የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ይገለጥ

እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ /ዮሐ. 1፡31/።
 መጥምቁ  ዮሐንስ እጅግ የተከበረ አገልጋይ ባለ ብዙ መጠሪያ ሐዋርያ ነው። መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ራሱ ሲጠየቅ ስለ ክርስቶስ ይመሰክር ነበር። አባቱ ዘካርያስም በልጁ መወለድ ትንቢት የተናገረው ስለ ክርስቶስ ነው። የእስራኤል ጌታ አምላክ ይባረክ፥ ጐብኝቶ ለሕዝቡ ቤዛ አድርጎአልና በማለት ይጀምራል /ሉቃ. 1፡68/። ዮሐንስ የተወለደበት ዋነኛ ዓላማ ለመሲሑ መንገድ እንዲጠርግ መሆኑን ጻድቁ ዘካርያስ ተናገረ። ጻድቁ ዘካርያስ በእርጅና መውለዱ ብቻ ሳይሆን የተወለደው ሕጻንም መለኮታዊ ጥሪ እንዳለው እየተናገረ ነው። ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ለእግዚአብሔር እየሰጠ ነው። ልጆች ከእኛ ደስታ ይልቅ ለእግዚአብሔር ዓላማ የተፈጠሩ ናቸው። ወላጆች ሁሉ ለልጆቻቸው ባለቤት ሳይሆኑ ባለ አደራ ናቸው። ልጆች ዛሬ እያመለጡን ያሉት ለምንድነው? ስንል የእኛ ስለሆኑ ነው። ለእግዚአብሔር የሰጠነውንና እግዚአብሔር ጋር ያስቀመጥነውን ከርሞም እናገኘዋለን። የእኛ የሆኑ ለእግዚአብሔር ላይሆኑ ይችላል። የእግዚአብሔር የሆነ ግን የእኛ ነው። ዘካርያስ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ዲዳ ሆኖ የተናገረው ስለ ቤዛ ኩሉ ዓለም ስለ ክርስቶስ ነው። አፉ ሲከፈት ስለ መሢሑ ተናገረ። ዝምታ መልካም ነው። ስለ መሢሑ ግን ዱዳም ይናገራልና ልንመሰክር ይገባናል። ዘካርያስ በዱዳነትም ተባረከ። መልአኩ ገብርኤል የምሥራች ሊነግር መጥቶ ዱዳ አድርጎት የሄደው በቊጣ ሳይሆን ዘካርያስ አንዳች የጥርጥር ቃል እንዳይናገር ነው። “ዛሬ መልአክ ይሁን ሌላ፥ ትወልዳለህ አለኝ። አይገርምም ወይ?” እንዳይል መልአኩ የተናገረው እስከሚሆን አንደበቱን ዘጋው። ጥርጥር መናገርም መካድም ሁለቱም ያው ነው። በምሥራቹ እንዳይበድል አንደበቱ ዲዳ ሆነ።በጎ በረከቶች ከመጡ በኋላ ችግሮች አብረው የሚመጡት በበጎ ነገር እንዳንበድል ለመከለል ነው። ተጠራጥረን እንዳናጠራጥር አንደበታችን ዲዳ ቢሆን ይሻለናል። ዘካርያስ አንደበቱ የተከፈተው የመልአኩ ቃል ሲፈጸም ነውና በአንደበቱ ምስጋና ሞላ። በዓለም ላይ ሦስት ነገሮች አያጸጽቱም፡- ዝምታ፥ ትዕግሥትና የተቆጠበ ግንኙነት።
 መጥምቁ ዮሐንስም ስለ ራሱ ሲጠየቅ ስለ መሢሑ ተናገረ። ይህ ነቢይ ወላጆቹ ያላሳደጉት፥ እርሱም ወላጆቹን ያልጦረ ነው። እግዚአብሔር ራሱ አሳደገው። ምንም እንኳ ልደቱ የወላጆቹ የጸሎት መልስ ቢሆንም እነርሱ ብዙ ዓመት አላገኙትም። እነርሱም እግዚአብሔርን ብቻ አገልግለው አለፉ። በስተርጅና ልጅ ጣኦት ሆኖባቸው፡- “ልጄ ከሌለ እኔ አልኖርም” ብለው ከፈጣሪ ጋር አልተጣሉም። እኔ ባልኖር ልጄ ምን ይሆናል እንዳይሉ የዛሬን ወላጆች በዮሐንስ መጥምቅ አስተዳደግ እንመክራለን። እግዚአብሔር ያሳድጋል። የዛሬ ጸሎታችንና ደግነታችን ለልጆቻችን ይጠቅማል። ጸሎትና ደግነት ወይ በራስ ወይ በልጅ ይታጨዳል። ዮሐንስ የእግዚአብሔር ነውና ለሁሉ ተረፈ። ዛሬም ያነጋግረናል። የማይጠፋ ኮከብ ሆኖ ወደ ክርስቶስ ያመለክተናል። ዮሐንስ ለአይሁዳውያን ስለ ክርስቶስ ቀዳማዊነትና ታላቅነት ተናገረ። ሰልፍ ይዘው ለሚናዘዙት ኃጢአተኞች ግን ክርስቶስ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን መሰከረ። መሥዋዕት በሌለበት ስርየት የለምና ለኃጢአተኞች ስለ ቤዛ ኩሉ ዓለም መናገር ትልቅ ዕረፍት ነው። እንኳን የእኔን የመላው ዓለም ኃጢአት ያስወግዳል እንዲሉ አስረግጦ ተናገረ። ከሚያስመኩ ነገሮች ቀዳሚው የእግዚአብሔር ምሕረት ወይም ያለ ወቀሳ እኛን መቀበሉ ነው። በዓለም ላይ ሦስት ነገሮች ያደናግራሉ። የመጀመሪያው አለማወቅ ያደናግራል። ሁለተኛ ፍቅርን ዘርቶ ጥላቻን ማጨድም እንዲሁ ግር ያሰኛል። ሦስተኛው ግን ከሁሉ የበለጠ ግር ይላል። እርሱም የኃጢአትን ስርየት አለማግኘት ነው። ይህ እንደ ቃየን ቀበዝባዛ ያደርጋል። ዮሐንስ ኢየሱስ ክርስቶስ መድኃኔዓለም መሆኑን ተናገረ። አዋቂዎች በማያውቁት ላይ ይመካሉ፥ ግን እነርሱም አያውቁም ነበር። ከዳተኞች በአፍቃሪዎች ላይ ይመካሉ፥ ግን እነርሱም መከዳት ሕመም እንዳለው ያዩ ናቸው። ንጹሐን በኃጢአተኞች ላይ ይመጻደቃሉ፥ ግን እነርሱም ይቅር የተባሉ ናቸው። ሌላውን ሳይንቁ ማሳወቅ፥ ሳይጠሉ መውደድ፥ ሳይፈርዱ መጸለይ ትልቅ ብቃት ነው። ዮሐንስ በነፍስ በሥጋ ሕመም ያለውን ኃጢአት መፍትሔ እንዳገኘ ለመንፈስ በሽተኞች ተናገረ። ዛሬ መድኃኒት የሌላቸው በሽታዎች መድኃኒት እንደተገኘላቸው ብናውቅ ምን ያህል ተመክተንና ጮኸን እናወራ ይሆን? ዮሐንስን ያስጮኸው ዝም የማያሰኘው ይህ መፍትሔ ነው። ዓለሙ ችግሩ አስጨንቆታል፥ መድኃኒቱን ግን አያውቅም። ችግርን ያለ መፍትሔው ማወቅ ከባድ ነው። መፍትሔ ያለው ችግር ደግሞ አስደሳች ነው።
 መጥምቁ ዮሐንስ፡- እኔም አላውቀውም ነበር፥ ዳሩ ግን ለእስራኤል ይገለጥ ዘንድ ስለዚህ በውኃ እያጠመቅሁ እኔ መጣሁ አለ /ዮሐ. 1፡31/። መጥምቁ ዮሐንስ ከጌታችን ጋር የሥጋ ዘመድ ነው። ጌታን ግን ያወቀው በመለኮታዊ ክብሩ ነው። በትንሹ እውቀት ውስጥ ትልቅ አለማወቅ አለ። እንኳን እግዚአብሔርን  ሰውንም በሙሉነት ማወቅ አይቻልም። ማወቅ በመጨረሻ የሚሰጠን የምስክር ወረቀት ከምታውቁት የማታውቁት ይበዛል የሚል ነው። መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ጌታ የነበረው እውቀት በመንፈስ የሚመረመር ነው። ስለ ጌታ ለማወቅ የረዳው ማየቱ ሳይሆን ማመኑ ነው። ሰው ሳያይም የመረጃ እውቀት አለው። ክርስቶስን በመረጃ እውቀት ማወቅ ይቻላል። ሕይወት ግን የሚሆንልን በእምነት ስናውቀው ነው። የመረጃ እውቀቶች ለፍላፊ ያደርጋሉ። መንፈሳዊ እውቀት ግን ልብን በመለኮታዊ ፍቅር ያደቅቃል። የእውቀት ተዘዋዋሪ ጉዳቱ ትዕቢትን ማምጣቱ ነው። መንፈሳዊ እውቀት ግን ትሑት ያደርጋል። ዮሐንስ አላውቀውም ነበር ይላል። እርሱ አገልግሎቱን ባፋጠነ ቁጥር ክርስቶስ እንደሚመጣ ግን አምኗል። ሥራችንን ከሠራን ክርስቶስ ይመጣል። ማራናታ ወይም “ጌታ ኢየሱስ ቶሎ ና” ላለፉት ሁለት ሺህ ዓመታት የቤተ ክርስቲያን የናፍቆት ጸሎቷ ነው። ያልተለያትን ክርስቶስ ቶሎ ና ትለዋለች። ጌታችን ግን ለምትናፍቀው ሙሽራይቱ ቤተ ክርስቲያን፡- ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል ብሏታል /ማቴ.24፡14/። ምን ማለት ነው? ስንል ክርስቶስ የሚመጣው ወንጌል ለዓለም ሁሉ ሲደርስ ነው። ክርስቶስን እንዲመጣ የሚያፋጥነው የአሕዛብ ወንጌልን መስማት ነው። ስለዚህ ማራናታ የናፍቆት ቃል ሲሆን ናፍቆትን የሚፈውሰው ግን ወንጌልን መስበክ ለዓለም ሁሉ ማድረስ ነው። ገና ወንጌልን ያልተቀበሉ ኦሪታውያን ደግሞም እስማኤላውያን አሉ። እነዚህ ሁሉ የእኛን ፍቅርና ዜና ወንጌል እየጠበቁ ነው።
መጥምቁ ዮሐንስ አላውቀውም ነበር አለ። ጌታችን የዕለት ጽንስ ሆኖ ዮሐንስ የስድስት ወር ጽንስ ሆኖ የእመቤታችን የድንግል ማርያምን የሰላምታ ድምፅ በሰማ ጊዜ በደስታ ዘሎ ነበር። እናቱ ቅድስት ኤልሳቤጥም፡- እነሆ፥ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ፅንሱ በማኅፀኔ በደስታ ዘሎአልና ብላለች /ሉቃ. 1፡44/። ዮሐንስ በሥጋ ጌታን ያየውና ከዚህ በፊት የሚያውቀው አይመስልም። ቀድሞ በእምነት አየው፥ አሁን ደግሞ በዓይኑ አየው። የእምነት ዋጋው ማየት ነውና ይኸው ተከፈለው። በእመቤታችን በድንግል ማርያም ማኅፀን ያለው ጌታና በኤልሳቤጥ ማኅጸን ያለው ዮሐንስ ቢነጋገሩ ምን ይሉ ይሆን? ዮሐንስ ምስክርነት ይወዳልና፡-
·       አንተ ጌታዬ ቃል ነህ፥ እኔ ግን ድምፅ ነኝ።
·       አንተ ጌታዬ በድንግልና ተወልደሃል፥ እኔ ግን በተአምራት ተወልጃለሁ።
·       አንተ ጌታዬ ከእኔ ስድስት ወር በሥጋ ጽንሰት ታንሳለህ፥ እኔን ግን በማኅጸን ያስቀመጥህ አንተ ነህ።
·       አንተ ጌታዬ ድምፅህ ያስደስተኛል፥ ቆሜ የምሰማህ ሚዜህ ነኝና /ዮሐ. 3፡29/።
·       አንተ ጌታዬ ለእናትህ አንድ ነህ፥ እኔም ለወላጆቼ አንድ ነኝ።
·       አንተ ጌታዬ ቀድሞም የእግርህ መረገጫ የነበረችውን ምድር አሁን በሥጋ ልትረግጣት ነው፥ እኔ ግን የማላውቃትን ምድር ላያት ነው።
·       አንተ ጌታዬ የከተማ መናኝ ትሆናለህ፥ እኔ ደግሞ የበረሃ መናኝ እሆናለሁ። ክርስትና የምናኔ ሕይወት መሆኑን እናሳያለን።
·       አንተ ጌታዬ ቤዛ ሆነህ ትሞታለህ፥ እኔ ሰማዕት ሆኜ አልፋለሁ።
·       አንተ ጌታዬ በራስህ ኃይል ትሠራለህ፥ እኔ በአንተ ኃይል እራመዳለሁ።
·       አንተ ጌታዬ ተራሮች ሳይወለዱ አንተ አለህ፥ እኔ ግን በሥጋ ቀድሜህ እወለዳለሁ… ሳይል አይቀርም።
በውኃ ማጥመቅ የመዳረሻ አገልግሎት ነው። ዋናው ሲመጣ ይነሣል። ዋናው ምግብ ሲመጣ መቆያው ምግብ ሳያልቅ ይነሣል። መቆያውን ምግብ እስከ መጨረሻ መመገብ ዋናውን ምግብና የተከፈለበትን መና እንደ መክሰር ነው። ዮሐንስ ግን ትልቁ አገልግሎት እስኪመጣ ትንሹን ይሠራ ነበር። ትንንሽ ድርሻዎች ለትልቅ ግብ ያበቁናል። በአንድ ጊዜ ትልቅ ሥራ መሥራት አንችልም። ትንንሽ ድርሻዎች ሲፈጸሙ ግን ትልቅ ይሆናሉ። የሚሊየን ቁጥር መነሻው አንድ ነው። አንድ ማለትን ከፈራን ሚሊየን ለማለት አንበቃም። በእግዚአብሔር ፊት ትንሽ ድርሻ የለም። የነቢያትን ማኅበር ስንከፍል ዐበይት ወይም ታላላቅ ነቢያትና ደቂቅ ነቢያት ወይም ታናናሽ ነቢያት እንላለን። ታናናሽ የተባሉት ባገለገሉበት ዘመንና በጻፉት መጽሐፍ መጠን ነው። ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ምንም ትንሽ ድርሻ የለም። ዮሐንስ የተሰጠውን አገልግሎት አከበረ። የብዙዎችን ንስሐ ይሰማል። ወዲያው ያጠምቃል። ታጥባችኋል ማለቱ ነው። የሌሎችን ችግር መስማት ከባድ ነው። ከዚያ በላይ ንስሐቸውን መስማት ይከብዳል። ይህ ሁሉ የሚቻለው በእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ጸጋዬ ምን ዓይነት ነው? ለሚል ጠያቂ በአንድ እግራችን ቆመን የምንመልሰው፡- “ስታደርገው የማይከብድህ እርሱ ጸጋህ ነው” እንለዋለን። ስትሰብክ የማትጨነቅ፥ የማትፎክር፥ የማትሳደብ ከሆነ እርሱ ጸጋህ ነው። ስትፈውስ ማስታወቂያ የማታሠራ፥ ለማውራት የማትቸኩል ከሆነ እርሱ ጸጋህ ነው እንለዋለን። ዮሐንስ የሌሎችን ንስሐ የመስማትና ስርየትን የማወጅ ጸጋ ነበረው። የሌሎችን ንስሐ ስንሰማ እንደ እግዚአብሔር ሆነናልና ልንሸፍን ይገባናል። አሊያ የሌሎችን ንስሐ የሚያወጣ አገልጋይ የሰማው ኃጢአት እርሱ እንዳደረገው ሆኖ ይቆጠርበታል። ከሁሉ በላይ በደል ያስጨነቃቸውን በምሕረት ድምፅ መሸኘት መታደል ነው። እግዚአብሔር ምሕረቱን ሳይሰፍር ለሁሉ ይሰጣል። እንደ እግዚአብሔር ያለ መሐሪ የለም። ሰዎች ደግመን ስንበድላቸው ያኔም ይህን አድርገህ ነበር በማለት ይቅርታቸውን ሰርዘው በደላችንን ይነግሩናል። ያኔ የማይል፥ የእንደገና አምላክ ስላለን ስሙ ይመስገን። ጌታችን በመስቀል ላይ ሳይውል፥ ካሣ ሳይከፈል እንዴት ስርየት ይገኛል? ዮሐንስ ይህን ስርየት እንዴት ያውጃል?  ብንል ብሉይ ኪዳን የተስፋ ወንጌል ነውና ክርስቶስ በተስፋም ያድን፥ ስርየትን ይሰጥ ነበር።  
 መሢሑ ለእስራኤል እንዲገለጥ ማዳኑም እንዲመጣ ዮሐንስ ሰዎችን ለንስሐ ያነቃቃ ነበር። በአደጋ ቀጠና ውስጥ ከለስላሳ ቃል ይልቅ ጠንከር ያለ ቃል እንዲሰማ ዮሐንስ ከሞት አፋፍ ላይ ላሉ የተግሳጽ ቃል ያሰማ ነበር። መገሰጽ የባለቤትነት ስሜት በውስጡ አለው። ማንም ማንንም አይገስጽም። የሚገስጹን ከሌሉ ወዳጆቻችን ተመናምነዋል ማለት ነው። በዚህ የመጠባበቅ ዘመን የሚመክረን አምልጦ የሚያስመልጠን፥ በዚህ የክስ ዘመን ራሳችንን አሳይቶ ወደ ንስሐ የሚመራን ያስፈልገናል። ዛሬም መሢሑ ለቤተ ክርስቲያን ለአገርና ለተራቆቱ ቤተሰቦች እንዲገለጥ ንስሐ መግባት አስፈላጊ ነው። የሐሜት ዘመን ንስሐን አይወድም። ሐሜት የሰውን፥ ንስሐ የራስን ኃጢአት ማውራት ነው። ከሐሜት ቀጥሎ መቆሸሽና ሌላውን ማቆሸሽ አለ። ከንስሐ ቀጥሎ ግን መንጻትና ሌላውንም ማንጻት አለ። ክርስቶስ በተዝረከረከው የእኛ ዓለም፥ ተግተን ባበላሸነው ምድር በኃጢአት በተወዳደርንበት ዘመን በምሕረት ሊገለጥ ግድ ነው። ሁሉም ነገር ቆም ብሎ ንስሐ ቢታወጅ መልካም ነው። ብሔራዊ ንስሐ ቢደረግ አማራጭ የሌለው ነው። አሊያ የግርፊያው ገመድ እየወፈረ፥ መቀጥቀጫውም ዘንግ እየጠነከረ ይመጣል። የንስሐ መንፈስና የንስሐ ፍሬ እጅግ እየጠፋ ነው።  ሁሉም አዋቂ፥ ሁሉም እኔ ነጻ ነኝ ባይ ነው። ሁላችንም ነጻ ከሆንን ለምን እንዲህ እንወዘወዛለን? ምድር የብረት ምጣድ ሆና ከአንዱ ወደ አንዱ ታገላብጠናለች? ግድ የለም ንስሐ ብቻ ይበጀናል። መጥምቁ ዮሐንስ ካህን ትምህርት፥ መናኝ ጥግ፥ ንጉሥ ፍርድ፥ ጎበዝ ጉልበት፥ ቆንጆ ራእይ፥ ሕዝብ ፍቅር ባጣበት ዘመን የክርስቶስ መምጣት እንዲሆን ንስሐን አወጀ። ችግሩ ዛሬም እንደ ጥንቱ ነው። ስለዚህ መድኃኒቱ አንድ ነው። ክርስቶስ ይገለጥ። 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ