የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

የዳስ በዓል

“የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር ።”/ዮሐ. 7፡1/ ።
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተለያዩ በዓላት ተጠቅሰዋል ። የፋሲካ በዓል ፣ የዳስ በዓል ፣ የመቅደስ መታደስ በዓላት ተጠቅሰዋል ። ዮሐ. 2 ፡ 23 ፤ 4 ፡45 ፤ 5 ፡ 1 ፤ 6 ፡ 4 ፤ 7 ፡ 2 ፤ 10 ፡ 22 ፤ 13 ፡ 1 ። በዓላት በብሉይ ኪዳንና በአይሁድ ዘንድ ከፍ ያለ ክብርና ዓላማ የያዙ ናቸው ። በዓላት ከእግዚአብሔር ለሕዝቡ የተሰጡ ሰንደቅ ዓላማዎች የነጻነት ምልክቶች ናቸው ። በእልልታ ፣ በሆታና በአጀብ በዓል የሚያከብር ነጻነት ያለው ሕዝብ ነው ። በዓላት እግዚአብሔርን ስላደረገው ነገር ምስጋና ለማቅረብ መከማቸት ነው ። እግዚአብሔር ከሺህ ዓመት በፊት ያደረገው ነገር የሚታሰበው በበዓላት ነው ። የሺህ ዓመታት የእግዚአብሔር ሥራዎች በበዓላት ይታሰባሉና በዓላት ትልቅ ትርጉም አላቸው ። እግዚአብሔር አምላክ በዓላትን በሚመለከት ለሕዝቡ ደጋግሞ የተናገረው እንዲህ በማለት ነው፡- ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፡- የተቀደሰ ጉባኤ ብላችሁ የምታውጁአቸው በዓላቶቼ ፥ የእግዚአብሔር በዓላት ፥ እነዚህ ናቸው ።” ዘሌዋ. 23 ፡ 2 ። የተቀደሰ ጉባዔ የሚለው ለበዓላት ወሳኝ ድምፅ ነው ። በዓላት ቅድስና ይፈልጋሉ ። የእግዚአብሔር ስም ስለሚጠራባቸው ከኃጢአትና ከሥጋዊ ተድላ የራቁ ሊሆኑ ይገባቸዋል ። ጉባዔ ስለሚልም በዓላት መሰባሰብና ኅብረት አላቸው ። በዓላት ከእግዚአብሔርና ከሰዎች ጋር ኅብረት ለማድረግ በጣም ይረዳሉ ።
በዓላት መንፈሳዊ ግብዣ ናቸው ። እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚጋብዝበትና ሕዝቡም እግዚአብሔርን በቤቱ የሚጋብዝበት ነው ። እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚጋብዝባቸው በዓላት በመቅደሱ የሚከናወኑ ሲሆኑ ሕዝቡ እግዚአብሔርን የሚጋብዝባቸው በዓላት ደግሞ በቤታቸው የሚያከብሯቸው ናቸው ። አንድ ልጅ በወግ በመዐርግ ተድሮ ከቤቱ ሲወጣ ወላጆቹን ሊጠይቅ ይሄዳል ፣ ወላጆቹም ወደ እርሱ ቤት ይመጣሉ ። በዓላት መንፈሳዊ ዝምድናን ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ኅብረት የሚጠቁሙ ናቸው።
በዘሌዋውያን 23 ላይ የተሰጡት ዋና ዋና በዓላት የሳምንት ፣ የዓመት ሲሆኑ በሰባት ዓመትም የሚከበር የሰንበት ዓመት በዓል ነበር ። በዓላቱ የሚከበርባቸው ወቅቶች ከሚያዝያ ወር እስከ ጥቅምት መጀመሪያ ድረስ ያሉ በመሆናቸው ደስታን ያመለክታሉ ። እነዚህ ወራቶች ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው መኸር ድረስ ያሉ ናቸው ። በእነዚህ ወራት ለገበሬ የፀሐይና የአጨዳ ወራቶች ናቸው ። በዓላቱ የሚውሉት በብርሃን ወቅት ነው ። በዓላቱም የመጀመሪያዎቹ ሦስቱ በሃምሳ ቀናት ውስጥ ሲጠናቀቁ ሌሎቹ ሦስቱ ደግሞ በሰባተኛው ወር ውስጥ የሚፈጸሙ ናቸው ። በዓላቱ ወደ ክርስቶስ የሚያመለክቱ አዲስ ኪዳንን የሚያብራሩ ናቸው ። ከእነዚህ በዓላት ባሉበት ቦታ የሚከበሩ ሲኖሩ በግድ አገራቸው ገብተው የሚያከብሯቸው በዓላትም ነበሩ  ። እነዚህም፡- የፋሲካ በዓል ፣ በዓለ ሰዊትና በዓለ መጸለት ወይም የዳስ በዓል ናቸው ። እነዚህን በዓላት ከኢየሩሳሌም ውጭ ማክበር አይፈቀድም ። በዚህም አገራቸውን እንዳይረሱ ያደርጋቸዋል ። በዓላት ብሔራዊ ስሜትን የመገንባት አቅማቸው ከፍተኛ ነው ።
የበዓላቱ ዓላማ ምንድነው ? የበዓላቱ ዓላማ ልዩ ልዩ ነው ፡-
1-  በዓላቱ ማደግን ያመለክታሉ፡- እያንዳንዱ እስራኤላዊ ከ12 ዓመቱ ጀምሮ በዓላትን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መውጣት ነበረበት ። 12 ዓመት በአይሁዳውያን የአካለ መጠንና የውሳኔ ዘመን ነው ። በዓላት የእግዚአብሔርን ውለታ ማስታወስ ስለሆኑ ለማስታወስ ማደግ ያስፈልጋል ማለት ነው ።
2-  ጌቶችና ሎሌዎች ከልፋታቸው ያርፋሉ፡- በዓላት እኩልነትንና ዕረፍትን ያውጃሉ ። የሰው ልጅ እያረፈ የሚጓዝ ፍጡር ነው ። ካላረፈ ለቀጣዩ ቀን አቅም ሊኖረው አይችልም ። የፋብሪካና የቤት ውስጥ ሠራተኞችም ዕረፍት ያስፈልጋቸዋል ። ዕረፍት ከሰብአዊና መንፈሳዊ መብቶች አንዱ ነው ። በዕረፍትም የሚያሳርፈውን አምላክ ማሰብ ይገባል ።
3-  መንፈሳዊ በረከትን ያስገኛሉ፡- በዓላት በውስጣቸው ብዙ መንፈሳዊ ነገሮች ስለሚከናወኑባቸው ውስጣዊ መታደስን ፣ መገዛትንና ሰማያዊ ሀብትን ያሰጣሉ ።
4-  ለሥጋዊ ጤንነት ያስፈልጋሉ፡- አካል ፣ ስሜትና መንፈሳችን ዕረፍት ይፈልጋል ። ዕረፍት ከሌለ ጤና ይቃወሳል ። ጤንነት ከተቃወሰ በኋላ መመለስ ይቸግራል ። ሰው በሰንበት ቀን ማረፍ የግድ ያስፈልገዋል ። አሊያ ሕይወት አንድ ዓይነት ገጽ ፣ አሊያም ድግግሞሽ ትሆናለች ማለት ነው ።
5-  ቅድስናን እንለማመዳለን፡- ከበዓላት አንዱ የሆነው የቂጣ በዓል ሰባት ቀን እርሾ ያለበት ምግብ መብላትን ይከለክላል ። እርሾ የኃጢአትና የዓለማዊነት መገለጫ ነው ። የእግዚአብሔር ሕዝብ ከዚህ መለየት እንዳለበት በዓሉ ያስረዳል ።
6-  ህርቅን ያወርዳል፡- ለእስራኤል ከተሰጡት በዓላት አንዱ የማስተስሪያ ቀን ነው ። የማስተስሪያ ቀን ማለት የይቅርታ ቀን ማለት ነው ። በዚህ ቀን ብሔራዊ ህርቅ ይወርዳል ። የተጣሉ ሁሉ ይታረቃሉ ። ቂምና በቀል እስከዚህ ቀን ቢቆይም ከዚህ ቀን በኋላ ዕድሜ የለውም ። በዓላት ማኅበራዊ ሰላምን ያመጣሉ ።
7-  ኅብረትን ያመጣሉ፡- በዓላት የነገድ ፣ የቋንቋ ልዩነትን ያፈርሳሉ ።ሰው የእግዚአብሔር በመሆኑ ብቻ የሚደሰትባቸው ቀኖች ቢኖሩ በዓላት ናቸው ። በበዓላት ቀናት ጦርነቶች ሲቆሙ ይታያል ። የሕዝቦች አንድነት የታሰረው በበዓላትም ነው ።
8-  ድሆችን ይታደጋል፡- ስለ በዓላት ከተሰጡት ድንጋጌዎች አንዱ ፡- የምድራችሁንም መከር በሰበሰባችሁ ጊዜ የእርሻችሁን ድንበር ፈጽማችሁ አትጨዱ ፥ የመከሩንም ቃርሚያ አትልቀሙ ለድሆችና ለእንግዶች ተዉት እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ ” ይላል ። ዘሌዋ. 23 ፡ 22 ። በበዓላት ድሆች ይጠግባሉ ፣ ሰው ልግስናን ይለማመዳል ።
9-  ቃለ እግዚአብሔር ይታወጃል፡- በዓላት ሰዎችን ስለሚሰበስቡ መጻሕፍት የሚተረጎሙት መንፈሳዊ ታሪኮች የሚብራሩት በዚህ ቀን ነው ። የእግዚአብሔር ቃል በተነገረበት ስፍራ ሁሉ ሰላም አለ ።
10-    ደስታን ያመጣሉ፡- በዓላት በሚደረጉበት ቀን በቅርብ ርቀት ጦርነቶች ቢኖሩ እንኳ የእልልታ ድምፅ ይሰማል ። እልልታ ገደቡን ጥሶ የወጣ ደስታ ነው ። ይህ የሕዝቦችን ጭንቀት የሚንድ መድኃኒት ነው ።
በምናጠናው በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ ሰባት ላይ ስለ ዳስ በዓል እናነባለን ። የእስራኤል ልጆች በምድራቸው በእስራኤል ተገኝተው የሚያከብሯቸው ሦስት በዓላት አሉ ። እነዚህም ፡-
1-  በዓለ ፋሲካ /የቂጣ በዓል/
2-  በዓለ ሰዊት/የእሸት በዓል- በዓለ ሃምሳ/
3-  በዓለ መጸለት /የዳስ በዓል/
በዓለ ፋሲካ ሚያዝያ በገባ በ14ኛው ቀን የሚከበር ነው ። በዓለ ሃምሳ ፋሲካ በዋለ በሃምሳኛው ቀን የሚከበር ነው ። ይህም በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ይሆናል ። የዳስ በዓል ግን በሰባተኛው ወር በእኛ መስከረም መጨረሻና ጥቅምት መጀመሪያ የሚከበር ነው ። የዳስ በዓል ዓላማው የእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ላይ አርባ ዓመት መጓዛቸውን የሚያስቡበት ነው ። ይህንም በዓል የሚያከብሩት ከቤታቸው ወጥተው ለሰባት ቀን የዳስ ጎጆ ሠርተው ነው።እግዚአብሔር በምድረ በዳ ውስጥ ሰማይን ጣራ ፣ ምድረ በዳውን ቀዝቃዛ አድርጎ እንዴት እንደተንከባከባቸው የሚያስቡበት ነው ። ይህ በዓልም የመኸር መክተቻ ወራት ላይ የሚውል ነው ። የዳስ ጎጆው ሥጋችንንና ዓለምን ይገልጣሉ ። ሥጋችን ፈራሽ ድንኳን ተብሏል ። 2ቆሮ. 5 ፡ 1-5። ድንኳን በጥሩ ካስማ ቢቆምም ንውጽውጽታ አያጣውም ። ሥጋም ቢማሩ ፣ ቢሰበስቡ ጭንቀት አያጣውም ። ዓለምም በእንግዳ ወሬዎች ስትናጥ የምትውል ድንኳን ናት ። ድንኳን ምንም ዕድሜው ቢረዝም ለሦስት ቀን ነው ። በዚህ ዓለም ብንቆይም ለጥቂት ዘመን ነው ። ዓለምም ኃላፊ ነው ። የዳስ በዓል ፈራሹን ሥጋና ዓለም ያስታውሰናል ። የመጨረሻው መኸር ደግሞ ምጽአትን ያሳስበናል ። ከምጽአት በፊት ብዙ መኸሮች አሉ ። አጠቃላዩና የመጨረሻው መኸር ግን ዳግም ምጽአት ነው ። የዳስ በዓል የመጨረሻው በዓልም ነው ። በዚህ ዓለም ላይ የሚቀረን የመጨረሻው በዓልና ጉባዔ ዕለተ ምጽአት ነው ።
“የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር”ይላል ። ዮሐ. 7 ፡ 1 ። የዳስ በዓሉ ትርጉሙም ዓላማውም ይህ ነው ።
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ