንም በጊዜ ውስጥ የሚፈታ ሳይሆን በደምና በሥጋ የተቋጠረ ነው ። ሕግም ፣ ጠላትም ሊለየው አይችልም ። የሚቃወሙትን ሁሉ አልተቀየማቸውም ። ይቅር ብሎ መኖርና ይቅር ለማለት መኖር ይለያያል ። እግዚአብሔር ግን ይቅር ብሎን ሊኖር ኪዳን ገብቷል ። የሰው ሲያልቅ የእግዚአብሔር የሚቀጥለው በኪዳን ፣ በልጅነት ሥርዓት ነው ። የተቃዋሚዎችን የመግደል ፍላጎት ጊዜ ገታው ። ሊገድሉት ቢሹም ሊያደርጉት ግን አልቻሉም ። የሚገድሉና ጥግ ይዘው ሌላው ሲገድል ለማየት የሚናፍቁ ሁለት ወገኖች አሉ ። ሁሉም ነፍሰ ገዳይ ናቸው ። በእግዚአብሔር መንግሥት ብዙ ዓይነት አገዳደል አለ ። ዓለሙ ግን መግደልን በአንድ አንጻር ብቻ ተርጉሞ አልገደልኩም ብሎ ይረጋጋል ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ